ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ ርዕሰ ትምህርቶች አንብበህ እውቀት አግኝተህባቸዋልን? ከሆነ፣ እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ትችል እንደሆነ ተመልከት።
◻ መንፈሳዊ እረኞች ተወግደው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ለማበረታታት ቅድሚያ ወስደው ሊያነጋግሩአቸው የሚችሉት በምን ምክንያት ነው?
እስራኤላውያን ገና ንስሐ ሳይገቡ በምርኮ በነበሩበት ጊዜም እንኳ ቢሆን ይሖዋ እንደ አንድ እረኛ እነርሱን ለመፈለግና ነቢያቶቹን ወደ እነርሱ ለመላክ ቅድሚያ ወስዶ ነበር። ክርስቲያን እረኞች እንደ ጠፉ በጎች የሆኑትን ንስሐ የገቡ ሰዎች ለመርዳት ፍላጎት አላቸው። (ከሉቃስ 15:4-7 ጋር አወዳድር።)—4/15 ገጽ 21-3
◻ ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ምሳሌ አንድ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበረ ሰው ከውገዳ ሲመለስ ሊኖረን የሚገባውን ስሜትና ሁኔታ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሉቃስ 15:22-32)
ግባችን አባካኙ ልጅ በተመለሰ ጊዜ የተደሰተውን አባት ለመምሰል መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ እንደገና ከተመለሰው ወንድም ጋር በነፃነት ልንነጋገርና በእውነት ውስጥ እድገት እንዲያደርግ ልናበረታታው ይገባናል።—4/15 ገጽ 25
◻ የወንጀል ጥቃት እንዳይደርስብን ለመከላከል ምን ተግባራዊ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይቻላል?
በተቻለ መጠን በአደገኛ አካባቢዎች በምሽት ጊዜ ከመዘዋወር ራቁ። ማንኛውንም ጌጣ ጌጥ ደብቁ፤ እንደ ካሜራ ያሉትን ዕቃዎች የገበያ ዕቃ በምትይዙበት ቦርሳ ውስጥ ያዙት። በተለይ ማንኛውንም የልብስ ሻንጣ ወይም ቦርሳ ይዘህ ከሆነ የእግረኛውን መንገድ ጠርዝ ይዘህ አትሂድ። (ምሳሌ 3:21-23)—5/1 ገጽ 5-6
◻ በሶፎንያስ 2:3 ላይ የሚገኘው ትንቢት “ምናልባት በይሖዋ ቁጣ ቀን ትሠወሩ ይሆናል” የሚለው ለምንድን ነው?
ምክንያቱም መዳን በታማኝነትና በጽናት ላይ የተመካ በመሆኑ ነው። (ማቴዎስ 24:13) ስለዚህ ከአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች ጋር የሚስማሙና ንጹሑን ልሳን በመናገር የሚቀጥሉ ከይሖዋ ቁጣ ቀን ይሰወራሉ። (ሶፎንያስ 2:1, 2)—5/1 ገጽ 14
◻ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ አምላክን ማስቀደም ምን ነገሮችን ይጨምራል?
ወላጆችና ልጆች ይሖዋን ማምለክና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን የአምላክ ሕግጋት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።—5/15 ገጽ 5
◻ ይሖዋ ኃጢአተኞችን ወዲያው ያልቀጣው ለምንድን ነው?
አንደኛው ምክንያት የአምላክ ስም በምድር በሙሉ መታወቅ ስለሚኖርበት ነው። (ከሮሜ 9:17 ጋር አወዳድር) ሌላው ምክንያት ደግሞ በኤደን ተደርጎ በነበረው አመጽ ምክንያት በአምላክ ልዕልናና በሰው ልጅ ታማኝነት ላይ ለተነሣ ግድድር ምላሽ ለማስገኘት ነው። በተጨማሪም የአምላክ ትዕግሥት ስተው የነበሩ ሰዎች ንሥሐ ገብተው መንገዳቸውን የሚያስተካክሉበትን አጋጣሚ ሰጥቶአቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:9)—5/15, ገጽ 11-12
◻ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ ኃይል የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከተለያዩ የኑሮ መስኮች በተውጣጡና በ1,600 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ 40 በሚያክሉ የተለያዩ ፀሐፊዎች ነው። ሆኖም ግን እነዚህ ፀሐፊዎች በሙሉ የጻፉት በአንድ መሠረታዊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ለአጋጣሚ ዕድል ወይም ለተራ ሰዎች አመራር የተተወ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለው ውስጣዊ ስምምነት ሊገኝ አይችልም ነበር።—6/1 ገጽ 5
◻ ይሖዋ በዘመናችን የሚፈጽመው የትኛውን በኢሳይያስ 28:21 ላይ የተገለጸ እንግዳ ሥራ ነው?
