የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 7/15 ገጽ 12-17
  • ደግነት በማሳየት ይሖዋን አስደስት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ደግነት በማሳየት ይሖዋን አስደስት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደግነት ምንድን ነው?
  • የተሳሳተ ደግነት አስወግድ
  • ደግነት ከፍቅር ጋር የተያያዘ ነው
  • ደግነት በአጸፋው የሚያመጣቸው በረከቶች
  • ይገባኛል የማትለውን የአምላክን ደግነት አድንቅ
  • የአምላክ ሕዝቦች ደግነትን መውደድ ይኖርባቸዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ጥላቻ በነገሠበት ዓለም ደግነት ለማሳየት መጣር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ደግነት—በቃልና በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • “የደግነት ሕግ” ይምራችሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 7/15 ገጽ 12-17

ደግነት በማሳየት ይሖዋን አስደስት

“ይሖዋ ከአንተ በአጸፋው የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግና ደግነትን እንድትወድ፣ ቦታህንም ጠብቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ አይደለምን?”​—ሚክያስ 6:8 አዓት

1. ይሖዋ ሕዝቡ ደግነት እንዲያሳዩ የሚጠብቅባቸው መሆኑ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድነው?

ይሖዋ ሕዝቡ ደግነት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል። ይህም ሊያስደንቀን አይገባም። አምላክ ራሱ ለማያመሰግኑ ክፉ ሰዎች እንኳ ሳይቀር ለሁሉም ሰው ደግ ነው። ይህን በሚመለከት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፦ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ። ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል። የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር (ደግ) ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።”​—ሉቃስ 6:35, 36

2. ደግነትን በሚመለከት ልንወያይባቸው የሚገቡን ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?

2 ሚክያስ 6:8 እንደሚናገረው አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር የሚያደርጉ ሰዎች ‘ደግነትን መውደድ’ አለባቸው። ይሖዋ አገልጋዮቹ ደግነትን ሲወዱና ልባዊ በሆነ መንገድ ሲያሳዩት እንደሚደሰት ግልጽ ነው። ግን ደግነት ምንድን ነው? ይህን ጠባይ ከማሳየት የሚመጡት ጥቅሞች ምንድን ናቸው? ይህንንስ ጠባይ እንዴት ማሳየት ይቻላል?

ደግነት ምንድን ነው?

3. ደግነትን የምትገልጸው እንዴት ነው?

3 ደግነት ለሌሎች ሰዎች የሚጠቅም ነገር የማድረግ ወይም የማሰብ ባሕርይ ነው። የሚገለጸውም ሌላውን የሚረዳ ነገር በማድረግና የአሳቢነት ቃላት በመናገር ነው። ደግ መሆን ማለት ማናቸውም የሚጐዳ ነገር በማድረግ ፋንታ መልካም ማድረግ ማለት ነው። ደግ ሰው የወዳጅነት ሁኔታ ይታይበታል፣ የሚናገረው አይጐረብጥም፣ ለሰው ያዝናል፤ ቸር ነው። ለሌሎች የለጋስነትና የአሳቢነት ጠባይ አለው። ጳውሎስ “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን (ደግነትን)፣ ትሕትናን፣ የዋህነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” በማለት ስላሳሰበ ደግነት የእያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ምሳሌያዊ ልብስ ድረ ማግ ክፍል ነው።​—ቆላስይስ 3:12

4. ይሖዋ ለሰው ዘር ደግነትን በማሳየት በኩል ቀዳሚ የሆነው እንዴት ነው?

4 ደግነትን በማሳየት ረገድ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው ይሖዋ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው “የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር [ደግነትና አዓት] መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምህረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን።” (ቲቶ 3:4, 5) አምላክ የክርስቶስን ቤዛዊ መስዋዕት በእነርሱ ላይ በመጠቀም ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በኢየሱስ ደም ያነፃቸዋል ወይም ያጥባቸዋል። በተጨማሪም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አዲስ ይደረጋሉ፤ በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች በመሆን “አዲስ ፍጥረት” ይሆናሉ። (2 ቆሮንቶስ 5:17) እርግጥ የአምላክ ደግነትና ለሰው ያለው ፍቅሩ “ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ላነፁ” ከልዩ ልዩ ብሔራት ለመጡ “እጅግ ብዙ ሰዎችም” ጭምር የተዘረጋ ነው። (ራእይ 7:9, 14፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) ከዚህም በላይ ቅቡዓንና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች ከኢየሱስ “ደግነት” ቀንበር በታች ናቸው።​—ማቴዎስ 11:30

5. በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሰዎች ለሌሎች ደግነትን እንዲያሳዩ መጠበቅ ያለብን ለምንድነው?

