የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 5/1 ገጽ 10-14
  • ንጹሑ ልሳን አንድ ያድርጋችሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ንጹሑ ልሳን አንድ ያድርጋችሁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዛሬም ከአምላክ የተሰጠ ቋንቋ አለ!
  • ንጹሑ ልሳን ምን እንደሆነ ሲብራራ
  • ንጹሑን ልሳን አሁንኑ ተማር
  • ለሁሉም ሕዝቦች የሚሆን ንጹሕ ልሳን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንጹሑን ልሳን ተናገርና ለዘላለም ኑር!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ‘ንጹሑን ቋንቋ’ አጥርተህ ትናገራለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ተመልሰው የተቋቋሙት የይሖዋ ሕዝቦች በመላው ምድር ያወድሱታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 5/1 ገጽ 10-14

ንጹሑ ልሳን አንድ ያድርጋችሁ

“በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው (ይሖዋን) ያገለግሉ ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሁን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።”​—ሶፎንያስ 3:9

1. ሰዎች ይሖዋ አምላክ ሲናገር ሰምተውት ያውቃሉን?

የይሖዋ አምላክ ልሣን ንጹህ ነው። ግን እርሱ ሲናገር ሰዎች ሰምተውት ያውቃሉን? እንዴታ! ያም የሆነው ከ19 መቶ ዓመታት በፊት ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ አምላክ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ተሰምቷል። (ማቴዎስ 3:13-17) ያ ቃል በሰው ቋንቋ ለኢየሱስና ለዮሐንስ መጥምቁ የተሰማ የንጹህ እውነት መግለጫ ነው።

2. ሐዋርያው ጳውሎስ “የመላእክት ልሣን” ሲል የጠቀሰው ቃል ምን ያመለክታል?

2 ከጥቂት ዓመታት በኋላም ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሰዎችና ስለ መላእክት “ልሣን” ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 13:1) ይህስ ምን ያመለክታል? ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራንም ቋንቋና ንግግር እንዳላቸው ያመለክታል! እርግጥ አምላክና መላእክቱ እርስ በርሳቸው የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉት ለእኛ በሚሰማንና በሚገባን ድምጽና ቋንቋ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ሰዎች የሚሰሙትና የሚረዱት የድምጽ ሞገድን ለማሠራጨት በምድር ዙሪያ እንዳለው ከባቢ አየር ስለሚያስፈልግ ነው።

3. ሰብዓዊ ቋንቋ እንዴት መጣ?

3 የሰው ቋንቋ እንዴት ተጀመረ? ቅድመ አያቶቻችን በማጓራትና በማቃሰት ዓይነት ድምጽ እርስ በርሳቸው ለመነጋገር ይታገሉ ነበር በማለት አንዳንዶች ይናገራሉ። ኢቮሉሽን (ላይፍ ኔቸር ላይብረሪ) የተሰኘው መጽሐፍ “ከአንድ ሚልዮን ዓመታት በፊት የነበረው ጦጣ መሰል ሰው ጥቂት የንግግር ድምጾችን ጠንቅቆ ሳያውቅ አልቀረም” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ የታወቁት መዝገበ ቃላት ጸሐፊ ሉዲዊግ ከውኽለር “የሰው ቋንቋ ምስጢር ነው፤ መለኰታዊ ስጦታና ተዓምርም ነው” ብለዋል። አዎ፤ አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም ቋንቋን ስለሰጠው ሰብዓዊ የንግግር ችሎታ መለኰታዊ ስጦታ ነው። ያም ቋንቋ በኋላ ዕብራይስጥ የተባለው እንደሆነ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ያ ቋንቋ አያቱ የመርከብ ሠሪው የኖህ ልጅ ሴም የሆነው ታማኝ አበው የ“ዕብራዊው አብርሃም” ዘሮች የእሥራኤላውያን መነጋገሪያ ቋንቋ ነበር። (ዘፍጥረት 11:10-26፤ 14:13፤ 17:3-6) አምላክ ሴምን ከባረከበት ትንቢታዊ በረከት አንጻር ሲታይ ቋንቋው ከ43 መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ በተዓምር ባደረገው ነገር አልተነካም ነበር ብሎ መናገር ምክንያታዊ ነው።​—ዘፍጥረት 9:26

4. ናምሩድ ማን ነበር? ሰይጣን ዲያብሎስ የተጠቀመበትስ እንዴት ነው?

4 በዚያን ጊዜ “ምድር ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች።” (ዘፍጥረት 11:1) በዚያን ጊዜ “[ይሖዋን በመጻረር (አዓት)] ኃያል አዳኝ” የነበረ ናምሩድ የሚባል ሰው ነበረ። (ዘፍጥረት 10:8, 9) በዓይን የማይታየው የሰው ልጅ ቀንደኛ ጠላት ሰይጣን የራሱን ድርጅት ምድራዊ ክፍል እንዲያቋቁም ናምሩድን ተጠቀመበት። ናምሩድ ለራሱ ታላቅ ስም ለማትረፍ ፈለገ። የሱ የዕብሪት ዝንባሌ በሰናዖር ምድር ልዩ የግንባታ ሥራ በጀመሩት የእሱ ተከታዮች ዘንድም ተዛመተ። በዘፍጥረት 11:4 መሠረት “ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው” ተባባሉ። “ምድርን ሙሉ” የሚለውን የአምላክን ትዕዛዝ የሚቃወመው ያ ዕቅድ ይሖዋ የዐመጸኞቹን ቋንቋ በደባለቀ ጊዜ አከተመ። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ “እግዚአብሔር ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው። ከተማይቱንም መሥራት ተዉ” ይላል። (ዘፍጥረት 9:1፤ 11:2-9) ከተማዋም ባቤል ወይም ባቢሎን ተብላ ተጠራች፤ ትርጉሙም “መዘበራረቅ” “መደበላለቅ” ማለት ነው። ምክንያቱም “ይሖዋ በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና።”

5. (ሀ) አምላክ የሰው ልጆችን ቋንቋ በደባለቀ ጊዜ የታገደው ምን ነበር? (ለ) ስለ ኖህና ስለ ሴም ቋንቋ ምን ብለን መደምደም እንችላለን?

5 ያ ተአምር ማለትም አንዱን ሰብአዊ ቋንቋ ማደባለቁ አምላክ ለኖኅ ምድርን እንዲሞሉአት የሰጠውን ትእዛዝ ወደመፈጸም አምርቷል፤ ሰይጣንም የሰማይና የምድር ልዑል ጌታ በሆነው በይሖዋ ላይ ባመጹ ሰዎች አማካኝነት ለራሱ አንድነት ያለው እርኩስ አምልኮ ለማቋቋም የነበረው እቅድ ተደናቀፈ። እርግጥ ነው ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት በመያዛቸው ዞሮ ዞሮ የዲያብሎስ አምላኪዎች ከመሆን አላመለጡም። አማልክትን በተባዕታይና አነስታይ ጾታ ሠርተው በተለያዩ ቋንቋዎቻቸውም ስም ሰጥተው ባመለኩአቸው ጊዜ አጋንንትን ማምለካቸው ወይም ማገልገላቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 10:20) ይሁን እንጂ በባቢሎን ላይ በአንዱ እውነተኛ አምላክ የተወሰደው እርምጃ ሰይጣን በግልጽ ተመኝቶት የነበረውን አንድነት ያለው የሐሰት ሃይማኖት እንዳያቋቁም አግዷል። ጻድቁ ኖኅና ልጁ ሴም በሰናዖር ምድር በደረሰው ውድቀትና ምስቅልቅል ውስጥ አልገቡም። ስለዚህ ቋንቋቸው ቀጠለና የታማኙ የአብራም (አብርሃም) መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። ያው ቋንቋ ነበር አምላክ በዔድን ገነት ከአዳምና ከሔዋን ጋር የተነጋገረበት።

6. በ33 እዘአ የጰንጤቆስጤ ዕለት ይሖዋ በልሣናት መናገርን መስጠት እንደሚችል እንዴት አሳየ?

6 የሰው ልጆችን የመጀመሪያ ቋንቋ የደባለቀው ይሖዋ በልሳናት የመናገርን ችሎታም ሊሰጥ ይችላል። በ33 እዘአ በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ያደረገውም ያንኑ ነው። በሥራ 2:1-11 መሠረት በዚያን ጊዜ 120 የሚያህሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በሰገነት ላይ ተሰብስበው ነበር። (ሥራ 1:13, 15) በድንገትም “እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ” ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ። “እሳት የመሰሉ ልሳኖች” ታዩና ተከፋፈሉ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” በነዚያ መለኮታዊ ስጦታ በሆኑ ቋንቋዎች “የእግዚአብሔርን አስደናቂ ነገሮች መናገር ጀመሩ።” እንደ ሜሴፖታሚያ፣ ግብፅ፣ ሊብያና ሮም ከመሳሰሉት የተለያዩ ሩቅ ቦታዎች የመጡ አይሁድና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ያን ሕይወት ሰጪ መልእክት መስማት ችለው ስለነበር ያ እንዴት ዓይነት ተአምር ነበር!

