የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ ወጣቷ አይሁዳዊት ሴት አስቴር በንጉሡ ፊት ሞገስና በዚያውም ጥቅሞችን ለማግኘት ከፋርሱ ንጉሥ ጋር ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ የጾታ ግንኙነት ፈጽማ ነበር?
ከዓለማዊ ትረካ በመነሳት አንዳንዶች ወደዚህ መደምደሚያ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው አስተማማኝ ታሪክ ይህን ግምታዊ አስተሳሰብ ይቃረናል።
አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ የፋርስ ንግሥት በባሏ በንጉሥ አርጤክስስ ፊት ለመታየት እንቢ እንዳለች የሚገልጽ ዓለማዊ ዘገባ ያቀርብልናል። በዚህ ምክንያት በ5ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረው አርጤክስስ ቀዳማዊ ለቁጣ ተነሳስቶ አስጢንን ተዋትና አዲስ ንግሥት ለማግኘት በግዛቱ ሁሉ ፍለጋ እንዲካሄድ ተስማማ። ውብ የሆኑ ወጣት ደናግል ተሰበሰቡና ረጅም ጊዜ የወሰደ የቁንጅና አያያዝ ዝግጅት ተደረገላቸው።
“ከዚያም [የንጉሡ ጃንደረባ] ደናግሉ በቂ እንክብካቤ እንደተደረገላቸውና ወደ ንጉሡ አልጋ ለመምጣት መብቃታቸውን ሲያምንበት በየቀኑ አንዲቱ ድንግል ከንጉሡ ጋር እንድትተኛ ይልክ ነበር። ንጉሡም ከድንግሊቱ ጋር ግንኙነት ካደረገ በኋላ ወዲያው ወደ ጃንደረባው መልሶ ይልካት ነበር። አስቴር ወደ ንጉሡ በመጣች ጊዜ ግን ደስ አሰኘችው ወደዳትም ሕጋዊ ሚስቱም አደረጋትና ጋብቻቸውን አከናወኑ።” (ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ 11ኛ መጽሐፍ 184-202 በራልፍ ማርከስ የተተረጎመ፤ ወይም 11ኛ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 አንቀጽ 1ና 2 በዊልያም ዊስተን ትርጉም)
ይህ ዓለማዊ የታሪክ ምንጭ አንድን ሰው ልጃገረዶቹ ከንጉሡ ጋር የጾታ ብልግና እንደፈጸሙና አስቴርን ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርጋት የእርስዋ የጾታ ብልግና ድርጊት ወደ ጋብቻና ንግሥት ወደመሆን ሊመራት መቻሉ ብቻ ነው ብሎ ወደማሰብ ሊመራው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይበልጥ ትክክለኛና አጥጋቢ ሐሳብ ያቀርብልናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለቁንጅናው ዝግጅቶች ከገለጸ በኋላ እንዲህ ይላል፦ “በዚህ ወግ ቆንጆይቱ ወደ ንጉሡ ትገባ ነበር፤ . . . ማታም ትገባ ነበር፣ ሲነጋም ተመልሳ ወደ ሁለተኛው ሴቶች ቤት ቁባቶችን ወደሚጠብቅ ወደ ንጉሡ ጃንደረባ ወደ ጋይ ትመጣ ነበር፤ ንጉሡም ያልፈለጋት እንደ ሆነ፣ በስምዋም ያልተጠራች እንደ ሆነ፣ ከዚያ ወዲያ ወደ ንጉሡ አትገባም ነበር።”—አስቴር 2:13, 14
ቅዱሳን ጽሑፎች ረጅም ጊዜ ለሚወስደው የቁንጅና ዝግጅት አስቴር “ወደ ሴቶች” ቤት “እንደተወሰደች” ይናገራሉ። “ከዚያም . . . አስቴር ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ተወሰደች፣ ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፣ በዓይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ የመንግሥቱንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ፣ በአስጢንም ፋንታ አነገሣት” ይላል።—አስቴር 2:8, 9, 16, 17
ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሴቶቹ ከንጉሡ ጋር ካደሩ በኋላ ወዴት እንደተወሰዱ አስተውላችኋልን? “ወደ ሁለተኛው ሴቶች ቤት ቁባቶችን ወደሚጠብቅ ወደ ንጉሡ ጃንደረባ” ነበር። ስለዚህ ቁባቶች ሆነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ መርዶክዮስ አይሁዳዊ ነበር። በዚያን ጊዜ በእርሱ ሕዝቦች (በአይሁዳውያን) መካከል ቁባት የሁለተኛ ሚስትነት ቦታ ነበራት። መለኮታዊው ሕግም አንድ እሥራኤላዊ ወንድ በጦርነት ወቅት የተማረከች አንዲት የባዕድ አገር ልጃገረድን ሊወስዳት እንደሚችል ከፈቀደ በኋላ ቁባቱ ወይም ሁለተኛ ሚስቱ ሊያደርጋት እንደሚችልና ከተለያዩ መብቶች ጋር ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላት አዟል። (ዘዳግም 21:10-17፤ ከዘፀአት 21:7-11 ጋር አወዳድር።) ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሕጋዊ ቁባቶች የተወለዱ ልጆች ሕጋዊ ልጆች ናቸው። ስለዚህ ውርሻም ሊያገኙ ይችላሉ። የአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ አባቶች የሆኑት የያዕቆብ 12ቱ ልጆች የሚስቶቹና የሕጋዊ ቁባቶቹ ልጆች ነበሩ።—ዘፍጥረት 30:3-13
በሥርዓቱ መሠረት ደናግሉ ከንጉሡ ጋር ካደሩ በኋላ ወደ ቁባቶች ቤት ይላኩ ነበር። ይህም የሚያመለክተው ሁለተኛ ሚስቶቹ እንደሚሆኑ ነው።
ታዲያ የአስቴር ሁኔታ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ከንጉሡ ጋር ስለተኛች ሞገስን አገኘች አይልም። ወደ ቁባቶች ቤት ስለ መወሰዷም አይናገርም። ነገር ግን በአጭሩ፦ “አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች። ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ” ይላል። ቀደም ሲልም ገና ድንግል ሳለች በጨዋነቷ በሴቶች ጠባቂው በሐጌ ፊት ሞገስን እንዳገኘች አስታውሱ። በተጨማሪም “አስቴር በሚያዩአት ሁሉ ዓይን ሞገስ አግኝታ ነበር።” (አስቴር 2:8, 9, 15-17) ስለዚህ በግልጽ እንደምንረዳው ንጉሡን ማረከችው። ከሌሎች ክብርን እንዳገኘችው ሁሉ የንጉሡንም አክብሮት ለማግኘት ቻለች።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርብልንን ማስረጃዎችና ማስተዋል በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች መሆን እንችላለን! ምንም እንኳን ድርጊቶቹ ከተፈጸሙ በሺህ በሚቆጠሩ ዓመታት ርቀን የምንኖር ብንሆንም አስቴር በእውነተኛ ጥሩ ምግባርና ከአምላካዊ ሥርዓቶቹ ጋር በመስማማት ውሳኔ እንዳደረገች እርግጠኞች ለመሆን በቂ ምክንያት አለን።