ለአምላክ ማደር
ለአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ታማኝ በመሆን ለእሱ የምናሳየው ጥልቅ አክብሮት፣ ለእሱ የሚቀርብ አምልኮና አገልግሎት። ቅዱሳን መጻሕፍት ኤፍሴቪአ የተባለውን የግሪክኛ ቃልና ከዚህ ቃል ጋር የተያያዙ ቅጥያዎችን ይጠቀማሉ። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃል “በሚገባ ማክበር” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፤ ይህም ሙሉ በሙሉ ቅዱስና ጻድቅ ለሆነ አካል አክብሮት ማሳየትን ወይም ታማኝ መሆንን ያመለክታል። (ከ2ጴጥ 1:6 [ኢንተርሊንየር] ጋር አወዳድር።) “ፈሪሃ አምላክ የሌለው” ወይም “አክብሮት የጎደለው” የሚሉት አገላለጾች “ለአምላክ ማደር” የሚለው ሐረግ ተቃራኒ ናቸው (ግሪክኛ፣ አሴቪአ)።
ናይጅል ተርነር ክርስቺያን ወርድስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ኤፍሴቪአ የሚለው ቃል በዚያ ዘመን በነበሩ ጽሑፎች ላይ በአብዛኛው የተሠራበት አንድ ሰው ለሃይማኖቱ ያደረ መሆኑን ለማመልከት ነው። . . . በሮማውያን ዘመን ይነገር በነበረው ግሪክኛ ግን በስፋት የተሠራበት ‘ታማኝነትን’ ለማመልከት ነው። . . . ለክርስቲያኖች ደግሞ ኤፍሴቪአ ለአምላክ ማደርን በከፍተኛ ደረጃ ለመግለጽ የሚያገለግል መግለጫ ነው።” (1981 ገጽ 111) “ለአምላክ ማደር” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት አንድ ሰው ያለውን ለይሖዋ አምላክ የማደር ባሕርይ ለማመልከት ነው።
ኤፍሴቬስ የተባለው ቅጽል “ለአምላክ ያደረ” የሚል ትርጉም ሲኖረው በሐዋርያት ሥራ 10:2, 7 እና በ2 ጴጥሮስ 2:9 ላይ ይገኛል። ኤ ኤች ቲትማን እንደሚሉት ኤፍሴቬስ የሚለው ቃል “ለአማልክት የሚሰጠውን ክብር በተለይም ደግሞ ለእውነተኛው አምላክ የሚቀርበውን አምልኮ የሚያሳይ ሲሆን ይህም በተግባር የሚገለጽ ነገር ነው፤ . . . ለአምላክ ያደረ ሰው [ኤፍሴቬስ] የቅድስና ተግባር ያከናውናል።—ሪማርክስ ኦን ዘ ሲኖኒምስ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት፣ ኤድንበርግ 1833፣ ጥራዝ 1 ገጽ 253, 254
ኤፍሴቬኦ የተባለው ግስ በ1 ጢሞቴዎስ 5:4 ላይ ልጆች ወይም የልጅ ልጆች መበለት ለሆኑ እናቶቻቸው ወይም አያቶቻቸው ሊያሳዩ ከሚገባው ምግባር ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል። በኤድዋርድ ሮቢንሰን (1885 ገጽ 307) የተዘጋጀው ኤ ግሪክ ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደሚለው ኤፍሴቬኦ የሚለው ቃል ለማንኛውም አካል የሚደረግን የጽድቅ ሥራ ሊያመለክት ይችላል። በዚህ ምክንያት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል” በማለት ተርጉመውታል።” (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይሁን እንጂ የቤተሰብን ዝግጅት ያቋቋመው አምላክ ነው፤ (ኤፌ 3:14, 15) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ቤት ከቤተሰብ ጋር ያመሳስለዋል። ስለዚህ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ አክብሮት ወይም ለአምላክ የማደር ባሕርይ ማሳየት፣ አምላክን በጥልቅ ማክበር እንዲሁም ከቤተሰብና የቤተሰብ አባላት ሊኖራቸው ከሚገባው ተገቢ ምግባር ጋር በተያያዘ ለሰጠው መመሪያ ታዛዥ መሆን ማለት ነው። አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ጥቅስ “አንዲት መበለት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ካሏት እነዚህ ልጆች በመጀመሪያ በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅን . . . ይማሩ” ብሎ መተርጎሙ ከዚህ ሐሳብ ጋር ይስማማል።
“ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር።” ለአምላክ በማደር ረገድ ዋነኛው ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “በእርግጥም ይህ ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፦ ‘በሥጋ እንዲገለጥ ተደረገ፤ በመንፈስ ጻድቅ ተባለ፤ ለመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፤ በዓለም ያሉ አመኑበት፤ በክብር አረገ።’” (1ጢሞ 3:16) ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ለአምላክ በማደር ረገድ ፍጹም የሆነ አርዓያ አልተወም። ልጆቹም ቢሆኑ ፍጽምና የጎደላቸው ሆነው ስለተወለዱ ይህን ማድረግ አልቻሉም። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚችለው ማነው? የአምላክ ልጅ ወደ ምድር መምጣቱና ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መኖሩ ይህ ቅዱስ ሚስጥር ምን እንደሆነ እንዲታወቅ አድርጓል። ጢሞቴዎስ ለአምላክ የማደር ባሕርይ በማሳየት ረገድ ፍጹም የሆነ አርዓያው አድርጎ መከተል የሚኖርበት ኢየሱስን ነው።—1ጢሞ 3:15
ለአምላክ የማደር ባሕርይን በሁሉም ነገር ፍጹም በሆነ መልኩ ማሳየት የቻለው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሲሆን ይህም ሰዎች ይህን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ማሳየት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። ኢየሱስ ከባድ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ምድራዊ ሕይወቱን እስኪያጠናቅቅ ድረስ “ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣ ከኃጢአተኞች የተለየ” መሆኑን አስመሥክሯል። (ዕብ 7:26) ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ረገድ በአምላክ ፊት ሊያስከስሰው የሚችል አንዳች ጉድለት አልተገኘበትም። ከመሞቱ በፊት “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” እንዲሁም “የዚህ ዓለም ገዢ . . . በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም” በማለት መናገር ችሏል። (ዮሐ 16:33፤ 14:30) ምንም ዓይነት ኃጢአት አልተገኘበትም። ጠላቶቹን “ከመካከላችሁ እኔን ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ በማስረጃ ሊወነጅለኝ የሚችል ማን ነው?” ብሎ ጠይቋቸዋል። (ዮሐ 8:46) “ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር” ምንነት መገለጡ በመላው የሰው ዘር ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም በመላው ዓለም መታወጅ ይኖርበታል። ክርስቲያኖች የሚያሳዩት ለአምላክ የማደር ባሕርይና በጉባኤ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ምግባር ኢየሱስ ክርስቶስ በተወው አርዓያ ላይ የተመሠረተ ነው።
ራስን ማሠልጠንና ባለን ነገር ረክተን መኖር አስፈላጊ ነው። አንድ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ለማደር ከፈለገ ከባድ ሥልጠና ማግኘት ይኖርበታል። ተቃውሞና ስደትን መቋቋም ይጠይቃል። (2ጢሞ 3:12) አንድ ሰው ራሱን የሚያሠለጥንበት ዓላማ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት መሆን የለበትም። ያለኝ ይበቃኛል የሚል ማለትም ለአምላክ ያደረና ባለው ነገር ረክቶ የሚኖር ሰው ትልቅ ጥቅም ያገኛል። እንዲህ ያለው ሰው በመንፈሳዊ ጤናማ ስለሚሆን እንዲሁም እርካታ፣ ደስታና ዓላማ ያለው ሕይወት ስለሚኖረው ‘ለአሁኑ ሕይወቱ ተስፋ’ ይኖረዋል። በተጨማሪም “ለወደፊቱ ሕይወት ተስፋ” ይኖረዋል።—1ጢሞ 4:7, 8፤ 6:6-8፤ ምሳሌ 3:7, 8፤ 4:20-22
ለአምላክ ያደረ ሰው የተለያየ ስደትና መከራ ሊያጋጥመው ይችላል፤ ይሁንና “ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” ስለሚያውቅ አይፈራም። (2ጴጥ 2:9) ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን በጽናት ላይ ለአምላክ ማደርን እንዲጨምሩ መክሯል። (2ጴጥ 1:5, 6) በይሖዋ ቀን ከሚመጣው ፍርድ ለመትረፍ ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር መከተልና ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ተግባሮችን መፈጸም’ እንዳለባቸው መክሯቸዋል።—2ጴጥ 3:7, 10, 11፤ 1ጴጥ 4:18
