የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በጥንቃቄ ተከታተሉ
በሁለተኛ ጴጥሮስ ላይ ጎላ ብለው የሚታዩ ነጥቦች
የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ወይም መልእክት በጨለማ ስፍራ እንደሚያበራ መብራት ነው፤ እውነተኛ ክርስቲያኖችም እሱን በጥብቅ መከታተል አለባቸው። በተለይ የሐሰት አስተማሪዎች ክህደት በሚያስፋፉበት ወቅት እንደዚያ ማድረግ ቀላል አይደለም። በመለኮታዊ እርዳታ ግን እንደዚያ ማድረግ ይቻላል። በፍጥነት እየቀረበ ከመጣው የይሖዋ ቀን ለመዳን ከፈለግን የአምላክን ቃል አጥብቀን መከተል አለብን።
በመንፈስ መሪነትና አነሳሽነት የተጻፈው የሐዋርያው ጴጥሮስ ሁለተኛ መልእክት ለአምላክ ትንቢታዊ ቃል የማያቋርጥ ጥንቃቄ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ጴጥሮስ ይህን ደብዳቤ ምናልባት ከባቢሎን ሆኖ በ64 እዘአ ገደማ ጽፎታል። በደብዳቤው ውስጥ ለአምላክ እውነት ጠበቃ ሆኖ ቆሞአል፣ እንደ ሌባ ሆኖ ስለሚመጣው የይሖዋ ቀን የእምነት ጓደኞቹን አስጠንቅቋል፤ ሕግ አፍራሽ በሆኑ ሰዎች ስሕተት እንዳይወሰዱ አንባቢዎቹን የሚረዱ ጎላ ያሉ ነጥቦችን ጠቅሷል። የይሖዋ ቀን በእኛ ጊዜ ሊመጣ የተቃረበ ስለሆነ በመንፈስ አነሣሽነት ከተነገሩት የጴጥሮስ ቃላት ብዙ ልንጠቀም እንችላለን።
በትንቢታዊው ቃል ላይ ትምክህትህን ጣል
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አምላካዊ ጠባዮችን ለማሳየት ብርቱ ጥረት ማድረግና የትንቢቱን ቃል በጥንቃቄ መከተል ይገባናል። (2ጴጥ 1:1-21) እንዳንቀዘቅዝ ወይም ፍሬ ቢሶች እንዳንሆን ‘በእምነታችን ላይ በጎነትን፣ እውቀትን፣ ራስ መግዛትን፣ ጽናትን፣ ለአምላክ ያደሩ መሆንን፣ የወንድማማች መዋደድን እና ፍቅርን እንጨምር።’ ጴጥሮስ የኢየሱስን በክብር መለወጥ ሲመለከትና በዚያ ወቅት አምላክ ስለ ክርስቶስ ሲናገር ሲሰማ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ እርግጠኛ ሆነ። (ማርቆስ 9:1-8) ለዚያ በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት ለተነገረ ቃል ትኩረት ልንሰጠው ይገባናል።
ከከሀዲዎች ራሳችሁን ጠብቁ
ለትንቢታዊው የአምላክ ቃል ጥንቃቄ የሞላበት ትኩረት በመስጠት ከከሀዲዎችና ከሌሎች ብልሹ ሰዎች ልንጠበቅ እንችላለን። (2:1-22) ጴጥሮስ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ወደ ጉባኤው ሾልከው እንደሚገቡ አስጠንቅቋል። ይሁን እንጂ፣ ያልታዘዙትን መላእክት፣ በኖኅ ዘመን የነበረውን አምላክ የለሽ ዓለምና የሰዶምና የገሞራን ከተሞች እንደፈረደባቸው ሁሉ ይሖዋ በእነዚህ ከሀዲዎች ላይም በፍጥነት ይፈርዳል። ሐሰተኛ አስተማሪዎቹ ከአምላክ የተገኘን ሥልጣን የሚንቁ ናቸው፤ ደካማ የሆኑትን በስሕተት አድራጎታቸው እንዲተባበሯቸው ያጠምዷቸዋል። እነዚህ ከሀዲዎች “አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ” ባላወቋት ይሻላቸው ነበር።
የይሖዋ ቀን እየመጣ ነው!
በእነዚህ በመጨረሻ ቀኖች የትንቢቱን ቃል በጥንቃቄ የምንጠብቅ እንደመሆናችን ስለ ይሖዋ መገኘት በሚናገረው መልእክት ላይ በሚያሾፉት ዘባቾች እንዳንሳብ ራሳችንን መጠበቅ አለብን። (3:1-18) እነዚህ ሰዎች ይህንን የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት ዓላማ ያለው አምላክ ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ዓለም እንዳጠፋ ረስተዋል። ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ስለፈለገ እንጂ የይሖዋን ትዕግሥት እንደ መዘግየት ተደርጎ መታየት የለበትም። ይህ የነገሮች ሥርዓት “በይሖዋ ቀን” ይጠፋል፤ ከዚያም ‘ጽድቅ በሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ይተካል። ስለዚህ፣ “ያለነውርና ያለነቀፋ በሰላም” ለመገኘት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን። በሐሰተኛ አስተማሪዎች ከመታለል ይልቅ በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት እንደግ።
የጴጥሮስን ቃላት ልብ እንበላቸው። ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራሳችንን ለመጠበቅ ፈጽሞ ቸል አንበል። የይሖዋ ቀን በቶሎ እንደሚመጣ ባለመዘንጋት ነቅተን እንኑር። እንደዚሁም ለአምላክ የትንቢት ቃል የማያቋርጥ ጥንቃቄ እናድርግ።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ወደ እንጦርጦስ መጣል፦ ይሖዋ “ኃጢአት ያደረጉትን መላእክት ሳይራራላቸው [ወደ እንጦርጦስ (አዓት)] ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ሰጣቸው።” (2 ጴጥሮስ 2:4) ይህ በሆሜር ድርሰት በኢሊያድ ውስጥ የሚገኘው አነስተኞቹ አማልክት ማለትም እንደ ክሮኑስ እና እንደ ሌሎቹ የቲታን መናፍስት የታሰሩበት ከምድር በታች ያለ ቦታ ተደርጎ የሚቆጠረው አፈታሪካዊው እንጦርጦስ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። የመጽሐፍ ቅዱሱ እንጦርጦስ በኖኅ ዘመን አምላክ ዓመፀኞቹን መላእክት የጣለበትን የተዋረደ፣ እንደ እስር ቤት ያለ ሁኔታቸውን ያመለክታል። (ዘፍጥረት 6:1-8፤ 1 ጴጥሮስ 3:19, 20፤ ይሁዳ 6) “ድቅድቅ ጨለማ” ያጋጠማቸው ከይሖዋ ቤተሰብ በመወገዳቸው የተነሣ መንፈሳዊ ብርሃን የተቋረጠባቸው በመሆኑ ነው። አስከፊ ፍርድ ስለሚጠብቃቸው ከፊት ለፊት የሚታያቸው የጨለመ ነው። እንጦርጦስ የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከመጀመሩ በፊት ሰይጣንና አጋንንቱ በሚጣሉበት በጥልቁ ምን እንደሚገጥማቸው የሚያሳይ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ በኋላ ይጠፋሉ።—ማቴዎስ 25:41፤ ራእይ 20:1-3, 7-10, 14
[ሥዕል]
ዘዩስ አነስተኛ አማልክትን ወደ አፈታሪካዊው እንጦርጦስ ጣላቸው
[ምንጭ]
National Archaeological Museum, Athens, Greece