5 ከዚህም ሌላ ደግነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ፍሬ ነው። ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት (ደግነት)፣ በገነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።” (ገላትያ 5:22, 23) ስለዚህ በአምላክ መንፈስ ከሚመሩ ሰዎች መጠበቅ ያለብን ምንድነው? ለሌሎች ደግነት እንደሚያሳዩ የተረጋገጠ ነው።

6. ደግነት ሽማግሌዎችንና ሌሎች ክርስቲያኖችን በምን መንገድ እንዲሠሩ ሊያደርጋቸው ይገባል?

6 ደግነት በብዙ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል። መሐሪዎች ስንሆን ደግነትን እናሳያለን። ለምሳሌ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ንስሐ ለገባ በደለኛ ምህረት በሚዘረጉበት ጊዜና በመንፈሳዊ ሊረዱት በሚጥሩበት ጊዜ ደግነት ማሳየታቸው ነው። ከአምላክ የሚሰጠው የደግነት ጠባይ የበላይ ተመልካቾችን ትዕግሥተኞች፣ አሳቢዎች፣ አዛኞችና ገሮች ያደርጋቸዋል። መንጋውን “በመራራት እንዲይዙት” ይገፋፋቸዋል። (ሥራ 20:28, 29) እንዲያውም የመንፈስ ፍሬ የሆነው ደግነት ሁሉንም ክርስቲያኖች ርህሩሆች፣ ትዕግሥተኞች፣ አሳቢዎች፣ አዛኞች፣ ሰው ወዳዶችና እንግዳ ተቀባዮች ሊያደርጋቸው ይገባል።

የተሳሳተ ደግነት አስወግድ

7. የተሳሳተ ደግነት ደካማነት ነው የምትሉት ለምንድነው?

7 አንዳንድ ሰዎች ደግነትን እንደ ደካማነት ይመለከቱታል። ሰዎች በጥንካሬው እንዲያውቁት ክፉ መሆን፣ ሰዎችን የሚያቃልል ኃይለ ቃል የሚናገር መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ “ሰዎችን የሚያቃልል ኃይለ ቃል መናገር የደካማ ሰው ማስመሰያ ብርታት ነው” የሚል ጥሩ አባባል አለ። እንደ እውነቱ ከሆነ እውነተኛ ደግነት ለማሳየትም ሆነ የተሳሳተ ደግነት ለማስወገድ እውነተኛ ጥንካሬ ይጠይቃል። የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነው ደግነት ደካማ የሆነ ወይም ለመጥፎ ጠባይ ቦታ ለመስጠት አቋሙን የሚያላላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተሳሳተው ደግነት ነው አንድ ሰው መጥፎ አድራጐትን ችላ ብሎ እንዲያልፍ የሚያደርገው።

8. (ሀ) ልጆቹን በተመለከተ ዔሊ ልል ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ለተሳሳተ ደግነት ከመሸነፍ መጠበቅ ያለባቸው ለምንድነው?

8 የእሥራኤል ሊቀ ካህን የነበረው ዔሊ በመገናኛው ድንኳን በክህነት ይሠሩ የነበሩትን ልጆቹን ኦፍኒንና ፊንሐስን በመገሰጽ ረገድ ልል ነበር። በሕዝቡ ከሚቀርበው መሥዋዕት በአምላክ ሕግ ለእነርሱ በተወሰነላቸው ድርሻ ባለመርካት የመሥዋዕቱ ስብ በመሰዊያው ላይ ከመቃጠሉ በፊት ሎሌያቸውን እየላኩ መሥዋዕቱን ካቀረበው ሰው ጥሬ ሥጋ ያስመጡ ነበር። እንዲሁም የዔሊ ልጆች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነት ይፈጽሙ ነበር። ዔሊም ልጆቹን ከክህነት ሥራቸው በማባረር ፈንታ ከይሖዋ ይልቅ እነሱን በማክበር ለስለስ ብሎ ብቻ ይገስጻቸው ነበር። (1 ሳሙኤል 2:12-29) “በዚያ ዘመን የይሖዋ ቃል ብርቅ ነበር!” መባሉ አያስደንቅም። (1 ሳሙኤል 3:1) ስለዚህ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የጉባኤውን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ ለሚጥል የተሳሳተ አስተሳሰብ ወይም የተሳሳተ ደግነት መሸነፍ የለባቸውም። እውነተኛ ደግነት የአምላክን የአቋም ደረጃዎች የሚጥሱ መጥፎ ቃላትንና ድርጊቶችን አይቶ አያልፍም።

9. (ሀ) ለተሳሳተ ደግነት እንዳንሸነፍ ምን ዓይነት አቋም ሊረዳን ይችላል? (ለ) ኢየሱስ ከሃዲ ሃይማኖተኞችን በያዘበት መንገድ ጥንካሬ ያሳየው እንዴት ነው?

9 ከተሳሳተ ደግነት ለመራቅ በመዝሙራዊው ቃላት የተገለጸውን ዓይነት ጥንካሬ እንዲኖረን አምላክ እንዲረዳን መጸለይ አለብን፦ “እናንተ ኃጢአተኞች ከኔ ራቁ፤ የአምላኬንም ትዕዛዝ ልፈልግ” (ወይም እንደ አዓት “የአምላኬን ትዕዛዝ እንድጠብቅ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከኔ ራቁ”) (መዝሙር 119:115) ከዚህም ሌላ የተሳሳተ ደግነት በማሳየት ጥፋተኛ ሆኖ የማያውቀውን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት መከተል ያስፈልገናል። እንዲያውም ኢየሱስ የእውነተኛ ደግነት ምሳሌ ወይም መግለጫ ነው። ለምሳሌ “ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጐች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” ይህም በመሆኑ ቅን ልብ የነበራቸው ሰዎች ያለአንዳች ስጋት ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ ይችሉ ነበር። ሕፃናት ልጆቻቸውን ሳይቀር ወደ እሱ ያመጡአቸው ነበር። ‘ሕፃናቱን አቅፎና እጁን ጭኖባቸው በባረካቸው’ ጊዜ ኢየሱስ ያሳየውን ደግነትና ርህራሄ እስቲ ገምት! (ማቴዎስ 9:36፤ ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ ደግ ቢሆንም በሰማያዊ አባቱ ዓይን ትክክል ለሆነው ነገር ጥብቅ ነበር። ኢየሱስ መጥፎ ነገርን ፈጽሞ ችላ ብሎ አልፎ አያውቅም። ግብዞቹን የሃይማኖት መሪዎች ለማውገዝ ከአምላክ የተሰጠው ጥንካሬ ነበረው። በማቴዎስ 23:13-26 ላይ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ!” የሚለውን አነጋገር አያሌ ጊዜ ደጋግሞ ተናግሮታል። ይህን አነጋገር በተጠቀመበት በእያንዳንዱ ጊዜም ኢየሱስ በእነርሱ ላይ ለሚመጣው መለኰታዊ ፍርድ ምክንያቱን ይናገር ነበር።

ደግነት ከፍቅር ጋር የተያያዘ ነው

10. የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ለመሰል አማኞች ደግነትና ፍቅር ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?

10 ተከታዮቹን በሚመለከት ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:35) ታዲያ የኢየሱስን እውነተኛ ደቀመዛሙርት ለይቶ የሚያሳውቀው ፍቅር አንዱ ገጽታ ምንድነው? ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ፍቅር ይታገሳል፣ ቸርነት ያደርጋል” (እንደ አዓት “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው።”) (1 ቆሮንቶስ 13:4) ታጋሽና ደግ መሆን ማለትም ይሖዋ እንደሚያደርገው የሌሎችን አለፍጽምናና ድካም ችለን እንኖራለን ማለት ነው። (መዝሙር 103:10-14፤ ሮሜ 2:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 15) በምድር ላይ በሆነ አካባቢ የሚገኙ አማኝ ባልንጀሮች በችግር በሚጠቁበት ጊዜም ክርስቲያናዊ ፍቅርና ደግነት ይገለጻሉ። በሌላ ቦታ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቶቹን የይሖዋ አምላኪዎች ለመርዳት ቁሳዊ ነገሮችን በማዋጣት ከ“ሰብዓዊ ደግነት” በላይ በሆነ የወንድማማች ፍቅር ምላሽ ሰጥተዋል።​—ሥራ 28:2

11. በቅዱስ ጽሑፉ አነጋገር ፍቅራዊ ደግነት ምንድነው?

11 ደግነት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ በተሠራበት “ፍቅራዊ ደግነት” በሚለው ቃል ውስጥ ገብቶ ስለሚገኝ ደግነት ከፍቅር ጋር ተያይዞ ተገልጾአል። ይህ ደግነት ከታማኝ ፍቅር የሚመነጭ ነው። “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል (ቼሴድህ) ከርህራሄ አመለካከት በላይም ይጨምራል። ከአንድ ነገር ጋር ያለው ዓላማው ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ከዚያ ነገር ጋር በፍቅር የሚጣበቅ ዓይነት ደግነት ነው። የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ተገልጾአል። ለምሳሌ ሕዝቡን በማዳንና በመጠበቅ ሥራዎቹ ተገልጾአል።​—መዝሙር 6:4፤ 40:11፤ 143:12

12. የይሖዋ አገልጋዮች አምላክ እንዲረዳቸው ወይም ከመከራ እንዲያድናቸው በሚጸልዩበት ጊዜ ስለምን ነገር እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ?

12 እንግዲያው የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ሰዎችን ወደ እሱ የሚስብ መሆኑ አያስደንቅም። (ኤርምያስ 31:3) የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከመከራ መዳን ወይም እርዳታ ሲሹ የሱ ፍቅራዊ ደግነት በእርግጥ ታማኝ ፍቅር እንደሆነና ፈጽሞ እንደማይተዋቸው ያውቃሉ። ስለዚህ መዝሙራዊው “እኔ ግን በቸርነትህ (በፍቅራዊ ደግነትህ አዓት) ታመንሁ። ልቤም በመድኃኒትህ (በማዳንህ) ደስ ይለዋል” እንዳለው በእምነት ሊጸልዩ ይችላሉ። (መዝሙር 13:5) የአምላክ ፍቅር ታማኝ ስለሆነ አገልጋዮቹ በፍቅራዊ ደግነቱ የሚታመኑት በከንቱ አይደለም። እንዲረዳቸው ወይም ከመከራ እንዲያድናቸው በሚጸልዩበት ጊዜ “ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልምና ርስቱንም አይተውም” የሚለው ማረጋገጫ አላቸው።​—መዝሙር 94:14

ደግነት በአጸፋው የሚያመጣቸው በረከቶች

13, 14. ደግ ሰው ታማኝ ወዳጆች የሚኖሩት ለምንድነው?

13 ይሖዋን በመምሰል አገልጋዮቹ እርስ በርሳቸው ፍቅራዊ ደግነትንና ምህረትን ያሳያሉ። (ዘካርያስ 7:9፤ ኤፌሶን 5:1) ከምድራዊ ሰው የሚፈለገው ነገር ፍቅራዊ ደግነቱ ሲሆን ይህን ባሕርይ የሚያሳይ ሰው ብዙ በረከቶችን በአጸፋው ያገኛል። (ምሳሌ 19:22) ከእነዚህ በረከቶች አንዳንዶቹ ምንድናቸው?

