ተጨማሪ መረጃ
ለክርስቲያን ወላጆች፦
ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን የምትሳሱላቸው ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱና ራሳቸውን ለእሱ እንዲወስኑ መርዳት እንደምትፈልጉ የታወቀ ነው። ልጆቻችሁ ለጥምቀት እንዲዘጋጁ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ይህን ትልቅ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ የሚሆኑት መቼ ነው?
ኢየሱስ ለተከታዮቹ ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ አጥምቋቸውም’ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:19) በዚህ መሠረት ለመጠመቅ የሚያስፈልገው ዋነኛው ብቃት ደቀ መዝሙር መሆን ነው። ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ክርስቶስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች መረዳትና ማመን ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን ምንጊዜም ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልገዋል። በዕድሜ ለጋ የሆኑ ልጆችም እንኳ ይህን ማድረግ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ፤ እንዲሁም የይሖዋን ትምህርት በልባቸው ላይ ቅረጹ። (ዘዳ. 6:6-9) ይህ ደግሞ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ማስተማርንና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር ማሰብ እንዲችሉ እንዲሁም በዚያ መሠረት ሕይወታቸውን እንዲመሩ ማዘጋጀትን ይጨምራል። ልጆቻችሁ የሚያምኑበትን ነገር በራሳቸው አባባል መግለጽ እንዲችሉ እርዷቸው። (1 ጴጥ. 3:15) ከእናንተና በጉባኤ ውስጥ ካሉ ጥሩ ወዳጆች የሚያገኙት ማበረታቻ እንዲሁም የግል ጥናትና የቤተሰብ አምልኮ በማድረግ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የሚያገኙት እውቀት እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ብሎም ሌሎች መንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲደርሱ ይረዳቸዋል። መንፈሳዊ ግቦች እንዲያወጡ እርዷቸው።
ምሳሌ 20:11 “ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ በአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። አንድ ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆነና ለመጠመቅ ብቃቱን እንዳሟላ የሚጠቁሙ አንዳንድ ድርጊቶች ምንድን ናቸው?
ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጥረት እያደረገ ያለ ልጅ፣ ለወላጆቹ (ለወላጁ) ታዛዥ መሆን አለበት። (ሥራ 5:29፤ ቆላ. 3:20) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ “እንደ ወትሮውም [ለወላጆቹ] ይገዛላቸው ነበር” በማለት ይናገራል። (ሉቃስ 2:51) እርግጥ፣ ከልጃችሁ ፍጽምና መጠበቅ አይኖርባችሁም። ይሁንና የመጠመቅ ፍላጎት ያለው ልጅ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት እንደሚያደርግ የታወቀ ነው፤ እንዲሁም ሰዎች የሚያውቁት ለወላጆቹ የሚገዛ ልጅ በመሆኑ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ልጁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመማር ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያሳያል። (ሉቃስ 2:46) ልጃችሁ ስብሰባ ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ ይወዳል? (መዝ. 122:1) ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብና የግል ጥናት የማድረግ ፍላጎት አለው?—ማቴ. 4:4
ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ጥረት እያደረገ ያለ ልጅ፣ ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ማሳየት ይኖርበታል። (ማቴ. 6:33) የሚያምንበትን ነገር ለሌሎች የመናገር ኃላፊነት እንዳለበት ይገነዘባል። በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የሚሳተፍ ከመሆኑም ሌላ ለአስተማሪዎቹና አብረውት ለሚማሩ ልጆች የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ማሳወቅ አያሳፍረውም። በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚሰጠውን ክፍል በቁም ነገር ይመለከታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከመጥፎ ጓደኞች በመራቅ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን ጠብቆ ለመኖር ጥረት ያደርጋል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:33) በዚህ ረገድ የሚያደርገው ውሳኔ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራምና በቪዲዮ ጨዋታ ምርጫው እንዲሁም በኢንተርኔት አጠቃቀሙ ላይ ይንጸባረቃል።
ብዙዎች፣ ወላጆቻቸው ላደረጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው እውነትን የራሳቸው በማድረግ በለጋ ዕድሜያቸው ለመጠመቅ ብቁ ሆነዋል። ልጆቻችሁ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና የሚነካውን ይህን ወሳኝ እርምጃ እንዲወስዱ በምትረዱበት ወቅት ይሖዋ እንዲባርካችሁ ምኞታችን ነው።
ላልተጠመቀ አስፋፊ፦
ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ከጉባኤው ጋር ማገልገል መቻል ትልቅ መብት ነው። ያደረግከው መንፈሳዊ እድገት በእጅጉ የሚያስመሰግን ነው። ቃሉን በማጥናት አምላክን ማወቅ ችለሃል፤ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይም እምነት እንዳለህ አሳይተሃል።—ዮሐ. 17:3፤ ዕብ. 11:6