ዛሬም ከአምላክ የተሰጠ ቋንቋ አለ!

7. በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያውና መግባቢያው አንድ ቋንቋ ብቻ ቢሆን ኖሮ ምን ሁኔታዎች ይኖሩ ነበር?

7 አምላክ በተአምር የተለያዩ ልሳናትን ሊሰጥ የሚችል ስለሆነ በዓለም ዙሪያ አንድ ቋንቋ ብቻ እንዲነገርና መግባቢያ እንዲሆን ቢያደርግ ግሩም አይሆንምን? እንደዚያ ቢሆን በሰብአዊ ቤተሰብ መካከል የበለጠ መግባባት ሊኖር ይችል ነበር። ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደገለጸው “ሁሉም ሕዝቦች አንድ ቋንቋ ቢናገሩ ኖሮ ባሕላዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በጣም የበለጠ የተቀራረቡ ይሆኑ ነበር። በአገሮች መካከል መተማመን ይጨምር ነበር።” ባለፉት ዘመናት ቢያንስ 600 ዓይነት ቋንቋዎች ዓለም አቀፋዊ መግባቢያ እንዲሆኑ ሐሳብ ቀርቦ ነበር። ከእነዚህ መካከል ኢስቀራንቶ የተባለው ቋንቋ ከፍተኛ ኃይል ነበረው፤ ምክንያቱም በ1887 ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ 10,000,000 ያህል ሕዝብ ሊማረው ችሏል። ሆኖም በአንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ አማካኝነት የሰው ልጅን ለማስተባበር የተደረገው የሰው ጥረት ስኬታማ አልሆነም። እንዲያውም “ክፉ ሰዎች በክፋት እየባሱ” ሲሄዱ ተጨማሪ ችግሮች በዚህ ዓለም መከፋፈልን እያስከተሉ ነው።​—2 ጢሞቴዎስ 3:13

8. በአሁኑ ዓለም አንድ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ መምረጥና በሥራ ላይ ማዋል ቢቻልም ኖሮ እንኳን ገና ምን ይኖራል? ለምንስ?

8 በሃይማኖት ረገድ ከፍተኛ መዘበራረቅ አለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ የዓለምን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት “ታላቂቱ ባቢሎን” ብሎ ስለሚጠራ ይህ መዘበራረቅ እንደሚኖር መጠበቅ አይገባንምን? (ራእይ 18:2) አዎን “ባቢሎን” ማለት “መዘበራረቅ” ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባናል። ባሁኑ ዓለም ሰው ሠራሽ ቋንቋ ወይም እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ ወይም ሩሲያኛ የመሳሰሉት ልሳኖች በዓለም አቀፋዊ መግባቢያነት ተመርጠው ቢያዙም ኖሮ በሃይማኖትና በሌላም መከፋፈል ይኖራል። ለምን? ምክንያቱም “ዓለምም በሞላው በክፉው [በሰይጣን ዲያብሎስ] ተይዟል።” (1 ዮሐንስ 5:19) እሱ ሁለንተናው ራስ ወዳድ ነው። ስለዚህ በናምሩድና በባቢሎን ግንብ ጊዜ እንዳደረገው በራስ ወዳድነት በሰው ልጅ ሁሉ እንዲመለክ ይመኛል። በኃጢአተኛ ሰዎች የሚነገር አንድ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ለሰይጣን አንድነት ያለው የዲያብሎስ አምልኮ ሊያስገኝለት ይችል ነበር። ይሖዋ ግን ያንን ፈጽሞ አይፈቅድም። እንዲያውም ማንኛውንም ዲያብሎሳዊ የሆነ የሐሰት ሃይማኖት በቅርቡ ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል።

9. ከሁሉም ሕዝቦችና ዘሮች የመጡ ሰዎች አሁን አንድ እየሆኑ ያሉት እንዴት ነው?