14 ደግነት ሰውን በጥበብ እንድንይዝ ስለሚያደርገን ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ይረዳናል። ሌሎችን በጥበብ የሚይዝ ሰው ነገሮችን የሚናገረው ወይም የሚያደርገው ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የሚይዘው አሳቢነት በተሞላበትና ቅር በማያሰኝ መንገድ ነው። “ጨካኝ ሰው” መከራ ይደርስበታል። “ደግ ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል።” (ምሳሌ 11:17) ጨካኝን ሰው ሰዎች ይርቁታል፤ ፍቅራዊ ደግነት ወደሚያሳያቸው ግን ይጠጋሉ። ስለዚህ ደግ ግለሰብ ታማኝ ወዳጆች አሉት።​—ምሳሌ 18:24

15. በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ደግነት ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል?

15 የማያምን ባል ያላት ክርስቲያን ሚስት እንዲህ በመሰለው የደግነት ባሕርይ ባሏን ወደ አምላክ እውነት ልትስበው ትችላለች። እውነትን ከመማሯና ‘እውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ከመልበሷ’ በፊት ክፉ እንዲያውም ጠበኛ ኖራ ልትሆን ትችላለች። (ኤፌሶን 4:24) ባሏ የመጽሐፍ ቅዱስን አንዳንድ ምሳሌዎች አውቆ ቢሆን ኖሮ “ጠበኛ ሚስት እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት” ለሚለውና “ከጠበኛ ሴት ጋር (በብስጭት) በአንድ ቤት ከመቀመጥ በውጭ በቤት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል” በሚሉት አባባሎች ይስማማ ነበር። (ምሳሌ 19:13፤ 21:19) አሁን ግን የክርስቲያኗ ሚስት ንጹሕ ጠባይና ጥልቅ አክብሮት እንዲሁም የደግነት ባሕርይ የትዳር ጓደኛዋን ወደ እውነተኛው እምነት ሊመልሱት ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) አዎን፤ ይህ ደግነቷ ያስገኘው አንዱ ውጤት ሊሆን ይችላል።

16. ለእኛ ከተደረገልን ደግነት ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

16 ሌላው ሰው ለእኛ ያሳየው ደግነት እኛንም ርህሩሆችና ይቅር ባዮች እንድንሆን በማድረግ ሊጠቅመን ይችላል። ለምሳሌ መንፈሳዊ ዕርዳታ አስፈልጎን የነበረ ቢሆንና በደግነትና በገርነት ተይዘን ከነበረ ለሌሎችም እንዲሁ ወደማድረግ እንድናዘነብል አያደርገንምን? ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ ሰው በማናቸውም በደል እንኳ ቢገኝ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት” በማለት ስለጻፈ የደግነትና የገርነት አያያዝ መንፈሳዊ ብቃት ካላቸው ሰዎች ሊጠበቅ ይችላል። (ገላትያ 6:1) ጥፋት የፈጸሙ አንዳንድ መሰል አማኝ ክርስቲያኖችን ሊረዱ በሚፈልጉበት ጊዜ ኃላፊነት ያላቸው ሽማግሌዎች በየዋህነትና በደግነት ይናገራሉ። እኛ በግላችን እንዲህ ዓይነት የደግነት እርዳታ ተቀብለን ይሁንም አይሁን አምላክ ከሚያገለግሉት ሰዎች ሁሉ ምን ይጠብቃል? ሁሉም ክርስቲያኖች ለሌሎች ደግነት ሊያሳዩና “እርስ በርሳችሁም [ደጎችና] ርህሩሆች ሁኑ። እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” ሲል ጳውሎስ የሰጠውን ምክር መቀበል ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 4:32) እርግጥ በአንድ ሌላ ሰው ይቅርታ ተደርጎልን ከሆነ ወይም ከአንድ መንፈሳዊ ችግር እንድንወጣ በደግነት መንገድ እርዳታ ተደርጎልን ከነበረ ይህ ሁኔታ ይቅር ለማለትና የርህራሄና የደግነት ጠባይ ለማሳየት የነበረንን ችሎታ ሊጨምረው ይገባል።

ይገባኛል የማትለውን የአምላክን ደግነት አድንቅ

17. ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ስለሆንን በተለይ ስለ የትኛው ደግነት አመስጋኞች መሆን ይገባናል?

