የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በባሕላዊ ወግ ላይ ድል ይቀዳጃል
ሃይማኖታዊ ወግ በጣም ሥር የሰደደ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች ሃይማኖትን መለወጥ ስህተት ነው ብለው ያስባሉ። በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የሆነው ሳውል እንደሚከተለው ሲል በመናገሩ እንዲሁ ተሰምቶት እንደነበረ ግልጽ ነው። “ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።” (ገላትያ 1:13-16) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከባሕላዊ ወግ ከሚበልጥ ከፍተኛ ምንጭ እንደሚመጣ ሊገነዘቡ ችለዋል። በኢጣልያ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዴት ድል እንደተቀዳጀ ተመልከቱ።
አንዲት ሴት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “እህቴና እኔ ለረዥም ጊዜ የኖረ የካቶሊክ ወግ በሚከተል አንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ አደግን። ስለዚህ እኛም ቀናተኛ ካቶሊኮች ነበርን። ከጊዜ በኋላ አገባሁ። ከዚያም ባሌን በሞት አጣሁና ለብዙ ዓመታት ከልጆቼ ጋር ብቻዬን ተቀመጥኩ። የእህቴ ልጅ በጥያቄና መልስ የተዘጋጀ የሃይማኖት ትምህርት ታስተምር ስለነበር ቄሱን አዘውትራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ትጠይቀው ነበር። ሆኖም ምንም አጥጋቢ መልስ አላገኘችም።
“ወደተወለድኩባት ከተማ ቤተሰብ ለመጠየቅ ስሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልኝ የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። የቀድሞ የካቶሊክ ጓደኞቼ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቴ አፌዙብኝ። ይሁን እንጂ ተበሳጭቼ ጥናቴን አልተውኩም። ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ሆንኩ። ይህንንም ማንም አልቀማኝም። እህቴም ለይሖዋ አቋም ወሰደችና ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ሁለታችንም ተጠመቅን።
“ለመጀመሪያ ጊዜ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስለይ ለ76 ዓመታት በውስጤ የተተከሉትን ወጎች መተውን ስለፈራሁ አለቀስኩ። አሁን ግን በይሖዋ መንገዶች በመመላለሴና ሌሎችም ከሃይማኖታዊ ጨለማ እንዲወጡ የተቻለኝን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ።”—ከ1 ጴጥሮስ 2:9 ጋር አወዳድር።
የፀጉር አስተካካዩ የተሳሳተ አስተሳሰቡን አረመ
በጃፓን አገር የሚኖር አንድ ፀጉር አስተካካይ የደንበኞቹን ፀጉር በሚያስተካክልበት ጊዜ ስለ አጋንንትና ኡፎ (UFO)(ያልታወቁ በራሪ ነገሮች)ማውራት ደስ ይለው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ በኋላ ግን ይህ ድርጊት አደገኛ መሆኑን ተገነዘበ። ስለዚህም ይህን ከማድረግ ይልቅ ደንበኞቹ አብረውት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ጋበዛቸው። ለወጣት ደንበኞቹ ስለ ፍጥረት መሰከረላቸው፤ ለደንበኞቹ ለማበርከት ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስጠናው ወንድም መጽሐፍ ቅዱስንና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚባለውን መጽሐፍ ቅጂ በየሣምንቱ ይጠይቅ ነበር።
ገና የይሖዋ ምሥክር ሳይሆን ማጥናት በጀመረበት ዓመት ከ30 በላይ መጽሐፍ ቅዱሶችና ለዘላለም መኖር መጽሐፎችን አበርክቷል። እርሱ ባደረገው ያጋጣሚ ምሥክርነት ምክንያት ከ25 በላይ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። በቡድን በሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ላይ አንዳንዴ እስከ አሥር የሚደርሱ ሰዎች ይሳተፉ ነበር። ፀጉራቸውን ሲያስተካክል የመሠከረላቸው ሰባት ሰዎች የተሳሳተ አስተሳሰባቸውን አርመው አሁን የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል!