በብርሃንና በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ
ከአንደኛ ዮሐንስ የተገኙ ዋና ዋና ነጥቦች
ይሖዋ የብርሃንና የፍቅር ምንጭ ነው። መንፈሳዊ ብርሃን ለማግኘት ወደ አምላክ መመልከት ያስፈልገናል። (መዝሙር 43:3) ፍቅር ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው።—ገላትያ 5:22, 23
ስለ ብርሃን፣ ስለ ፍቅርና ስለ ሌሎች ጉዳዮች በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጀመሪያው የዮሐንስ ደብዳቤ ላይ ተብራርቷል። ይህ ደብዳቤ የተጻፈው በ98 እዘአ አካባቢ በኤፌሶን አጠገብ ሳይሆን አይቀርም። መልዕክቱ የተጻፈበትም ዋና ምክንያት ክርስቲያኖችን ከከሃዲዎች ለመጠበቅና በብርሃን በመመላለስ እንዲቀጥሉ ለመርዳት ነበር። እኛም በፍቅራችን፣ በእምነታችንና ለእውነት ባለን ጽኑ አቋም ፈተናዎች ስለሚያጋጥሙን ይህን ደብዳቤ መመርመራችን ጥቅም ያመጣልናል።
‘በብርሃን ተመላለሱ’
ዮሐንስ ታማኝ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ብርሃን መጓዝ እንዳለባቸው በግልጽ ተናግሯል። (1ዮሐ 1:1 እስከ 2:29) እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም [ክፉ፣ ከሥነምግባር ውጭ የሆነ፣ ሐሰት፣ ወይም ርኩስ የሆነ ነገር] በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም።” በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ‘በብርሃን ስለሚመላለሱ’ ከአምላክ፣ ከክርስቶስ ጋርና እርስ በርሳቸው “ኅብረት” አላቸው። በተጨማሪም በኢየሱስ ደም ነጽተዋል።
ሰማያዊ ተስፋ ያለን ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆንን ወይም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምንጠባበቅ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ መስዋዕት ልንጠቀም የምንችለው ዓለምን ሳይሆን ወንድሞቻችንን የምንወድ ከሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም አብንም ሆነ ወልድን የሚክደውን “የክርስቶስ ተቃዋሚ” የሚመስሉት ከሃዲዎች እንዳይስቡን መጠንቀቅ ይኖርብናል። እንዲሁም የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ከእውነት ጋር የተጣበቁትና ጽድቅን የሚያደርጉት ብቻ መሆናቸውን መርሳት የለብንም።
የአምላክ ልጆች ፍቅር ያሳያሉ
ዮሐንስ ቀጥሎ የአምላክ ልጆች እንዴት ያሉ እንደሆኑ ገለጸ። (3:1 እስከ 4:21) በመጀመሪያ ደረጃ ጽድቅን ያደርጋሉ። እንዲሁም ‘በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲያምኑና እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ ይሖዋ አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ ያከብራሉ።
‘አምላክን የሚያውቅ’ ግለሰብ ስለ ይሖዋ ዓላማዎችም ሆነ ፍቅሩ እንዴት እንደተገለጸ ያውቃል። ይህም ሰውየው ፍቅርን እንዲያሳይ ሊረዳው ይገባል። እንዲያውም “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” አምላክ “ስለ ኃጢአታችን ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን” በላከ ጊዜ መለኮታዊው ፍቅር ታይቷል። ይሖዋ ይህን ያህል ከወደደን እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን። አዎን አምላክን እወደዋለሁ የሚል ሁሉ መንፈሳዊ ወንድሙንም መውደድ ይኖርበታል።
እምነት ‘ዓለምን ያሸንፋል’
ፍቅር የአምላክን ልጆች ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ ይገፋፋቸዋል። ‘ዓለምን ሊያሸንፉ’ የሚችሉት ግን በእምነት ነው። (5:1-21) በአምላክ፣ በቃሉና በልጁ ላይ ያለን እምነት የዓለምን የተሳሳተ አስተሳሰብና መንገዶች አልቀበልም ብለን በመቃወምና የይሖዋን ትእዛዛት በመጠበቅ ‘ዓለምን እንድናሸንፍ’ ያስችለናል። አምላክ ‘ዓለምን ለሚያሸንፉት’ የዘላለም ሕይወትን ተስፋ ሰጥቷቸዋል፣ ከፈቃዱ ጋር የሚስማማውን ጸሎታቸውንም ይሰማል። “ከአምላክ የተወለደ” ኃጢአትን እያደረገ ስለማይኖር ሰይጣን እንዲህ ያለውን ሰው ጨምድዶ አይዘውም። ነገር ግን ቅቡዓኑም ሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች ‘ዓለም በሙሉ በክፉው መያዙን’ ማስታወስ ይገባቸዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የማስተሰሪያ መስዋዕት፦ ኢየሱስ ‘የኃጢአታችን [ቅቡዓን ተከታዮቹ ለሆኑት] ማስተሰሪያ መስዋዕት ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት’ ማለትም ለቀረው የሰው ዘር ሁሉ ኃጢአት ጭምር እንጂ። (1 ዮሐንስ 2:2) የእርሱ ሞት ማስተሰሪያ ነበር፤ (በግሪክ ሂላስሞስ ሲተረጎም “ማስታረቂያ መንገድ” “ስርየት”) ሆኖም ማስተሰሪያ የሆነው አምላክ የተሰማውን ኀዘን በማስታገስ መንፈስ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስ መስዋዕት ፍጹም የሆነው መለኮታዊ ፍትሕ የሚጠይቃቸውን ነገሮች አሟልቷል ወይም አበርክቷል። እንዴት? አምላክ ‘በኢየሱስ የሚያምነውን [ኃጢአትን የወረሰውን ሰው] ሲያጸድቅ ራሱም ትክክለኛ ይሆን ዘንድ’ ለኃጢአት ይቅርታ መሠረት የሚሆነውን ጽድቅና ፍትሕ በማዘጋጀቱ ነው። (ሮሜ 3:23-26፤ 5:12) የሰውን ኃጢአት ይቅር ለማለት የሚያስፈልገውን ሁሉ በማሟላት የኢየሱስ መስዋዕት ሰው ከይሖዋ ጋር ትክክለኛ ዝምድና እንደገና ለማግኘት ተስማሚ፣ ወይም ምቹ አድርጎለታል። (ኤፌሶን 1:7፤ ዕብራውያን 2:17) ለዚህ ሁላችንም የቱን ያህል አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል!