ከበሽታና ከሞት ጋር በሚደረገው ውጊያ ድል እየተገኘ ነውን?
ከእንግዲህ ወዲህ በሽታ አይኖርም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም! ይህ አባባል ለአብዛኞቹ ሰዎች ምኞታዊ አስተሳሰብ እንጂ ሌላ ቁም ነገር ያለው መስሎ ላይታይ ይችላል። የሕክምና ዶክተርና የባክቴሪዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዌድ ደብልዩ ኦሊቨር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ታሪክ መጻፍ ከጀመረበት ከጥንት ዘመን ጀምሮ በሽታ የሰውን ዘር ዕጣ በከፍተኛ ደረጃ ቀርጾታል። . . . ታላላቅ የሆኑ ወረርሽኝ በሽታዎች በአስፈሪ ፍጥነት በሰው ልጅ ላይ መዓት አውርደዋል . . . በሽታ ያለ ማቋረጥ እግር በግር ሲከታተለው ቆይቷል።”
ሥር ነቀል ለውጥ በቅርቡ እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችለን ምክንያት ይኖራልን? የሕክምናው ሳይንስ ሁሉንም ዓይነት በሽታ ምናልባትም ሞትንም ጭምር ለማጥፋት እየተቃረበ ነውን?
ዶክተሮችና ተመራማሪዎች በሽታን ለመዋጋት አስደናቂ የሆነ ሥራ መሥራታቸው ምንም አያጠያይቅም። ስለ ሁኔታው የሚያውቁ ሰዎች በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ለኮሌራ በሽታ ውጤታማ ሕክምና ስለመገኘቱ ወይም ለአስፈሪው የፈንጣጣ በሽታ ክትባት ስለመፈጠሩ አመስጋኞች ሳይሆኑ መቅረት ይችላሉን? ይህ ክትባት የተፈለሰፈው በ1796 በኤድዋርድ ጄነር ከላም በተገኘና የመግደል ኃይሉ አነስተኛ ከሆነ የከብት ፈንጣጣ ነበር። በ1806 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ቶማስ ጀፈርሰን እንደሚከተለው ብለው ወደ ጄነር በጻፉበት ጊዜ የብዙ ሌሎች ሰዎችን ስሜት ገልጸዋል፦ “ያደረግኸው ነገር የሰው ዘር እንኳንም ተወለደ እያለ በፍጹም ሊረሳው የማይችል ትዝታ ነው። ወደፊት የሚኖሩት ሕዝቦች አስቀያሚ የሆነው ፈንጣጣ መኖሩን የሚያውቁት በታሪክ ብቻ ይሆናል።”
ከዚህም በላይ እንደ ትክትክና መንጋጋ ቈልፍ ያሉትን በሽታዎች በተመለከተ የተደረገው የሕክምና ምርምር ያስገኛቸው ውጤቶችም በጥሩ ስሜትና በምስጋና ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ሰዎችም በቅርቡ የልብ ሕመምንና ካንሰርን ለማከም ስለተገኘው ውጤት አመስጋኞች መሆን ይገባቸዋል። ያም ሆኖ ግን ሰዎች አሁንም በልብ ሕመምና በካንሰር ይሞታሉ። ሁሉንም ዓይነት በሽታና ሕመም የማጥፋቱ ግብ አልጨበጥ ብሎ አስቸግሯል።
“አዲሶቹ” በሽታዎች
ይህ የአሁኑ ዘመን ምርመራን በቴሌቪዥን የሚያሳዩ መሣሪያዎችንና አዲስ የተፈለሰፉ የቀዶ ጥገና ዘዴዎችን የተመለከተ ቢሆንም በአንፃሩ የለጀኔር በሽታዎችን በሰውነት ውስጥ በሚፈጠር መርዝ ድንገት መታመምና በከፍተኛ ደረጃ የተወራለትን ገዳይ ኤድስ የተባለውን በሽታ ተመልክቷል።
ብዙ ሰዎች እነዚህ በሽታዎች ምን ያህል አዲስ ስለመሆናቸው ይጠይቃሉ። በዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ በአንዳንድ ሁኔታዎች በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የቆዩ የበሽታ ዓይነቶች ይበልጥ በትክክል ተመርምረው ሁኔታቸው ይጣራና አዲስ ስም ይሰጣቸዋል በማለት ይዘግባል። ለምሳሌ ያህል ለጀኔር የሚባለው በሽታ በመጀመሪያ የታወቀው በ1976 ነበር። በፊት ግን በቫይረስ የሚመጣ የሳንባ ምች በሽታ ነው እየተባለ በስሕተት ይነገርለት እንደነበር በቅርቡ ተገልጿል። በተመሳሳይ በውስጥ በሚፈጠር መርዝ የሚመጣው ድንገተኛ ሕመም ድሮ የትኩሳት በሽታ የሚል ስም ይሰጠው የነበረው ይመስላል።
ይሁን እንጂ ብዛት ያላቸው በሽታዎች ያለ ጥርጥር አዲስ ይመስላሉ። ከእነዚህ ውስጥ በጣም ታዋቂው ኤድስ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ይህ የሚያሽመደምድና ገዳይ የሆነ በሽታ በመጀመሪያ የታወቀውና ስያሜ የተሰጠው በ1981 ነበር። ሌላው አነስተኛ ታዋቂነት ያለው “አዲስ” በሽታ የብራዚሉ ፐርፐሪክ ፊቨር ነው። ይህ በሽታ ተለይቶ የታወቀው በ1984 በብራዚል ሲሆን የመግደል ችሎታው 50 ከመቶ እንደሆነ ይገመታል።
ምንም መድሃኒት አልተገኘም
ሰው የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ቢሆንም በየትኛውም ቦታ ለሰብዓዊ በሽታዎች የተሟላና ዘላቂ የሆነ ፈውስ አልተገኘም። ከ1900 ዓመት ጀምሮ አማካኙ የሰው የዕድሜ ርዝመት በ25 ዓመታት መጨመሩ እውነት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ለውጥ ሊመጣ የቻለው በሕፃንነት ወይም በልጅነት የመሞትን አደጋ የሚቀንሱ የሕክምና ዘዴዎች በመገኘታቸው ነው። በመሠረቱ የሰው የመኖሪያ ዕድሜ መጽሐፍ ቅዱስ በጠቀሰው “ሰባ ዓመት” አካባቢ ነው።—መዝሙር 90:10
በዚህ ምክንያት አና ዊልያምስ ታህሣስ 1987 በ114 ዓመት ዕድሜያቸው ሲሞቱ ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር። በወይዘሮ ዊልያምስ ሞት ላይ በመተቸት አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “ሳይንቲስቶች የመጨረሻው ረጅም የሰው ዕድሜ ጣሪያ ከ115 እስከ 120 ዓመት እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ግን ለምን እንደዚያ ይሆናል? የሰው አካል 70፣ 80፣ ወይም 115 ዓመት ከቆየ በኋላ ለምን እጅ ይሰጣል?”
በ1960ዎቹ ዓመታት የሕክምና ሳይንቲስቶች የሰው ሴሎች ለመከፈል የሚችሉት እስከ 50 ጊዜ ብቻ መሆኑን በምርምር ደርሰውበት ነበር። ወደዚህ ወሰን ላይ ከተደረሰ ሴሎቹን ሕያው አድርጎ ለማቆየት ምንም ሊደረግ እንደማይቻል መስሎ ይታይ ነበር። ይህ አስተሳሰብ ቀደም ሲል የነበረውንና የሰው ሴሎች ተስማሚ ሁኔታዎች ቢፈጠሩላቸው ለዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ የሚለውን ሳይንሳዊ ንድፈ አሳብ የሚቃረን ይመስላል።
አብዛኛው የሰው ሥቃይ ሰው ሠራሽ መሆኑን በዚህ ላይ ደምሩት። አንድ ተመራማሪ በአስተዋይነት እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል፦ “በሽታዎች በሕክምና ዘዴዎች ብቻ ድል አልተደረጉም። የበሽታ ታሪክ ከማኅበራዊና ከስነ ምግባራዊ ጉዳዮች ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው።”
የዓለም የጤና ድርጅት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ከመጀመሪያውኑ የበሽታን መነሻዎች ከመከላከል ይልቅ ሳይንስ፣ ዶክተሮችና ሆስፒታሎች ይፈውሱናል ብለን በማመን በራሳችን ላይ ሥቃይ አምጥተናል። እርግጥ ሕይወትን ማዳን የሚችሉ የሕክምና እንክብካቤ ድርጅቶች የግድ ያስፈልጉናል፤ ነገር ግን ግልጽ እንዲሆንልን የሚያስፈልገው እነዚህ ድርጅቶች እንዳንሞት ይረዱናል እንጂ ‘ጤንነት’ አይጨምሩልንም . . . ራስን በራስ ለመግደል የሚገፋፋው የሲጋራ ሱስ፣ ጠጪነት፣ ሥራ አጥነት በአእምሮና በአካል ላይ የሚያስከትላቸው ውጤቶች እነዚህ ናቸው አንዳንዶቹ ‘አዲስ በሽታዎች።’ ሕይወትን እየቀጠፈ ያለውንና የገንዘብ ሃብታችንን ያሟጠጠውን ‘የመኪና አደጋ ወረርሽኝ’ ለምን እንዲደርስ እንፈቅዳለን?”