በራዕይ 17:16 የተሰጠው ማስጠንቀቂያ የታላቂቱ ባቢሎን ፖለቲካዊ ወዳጆች አንድ ቀን እንደሚነሱባት ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ሕዝበክርስትና ከሌሎቹ የሐሰት ሃይማኖቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ትወድማለች። በዘመናችን የሚፈጸመው የይሖዋ እንግዳ ሥራ ይህ ነው።—6/1 ገጽ 22-3
◻ ክርስቲያን ሴቶች ስለጌጣጌጥ አጠቃቀም ምን ነገር በአእምሮአቸው መያዝ ይኖርባቸዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ ማጌጥን ወይም መኳኳልን አይከለክልም። (ዘፀአት 32:2, 3፤ አስቴር 2:7, 12, 15) ይሁን እንጂ የልከኝነት መንፈስ መኖር ይገባዋል። አንዲት ሴት ከመጠን ያለፈ የከንፈር ቀለም፣ የዐይን ኩል ወይም የፊት ቅባት በመቀባት ኢዛቤልን በመምሰል የዚህን ዓለም አጋጌጥ ልትከተል ትችላለች። (2 ነገሥት 9:30) በቅባቶችና በጌጣጌጦች አጠቃቀም ረገድ ከልከኝነት ላለማለፍ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።—6/1 ገጽ 30-1
◻ እሥራኤላውያን በጥንት ዘመን በግብጽ ምድር ተስፋፍተው ከነበሩት በሽታዎች ሊጠበቁ የቻሉት እንዴት ነበር? (ዘዳግም 7:15)
እንደነዚህ ካሉት በሽታዎች ሊጠበቁ የቻሉት በአብዛኛው በሙሴ ሕግ የታዘዙትን የንጽሕና ሕጎች በመጠበቃቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።—6/15 ገጽ 4
◻ ሰዎች ደም እንዳይበሉ አምላክ ያዘዘው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:10, 11፤ ሥራ 15:22-29)
ሕይወት የአምላክ ሥጦታ ሲሆን ሕልውናው ደም በሚባለው ሕይወት ጠባቂ ሕዋስ ላይ የተመካ ነው። (መዝሙር 36:9) የሰው ልጆች ለደም ልዩ አክብሮት በማሳየት ለሕይወታቸው የሚመኩት በአምላክ ላይ መሆኑን ያሳያሉ። ስለዚህ አምላክ ስለደም ያወጣውን ትዕዛዝ የሰጠበት ዋነኛ ምክንያት ደም መውሰድ ጤንነት ስለሚጎዳ ሳይሆን ደም ልዩ የሆነ ትርጉም ስላለው ነው።—6/15, ገጽ 8-9
◻ ክርስቲያን ወላጆች ሕጻን ልጃቸውን ደም አልወስድም ብሎ የሚያቀርበው ተቃውሞ እንዲከበርለት ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
አንድ ክርስቲያን ወጣት በሕግ ፊት እንደ ሙሉ ሰው የማይቆጠር ቢሆንም ደም የማይወስድበትን ሃይማኖታዊ ምክንያት በግልጽና በቁርጠኝነት ለማስረዳት መቻል ይኖርበታል። ወላጆች ልጆቻቸው እምነታቸውን የመግለጽ ልምድ እንዲያገኙ ከልጆቻቸው ጋር ልምምድ ሊያደርጉ ይችላሉ።—6/15 ገጽ 18
◻ ሴቶች በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ዘመን በጣም የተባረኩት እንዴት ነበር?
ኢየሱስ የጀመረው ሥራ የማንኛውም ዘር አባል ለሆኑ ሴቶች መጽናኛ፣ ተስፋና አዲስ ዓይነት ክብር የሚያስገኝ ነበር። ለሴቶች ጥልቅ የሆኑ ሃይማኖታዊ እውነቶችን ያስተምራቸው ነበር። (ዮሐንስ 4:7, 24-26) በአገልግሎት ዘመኑ በይሁዳ ምድር ይዘዋወር በነበረበት ጊዜ የሴቶችን አገልግሎት ተቀብሎ ነበር። (ማርቆስ 15:40, 41)—7/1, ገጽ 14-15
◻ ወላጆች በጣም ጠቃሚ ሆነው ያገኙት የትኛው የኢየሱስ የማስተማር ዘዴ ነው?
ወላጆች ክርስቲያናዊ እውነቶች የልጆቻቸውን ልብ የሚነኩ እንዲሆኑ በምሳሌዎች ቢጠቀሙ ጥሩ ነው። በተጨማሪም በዕድሜ ከፍ ያሉ ልጆቻቸው በልባቸው ምን እንደሚያስቡ ለማወቅ በሚገባ በታሰበባቸው ጥያቄዎች ቢጠቀሙ ጥሩ ነው። (ከማቴዎስ 17:24-27 ጋር አወዳድር)—7/1 ገጽ 26
◻ ፍቅራዊ ቸርነትን መከታተል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
የፍቅራዊ ቸርነት ባሕርይ በአምላክም ሆነ በሰዎች ዘንድ ተወዳጆች እንድንሆን ያስችለናል። የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲኖረን ያደርጋል፣ ለሰዎችም አሳቢዎች እንድንሆን ያስችለናል። በቤተሰብም ሆነ በክርስቲያኖች ጉባኤው ውስጥ የጠነከረ መተሳሰር እንዲኖር ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍቅራዊ ቸርነት ለይሖዋ ክብር ያመጣል።—7/15, ገጽ 22
◻ አንድ ክርስቲያን በጓደኝነት ረገድ ሊሳሳት የሚችለው ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 15:33)
አንድ ሰው ጥሩ ጠባይ ያለው መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋ አገልግሎት አጥብቆ የማያስብና በመጽሐፍ ቅዱስ እንኳን የማያምን እስከሆነ ድረስ መጥፎ ባልንጀራ ነው። ለምን? ምክንያቱም የዚህ ሰው ሕይወት ከክርስቲያኑ በተለየ ሥርአቶች ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። ለአንድ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ለዚህ ሰው ምንም ትርጉም ላይኖራቸው ይችላል።—7/15 ገጽ 23
◻ የፍርድ ቀን የብሩሕ ተስፋ ጊዜ የሆነው ለምንድን ነው?
የፍርድ ቀን የሺህ ዓመት ጊዜ ነው። የፍርዱ ቀን የበላይ ገዥ አምላክ ራሱ ሲሆን ዋና ፈራጅ አድርጎ የሾመው ደግሞ ልጁን ክርስቶስ ኢየሱስን ነው። ይህ ጊዜ አዳም ከልጆቹ ያስወሰደባቸው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የሚመለስበት ጊዜ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22)—8/1 ገጽ 5-7