በእውነት ውስጥ የሥራ ጓደኞች በመሆን ተመላለሱ
ከሁለተኛና ከሦስተኛ ዮሐንስ የተገኙ ዋና ዋና ነጥቦች
የእውነት እውቀት የይሖዋ አምላኪዎች ከሌሎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነው። (ዮሐንስ 8:31, 32፤ 17:17) በመለኮታዊው እውነት መመላለሱ ለደኅንነት አስፈላጊ ነው። የአምላክ አገልጋዮችም ለእውነት አብረው የሚሠሩ መሆን ይገባቸዋል።
ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ መሪነትና አነሳሽነት የጻፋቸው ሁለተኛና ሦስተኛ መልእክቶች ‘በእውነት ስለመመላለስ’ ይናገራሉ። (2 ዮሐንስ 4፤ 3 ዮሐንስ 3, 4) ሦስተኛ ዮሐንስ ‘ለእውነት አብረን የምንሠራ ባልደረቦች’ በመሆን ኅብረት እንዲኖር ያበረታታል። (3 ዮሐንስ 5-8) ሁለቱም ደብዳቤዎች በ98 እዘአ በኤፌሶን ውስጥ ወይም በኤፌሶን አጠገብ ሳይጻፉ አይቀሩም። ሆኖም የያዙት ሐሳብ ዛሬ ያሉትን የይሖዋ ሕዝቦች ሊጠቅም ይችላል።
ሁለተኛ ዮሐንስ እውነትን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል
ሁለተኛ ዮሐንስ በመጀመሪያ እውነትንና ፍቅርን ጎላ አድርጎ ከገለጸ በኋላ ‘ከክርስቶስ ተቃዋሚ’ ያስጠነቅቃል። (ቁጥር ከ1-7) ደብዳቤው የተጻፈው ለአንዲት “ለተመረጠች እመቤት” ነው። ምናልባት ለአንዲት ግለሰብ ሊሆን ይችላል። ለአንድ ጉባኤ የተጻፈ ከሆነ ግን “ልጆችዋ” የተባሉት ለሰማያዊ ሕይወት በአምላክ ‘የተመረጡ’ በመንፈስ የተዋጁ ክርስቲያኖች ነበሩ። (ሮሜ 8:16, 17፤ ፊልጵስዩስ 3:12-14) ዮሐንስ አንዳንዶቹ ‘በእውነት በመሄዳቸው’ እና ክህደትን በመቃወማቸው ተደስቶ ነበር። ቢሆንም ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን ከሚክደው “የክርስቶስ ተቃዋሚ” መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ዛሬ ያሉት የይሖዋ ምስክሮች እንደነዚህ ያሉትን ከክሕደት ስለ መራቅ የሚገልጹ ማስጠንቀቂያዎች ይከተላሉ።
ዮሐንስ ቀጥሎ ከከሃዲዎች ጋር ስለመገናኘት ምክር ሰጠና የግል ምኞቱንና ሰላምታውን በመግለጽ ደመደመ። (ቁጥር 8-13) እንደ ስብከት ባሉት ሥራዎች እርሱና ሌሎች ይህንን ደብዳቤውን የጻፈላቸው ሰዎች ወደ ክርስትና እንዲለወጡ በማድረግ ፍሬ አፍርተዋል። ለታማኝ ቅቡዓን ተጠብቆ ያለውን ሰማያዊ “አክሊል” የሚጨምረውን “ሙሉ ሽልማት” ሊያገኙ የሚችሉት በመንፈሳዊ ለራሳቸው ‘ሲጠነቀቁ’ ብቻ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) ማንም ‘በክርስቶስ ትምህርት የማይኖር’ ወደ እነርሱ ቢመጣ ‘በክፉ ሥራው እንዳይተባበሩ ሲሉ በቤታቸው አይቀበሉትም፣ ሰላምም አይሉትም።’ ወደ እነዚህ የእምነት ጓደኞቹ መጥቶ ከእነርሱ ጋር ፊት ለፊት እንደሚነጋገር ያለውን ተስፋ ከገለጸ በኋላ ዮሐንስ ደብዳቤውን በሰላምታ ዘጋው።