ስለዚህ በሽታ፣ ሕመም፣ ሥቃይና ሞት በአሁኑም ጊዜ ቢሆን ገና ከእኛው ጋር ናቸው። ይሁን እንጂ ወደፊት በሽታና ሞት የማይኖርበትን ጊዜ በትምክህት ለመጠባበቅ ምክንያት አለን። ከዚህም በላይ ይህ ጊዜ በጣም እንደቀረበ ለማመን ብዙ ምክንያት አለ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“የግብጽ በሽታዎች”
ሰዎች ከጥንት ጀምሮ በሽታን ለመዋጋት ያደረጉት ጥረት ከንቱ መሆኑን በመጽሐፍ ውስጥም እንኳ ሳይቀር ተገልጾአል። ለምሳሌ ሙሴ “ክፉውን የግብጽ በሽታ ሁሉ” በማለት ለመረዳት የሚያስቸግር ቃል ጽፎአል።—ዘዳግም 7:15
በግልጽ ለማወቅ እንደሚቻለው እነዚህ የዝሆኔ በሽታን፣ ተቅማጥ የሚያስከትል የሆድ ሕመምን፣ ፈንጣጣን፣ እባጭን፣ የዓይን ሕመምን ይጨምራሉ። የሙሴ ሕዝቦች የሕጉ ቃል ኪዳን እንዲፈጽሙት ባዘዛቸው የላቁ የንጽሕና ሥርዓቶች ምክንያት ከእነዚህ በሽታዎች ለማምለጥ ችለው ነበር።
ሆኖም በመድሃኒት እንዳይፈርሱ በተደረጉት የግብጻውያን የሙታን አካላት ላይ የተደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ ሌሎች ‘የግብጽ በሽታዎችን’ ለይቶ ለማወቅ አስችሏል። እነዚህም አርትራይቲስ የተባለውን የመገጣጠሚያዎች በሽታ፣ የጥርስ ሕመምን፣ የትርፍ አንጀት በሽታን፣ ዩሪክ አሲድ በሽታን ይጨምራሉ። ኤበርስ ፓፒረስ በመባል የሚታወቁት ጥንታዊ የሆኑ የሕክምና ጽሑፎች እንደ ነቀርሳ፣ የሆድና የጉበት ሕመሞች፣ የስኳር በሽታ፣ ቁምጥና፣ የዓይን በሽታዎችና ዲዳነት ያሉትን በሽታዎች እንኳ ሳይቀር ጠቅሰዋል።
ጥንታዊ የግብጽ ሐኪሞች እነዚህን በሽታዎች ለመዋጋት የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። አንዳንዶቹም በሕክምና መስካቸው ልዩ ችሎታ ያገኙ ሆነዋል። የግሪኩ ታሪክ ጸሐፊ ሔሮዶተስ እንዲህ በማለት ጽፎአል፦ “አገሪቱ [ግብጽ] ብዙ የሕክምና አዋቂዎች ያሉባት ነች፤ አንዱ የዓይን በሽታዎችን ብቻ ያክማል፤ ሌላው ራስን፣ ጥርስን፣ ሆድን፣ ወይም ውስጣዊ የአካል ክፍሎችን ያክማል።” ይሁን እንጂ አብዛኛው የግብጽ “መድሃኒት” ሃይማኖታዊ የሆነ ማጭበርበሪያ ያለበትና ከሳይንስ በጣም የራቀ ነው።
ዘመናዊ የሕክምና ባለሞያዎች በሽታን ለማጥፋት ባደረጉት ትግል የበለጠ ውጤት አግኝተዋል። ይሁን እንጂ የሕክምና ተመራማሪ የሆኑት ጄሲ ዶብሰን ወደዚህ ስሜት ቀስቃሽ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “ባለፉት ዘመናት በበሽታዎች ላይ ከተደረገው ጥናት ምን ነገር ለመማር ይቻላል? በማስረጃዎቹ ላይ ከተደረገው ጥናት የተገኘው አጠቃላይ መደምደሚያ ባለፉት ሩቅ ዘመናት የነበሩት ሕመሞችና በሽታዎች በአሁኑ ጊዜ ካሉት በጉልህ የሚለዩ አይደሉም የሚል ነው። . . . በግልጽ እንደሚታወቀው በሽተኞችን ለመመርመር በሥራ ላይ የዋሉት ጥበቦችና ጥረቶች ሁሉ በሽታን ለማጥፋት ምንም አልቻሉም።”—በጥንታዊ ሰው ላይ የነበሩ በሽታዎች