9 ሆኖም አስደናቂው ነገር ከሁሉም ብሔራትና ዘሮች የተውጣጡ ጥሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድነት የመጡ መሆናቸው ነው። ይህም እየተፈጸመ ያለው አምላክ በፈለገው መንገድና ለራሱ አምልኮ ሲባል ነው። ባሁኑ ጊዜ አምላክ የሰው ልጆችን በምድር ላይ አንዱን ብቸኛ ንጹሕ ልሳን እንዲማሩና እንዲናገሩ እያስቻላቸው ነው። እሱም በእርግጥ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው። በእርግጥም ይሖዋ ባሁኑ ጊዜ ይህን ንጹሕ ልሳን ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለተውጣጡ ሰዎች እያስተማራቸው ነው። ይህም አምላክ የራሱ ነቢይና ምስክር በሆነው በሶፎንያስ በኩል ያስነገረው ትንቢታዊ ቃል ፍጻሜ ነው። “በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን [ቃል በቃል ሲተረጐም “ንጹሕ ከንፈር”] እመልስላቸዋለሁ። (ሶፎንያስ 3:9) ይህ ንጹሕ ልሳን ምንድን ነው?

ንጹሑ ልሳን ምን እንደሆነ ሲብራራ

10. ንጹሕ ልሣን ምንድን ነው?

10 ንጹሑ ልሳን የአምላክ ቃል በሆኑት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው የአምላክ እውነት ነው። በተለይም ደግሞ ለሰው ልጆች ሰላምና ሌሎች በረከቶች የሚያመጣውን የአምላክን መንግሥት የሚመለከተው እውነት ነው። ንጹሑ ልሳን ሃይማኖታዊ ስሕተትንና የሐሰት አምልኮን ያስወግዳል። ይህ ቋንቋ ተናጋሪዎቹን ሁሉ በሕያውና በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ የጠራ፣ ንጹሕና ጤናማ አምልኮ ያስተባብራቸዋል። ባሁኑ ጊዜ 3,000 የሚሆኑ ቋንቋዎች ለመግባባት መሰናክል ሆነዋል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ደግሞ የሰው ልጆችን ግራ አጋብተዋል። ስለዚህ አምላክ ወደ ግሩምና ንጹሕ ልሳን የመለወጥን ዕድል ለሰዎች እየሰጠ በመሆኑ ምን ያህል ደስተኞች ነን!

11. ንጹሕ ልሣን ለሁሉም ሕዝቦችና ዘሮች ምን አድርጎላቸዋል?

11 አዎን፣ ንጹሑን ቋንቋ ከሁሉም ብሔራትና ዘሮች የተውጣጡ ሰዎች በደንብ አጣርተው እየተናገሩት ነው። በምድር ላይ ያለ ብቸኛ መንፈሳዊ ንጹሕ ልሳን እንደመሆኑ ኃይለኛ አስተባባሪ ኃይል ሆኖ ያገለግላል። በሱ የሚጠቀሙትን ሁሉ “የይሖዋን ስም እንዲጠሩና” “አንድ ሆነው” ወይም ቃል በቃሉ “በአንድ ትከሻ” እንዲያገለግሉት እያስቻላቸው ነው። ስለዚህ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብልና ዘ አምፕሊፋይድ ባይብል እንዳቀረቡት “ባንድ ድምፅ ወይም ሐሳብ” እና “ባንድ ሙሉ ድምፅ” ወይም ሐሳብ ወይም ስምምነትና በአንድ የተባበረ ትከሻ ወይም ክንድ” እያገለገሉት ነው። የእስቴቬን ቲ ባይንግተን ትርጉም እንዲህ ይነበባል፦ “በዚያን ጊዜ እኔ [ይሖዋ አምላክ] ሁሉም ሕዝቦች የይሖዋን ስም ይጠሩና በአገልግሎቱ አንድ ይሆኑ ዘንድ ልሳናቸውን ንጹሕ አደርጋለሁ።” በብዙ ቋንቋዎች በአምላክ አገልግሎት ይህን መሳይ አንድነት ያለው በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ብቻ ነው። ባሁኑ ጊዜ ከአራት ሚልዮን በላይ የሆኑ እነዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በ212 አገሮች የምሥራቹን በብዙ ቋንቋዎች እየሰበኩት ነው። ሆኖም ምስክሮቹ የሚናገሩት “በስምምነት” እና “በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበሩ” በመሆን ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት በምድር በየትኛውም ቦታ ቢኖሩም ሁሉም የይሖዋ ምስክሮች ለሰማያዊ አባታቸው ምስጋናና ክብር አንዱን ንጹሕ ልሳን ስለሚናገሩ ነው።

ንጹሑን ልሳን አሁንኑ ተማር

12, 13. (ሀ) ንጹሕ ልሣን የመናገሩ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድነው? (ለ) የሶፎንያስ 3:8, 9 ቃላት በዛሬው ጊዜ ትልቅ ቁም ነገር ያላቸው ለምንድነው?

12 ንጹሑን ልሳን የመናገሩ ጉዳይ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው? መጀመሪያ ነገር ሕይወትህ የተመካው ይህን ቋንቋ በመማርህና በመናገርህ ላይ ስለሆነ ነው። አምላክ ለአሕዛብ ወደ ንጹሑ ልሳን የመለወጥን ዕድል እንደሚሰጥ ተስፋ ከመስጠቱ ቀደም ብሎ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ ይላል [ይሖዋ (አዓት)]።”​—ሶፎንያስ 3:8

13 እነዚያ የሁሉም የበላይ ገዥ የሆነው የይሖዋ ቃላት የተነገሩት መናገሻዋ ኢየሩሳሌም በነበረው በይሁዳ ውስጥ ከ26 መቶ ዘመናት በፊት ነው። ይሁን እንጂ እነዚያ ቃላት የተነገሩት በተለይ ለዘመናችን ነው። ምክንያቱም ኢየሩሳሌም የሕዝበ ክርስትና ምሳሌ ስለሆነች ነው። እንደዚሁም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በ1914 ስለተቋቋመች ዘመናችን አምላክ አሕዛብን የሚሰበስብበትና መንግሥታትንም የሚያከማችበት የይሖዋ ቀን ነው። በታላቅ ምስክርነት የመስጠት ሥራ አማካኝነት ሁሉንም አሰባስቦ በትኩረቱ ሥር እያደረጋቸው ነው። ይህ ደግሞ ዓላማውን በመፃረር እንዲነሱ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በምሕረቱ ከነዚህ ብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ንጹሑን ልሳን በመናገር እንዲተባበሩ እያስቻላቸው ነው። ሁሉም አሕዛብ አርማጌዶን በመባል በሚታወቀው “በታላቁ ሁሉን በሚችለው አምላክ ጦርነት” ቀን በእሳታማው የመለኮታዊ ቁጣ መግለጫ ከመቃጠላቸው በፊት አምላክ ተስፋ በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በዚህ ቋንቋ አማካኝነት እንደ አንድ ሆነው ያገለግሉታል። (ራእይ 16:14, 16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የሚያስደስተው ነገር ንጹሑን ልሳን የሚናገሩና እውነተኛ አምላኪዎቹ በመሆን በእምነት ስሙን የሚጠሩ ሁሉ በዚያ ዓለም አቀፍ የትኩሳት መዓት ወቅት መለኮታዊ ጥበቃ የሚያገኙ መሆናቸው ነው። አምላክ ከዚያ ጠብቆ ወደ አዲሱ ዓለም ያስገባቸዋል። በዚያም ውስጥ በሁሉም የሰው ዘር ከንፈሮች የሚነገረው ንጹሑ ልሳን ብቻ ይሆናል።

14. የዚህን የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ማለፉ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድን እንደሚጠይቅ አምላክ በሶፎንያስ በኩል ያሳየው እንዴት ነው?

14 ከአሁኑ ክፉ ሥርዓት በሕይወት ለመትረፍ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች አጣዳፊ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ይሖዋ በነቢዩ በሶፎንያስ በኩል ግልጽ አድርጎላቸዋል። በሶፎንያስ 2:1-3 መሠረት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ እፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፣ ትእዛዝ ሳይወጣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ የይሖዋም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ የይሖዋም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፤ ተከማቹም። እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ [ይሖዋን (አዓት)] ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፤ ትሕትናንም ፈልጉ። ምናልባት በ[ይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”

15. (ሀ) የሶፎንያስ 2:1-3 የመጀመሪያ ፍጻሜ ምን ነበር? (ለ) በይሁዳ ላይ ከመጣው የአምላክ የጥፋት ፍርድ ያመለጡት እነማን ነበሩ? በዘመናችን ይህን መዳን የሚመሳሰለውስ ምንድን ነው?

