የጊልያድ ምሩቃን አርኪ የሆነውን የሕይወት መንገድ ተያያዙት
“ይህ 90ኛው የጊልያድ ኮርስ ተካፋዮች ምረቃ እንዴት ያለ አስደሳች ወቅት ነው!” የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሊቀመንበሩ ካርል ኤፍ ክላይን የምረቃ ፕሮግራሙን የጀመረው በእነዚህ ቃላት ነበር። የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የጀመረበትን ጊዜ በማስታወስ እንዲህ በማለት ጨምሮ ተናገረ፦ “በ1943 የመጀመሪያው የጊልያድ ኮርስ ተካፋዮች ሲመረቁ ከዚያ በኋላ 48 ዓመታት ቆይቶ ገና ለሌላ ማለትም ለ90ኛ ኮርስ ተካፋዮች ምረቃ እንሰበሰባለን ብሎ ያሰበ ማን ነበር?”
ይሁን እንጂ መጋቢት 3, 1991 በኒው ጀርሲ ውስጥ ያለ ወቅቱ ሞቃት በሆነው በዚህ ቀን ለእነዚህ አዲስ ሚስዮናውያን ምረቃ ከ4,000 በላይ የተጋበዙ እንግዶችና የቤቴል ቤተሰብ አባሎች ከኒው ዮርክ ከተማ ከወንዙ ባሻገር በሚገኘው የጀርሲ ከተማ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰበሰቡ። ምሩቃኑ የሚስዮናዊነትን ሕይወት ከመጀመራቸው በፊት በምረቃቸው ቀን አንዳንድ የመሰነባበቻ ምክር ይቀበላሉ።
ፕሮግራሙ የተከፈተው በመዝሙር ነበር። ከዚያ በኋላ የ97 ዓመት ዕድሜ ያለው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ፕሬዝዳንት ፍሬድሪክ ደብልዩ ፍራንዝ የመክፈቻ ጸሎት ሲያቀርብ በዚያ የነበሩት የሁሉም ተሰብሳቢዎች ልብ በጥልቅ ተነካ። ከዚያም ሊቀ መንበሩ የመግቢያ አስተያየት ከሰጠ በኋላ ምሩቃኑና በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ አጫጭርና ተከታታይ የሆኑ ተግባራዊ ንግግሮችን በጥሞና አዳመጡ።
የፋብሪካው ኮሚቴ አባል የሆነው ማክስ ኤች ላርሰን “ከይሖዋ ጋር አብረው የሚሠሩ ሠራተኞች” በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ንግግር አቀረበ። ኖኅና ቤተሰቡ ወደሠሩት የመዳኛ መርከብ ትኩረትን ከሳበ በኋላ እንዲህ አለ፦ ‘ባሁኑ ጊዜ ይሖዋ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብን እያሰባሰበ ነው፤ ይህን ትልቅ ቤተሰብም ታላቁን መከራ ሊያሻግረው ዓላማ አድርጓል። እንዴት? በዘመናዊው መርከብ በተመሰለው መንፈሳዊ ገነት አማካኝነት ነው! ቀጥሎም ምሩቃኑን “እናንተ ዘመናዊውን መርከብ በመገንባት ከይሖዋ ጋር ሠራተኞች ወደምትሆኑባቸው ልዩ ልዩ የምድር ክፍሎች ልትሄዱ ነው” ሲል አሳሰባቸው። ወደፊት ለሚጠብቃቸው ሥራ ሲያዘጋጃቸውም እንዲህ አለ፦ “በእናንተ በኩል ሥራ መሥራትን ይጠይቅባችኋል። እንቅፋቶችም ሊያጋጥሟችሁ ነው። ከስልጠናችሁ ያገኛችኋቸው ጥበቦች የሚያስፈልጓችሁ እዚህ ላይ ነው።”
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ በጃፓንና በኮስታ ሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሚስዮናውያንን ጎብኝቶ ነበር። “የእናንተ ኑሮ በረከት ያለበት ነው” የሚለውን አጠቃላይ መልዕክት በማብራራት ከእነዚህ ውጤታማ የሆኑ ሚስዮናውያን የቃረማቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች አካፈላቸው። አንዲት እህት እናቷ ‘የመስክ አገልግሎትን ውደጂ። ከሰዎች ጋር ወዳጅነትን መሥርቺ። ሕይወትሽን ለሌሎች አካፍይ፤ ይህም ላንቺ ደስታን ያመጣልሻል’ ስትል የሰጠቻትን ምክር እንዳስተላለፈች ገለጸ። ሌላዋም እህት፦ ‘ባለፉት ዓመታት ከሌሎች ሰዎች ብዙ ነገር ካልጠበቅን በቀላሉ ተስፋ እንደማንቆርጥ ለማወቅ ችለናል። ማንኛውም ዓይነት ደግነትና አሳቢነት ሲደረግልን ለእኛ በጣም ትልቅ ነገር አድርገን እንቆጥረዋለን’ ብላለች። እንዲህ ዓይነቱን ተግባራዊ ምክር በሥራ ላይ ማዋሉ ምሩቃኑ የተሳካላቸው ሚስዮናውያን እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው አያጠራጥርም።
1 ተሰሎንቄ 5:14 “ሰውን ሁሉ ታገሡ” ይላል። የአገልግሎት መምሪያ ኮሚቴ አባል የሆነው ሊዮን ዊቨር “በሥራችሁ ሁሉ ታጋሾች ሁኑ” በሚለው አጠቃላይ መልዕክት ንግግር ሲያቀርብ በዚህ ጥቅስ ላይ ማብራሪያ ሰጥቶበታል። ትዕግሥት ልናሳያቸው የሚገባን “ሰውን ሁሉ” የተባሉት እነማንን ይጨምራሉ? ተናጋሪው መልስ ሲሰጥ “በመስክ አገልግሎት የምታገኙአቸው ሰዎች ናቸው። በአዲሱ ጉባኤያችሁ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ናቸው። ሚስዮናዊ የሆኑት ጓደኞቻችሁ ናቸው። በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ያሉት ናቸው። የትዳር ጓደኛችሁ፣ ራሳችሁ ናችሁ’ አለ። በሥራችን ሁሉ ታጋሾች መሆን ያለብን ለምንድን ነው? ተናጋሪው እንዲህ ሲል ገለጸ፦ ‘ወንድሞችና እህቶች፤ ትዕግሥት ውጥረትንና ጭንቀትን ይቀንሳል። ትዕግሥት ሰላምን ያስገኛል። ትዕግሥት ተስፋን ሕያው አድርጎ ያቆያል። ትዕግሥት በአገልግሎት ያለንን ደስታ ይዘን ለመቆየት ይረዳናል።’
ቀጥሎ ንግግር ያደረገው የአስተዳደሩ አካል አባል የሆነውና የጊልያድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ሬጅስትራር የነበረው አልበርት ዲ ሽሮደር ነው። “ምሳሌያችሁ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መከተላችሁን ቀጥሉ” በሚለው አጠቃላይ መልዕክት ንግግር ሲያደርግ ላቀረባቸው ሐሳቦች መሠረት ያደረገው ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2ን ነበር። ፊልጵ 2 ቁጥር 5 “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን” ይላል። ተናጋሪው እንዲህ ሲል ገለጸ፦ ‘ይህ የሚያመለክተው ልክ ኢየሱስ ራሱ ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንደነበረው እኛም ሚዛናዊ አስተሳሰብ ሊኖረን እንደሚያስፈልግ ነው።’ ቀጥሎም ከፊልጵ 2 ቁጥር 6 በመጀመር ኢየሱስ ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንደነበረው ጳውሎስ በመጀመሪያ ማስረጃዎችን ስለመስጠቱ ግሩም የሆነ ትንተና አደረገ፤ (ፊልጵ 2 ቁጥር 6-8) ከዚያም የታዛዥነት መንገድ በመከተሉ ይሖዋ በምን መንገዶች እንደባረከው አብራራ። (ፊልጵ 2 ቁጥር 9-11) ‘ኢየሱስ ክርስቶስን መስበኩ፣ ሌሎችም እርሱ የነበረውን ዓይነት የአእምሮ ዝንባሌ እንዲኖራቸው መርዳቱ የመብታችሁ ክፍል ነው’ በማለት ደመደመ።
