ነፃዪቱ ሴት
በባርነት ሥር ያልሆነች ሴት ማለት ነው። ይህ ስያሜ የተሠራበት የአብርሃምን ሚስት ሣራን እና ‘ላይኛይቱ ኢየሩሳሌምን’ ለማመልከት ነው። ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፃውያን ባርነት ነፃ አውጥቶ በሲና ተራራ ላይ ሕጉን ከሰጣቸው ጊዜ ጀምሮ የሕጉ ቃል ኪዳን በ33 ዓ.ም. እስካከተመበት ጊዜ ድረስ ይሖዋ የእስራኤልን ብሔር እንደ ሁለተኛ ሚስቱ አድርጎ ይመለከተው ነበር። (ኤር 3:14፤ 31:31, 32) ይሁን እንጂ ሕጉ እስራኤላውያን የኃጢአት ተገዢዎች ማለትም ባሪያዎች መሆናቸውን ስላጋለጠ የእስራኤል ብሔር እንደ ነፃ ሴት የመቆጠር መብት አላገኘም። በመሆኑም ጳውሎስ በእሱ ዘመን በባርነት ሥር የነበረችውን ኢየሩሳሌምን አገልጋይ ከነበረችው ከአብርሃም ቁባት ከአጋር ጋር፣ የኢየሩሳሌምን “ልጆች” ወይም ዜጎች ደግሞ ከአጋር ልጅ ከእስማኤል ጋር ማመሳሰሉ በጣም ተገቢ ነበር። በአንፃሩ ግን የአምላክ የመጀመሪያ ሚስት የሆነችው ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም እንደ ሣራ ሁሉ ነፃ ሴት ሆና የኖረች ሲሆን ልጆቿም እንደዚሁ ነፃ ናቸው። የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ልጅ ለመሆንና የእሷን ዓይነት ነፃነት ለማግኘት በአምላክ ልጅ አማካኝነት ከኃጢአት ባርነት ነፃ መውጣት የግድ አስፈላጊ ነው።—ገላ 4:22–5:1፤ ዮሐ 8:34-36