ለአምላክ ማደር ያለው ኃይል። አንድ ሰው ለአምላክ የማደር ባሕርይ አለኝ ሊል የሚችለው ይህ ባሕርይ ማንነቱን የመለወጥ ኃይል እንዳለው አምኖ ሲቀበል እንዲሁም ከልቡና እውነተኛ በሆነ መንገድ ለአምላክ ያደረ መሆኑን ሲያሳይ ነው። (1ጢሞ 6:11፤ ኤፌ 4:20-24) የአምላክ ቃል ለአምላክ የማደር ባሕርይ ምን ማለት እንደሆነ አምላክ የገለጸበት መጽሐፍ መሆኑን መገንዘብ እንዲሁም በውስጡ ከሰፈሩት ትእዛዛትና ደንቦች ጋር ተስማምቶ መኖር አለበት። (ቲቶ 1:1፤ 2ጴጥ 1:3) ለአምላክ ማደር በቀጥታ ከአምላክ ጋር የሚያገናኝ ባሕርይ በመሆኑ ቃሉና መንፈሱ አንድ ሰው ይሖዋን በቅርበትና በጥልቀት እንዲያውቀው እንዲሁም እሱን ይበልጥ እየመሰለ እንዲሄድ ይረዳዋል። (ኤፌ 5:1) እንዲህ ያለው ሰው የይሖዋ አምላክን ግሩም ባሕርያት በተሻለ ሁኔታ ያንጸባርቃል።—2ቆሮ 3:18
አንድ ሰው አምላክን አገለግላለሁ እያለ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በጥብቅ ከመከተል ይልቅ በራሱ አስተሳሰብ የሚመራ ከሆነ እንዲሁም የሚያስተምረው ትምህርት ‘ለአምላክ ማደርን የሚያበረታታ’ ካልሆነ በሌላ አባባል አስተማሪው ለአምላክ ያደረ እንዳልሆነ የሚያሳይ ከሆነ ይህ ሰው “የመከራከር አባዜ የተጠናወተው” ነው ማለት ነው። (1ጢሞ 6:3, 4) ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ አምላክ የለሽ ሰዎችን አስመልክቶ ከእሱ በዕድሜ ለሚያንሰው የአገልግሎት ባልደረባው ለጢሞቴዎስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል። ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንዳይተው የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮች እንዲርቅ ጢሞቴዎስን መክሮታል። ከዚያም የተለያዩ የክፋት ድርጊቶችን የሚፈጽሙና ለአምላክ ያደሩ መስለው የሚታዩ በሥራቸው ግን ኃይሉን የሚክዱ ግብዝ ሰዎች እንደሚኖሩ ተናግሯል። (2ጢሞ 2:15, 16፤ 3:1-5) ይሁዳም፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች ፈሪሃ አምላክ እንደሌላቸው ወይም ለአምላክ ያደሩ እንዳልሆኑ እንዲሁም ለአምላክ ጸጋ ምንም ዓይነት አድናቆት እንደሌላቸው ገልጿል። እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ማደርን ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ይጠቀሙበታል። የሚፈጽሙት ዓይን ያወጣ ምግባር ግብዝ እንደሆኑ ይመሠክራል።—ይሁዳ 4
ጳውሎስ “ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ” በማለት የጠራው ምንድን ነው?
ይህ ከይሖዋ “ቅዱስ ሚስጥር” ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ሌላ ሚስጥር ነው። ይህ ‘ሚስጥራዊ የሆነ ዓመፅ’ ነው። ይህ “የዓመፅ ሰው” በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ሙሉ በሙሉ ስላልተቋቋመና ማንነቱ ግልጽ ስላልነበር ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ሚስጥር ነበር። ይህ “ሰው” በይፋ ከተቋቋመ በኋላም ቢሆን ለአብዛኛው የሰው ዘር ማንነቱ ሚስጥር ሆኖ ቀጥሏል፤ ምክንያቱም ክፋቱን የሚፈጸመው ማንነቱን ደብቆና ለአምላክ ያደረ በመምሰል ነው። እንዲያውም በትክክል ለአምላክ ካደሩ ሰዎች መካከል የሚነሳ ከሃዲ ነው። ጳውሎስ “ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ” በእሱ ዘመንም እንደነበር ተናግሯል፤ ምክንያቱም ውሎ አድሮ የዚህ ከሃዲ ቡድን አባላት የሚሆኑት ዓመፀኞች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነበር። በመጨረሻም ይህ የዓመፅ ሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ ይወገዳል። ይህ ከሃዲ ማለትም ሰይጣን የሚጠቀምበት ይህ “ሰው” “አምላክ ተብሎ ከሚጠራ ወይም ከሚመለክ ነገር (በግሪክኛ ሰባስማ) ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ” ያደርጋል። በመሆኑም የሰይጣን መሣሪያ የሆነው ይህ ዋነኛ የአምላክ ተቃዋሚ ከፍተኛ የሆነ ማታለል ኃይል አለው፤ እንዲሁም የእሱ ዓይነት ድርጊት በሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ላይ ጥፋት ይመጣባቸዋል። “የዓመፅ ሰው” ይህን ያህል የሚሳካለት፣ ክፋቱን የሚፈጽመው ለአምላክ ያደረ መስሎ ስለሆነ ነው።—2ተሰ 2:3-12፤ ከማቴ 7:15, 21-23 ጋር አወዳድር።