የትምህርት ቤቱ መምህራንስ ለተማሪዎቻቸው ምን የመሰነባበቻ ቃላት ነበራቸው? ጃክ ዲ ሬድፎርድ “የማሰብ ችሎታ ይጠብቅሃል” በሚል ርዕስ ንግግር አደረገ። (ምሳሌ 2:10, 11) እንዲህ ሲል ገለጸ፦ ‘አሁን ከዚህ ስትወጡ ደስታችሁ የሚመካው እነማን በመሆናችሁ ወይም ባላችሁ ነገር፣ ወይም የጊልያድ ምሩቃን በመሆናችሁ ላይ አይደለም። ደስታችሁ የሚመካው በአስተሳሰባችሁ ሁኔታ ላይ ነው። በማሰብ ችሎታችሁ ከተጠቀማችሁበትና እውቀታችሁን በሥራ ላይ ካዋላችሁ ደስተኞች ትሆናላችሁ።’ የማሰብ ችሎታን አስፈላጊነት በማሳየትም እንዲህ ሲል ገለጸ፦ ‘በትክክለኛና በተሳሳተ ድርጊት መካከል ያለው ልዩነት አስተሳሰብ ነው። የምታስቡት ነገር የምታደርጉትን ነገር ይወስናል።’ ጄ ዲ ሬድፎርድ ለተማሪዎቹ የሚከተሉትን የማበረታቻ ቃላት በመናገር ንግግሩን ደመደመ፦ ‘በዓለም ላይ ብልህ ሆነው ግን ደካማ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ። መካከለኛ የሆነ ብልህነት ኖሮአቸው ጥሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎችም አሉ። ስለዚህ ይህንን ችሎታ አግኙ። አእምሮአችሁን ልትጠቀሙበት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እውቀታችሁን ተጠቀሙበት። ችግሮችን ተቋቋሙ። ከሰዎች ጋር ተስማምታችሁ ኑሩ። የበላይ ሥልጣንን ተቀበሉ። በሥራችሁ ፍሬያማ ሁኑ። በምድብ ሥራችሁ ጽኑ።’
የትምህርት ቤቱ ሬጂስትራር ዩሊሰስ ቪ ግላስ በመዝሙር 37:23, 24 ላይ የተመሠረተውን “ይሖዋ እጃችንን ይደግፋል” የሚል ርዕስ መረጠ። ‘ለመማር ባላቸው ፍላጎት ምክንያት የዚህን ክፍል ተማሪዎች ማመስገን ይገባኛል’ ሲል ገለጸ። ይሖዋ እነርሱን ለመርዳት የሰጣቸውን አንዳንድ እርዳታዎች አስታወሳቸው። እነዚህም የአምላክ ቃል፣ የቅዱሳን ጽሑፎችን ትርጉም ለማወቅና ለመረዳት በኢየሱስ አመራር ሥር የሚገኘውን ታማኝና ልባም ባሪያ፣ የተለያዩ ጽሑፎች፣ ስብሰባዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች ናቸው። ‘በትምህርታችሁ ላይ የተጠቀማችሁባቸው እርዳታዎች እንደ መንፈሳዊ ዘንግና በትር ናቸው። መንፈሳዊ ድጋፍ ለማግኘት ያስፈልጉናል። የአምላክን ቃል ለሌሎች በምናስተላልፍበት ጊዜም በሥልጣን እንድንናገር ያስችሉናል።’ በመደምደሚያውም ላይ ለተማሪዎቹ የሚከተሉትን የምክር ቃላት ተናገረ፦ ‘ልባችሁ ለሰዎች ባላችሁ ፍቅር የተሞላ ከሆነ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምላሽ ይሰጣሉ። በአገልግሎታችሁም ውጤታማ ትሆናላችሁ። ይሖዋ እጃችሁን ደግፎ እንደያዘ ለማወቅ ትችላላችሁ።’
በጠዋቱ ፕሮግራም ላይ የመጨረሻው ተናጋሪ የነበረው የአስተዳደሩ አካል አባል የሆነው ካሪ ደብልዩ ባርበር ሲሆን “በጠበበው በር ግቡ” የሚለውን አርዕስት መርጦ ነበር። በሉቃስ 13:23, 24 ላይ ማብራሪያውን ሲሰጥ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ ‘የሕይወትን በረከቶች ለማግኘት የሚፈልጉትን ብዙዎች ናቸው፤ ይሁን እንጂ እነዚህን በረከቶች ለማግኘት በሙሉ ኃይላቸው ለመጋደል ፈቃደኞች የሆኑት በጣም ጥቂቶች ናቸው።’ እኛስ እንዴት ነን? ‘ራሳችንን “ለእኔ በግሌ የዚህ የጠባብ በር ምስል ምን ትርጉም አለው?” ብለን መጠየቃችን ጥሩ ነው።’ በጠባቡ በር ሳይገቡ የቀሩት ለመግባት ያልቻሉት የማይቻል ስለሆነ ሳይሆን ለመጋደል ፈቃደኞች ስላልሆኑ ነው። ተናጋሪው ቀጥሎ እንዲህ ሲል ገለጸ፦ ‘ይሖዋ ከእኛ ብዙ ነገር አይጠይቅብንም።’ በመደምደሚያውም ላይ ‘ሁላችንም በይሖዋ እርዳታ በጠባቡ በር በኩል ለይሖዋ ክብር የዘላለም ሕይወት፣ ሰላም፣ ደስታ ወደሚገኝበት አዲስ ዓለም በደስታ ባለን ኃይል ሁሉ ለመግባት እንጋደል!’
