ይሖዋ “ጀግና ተዋጊ ነው”
ምርጥ የሆነው የግብፃውያን ጦር ሠራዊት ተደምስሶአል። የሰረገለኞችና የፈረሰኞች ሬሳ በውሃው ማዕበል በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ተወርውሮአል። የጦር መሣሪያውም በባሕሩ ዳር ተበታትኖ ይታያል። እስራኤላውያን በሙሴ እየተመሩ ባሰሙት የድል መዝሙር እንዲህ በማለት ውዳሴ ያቀርባሉ፦ “በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና [ለይሖዋ (አዓት)] እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። [ይሖዋ (አዓት)] ተዋጊ ነው፣ ስሙም [ይሖዋ (አዓት)] ነው።”—ዘፀዓት 15:1, 3
ይሖዋ በቀይ ባሕር ያገኘው ድል በእርግጥም በጦርነት ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ መሆኑን አረጋግጦአል። እስራኤላውያን ከግብፅ ለመውጣት የቻሉት በጦር ኃይል ቢሆንም ብዙ የውጊያ ችሎታ አልነበራቸውም። ይሖዋ ሌሊት ሌሊት የእሳት ዓምድ ሆኖ በሚቀየረው የዳመና ዓምድ ከራምሴ በኤታም እስከሚገኘው እስከ “ምድረ በዳው ዳር” መራቸው። (ዘፀአት 12:37፤ 13:18, 20-22) ከዚያም ይሖዋ ለሙሴ እንዲህ አለው፦ “ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፣ በበአልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ . . . ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ በምድር ይቅበዘበዛሉ፣ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው ይላል። . . . እርሱም ያባርራቸዋል።” (ዘፀዓት 14:1-4) እስራኤላውያንም ይህን በመታዘዝ አቅጣጫቸውን ቀይረው ወደ ፊሀሒሮት ተጓዙ። የፈርዖን ሰላዮች እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው የተቅበዘበዙ መስሎአቸው ይህንኑ ለፈርኦን ነገሩት። ይሖዋ አስቀድሞ እንደተናገረው ፈርዖን ለማሳደድ ጦር ሠራዊቱን አዘጋጀ።—ዘፀዓት 14:5-9
ወጥመዱ—ለእስራኤላውያን ነበር ወይስ ለፈርዖን?
በሁለቱም አቅጣጫ በተራሮች ተከብበው ስለነበሩና፣ ከፊት ለፊታቸው ያለው ባሕር በመሆኑ፣ ከኋላቸው ደግሞ ግብፃውያን ስለመጡባቸው በፍርሃት የተዋጡት እስራኤላውያን በወጥመድ ውስጥ እንደገቡ ሆኖ ተሰማቸው። ስለዚህ አምላክ እንዲረዳቸው ልመና አቀረቡ። ሕዝቡን ለማረጋጋት ሙሴ እንዲህ አለ፦ “አትፍሩ፣ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፣ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን [የይሖዋን (አዓት)] ማዳን እዩ። [ይሖዋ (አዓት)]ስለ እናንተ ይዋጋል፣ እናንተም ዝም ትላላችሁ።”—ዘፀዓት 14:15-20.
ይሖዋ ሙሴ በትሩን አንስቶ እሥራኤላውያን የሚያልፉበትን ውሃ እንዲከፍል ነገረው። ከዚያም አስደናቂ የሆነ ተዓምር ተፈጸመ። (ዘፀዓት 14:16, 21) ከምሥራቅ የተነሣ ኃይለኛ ነፋስ የቀይ ባሕርን ውሃዎች መክፈል ጀመረ፤ በዚህም ሦስት ሚልዮን የሚሆነው ሕዝብ በሙሉ በተከፈተለት በቂ መተላለፊያ ለማለፍ ቻለ። በእስራኤላውያን ሰልፍ በግራና በቀኝ ጫፍ ‘የተከመረው’ ውሃ እንደ ሁለት ትልልቅ ግድግዳዎች ቆመ።—ዘፀዓት 15:8
ከእሳቱ ዓምድ በሚወጣው ብርሃን በመመራት እስራኤላውያን በነፋስ በደረቀው የባሕር ወለል ላይ አልፈው አመለጡ። ጠዋት ሲሆንም የመጨረሻዎቹ እስራኤላውያን በሌላው የባሕር ዳርቻ ብቅ አሉ። “ግብፃውያንም፣ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፣ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ።” አሳዳጆቹ ወደ ወጥመዱ ተቻኩለው ገቡ!—ዘፀዓት 14:23
“[ይሖዋ] የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኮራኩር አሰረ፣ ወደ ጭንቅም አገባቸው።” ሙሴ አሁን እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ “ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ።” የውሃው ግድግዳ ፈረሰና ግብፃውያንን አጥለቀለቀ። ለመሸሽ ሙከራ አደረጉ፣ “[ይሖዋ] ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው።” ከእነርሱ ማንም የተረፈ አልነበረም! እስራኤላውያን በከፍተኛ ደስታ ለይሖዋ የድል መዝሙራቸውን ዘመሩ።—ዘፀዓት 14:24 እስከ 15:3፤ መዝሙር 106:11
ይሖዋ ለኢያሱ ተዋጋለት
ይሖዋ በሌሎች ጦርነቶችም ቢሆን “ብርቱ ተዋጊ” መሆኑን አረጋግጧል። አንዱ በአይ (ጋይ) የተደረገው ጦርነት ነው። በመጀመሪያ በከተማዋ ላይ የተደረገው ጥቃት አካን በሠራው ከባድ ኃጢአት ምክንያት ከሽፎ ነበር። ይህ ሁኔታ ከተስተካከለ በኋላ ይሖዋ ለኢያሱ የጦርነት ትዕዛዝ ሰጠው።—ኢያሱ 7:1, 4, 5, 11-26፤ 8:1, 2
ኢያሱ የይሖዋን መመሪያ በመከተል ሌሊት ላይ በምዕራብ በኩል በሚገኘው በከተማዋ በስተኋላ ሸምቆ ተቀመጠ። ዋነኛው ኃይሉ ከአይ ከተማ ውጭ ወደሚገኘው ሸለቆ ወደ ሰሜን ተጓዘና ፊት ለፊት ለመዋጋት የተዘጋጀ መሰለ። የአይ ሰዎችም ለማሳደድ ወጡ። አሁንም ቀደም ሲል ባገኙት ድል ተኩራርተው ከከተማዋ ውጭ እስራኤላውያንን እያባረሩ ሄዱ። እስራኤላውያን እያፈገፈጉ ያሉ በማስመሰል የጠላትን ጦር ከአይ እያራቁት “በምድረ በዳው መንገድ” በጣም ርቀው ሸሹ።—ኢያሱ 8:3-17
ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ ለኢያሱ “ጋይን በእጄ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ አለው።” ይህን ምልክት ሲመለከቱም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች ወደ ከተማይቱ ገብተው ያዟት በሰይፍ መቷት፣ አቃጠሏት። በውጭ ያሉት የጠላት ኃይሎችም ጢሱን ሲመለከቱ ሙሉ በሙሉ ሞራላቸው ተሰበረ። ኢያሱ ከመሸሽ ይልቅ የማጥቃት እርምጃ በመውሰዱ የጠላት ኃይል በሁለቱ ኃይሎች ወጥመድ ውስጥ ወደቀ። ይህ ሰብዓዊ ድል ነበርን? አልነበረም። በኋላ ኢያሱ “ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ አምላካችሁ [ይሖዋ (አዓት)]ነው” ብሎ እንደተናገረው እስራኤላውያን ሊያሸንፉ የቻሉት በይሖዋ ምክንያት ነው።—ኢያሱ 8:18-27፤ 23:3