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከመጀመርህ በፊት በሆነ መንገድ ከሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት ጋር ግንኙነት የነበረህ ልትሆን ትችላለህ፤ ወይም ደግሞ ከየትኛውም ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረህ ይሆናል። ምናልባት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሌላ ድርጊት ትፈጽም የነበርክ ልትሆን ትችላለህ። አሁን ግን ንስሐ በመግባት ማለትም ቀደም ሲል በፈጸምከው መጥፎ ድርጊት ከልብ በመጸጸት እምነትህን ገልጸሃል፤ በተጨማሪም በመለወጥ ማለትም ቀደም ሲል ትከተለው የነበረውን የተሳሳተ ጎዳና እርግፍ አድርገህ በመተውና በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ እምነትህን በተግባር አሳይተሃል።—ሥራ 3:19
በሌላ በኩል ደግሞ ‘ከጨቅላነትህ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያወቅህ’ ልትሆን ትችላለህ፤ ይህም ክርስቲያናዊ ያልሆነ ምግባር ከማሳየትና ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም እንድትርቅ ረድቶህ ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:15) የእኩዮችህን ተጽዕኖና በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር እንድታደርግ የሚገፋፉ ሌሎች ተጽዕኖዎችን እንዴት መቋቋም እንደምትችል ተምረሃል። እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍና የምታምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች በመንገር እምነትህን በተግባር አሳይተሃል። በተጨማሪም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ጥሩ ሥልጠና አግኝተሃል። ስለሆነም ያልተጠመቅክ አስፋፊ ሆነህ ይሖዋን ለማገልገል ወስነሃል።
የይሖዋን መንገዶች የተማርከው ከጊዜ በኋላም ይሁን ከጨቅላነትህ ጀምሮ፣ አሁን በመንፈሳዊ እያደረግክ ባለኸው እድገት ሁለት ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ማለትም ራስህን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ እያሰብክ ይሆናል። ራስህን ለይሖዋ የምትወስነው፣ ለዘላለም እሱን ብቻ እያመለክ ለመኖር ያደረግከውን ውሳኔ ለእሱ በጸሎት በመንገር ነው። (ማቴ. 16:24) ከዚያም ይህን ውሳኔ እንዳደረግክ ለማሳየት በውኃ ትጠመቃለህ። (ማቴ. 28:19, 20) ራስህን ስትወስንና ስትጠመቅ የተሾምክ የይሖዋ አምላክ አገልጋይ ትሆናለህ። ይህ እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው!
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና እንደተገነዘብከው የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ “ዲያብሎስ ይፈትነው ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ [እንደመራው]” አስታውስ። (ማቴ. 4:1) የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆነህ ከተጠመቅክ በኋላ ተጨማሪ ፈተናዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ መጠበቅ ይኖርብሃል። (ዮሐ. 15:20) ፈተናዎች በተለያየ መልክ ሊመጡ ይችላሉ። ቤተሰቦችህ ይቃወሙህ ይሆናል። (ማቴ. 10:36) አብረውህ የሚማሩ ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦችህ ወይም የቀድሞ ጓደኞችህ ሊያፌዙብህ ይችላሉ። ምንጊዜም ቢሆን በማርቆስ 10:29, 30 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ አስታውስ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።” ስለዚህ ይሖዋን የሙጥኝ ብለህ ለመኖርና የጽድቅ መሥፈርቶቹን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግህን ቀጥል።
ለመጠመቅ ካሰብክ፣ ፍላጎትህን ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ማሳወቅ ትችላለህ። ሽማግሌዎች ለጥምቀት ብቁ መሆን አለመሆንህን ለመወሰን ከዚህ መልእክት ቀጥሎ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ተመሥርተው ከአንተ ጋር ውይይት ያደርጋሉ። በግል ጥናት ፕሮግራምህ ላይ ጥያቄዎቹን በግልህ መከለስ ልትጀምር ትችላለህ።
ከሽማግሌዎቹ ጋር ለምታደርገው ውይይት ስትዘጋጅ ጥቅሶቹን ጊዜ መድበህ አንብባቸው እንዲሁም አሰላስልባቸው። በዚህ መጽሐፍ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ማስታወሻ መያዝ ትችላለህ። ከሽማግሌዎቹ ጋር በምትወያይበት ጊዜ በያዝካቸው ማስታወሻዎች መጠቀም እንዲሁም መጽሐፉን ገልጠህ መያዝ ትችላለህ። ለመረዳት የከበደህ ጥያቄ ካለ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናህ ሰው ወይም ከሽማግሌዎቹ አንዱ እንዲረዳህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል።
ከሽማግሌዎቹ ጋር በምትወያይበት ጊዜ ለሚቀርቡልህ ጥያቄዎች ረጅም ወይም የረቀቀ መልስ መስጠት እንዳለብህ አይሰማህ። እንዲያውም በራስህ አባባል ግልጽና ቀጥተኛ መልስ መስጠትህ ይመረጣል። በተጨማሪም አብዛኞቹን ጥያቄዎች በምትመልስበት ጊዜ ለመልስህ መሠረት የሆነውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ የያዙ አንድ ወይም ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መጥቀስህ ጠቃሚ ነው።
መሠረታዊ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በቂ እውቀት ከሌለህ ሽማግሌዎቹ እርዳታ የምታገኝበትን ዝግጅት ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙትን ትምህርት በትክክል ተረድተህ በራስህ አባባል መግለጽ እንድትችል እንዲሁም በሌላ ጊዜ ለመጠመቅ ብቁ እንድትሆን ይረዳሃል።
[ለጉባኤ ሽማግሌዎች የተሰጠ ማሳሰቢያ፦ ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር ውይይት የሚደረግበትን መንገድ የሚመለከት መመሪያ ከገጽ 208-212 ላይ ማግኘት ይቻላል።]