ከእነዚህ አስተያየቶች በመቀጠል ሊቀመንበሩ ከተለያዩ የምድር ክፍሎች የተላኩትን ሰላምታዎች አስተላለፈ። አሁን ተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውን የሚቀበሉበት ሰዓት ነው። ተማሪዎቹ ከስድስት አገሮች ይኸውም ከካናዳ፣ ከፊንላንድ፣ ከጀርመን፣ ከእንግሊዝ፣ ከስዊዘርላንድና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ነበሩ። ሆኖም ምድባቸው እንደ አርጀንቲና፣ ቤኒን፣ ቦሊቪያ፣ የዶሜኒካ ሪፓብሊክ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ፔሩ፣ ሴንት ሉሲያና ታይዋን ወደ መሳሰሉት አገሮች የሚወስዳቸው ነበር። ተመራቂዎቹ በምረቃቸው ቀን እንዴት ያለ ስሜት ተሰምቷቸው ነበር? ለአስተዳደር አካሉና ለቤቴል ቤተሰብ በላኩት ልብን በሚነካ ደብዳቤያቸው ላይ በከፊል እንዲህ ብለዋል፦ “የአስተዳደር አካሉ፣ የቤቴል ቤተሰብና የመላው የይሖዋ ድርጅት ድጋፍ እንዳለን እንተማመናለን። ወደፊት ችግሮች ሲያጋጥሙን እንደ ውድ ሃብት አድርገን የምንመለከተው ይህንን ድጋፍ ነው። ለዚህ ሁሉ በጣም አመስጋኞች ነን።”
ከእረፍት በኋላ የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም በካርል ኤ አዳምስ አጠር ተደርጎ በተመራው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ተጀመረ። ከዚህም በኋላ ተማሪዎቹ የአምላክን ቃል በማስተማር ልብን ለመንካት እውነተኛ የሆኑ ተሞክሮዎችን በድራማ መልክ አሳዩ። በመጨረሻም ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ የ90ኛው ክፍል ተመራቂዎችም ጭምር ከሕይወት ጭንቀቶች ማምለጥ በሚል ርዕስ በአካባቢው ጉባኤ አስፋፊዎች በቀረበው ወቅታዊ ድራማ ተደስተው ነበር።
ሊቀመንበሩ ካርል ክላይን በመደምደሚያ አስተያየቱ ላይ “በዚህ በመጋቢት 1991 ሦስተኛ ቀን ላይ እዚህ መገኘታችን በእርግጥም መልካም ነው” በማለት ለሁሉም ተናገረ። አስደሳቹ ፕሮግራም የመደምደሚያው መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ሀሮልድ ጄ ዳይስ ባቀረበው ጸሎት ተደመደመ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የክፍሉ ስታትስቲክስ
የተወከሉት አገሮች ቁጥር፦ 6
የተመደቡባቸው አገሮች ቁጥር፦ 10
ጠቅላላ የተማሪዎች ቁጥር፦ 24
አማካይ ዕድሜ፦ 31.2
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው አማካይ ዓመታት፦ 15
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው አማካይ ዓመታት፦ 11
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
90ኛው የተመራቂ ተማሪዎች ክፍል
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ተርታዎቹ ቁጥር የተሰጣቸው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን የስም ዝርዝሮቹ ደግሞ በእያንዳንዱ ተርታ ከግራ ወደ ቀኝ በዝርዝር ተጽፈዋል። (1) ሚለር፣ ኤም፤ ሄለንየስ፣ ኤስ፤ ማርሽ ኤል፤ ከሊማን፣ ኤ፤ ሉስሊ፣ ዋይ፤ ኒዛን ኤች፤ (2) ስኮገን አር፤ ነተር ዲ፤ ኖአክ ኢ፤ ዳይል ኤል፤ ሄይር ጄ፤ (3) ማርሽ ሲ፤ ሄለንየስ ኤች፤ ሉስሊ ኤም፤ ዳንኦ ኤ፤ ኒዛን ዲ፤ (4) ሚለር ኤል፤ ኖአክ ጄ፤ ሄይር ኤል፤ ክሊማን ደብልዩ፤ ስኮገን ዲ፤ ዳይል ኤስ፤ ነተር ደብልዩ።