በቂሶን የተደረገ ውጊያ
ይሖዋ በጦርነት ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑ በመጊዶ አጠገብ በሚገኘው በቂሶን ሸለቆ በድጋሚ ታይቷል። ከነዓናዊው ንጉሥ ያቢን እስራኤላውያንን ለ20 ዓመታት ጨቁኖ ነበር። በሲሣራ ይመራ የነበረው የያቢን ጦር ሠራዊት በዘመኑ የማይበገር ኃይል የሚመስሉ በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ የብረት ማጭድ የነበራቸው 900 የጦር ሰረገሎች የነበሩት ነበር።—መሳፍንት 4:1-3
ይሁን እንጂ በታቦር ተራራ ላይ የያቢንን ኃይሎች የሚወጉ አሥር ሺህ ተዋጊዎችን እንዲሰበስብ ይሖዋ በነቢይቱ በዲቦራ በኩል መስፍኑን ባርቅን አዘዘው። ሲሣራም ይህን ወታደራዊ ክምችት ሲመለከት በታቦር ተራራና በመጊዶ መካከል ወደሚገኘው ሸለቆ ፈጥኖ በመሄድ ፈጣን እርምጃ ወሰደ። በዚህ ጠፍጣፋ በሆነ መሬት ላይ የሚረባ መሣሪያ የሌላቸው የእስራኤል እግረኛ ወታደሮች የእርሱን ሰረገሎች የመቋቋም ምንም ዕድል እንደሌላቸው አስቦ እንደነበረ አያጠራጥርም። ሆኖም ከሰማያዊ ጠላት ጋር እዋጋለሁ ብሎ አልገመተም ነበር።—መሳፍንት 4:4-7, 12, 13
ይሖዋ የሲሣራን ሠራዊት ወደ ጦርነቱ እንዲገቡ ለማድረግ ሲል ባርቅን ከጥቃት ርቀው ከሚገኙት የታቦር ከፍተኛ ቦታዎች ወደ ሸለቋማው ሜዳ እንዲንቀሳቀስ አዘዘው። ከዚያም ይሖዋ ጥቃቱን ከፈተ። ከፍተኛ የሆነ ደራሽ ጎርፍ የጦር ሜዳውን ወደ ረግረግ መሬትነት ለወጠው። የሲሣራንም ሠራዊት እንዳይነቀሳቀስ አደረገው። በዚህ የመሸበር ሁኔታ ላይ እያሉ የእስራኤል የእግረኛ ወታደሮች በቀላሉ ጠላቶቻቸውን አባረሩ። “የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም።” መጠኑ እየጨመረ የሄደው የቂሶን ወንዝ ጎርፍ የከነዓናውያንን ሰረገላዎች ጠርጎ ወሰዳቸው፣ አንዳንዶቹንም አስከሬኖች ጠርጎ ሳይወስዳቸው አልቀረም።—መሳፍንት 4:14-16፤ 5:20, 21
በጎግና በሠራዊቱ ላይ የሚገኘው ድል
እነዚህ ጥንታዊ ታሪኮች ገና ሊመጣ ላለው የይሖዋ ድል ጥላ ሆነው ያገለግላሉ። “በዘመኑ ፍጻሜ” የሚደረገው ጦርነት የቀረበ መሆኑ እየታየ ነው። በሕዝቅኤል ትንቢት መሠረት “የዚህ ዓለም ገዥ” የሰይጣን ዲያብሎስ ምሳሌ የሆነው ጎግ አንድ ዓለም አቀፋዊ የሆነ አጥቂ ኃይል ያዘጋጃል። ምሳሌያዊውን “የእስራኤል ተራራ” ይኸውም ከፍ ብሎ ያለውን የክርስቲያን “የአምላክ እስራኤል” መንፈሳዊ ግዛት ለመውረር ሠራዊቱን ያዛል።—ሕዝቅኤል 38:1-9፤ ዮሐንስ 12:31፤ ገላትያ 6:16