ሦስተኛ ዮሐንስ ትብብርን ያጎላል
ሦስተኛ ዮሐንስ በቀጥታ የተጻፈው ለጋይዮስ ሲሆን በመጀመሪያው ላይ የሚገልጸው እርሱ ለእምነት ጓደኞቹ ያደርጋቸው ስለነበሩት ነገሮች ነው። (3ዮሐ ከቁጥር 1-8) ጋይዮስ ከሁሉም የክርስቲያን ትምህርቶች ጋር በመጣበቅ ‘በእውነት ይመላለስ ነበር።’ በተጨማሪም ለመጠየቅ የመጡ ወንድሞችን በመርዳት “የታመነ ሥራ” ይሠራ ነበር። ዮሐንስ “እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል” ሲል ጻፈ። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምስክሮች ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ተመሳሳይ እንግዳ ተቀባይነት ያሳያሉ።
የዲዮጥራጢስን መጥፎ ባሕርይ ከዲሜጥሮስ ጋር ካነጻጸረ በኋላ ዮሐንስ ደብዳቤውን ዘጋው። (ቁጥር ከ9-14) ክብር ፈላጊው ዲዮጥራጢስ ለዮሐንስ አክብሮት አላሳየም፤ እንዲያውም ወንድሞችን እንግድነት የሚቀበሉትን ከጉባኤ ለማስወጣት ይሞክር ነበር። ሆኖም ዲሜጥሮስ የሚባለው በጥሩ ምሳሌነቱ ተጠቅሷል። ዮሐንስ ጋይዮስን በቅርቡ እንደሚያየው ያለውን ተስፋ ከገለጸ በኋላ ደብዳቤውን በሰላምታና ለጋይዮስ ሰላም በመመኘት ደመደመ።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]
በወረቀት፣ በብርዕና በቀለም፦ ዮሐንስ “በወረቀትና በቀለም” ብዙ ነገሮችን በመጻፍ ፋንታ “የተመረጠችውን እመቤት” እና “ልጆችዋን” ለመጎብኘት ፈልጎ ነበር። ለጋይዮስም “በቀለምና በብርዕ” መጻፉን ከመቀጠል ይልቅ ሐዋርያው በቅርቡ እንደሚያየው ተስፋ አድርጎ ነበር። (2 ዮሐንስ 1, 12፤ 3 ዮሐንስ 1, 13, 14) ብርዕ ተብሎ የተተረጎመው (ካላሞስ) የተባለው የግሪክኛ ቃል አገዳን ወይም ቀርከሃን የሚያመለክት ሲሆን “የመጻፊያ ቀርከሃ” የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይቻላል። የግሪኮችና የሮማውያን የመቃ ብርዕ በኋላ ተስለውና ተቀርጸው እንደተዘጋጁት የመቃ ብርዖች ነበር። “ቀለም” ተብሎ የተተረጎመው ሜላን የተባለው የግሪክኛ ቃል ጥቁር የሚል ትርጉም ካለው ሜላስ ከተሰኘው ተባዕት ፆታን ከሚያመለክተው ቅጽል የወጣ ነው። በጥንት ዘመን በነበሩት ቀለሞች ውስጥ ከሰላማ የሆነ ማቅለሚያ ይደረግ ነበር። ይህም ከተቃጠለ ዘይት ወይም እንጨት ከሚገኝ ጥቀርሻ ወይም ከዕፅዋት ወይም ከእንስሳት የሚገኝ የጠጠረ ከሰል ነበር። ብዙ ጊዜ ጭቃ ቀለሙ ተጠፍጥፎና ደርቆ ይቀመጥ ነበር፤ ከዚያም ጸሐፊው ሊጠቀምበት ሲፈልግ በውሃ ያርሰውና መቃውን እያጠለቀ ይጽፋል። በዚያን ጊዜ የነበረው ወረቀት ከደንገል ልጥ የተሠራ ስስ ነገር ነበር። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ለመጻፍ፣ የመጽሐፍ ጥቅልል ለማዘጋጀትና አሁን ያለው ዓይነት የተጠረዘ መጽሐፍ ለመሥራት በእንዲህ ዓይነቱ ወረቀት ይጠቀሙ ነበር።