አከራካሪው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይህን ያህል ጊዜ ለምን ፈጀ?
ከ6,000 ዓመታት በፊት የአምላክ የበላይ ገዥነት ጉዳይ አጠያያቂ አልነበረም። አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎችን ሲፈጽም “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍጥረት 1:31) ከዚያ በኋላ ወደ ረዥም “የዕረፍት” ጊዜ ገባ። እርግጥ ያ ማለት አካላዊ ድካም ተሰምቶት ነበር ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምድራዊ ፍጥረቶቹን በሚመለከት የነበረው መልካም ዓላማ እንደሚሳካ እርግጠኛ በመሆን በምድር ላይ ሲሠራው የቆየውን ፍጥረታዊ ሥራውን ስላቆመ አረፈ ማለት ነው።—ዘፍጥረት 2:1-3፤ ኢሳይያስ 55:11
ያ ዓላማው ምን ነበር? ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት የኤደን ገነት በተባለ ቦታ አስቀመጣቸው። የመጀመሪያው ኃላፊነታቸው የተለያዩ እንስሳቶቿን ጨምሮ ገነታዊ ቤተሰባቸውን መከባከብ ነበር። ከዚህም ሌላ ልጆችን መውለድና ማሳደግ ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ቤተሰባቸው እየበዛ ሲሄድ “ምድርን እንዲገዟት” አምላክ የሰጣቸውን ትዕዛዝ በመፈጸም ገነታቸውን እስከ ምድር ዳርቻ ማስፋፋት ነበረባቸው። በዚህ መንገድ ምድር እያደር በደስተኛና ፈጣሪያቸውን በሚያገለግሉ የተባበሩ ቤተሰቦች የተሞላች ዕፁብ ድንቅ ቤት ልትሆን ነበር። ያ ነበር የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:8, 15, 20-22
አዳምና ሔዋን ይህን ታላቅ ዓላማ ከግቡ ለማድረስ በሚደረገው ሥራ ይካፈሉ ይሆንን? ያ የተመካው ፈጣሪያቸውን በመታዘዝ ከዓላማው ጋር ተስማምተው መሥራታቸውን በመቀጠላቸው ላይ ነበር። ታዛዥነታቸው የማሰብ ችሎታ ያልታከለበትና እንዲሁ ጭፍን መሆን አልነበረበትም። አምላክ ከአድናቂ ልብ የተነሣ እንዲያገለግሉት ይፈልግ ስለነበረ ነፃ ምርጫ ተሰጥቷቸው ነበር። ሕጋዊ የበላይ ገዥነቱን ያስታውሳቸው ዘንድ በጣም ቀላል ፈተና አቀረበላቸው። ከአንዱ በስተቀር በገነት ከነበረው የምግብ አቅርቦት በሙሉ ሊካፈሉ ይችሉ ነበር። አምላክ “ከሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ብሎ የተናገረለት አንድ የፍሬ ዛፍ ነበር።—ዘፍጥረት 2:16, 17
እነዚህ ቃላት አዳምና ሔዋን ለማርጀትና ለመሞት እንዳልተፈጠሩ ይነግሩናል። ሞት የሚመጣው ይህን ቀላል ትዕዛዝ ካፈረሱ ብቻ ነበር። አዳምና ሔዋን ለአምላክ ታዛዥ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ በምድር ዙሪያ የፍጹም ዘሮች ቤተሰብ ወላጆች በመሆን እስከ አሁን ይኖሩ ነበር።—በመዝሙር 37:29 ላይ የተገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት ተመልከት።
ይሁን እንጂ አሁን ሰይጣን የሚባለው ከአምላክ መላእክታዊ ፍጥረቶች አንዱ የአምላክን አገዛዝ ነቀፈ። ከአምላክ የበላይ ገዥነት ወጥተው በራሳቸው ቢመሩ እንደሚሻላቸው የሚያታልል ሐሳብ ለሔዋን በማቅረብ ከተከለከለው ፍሬ እንድትበላ መከራት። ሰይጣን ይህን ሲናገር በውስጡ የነበረው እውነተኛ ፍላጎት ግን የመጪው የሰው ዘር ቤተሰብ አምላክ ለመሆን የነበረው ምኞት ነበር።—ዘፍጥረት 3:1-5፤ ማቴዎስ 4:8, 9፤ ዮሐንስ 8:44
ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሰጥቷቸው ስለነበር ሔዋን የይሖዋን የበላይ ገዥነት መደገፍና ሰይጣን ያቀረበውን ሐሳብ ውድቅ ማድረግ ነበረባት። የሚያሳዝነው ግን ቀድማ በመሄድ የአምላክን ሕግ አፈረሰች። በኋላም አዳም ጥበብ በጐደለው ተግባሯ ከሚስቱ ጋር መተባበርን መረጠ። በመሆኑም በራሳቸው ሐሳብ የሚመሩት ባልና ሚስትና ሰይጣን በአምላክ ላይ ዐመጹና የመለኮታዊው የበላይ ገዥነት ጥያቄ ተነሣ።—ዘፍጥረት 3:6
ዋና ዋናዎቹን ጥያቄዎች ለመመለስ ጊዜ አስፈለገ
ይሖዋ ሦስቱን ዐመጸኞች እዚያው ቦታ ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ በዐመጻቸው ለተነሣው ጥያቄ በማያጠራጥር ሁኔታ መልስ ሊያስገኝ አይችልም ነበር። ሰው ከአምላክ ተለይቶ ራሱን በተሳካ ሁኔታ መግዛት ይችል ይሆን? ሰው ለበላይ ገዥነቱ እንዲገዛ አምላክ መጠየቁስ ፍትሕ ነበርን? ከዚህም ሌላ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ካሳዩት ጠባይ አንጻር በሰይጣን በሚፈተኑበት ጊዜም ቢሆን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ አምላክን በገዛ ፈቃዳቸው ማገልገል የሚመርጡ ሰዎች ይኖሩ ይሆንን? (ኢዮብ 1:7-11፤ 2:4) እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ጊዜ ያስፈልግ ነበር። እንዲሁም የዚያን የመጀመሪያውን ዓመጽ ውጤቶች ለማስወገድ ምድርን በኃጢአት አልባ የሰው ዘሮች የተሞላች ገነት ለማድረግ የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም ጊዜ ይወስድ ነበር። ለእነዚህ ጥያቄዎች የመጨረሻ መልስ አሁንም እየተጠባበቅን ነው።
ከሰጠው ሕግ ጋር በመስማማት አምላክ አዳምንና ሔዋንን የዘላለም ሕይወት መብት ወሰደባቸው። ከዚያ ወዲያ በታላቅ ዓላማው አፈጻጸም ለማካፈል የማይበቁ ሆኑ። ይሁን እንጂ ከመሞታቸው በፊት ልጆች እንዲወልዱና እንዲያሳድጉ ተፈቀደላቸው። እርግጥ ነው አዳምና ሔዋን ለዘሮቻቸው ብሩሕና ኃጢአት የለሽ ሕይወት ሊያስተላልፉ አልቻሉም። (ሮሜ 5:12) ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ተከታዮቹ ትውልዶች ፍጽምና የሌላቸውና ሞት የተፈረደባቸው ሆነው ቢወለዱም ብዙ ግለሰቦች በበላይ ገዥነቱ ጥያቄ ረገድ አቋማቸው ምን እንደሆነ ለማሳየት አጋጣሚ ነበራቸው።
ለጥያቄው መፍትሔ መስጠት
አምላክ ከበላይ ገዥነቱ ጋር የተያያዙትን እነዚህን ጉዳዮች መፍትሔ የሚሰጣቸው እንዴት ነው? በአንድ በኩል ያኔ በኤደን ገነት የተነሱት ጥያቄዎች አሁንም መልስ አግኝተዋል። ሔዋን ከአምላክ ፈቃድ ወጥታ በራስ ብትመራ እንደሚሻላት ሰይጣን የተናገረው ነገር ሐሰት እንደነበረ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጅ ታሪክ በጣም ግልጽ አድርጐታል። አምላክን የዘነጋ ሰብዓዊ አገዛዝ በተደጋጋሚ ውድቅ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”—መክብብ 8:9