15 እነዚያ ቃላት የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በጥንቷ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ላይ ነው። የይሁዳ ኃጢአተኛ ሕዝብ ለይሖዋ ጥሪ እሺ የሚል ምላሽ አልሰጡም ምክንያቱም በ607 ከዘአበ በባቢሎናውያን እጅ ፍርዱን አስፈጽሞባቸዋል። ይሁዳ በአምላክ ፊት “እፍረት የሌለው” እንደነበረ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም በይሖዋ ፊት ሐፍረተ ቢስ “ሕዝብ” ሆናለች። ሆኖም የይሖዋን ታማኝ ነቢይ ኤርምያስን ጨምሮ አንዳንድ አይሁዳውያን የአምላክን ቃል በመስማታቸው ምክንያት ከጥፋቱ ሊተርፉ ችለዋል። ሌሎቹ ተራፊዎች ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክና የኢዮናዳብ ዘሮች ናቸው። (ኤርምያስ 35:18, 19፤ 39:11, 12, 16-18) ባሁኑ ጊዜም በተመሳሳይ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከአርማጌዶን ጥፋት ተርፈው ወደ አዲሱ የአምላክ ዓለም ይገባሉ። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:14-16) ንጹሑን ልሳን የሚማሩና የሚናገሩ ብቻ ናቸው የዚያ ጥፋት ደስተኛ ተራፊዎች የሚሆኑት።

16. “በይሖዋ የቁጣ ቀን” ለመሰወር አንድ ሰው ምን ማድረግ አለበት?

16 ይሁዳና ኢየሩሳሌም እንዲጠፉ የይሖዋ ብያኔ እንደነበረ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም መጥፋት አለባት። እንዲያውም የሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ጥፋት ቀርቧል። ስለዚህ ከጥፋቱ ሊተርፉ የሚፈልጉ ሁሉ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ይህንንም ማድረግ ያለባቸው ልክ በአውድማ ላይ እህል ከገለባው እንዲለይ ወደ ሰማይ ሲወረወር ገለባው በነፋስ ተጠርጎ እንደሚወስደው ዓይነት “ቀኑ እንደ ገለባ ከማለፉ” በፊት መሆን አለበት። ከአምላክ ቁጣ እንድንሰወር ከፈለግን የሚያቃጥለው የይሖዋ የቁጣ ቀን ሳይመጣብን ንጹሑን ልሳን መናገርና አምላክ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተን አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት አለብን። በሶፎንያስ ዘመንና ባሁኑ ጊዜም ትሑታን ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን ይፈልጋሉ። ይሖዋን መፈለግ ማለትም በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አእምሮአችንና ጉልበታችን እሱን ማፍቀር ማለት ነው። (ማርቆስ 12:29, 30) እንዲህ የሚያደርጉም “ምናልባት በይሖዋ ቁጣ ቀን ይሰወሩ ይሆናል።” ታዲያ ለምንድን ነው ትንቢቱ “ምናልባት” የሚለው? ምክንያቱም መዳን በታማኝነትና በጽናት ላይ የተመካ በመሆኑ ነው። (ማቴዎስ 24:13) ከአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች ጋር የሚስማሙና ንጹሑን ልሳን በመናገር የሚቀጥሉ ከይሖዋ ቁጣ ቀን ይሰወራሉ።

17. ልንመለከታቸው የሚገቡ ምን ጥያቄዎች ይቀራሉ?

17 የይሖዋ የቁጣ ቀን ቅርብ ስለሆነና መዳንም የተመካው ንጹሑን ልሳን በመማርና በመጠቀም ላይ በመሆኑ እሱን በማጥናትና በመናገር የምንዋጥበት ጊዜ አሁን ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ንጹሑን ልሳን ሊማር የሚችለው እንዴት ነው? እሱን በመናገርስ ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

እንዴት ትመልሳለህ?

◻ የሰው ንግግር እንዴት መጣ?

◻ ንጹሑ ልሳን ምንድን ነው?

◻ በሶፎንያስ 3:8, 9 ላይ ያሉት ቃላት ላሁኑ ጊዜ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ለምንድን ነው?

◻ “በይሖዋ የቁጣ ቀን” ለመሰወር ምን ማድረግ አለብን?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባቤል አምላክ የሰዎቹን ቋንቋ በመደበላለቅ እንዲበተኑ አደረጋቸው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