17 ሁላችሁም ሞት የተፈረደብን ኃጢአተኞች ሆነን ስለተወለድን በተለይ አመስጋኞች ልንሆንበት የሚያስፈልገን አንድ የደግነት አድራጎት አለ። እሱም ይሖዋ አምላክ ያሳየን ይገባናል የማንለው ደግነት ነው። ኃጢአተኞች ከሞት ኩነኔ ተላቀው ጻድቃን ሆናችኋል ቢባሉ ፈጽሞ የማይገባቸው ደግነት ነው። የአምላክን የማይገባ ደግነት በመንፈስ ተገፋፍቶ በጻፋቸው 14 መልዕክቶቹ ውስጥ 90 ጊዜ የጠቀሰው ጳውሎስ በጥንቷ ሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል። በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ” በማለት ነግሯቸዋል። (ሮሜ 3:23, 24) ይሖዋ አምላክ ያሳየንን የማይገባን ደግነት ምን ያህል ማድነቅ ይገባናል!

18, 19. የአምላክን የማይገባ ደግነት ዓላማ ከመሳት ልንቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

18 አድናቂዎች ባለመሆን የአምላክን የማይገባ ደግነት ዓላማ ልንስት እንችላለን። በዚህ ረገድ ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን። ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን። በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በማዳንም ቀን ረዳሁህ” ይላልና። (ኢሳይያስ 49:8) እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው። እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው። አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን።” (2 ቆሮንቶስ 5:20 እስከ 6:4) ይህን ሲናገር ጳውሎስ በአእምሮው የያዘው ምን ነበር?

19 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ክርስቶስን የሚወክሉ አምባሳደሮች ሲሆን እጅግ ብዙ ሰዎች ደግሞ መልእክተኞቹ ናቸው። አንድ ላይ ሆነው ሰዎች መዳን ያገኙ ዘንድ ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ ያሳስባሉ። ጳውሎስ ማንም ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰጠውን የይሖዋ አምላክን የማይገባ ደግነት ተቀብሎ ዓላማውን እንዲስት አልፈለገም። ያ የማይገባ ደግነት ለአንድ ሥራ ብቁ ያደረገን ሲሆን ያንን ሥራ መሥራት ካልቻልን እኛም የአምላክን የማይገባ ደግነት ተቀብለን ዓላማውን ልንስት እንችላለን። ከአምላክ ጋር የታረቅን እንደመሆናችን ከሱ ጋር በወዳጅነት ደረጃ ላይ ስለምንገኝ “የማስታረቁን አገልግሎት ማለትም እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር በማስታረቅ” ላይ እንደነበረ የሚገልጸውን አገልግሎት ከፈጸምን የማይገባውን ደግነት በከንቱ እየተቀበልን አንገኝም። (2 ቆሮንቶስ 5:18, 19) ሌሎችም ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ በመርዳት ተወዳዳሪ የሌለውን ደግነት እንሠራላቸዋለን።

20. ቀጥለን ምን እንመረምራለን?

20 የይሖዋ አገልጋዮች በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው አማካኝነት ሰዎችን ለመርዳት በሚጥሩበት ጊዜ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በደግነት ሥራዎች ላይ ያውላሉ። ይሁን እንጂ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ ከተገለጹት የደግነት አድራጐቶች ምን ልንማር እንችላለን? ከእነዚህ አንዳንዶችን ቀጥለን እንመርምርና ደግነትን በማሳየት ይሖዋን የምናስደስትባቸውን ሌሎች መንገዶች እንመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ደግነት ምንድነው?

◻ ለተሳሳተ ደግነት ከመሸነፍ ለመራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

◻ የይሖዋ ሕዝቦች እርሱ በሚያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ሊተማመኑ የሚችሉት ለምንድን ነው?

◻ ደግነት የሚያመጣቸው አንዳንድ ውጤቶች ምንድን ናቸው?

◻ ምን በማድረግ ነው የአምላክ የማይገባ ደግነት ዓላማ የማንስተው?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደግነት ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ትዕግሥተኞች፣ አሳቢዎችና ርኅሩሆች ያደርጋቸዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሚስት የምታሳየው ደግነት ባልዋን ወደ እውነት ሊስበው ይችል ይሆናል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌሎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ በመርዳት ተወዳዳሪ የሌለውን ደግነት ልናሳያቸው እንችላለን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