በሌላ በኩል አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ጀምሮ እስከ አሁን ባለፉት ረዥም ዘመናት ወቅት ብዙ መልካም ነገሮችም በማስረጃ ተረጋግጠዋል። ከሰው ልጆች መሃል ከይሖዋ የበላይ ገዥነት ጋር ፍጹም መጣበቅን ያሳዩ ብዙ ሰዎች ተገኝተዋል። ከሁሉ የላቀው ምሳሌም “የሰው ልጅ” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። (ማቴዎስ 20:18፤ ዕብራውያን 11:1 እስከ 12:3) የአምላክን ሕጎች የተከተሉና የበላይ ገዥነቱን የተቀበሉ ሰዎች ይህ አካሄዳቸው ከሁሉ የተሻለው መንገድ መሆኑን አምነዋል። “[የይሖዋ (አዓት)] በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፤ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም” የሚለውን የምሳሌ 10:22ን አባባል እውነትነት አይተዋል። ከዚህም ሌላ የትንሣኤ ዝግጅት ስላለ በመጨረሻው በአምላክ ታላቅ ዓላማ አፈጻጸም ለመካፈል ይበቃሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29
ይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማውን አልረሳውም። የበላይ ገዥነቱን የሚንቁ ሰዎች ለሁልጊዜ በምድር ላይ እንዲገዙ አይፈቅድላቸውም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ እንደሚነሣባቸው ያስጠነቅቃል፦ “በማንኛውም አመጸኝነት ላይ የአምላክ ቁጣ ከሰማይ ይገለጣል” የሚል ቃል እናነባለን። (ሮሜ 1:18) መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶን ብሎ የሚጠራው መጪው የአምላክ ቁጣ መግለጫ አምላክ በእርግጥ እንዳለ በማያጠራጥር ሁኔታ ያረጋግጣል። ከዚያ ሁኔታ የሚተርፉት የበላይ ገዥነቱን የሚቀበሉት ብቻ ይሆናሉ። “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና ኃጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ። አመጸኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22
ታላቁ ጥያቄና አንተ
እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ስላሉ እያንዳንዳችን እንደ አዳምና እንደ ሔዋን ምርጫ ቀርቦልናል። አምላክን ትተን በራሳችን ሐሳብ በመመራት ለመኖር እንሞክር ይሆን? ወይስ ለበላይ ገዥነቱ ራሳችንን እናስገዛለን? በአሁኑ ጊዜ በፊትህ የተደቀነው ተወዳዳሪ የሌለው ጥያቄ ይህ መሆኑን አትርሳ። ሌሎች ጥያቄዎች አስፈላጊ ቢሆኑም የአሁኑን ሕይወትህ ብቻ የሚመለከቱ ናቸው። ይኸኛው ግን የዘላለም ሕይወትን የሚነካ ነው። የምታደርገው ውሣኔ መጪውን ዘላለማዊ ሕይወትህን ይነካል።
የአምላክን የበላይ ገዥነት መቀበልህን ልታሳይ የምትችለው እንዴት ነው? ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናትና ከሌሎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር በመተባበርም ፈቃዱን ለመታዘዝ በመፈለግ ነው። (ሶፎንያስ 2:2, 3) እንዲህ ካደረግህ የአምላክ ታላቅ ዓላማ ሲፈጸም የማየት አስደሳች ተስፋ ይኖርሃል። የሚከተለውን ግሩም ተስፋ ፍጻሜ ለማየት ትበቃለህ፦ “ጥቂት ቆይቶ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:10, 11) ለአምላክ የበላይ ገዥነት ራሳቸውን ለሚያስገዙ ሁሉ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ውጤት ነው! በዚህ እጅግ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ላይ በጥበብ ለመወሰንስ እንዴት ያለ ኃይለኛ ምክንያት ነው!