ኢየሱስ ሕይወቱና አገልግሎቱ
በአምላክ ቀኝ በኩል
በጴንጠቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ለመመለሱ ማስረጃ ነው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ለደቀመዝሙሩ እስጢፋኖስ የተሰጠው ራእይ ኢየሱስ ወደ ሰማይ መድረሱን አረጋግጧል። እስጢፋኖስ በታማኝነት በሰጠው ምስክርነት ምክንያት በድንጋይ ከመወገሩ በፊት “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” ብሎ ነበር።
ኢየሱስ በአምላኩ ቀኝ ሆኖ አባቱ “ሂድ በጠላቶችህ መካከል ግዛ” የሚለውን ትእዛዝ እስኪሰጠው ድረስ ሲጠባበቅ ነበር። ሆኖም በጠላቶቹ ላይ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ምን ያደርጋል? በቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱ ላይ ይገዛል። ይኸውም በስብከት ሥራቸው ይመራቸዋል፣ ከሞት በመነሣት በአባቱ መንግሥት ውስጥ ከእርሱ ጋር ተባባሪ ነገሥታት እንዲሆኑ ያዘጋጃቸዋል።
ለምሳሌም ያህል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ወደ ሌሎች አገሮች ለማስፋፋት ሳውልን (በኋላ በይበልጥ ጳውሎስ በሚለው ሮማዊ ስሙ የሚታወቀውን) መረጠ። ሳውል ለአምላክ ሕግ ቀናተኛ ነበረ፤ ቢሆንም በአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች በስሕተት ተመርቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ሳውል በእስጢፋኖስ መገደል መስማማት ብቻ ሳይሆን ሊያገኛቸው የቻላቸውን የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑትን ወንዶችና ሴቶች በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ከሊቀ ካህናቱ ከቀያፋ የተቀበለውን ፈቃድ ይዞ ወደ ደማስቆ ሄደ። ሆኖም ሳውል በጉዞ ላይ እያለ በድንገት ደማቅ ብርሃን በዙሪያው አበራ፤ እርሱም በምድር ላይ ወደቀ።
ከአንድ ከማይታይ ምንጭ አንድ ድምጽ “ሳውል ሳውል ስለ ምን ታሳድደኛለህ?” ብሎ ጠየቀው። ሳውልም “ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ?” አለው።
“አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ” የሚል መልስ መጣለት።
በተዓምራዊው ብርሃን ዓይኑ ለታወረው ሳውል ኢየሱስ ወደ ደማስቆ እንዲገባና የሚሰጠውን መመሪያ እንዲጠብቅ ነገረው። ከዚያም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ለሆነው ለሐናንያ በራእይ ተገለጠለት። ኢየሱስ ስለ ሳውል ለሐናንያ እንዲህ ብሎ ነገረው፦ “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው።”
በእርግጥም ሳውል (በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ተብሎ የሚታወቀው) እና ሌሎች ወንጌላውያን ከኢየሱስ በሚያገኙት ድጋፍ በመስበክና በማስተማር ሥራቸው ከፍተኛ ውጤት አግኝተዋል። እንዲያውም ጳውሎስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ እያለ ኢየሱስ ከተገለጠለት ከ25 ዓመት አካባቢ በኋላ ጳውሎስ “ምሥራቹ” “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ” መሆኑን ጽፎ ነበር።
ሌሎች ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ኢየሱስ ለሚወደው ሐዋርያው ለዮሐንስ ተከታታይ የሆኑ ራዕዮችን ሰጥቶት ነበር። ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱሱ የራእይ መጽሐፍ ውስጥ በገለጻቸው በእነዚህ ራእዮች አማካኝነት ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን ሲመለስ የሚኖረውን ሁኔታ ለመመልከት ችሎ ነበር። ዮሐንስ “በመንፈስ” ወደፊት ወደሚመጣው “የጌታ ቀን” ተወስዶ እንደነበር ተናግሮአል። ያ “ቀን” ምንድን ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን፣ ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖች የሰጠውን የራሱን ትንቢት ጭምር በጥንቃቄ ማጥናቱ “የጌታ ቀን” የጀመረው በዚህ በዛሬው ትውልድ ውስጥ በታሪካዊው ዓመት በ1914 መሆኑን ያሳየናል! ስለዚህ ኢየሱስ በሕዝብ የሆታ አቀባበል ሳይደረግለት በማይታይ ሁኔታ የተመለሰው በ1914 ነበረ፤ መመለሱን የተገነዘቡት ታማኝ አገልጋዮቹ ብቻ ነበሩ። በዚህ ዓመት ኢየሱስ በጠላቶቹ መካከል እንዲገዛ ይሖዋ ትእዛዝ ሰጠው።
ኢየሱስ የአባቱን ትእዛዝ በማክበር ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር በመጣል ሰማያትን አጸዳ። ዮሐንስ ይህ ሲፈጸም በራእይ ከተመለከተ በኋላ አንድ ድምጽ ከሰማይ “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ!” ብሎ ሲያውጅ ሰማ። አዎን በ1914 ክርስቶስ ንጉሥ በመሆን መግዛት ጀምሮአል!