ጎግ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን ዓይነት አጠቃላይ የሆነ የጥቃት ሙከራ ያደርጋል? ትንቢቱ ሰላማዊና መንፈሳዊ የሆነውን የብልጽግና ሁኔታቸውን ያመለክታል። ጎግ እንዲህ ይላል፦ ‘ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ተዘልለውም ወደሚኖሩ፣ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤ ምርኮን ለመማረክ፣ ብዝበዛን ለመበዝበዝ፣ . . . ከአሕዛብም በተሰበሰበ፣ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፣ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅን ለመዘርጋት።’—ሕዝቅኤል 38:10-12
የይሖዋ ሕዝቦች ባጠቃላይ ሲታዩ በሥጋዊ ሁኔታ ባለጠጎች አይደሉም። ይሁን እንጂ በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራቸው ምክንያት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ሀብት አፍርተዋል። ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ተሰብስበዋል፤ በአሁኑ ጊዜም ቁጥራቸው ከአራት ሚልዮን በላይ ሆኗል። (ራእይ 7:9, 10) በእርግጥም ይህ ትልቅ ሀብት ነው! በዚህ መንፈሳዊ ብልጥግና የተቆጣው ሰይጣን የአምላክን ሕዝብ ለመደምሰስ ሙከራ ያደርጋል።
ይሁን እንጂ ጎግ በምሳሌያዊው የእስራኤል ምድር ላይ ሲመጣ ይሖዋ አምላክን ራሱን እንዳጠቃ ያህል ይሆናል። ለሕዝቡ የሚበቀለው ይሖዋ “ቁጣዬ በአፍንጫዬ ይመጣል” (አዓት)ይላል። የጎግ ሠራዊቶች ድራሻቸው ይጠፋል። “የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል።” ከዚያም ይሖዋ አውዳሚ ኃይሎቹን ማለትም ‘ዶፍ፣ የበረዶ ድንጋይ፣ እሳትና ድኝን’ ይልካል። በቀይ ባሕር፣ በአይ እና በቂሶን እንዳደረገው ሁሉ ይሖዋ አሁንም ለሕዝቡ ይዋጋል፤ ስሙንም ያስከብራል። “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም [ይሖዋ (አዓት)] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”—ሕዝቅኤል 38:18-23
ይሖዋ በጥንት ዘመናት ስላደረጋቸው ጦርነቶች የተጻፈው የታሪክ መዝገብ ወደፊት በሚሆነው “ታላቅ መከራ” ወቅት ስለሚሆነው ሁኔታ ሙሉ ትምክህት እንዲኖረን ምክንያት ይሆነናል። (ማቴዎስ 24:21, 22) ይሖዋ ሁሉ ነገር በቁጥጥሩ ሥር ስለሆነ ከጠላቶቹ የበለጠ ሊያስብ ይችላል፤ ለሕዝቡም ደኅንነት ሲል እርምጃ ይወስዳል። “[ይሖዋ ራሱ (አዓት)] እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል።” (ኢሳይያስ 42:13) በምስክሮቹም ፊት ለዘላለም ይሖዋ ‘ጀግናው ተዋጊ’ ይሆናል!—ዘፀዓት 15:3
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
እስራኤላውያን ከግብጽ የተጓዙበት መንገድ
ጎሸን
ሜምፊስ
ራምሴስ
ሱኮት
ሚግዶል
ፊሃሂሮት
ኤታም
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በዚህ በአይ አካባቢ ይሖዋ ኢያሱንና ሕዝቡን አስገራሚ ወደ ሆነ ድል መርቷቸዋል
የቂሶን ወንዝ በፍጥነት ሞላ፤ ይህም ለይሖዋ ጠላቶች ሽንፈት አስተዋጽዎ አደረገ
[ምንጭ]
Photos: Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.