ደቀ መዛሙርት ማድረግ
ምዕራፍ 12
ግልጽነት
መሠረታዊ ሥርዓት፦ “ዘይትና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ በቀና ምክር ላይ የተመሠረተ ጥሩ ወዳጅነትም እንዲሁ ነው።”—ምሳሌ 27:9
ኢየሱስ ምን አድርጓል?
1. ቪዲዮውን ተመልከት፤ ወይም ማርቆስ 10:17-22ን አንብብ። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦
ሀ. ኢየሱስ፣ ወጣቱ ገዢ ምን ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት ተመልክቶ ሊሆን ይችላል?
ለ. ኢየሱስ ወጣቱን ለመምከር ፍቅርና ድፍረት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ከኢየሱስ ምን እንማራለን?
2. የምናስጠናቸው ሰዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በፍቅር ሆኖም በግልጽ ምክር ልንሰጣቸው ይገባል።
ኢየሱስን ምሰል
3. ተማሪው ግቦች እንዲያወጣና ግቦቹ ላይ እንዲደርስ እርዳው።
ሀ. ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ የሚገኘውን “ግብ” የሚለውን ክፍል ተጠቀም።
ለ. የምታስጠናው ሰው የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ግቦቹ ላይ ለመድረስ የሚረዱትን እርምጃዎች እንዲገነዘብ እርዳው።
ሐ. ለሚያደርገው እድገት በየጊዜው አመስግነው።
4. ተማሪው እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት የሚሆኑበትን ነገሮች ለይ፤ እንቅፋቶቹን እንዲወጣም እርዳው።
ሀ. ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦
‘የማስጠናው ሰው ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን እርምጃ እየወሰደ ካልሆነ እንቅፋት የሆነበት ነገር ምንድን ነው?’
‘በየትኞቹ መንገዶች ላግዘው እችላለሁ?’
ለ. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ምን ማድረግ እንዳለበት በፍቅር ሆኖም በግልጽ መንገር እንድትችል ድፍረት እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ።
5. እድገት የማያደርጉ ሰዎችን ማስጠናትህን አቋርጥ።
ሀ. የምታስጠናው ሰው እድገት እያደረገ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦
‘ግለሰቡ የተማረውን በተግባር እያዋለ ነው?’
‘በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል? የተማረውን እውነት ለሌሎች ይናገራል?’
‘ለተወሰነ ጊዜ ሲያጠና ቆይቷል፤ ይሁንና የይሖዋ ምሥክር መሆን ይፈልጋል?’
ለ. የምታስጠናው ሰው እድገት የማድረግ ፍላጎት ከሌለው፦
እንቅፋት የሆነበት ነገር ምን እንደሆነ ቆም ብሎ እንዲያስብ ጠይቀው።
ጥናቱን የምታቆመው ለምን እንደሆነ በደግነት ንገረው።
ጥናቱን መቀጠል ከፈለገ ምን ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ንገረው።