ይህ በሰማይ ለሚኖሩት የይሖዋ አምላኪዎች እንዴት ያለ የምሥራች ነው! እነርሱ “ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ” ተብለዋል። በምድርስ ላይ ሁኔታው እንዴት ይሆናል? ከሰማይ የመጣው ድምጽ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”
አሁን የምንኖረው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው። ሰዎችም ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት ወይም የጥፋት ፍርድ ለመቀበል በመለየት ላይ ይገኛሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ የወደፊት ሁኔታህ በአሁኑ ጊዜ በክርስቶስ መሪነት በመላው ምድር ላይ ለሚሰበከው የአምላክ መንግሥት የምሥራች በምትሰጠው ምላሽ ይወሰናል።
ሰዎችን የመለያየቱ ሥራ ሲያበቃም ኢየሱስ ክርስቶስ መላውን የሰይጣን የነገሮች ሥርዓትና ደጋፊዎቹን በሙሉ ከምድር ጠራርጎ ለማጥፋት የአምላክ ወኪል በመሆን ይሠራል። ኢየሱስ ይህን ክፋትን ሁሉ የማስወገድ ሥራ የሚያከናውነው በመጽሐፍ ቅዱስ ሐርማጌዶን ወይም አርማጌዶን ተብሎ በሚጠራው ጦርነት ነው። ከዚያ በኋላ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከይሖዋ አምላክ ቀጥሎ በታላቅነቱ ወደር የለሽ የሆነው ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ይዞ ለአንድ ሺህ ዓመት “በጥልቁ” ይኸውም እንደ ሞት በሚቆጠር የበድንነት ሁኔታ ያስራቸዋል። ሥራ 7:55-60፤ 8:1-3፤ 9:1-19፤ 16:6-10፤ መዝሙር 110:1, 2፤ ዕብራውያን 10:12, 13፤ 1 ጴጥሮስ 3:22፤ ሉቃስ 22:28-30፤ ቆላስይስ 1:13, 23፤ ራእይ 1:1, 10፤ 12:7-12፤ 16:14-16፤ 20:1-3፤ ማቴዎስ 24:14፤ 25:31-33
◆ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ የት ተቀመጠ? ምንስ ይጠባበቅ ነበር?
◆ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ በነማን ላይ ይገዛ ነበር? ይህስ አገዛዝ የታየው እንዴት ነበር?
◆ “የጌታ ቀን” የጀመረው መቼ ነው? ያ ቀንስ ሲጀምር ምን ነገር ሆነ?
◆ ዛሬ እያንዳንዳችንን በግል የሚነካ ምን የመለያየት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል? መለያየቱስ የሚከናወነው በምን መሠረት ነው?
◆ የመለየቱ ሥራ ሲያበቃ ምን ሁኔታዎች ይከተላሉ?