ሱራፌል
በሰማይ በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ የሚቆሙ መንፈሳዊ ፍጥረታት። (ኢሳ 6:2, 6) ሴራፊም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “መቃጠል” የሚል ትርጉም ካለው ሳራፍ የተባለ ግስ የተገኘ ብዙ ቁጥርን የሚያመለክት ስም ነው። (ዘሌ 4:12) እንዲያውም ሴራፊም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የሚቃጠል” ወይም “የሚንበለበል” ማለት ነው። ቃሉ በሌሎች ቦታዎች ላይ በነጠላም (ዕብ.፣ ሳራፍ) ሆነ በብዙ ቁጥር የተሠራበት ሲሆን የሚያመለክተውም በምድር ያሉ ፍጥረታትን ነው። በዚህ መልኩ ሲሠራበት “መርዘኛ” እና “የሚያቃጥል” የሚል የተለያየ ፍቺ ተሰጥቶታል።—ዘኁ 21:6, 8 ግርጌ
ነቢዩ ኢሳይያስ የተመለከተውን ራእይ እንዲህ በማለት ገልጾልናል፦ “ንጉሥ ዖዝያ በሞተበት ዓመት ይሖዋን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፎች ነበሯቸው። እያንዳንዱ በሁለቱ ክንፍ ፊቱን ይሸፍን፣ በሁለቱ ክንፍ እግሩን ይሸፍን፣ በሁለቱ ክንፍ ደግሞ ይበር ነበር። አንዳቸውም ሌላውን እንዲህ ይሉ ነበር፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው። መላዋ ምድር በክብሩ ተሞልታለች።’ . . . በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ ‘ወዮልኝ! ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ስለሆንኩና የምኖረውም ከንፈራቸው በረከሰ ሕዝብ መካከል ስለሆነ በቃ መሞቴ ነው፤ ዓይኖቼ ንጉሡን፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ራሱን አይተዋልና!’ በዚህ ጊዜ ከሱራፌል አንዱ ወደ እኔ እየበረረ መጣ፤ እሱም ከመሠዊያው ላይ በጉጠት ያነሳውን ፍም በእጁ ይዞ ነበር። አፌንም ነክቶ እንዲህ አለኝ፦ ‘እነሆ፣ ይህ ከንፈሮችህን ነክቷል። በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኃጢአትህም ተሰርዮልሃል።’”—ኢሳ 6:1-7
እዚህ ላይ ስለተጠቀሰው መለኮታዊ አካል የተሰጠ መግለጫ የለም። ይሁን እንጂ ግርማ ያለው ልብሱ ዘርፍ፣ ምንም መቆሚያ ቦታ እስኪታጣ ድረስ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ዙፋኑ ምንም ነገር ላይ አላረፈም፤ ይሁን እንጂ ‘ረጅምና ከፍ ያለ’ ነበር። ሱራፌል “ቆመው” ነበር ሲባል ከክንፎቻቸው መካከል በሁለቱ ተጠቅመው ያንዣብቡ ነበር ማለት ሊሆን ይችላል፤ ይህም በምድረ በዳ በነበረው የይሖዋ ድንኳን መግቢያ ላይ ‘ይቆም’ ወይም ያንዣብብ ከነበረው ደመና ጋር የሚመሳሰል ነው። (ዘዳ 31:15) ፕሮፌሰር ፍራንዝ ዴሊች ሱራፌል ስለቆሙበት መንገድ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ሱራፌል ዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው አካል በላይ እንደማይቆሙ የታወቀ ነው፤ ከዚህ ይልቅ አዳራሹን ሞልቶት ከነበረው ልብሱ በላይ ያንዣብቡ ነበር።” (ኮሜንታሪ ኦን ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ 1973 ጥራዝ 7 ክፍል 1 ገጽ 191) የላቲኑ ቩልጌት “ሱራፌልም ከእሱ በላይ ቆመው ነበር” ከማለት ይልቅ “ከዙፋኑ” በላይ እንደቆሙ ይናገራል።—ኢሳ 6:1, 2
ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው። እነዚህ በሰማይ ያሉ ኃያላን ፍጥረታት መላእክት ሲሆኑ በአምላክ ዙፋን አካባቢ ቆመው ስለታዩ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንዳላቸው ግልጽ ነው። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የታዩት ኪሩቦች ከአምላክ ሰማያዊ ሠረገላ ጎን እንደሚሮጡ ተገልጿል። (ሕዝ 10:9-13) በሰማይ ላይ የተለያየ ማዕረግ ወይም ሥልጣን መኖሩ ‘በሰማያትና በምድር ስላሉ፣ ስለሚታዩና ስለማይታዩ ነገሮች፣ ስለ ዙፋኖችም ሆነ ስለ ጌትነት፣ ስለ መንግሥታትም ሆነ ስለ ሥልጣናት’ ከሚናገረው በቆላስይስ 1:16 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው።
ሥራቸውና ያለባቸው ኃላፊነት። የሱራፌል ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ የተጠቀሰ ነገር ባይኖርም እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ እንደነበር ተገልጿል፤ ይህም በቡድን ተከፋፍለው በዙፋኑ የተለያዩ ጎኖች ላይ ቆመው እየተቀባበሉ በመዘመር የይሖዋን ቅድስናና ግርማ ያወድሱ እንደነበር የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም፤ ይህን የሚያደርጉት አንዳቸው (ወይም አንደኛው ቡድን) ሌላው ያለውን በመድገም አሊያም “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው። መላዋ ምድር በክብሩ ተሞልታለች” የሚለውን ስንኝ ተከፋፍለው ተራ በተራ በመዘመር ሊሆን ይችላል። (ሕጉ በሚነበብበት ወቅት ሕዝቡ በምን መንገድ ምላሽ ይሰጥ እንደነበር ከሚገልጸው በዘዳ 27:11-26 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር አወዳድር።) በሁለቱ ክንፎቻቸው ፊታቸውን የሚሸፍኑት ከሁሉ የላቀ በሆነው አምላክ ፊት ስለቆሙ ትሕትናና አክብሮት ለማሳየት ሲሉ ነው፤ በሌላኛው ሁለት ክንፍ እግራቸውን የሚሸፍኑት ደግሞ ቅዱስ በሆነ ስፍራ የሚገኙ በመሆናቸው ለሰማያዊው ንጉሥ የሚገባውን ክብር ለማሳየት ሲሉ ነው።—ኢሳ 6:2, 3
ሱራፌል የአምላክን ቅድስና ማወጃቸው ምድርን ጨምሮ በመላው ጽንፈ ዓለም ቅዱስና ሊከበር የሚገባው አምላክ መሆኑን ከማሳወቅ ጋር በተያያዘ የሚያከናውኑት ሥራ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። ከሱራፌል አንዱ የኢሳይያስን ኃጢአትና በደል ለማንጻት ከመሠዊያው ላይ በወሰደው ፍም የኢሳይያስን ከንፈሮች ዳሷል። ይህም የተሰጣቸው ኃላፊነት የአምላክን ሕዝቦች ከኃጢአት ከማንጻት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል፤ ይህ የማንጻት ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ መሠዊያ ላይ ባቀረበው መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ ነው።—ኢሳ 6:3, 6, 7
በራእዩ ላይ የታዩበት መንገድ። ሱራፌል እግር፣ ክንፍና እንደዚህ የመሳሰሉ ነገሮች እንዳላቸው ተደርጎ መገለጹ ምሳሌያዊ እንደሆነ ማስተዋል ይገባል፤ በምድር ያሉ ፍጥረታት ያላቸው ዓይነት የአካል ክፍል እንዳላቸው ተደርጎ የተገለጸው ችሎታቸውን ወይም የሚያከናውኑትን ሥራ ለማጉላት ሲባል ነው፤ አምላክም ቢሆን እንደ ሰዎች ዓይን፣ ጆሮና ሌሎች አካላት እንዳሉት በምሳሌያዊ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ተናግሯል። ሐዋርያው ዮሐንስ የአምላክን መልክ ማንም ሰው አይቶት እንደማያውቅ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱን በእርግጥ እናየዋለን።”—1ዮሐ 3:2