‘እያለቀሱ መዝራት እና በዕልልታ ማጨድ’
በሚዮ አይዲ እንደተነገረው
“መሞቴ ነው!መሞቴ ነው! እርዱኝ!” ብሎ ለመጮህ አባቴ የጭንቅ ሙከራ ያደርግ ነበር። ከቤት ሮጬ ስወጣ ድምፁ አየሩን ሞልቶት ነበር። ጊዜው እኩለ ሌሊት ነው። አባቴ ድንገተኛ የልብ ሕመም ተነሥቶበት ነበር። እኔም በአቅራቢያው ይገኝ ወደነበረው አጎቴ ሮጥኩ። ሆኖም ስንመለስ የአባቴ የልብ ትርታ አቁሞ አገኘነው።
ይህ ነገር የሆነው ታህሳስ 14, 1918 ነበር። በ13 ዓመት ዕድሜዬ ያለ ወላጅ ቀረሁ። እናቴ በሰባት ዓመቴ ሞታለች። ሁለቱንም ወላጆቼን በልጅነት ዕድሜዬ በማጣቴ ‘ሰዎች ለምን ይሞታሉ? ከሞት በኋላስ ምን ይሆናሉ?’ እያልኩ መጠየቅ ጀመርኩ።
ከመምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ በቶኪዮ ውስጥ አስተማሪ በመሆን በሺናጋዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምር ነበር። በኋላም አንድ የማውቀው ሰው ሞቶሂሮ ከተባለ ወጣት ሰው ጋር አስተዋወቀኝ፤ እርሱንም በ 22 ዓመቴ አገባሁት። ላለፉት 64 ዓመታት ጣፋጩንም ሆነ መራራውን የሕይወት ተሞክሮ ተካፍለናል። ከዚያም ብዙ ሳንቆይ በዚያን ወቅት በጃፓን አገዛዝ ሥር ወደነበረችው ወደ ታይዋን ተዛወርን። በጊዜው በዚያ አገር ውስጥ በደስታ ዕልል የምልበት ምክንያት አገኛለሁ የሚል ምንም አሳብ አልነበረኝም።
እውነትን መማር
በ1932 የፀደይ ወቅት በማዕከላዊ ታይዋን በሚገኘው የቺአይ ዳርቻ ላይ እየኖርን እያለን ሳቡሮ ኦቺኣይ የሚባል አንድ ሰው መጥቶ አነጋገረን። እርሱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሙታን ትንሣኤ ተስፋን እንደሚጨምሩ ጠቀሰ። (ዮሐንስ 5:28, 29) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! እናቴንና አባቴን እንደገና ለማየት ከፍተኛ የሆን ፍላጎት አደረብኝ። በሚያቀርባቸው በማስረጃ የተደገፉ መከራከሪያ ነጥቦች፣ ምክንያታዊ ማብራሪያዎችና ጥልቅ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች የሚናገራቸው ቃላት የእውነት ደወል ይሰማባቸው ነበር። ቀኑን ሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ውይይት ስናደርግ ጊዜው በፍጥነት አለፈ። ከዚያን ሰዓት ጀምሮ ማራኪ መጽሐፍ ሆኖ ታየኝ።
ብዙም ሳይቆይ ሚስተር ኦቺአይ እንደ ፍጥረት፣ የአምላክ በገና፣ መንግሥት፣ ትንቢት፣ ብርሃን እና እርቅ የመሳሰሉትን በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር የታተሙ መጻሕፍት ትቶልን ወደ ሌላ ቦታ ሄደ። እነዚህንም መጻሕፍት በተመስጦ አነብባቸው ጀመር፤ ይህን ሳደርግም ያነበብኩትን ነገር ለሌሎች የማሳወቅ ግፊት አደረብኝ። ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው መኖሪያው በሆነችው የናዝሬት ከተማ ከነበረ እኔስ ለምን ከምኖርበት ቦታ አልጀምርም? ብዬ አሰብኩና በአጠገቤ ያለውን ጎረቤቴን ሄጄ አነጋገርኩ። እንዴት እንደምሰብክ ያስተማረኝ ማንም ሰው አልነበረም። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱሴንና ያነበብኳቸውን መጻሕፍት በመያዝ ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ የምችለውን ያህል ሰበክሁ። ሰዎች ጥሩ ስሜት በማሳየት መጽሔቶችን ወሰዱ። በዚያን ጊዜ በጃፓን ውስጥ ቶዳኢሻ በመባል ይታወቅ የነበረው የመጠበቂያ ግንብ ማኀበር የዓለም ተስፋ የሆነች መንግሥት የተሰኘውን ትንሽ መጽሐፍ 150 ቅጂ እንዲልኩልኝ ጥያቄ አቀረብኩ፤ እነርሱንም አበረከትኳቸው።
አንድ ቀን ጽሑፍ የወሰደ አንድ ሰው እኔ ከሄድኩ በኋላ ወዲያው ፖሊስ መጥቶ መጻሕፍቱን ቀምቶ እንደወሰደ ነገረኝ። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ አራት ወንጀል መርማሪዎች ወደ ቤቴ በመምጣት ያሉኝን መጻሕፍትና መጽሔቶች በሙሉ ወሰዱ። የተዉት መጽሐፍ ቅዱሱን ብቻ ነበር። ለአምስት ዓመታት ያህል ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አልተገናኘሁም፤ ቢሆንም የእውነት እሳት በልቤ ውስጥ መቀጣጠሉን ቀጥሎ ነበር።
ከዚያም ታህሳስ 1937 ደረሰ! ከጃፓን የመጡ ሁለት ኮልፖርተሮች (አቅኚዎች) ጉብኝት አደረጉልን። በጣም በመገረም “ስለ እኛ እንዴት ልታውቁ ቻላችሁ?” ብዬ ጠየቅኋቸው። እነርሱም “ስማችሁ እዚህ አለን” ብለው መለሱልን። ይሖዋ ያስታውሰን ነበር። ሁለቱ ምስክሮች፣ ዮሪቺ ኦ እና ዮሺኡቺ ኮሳካ በአሮጌ ብስክሌቶች ላይ በመሆን ዕቃዎቻቸውን ከኋላ ከምረው ከታይፔ እስከ ቺአይ ድረስ 240 ኪሎ ሜትር ተጉዘዋል። ከእኛ ጋር ሲነጋገሩም “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” ብሎ እንደተናገረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ያለ ስሜት ተሰማኝ። (ሥራ 8:36) እነርሱ በመጡበት ዕለት በነበረው ምሽትም እኔና ባለቤቴ ተጠመቅን።
የታሠሩ ወንድሞችን መንከባከብ
በ1939 በመላዋ ጃፓን ውስጥ የይሖዋ ምስክሮችን ማሰር ተስፋፍቶ ነበር። የስደቱ ማዕበል ብዙም ሳይቆይ ወደ ታይዋን ደረሰ። በሚያዝያ ወር ወንድም ኦኢ እና ኮሳካ ሁለቱም ተይዘው ታሰሩ። ከሁለት ወራት በኋላ እኛም ጭምር ታሰርን። እኔ አስተማሪ ስለነበርኩ በሚቀጥለው ቀን ተለቀቅሁ፤ ባለቤቴ ግን ለአራት ወራት በእስር ላይ ቆየ። ባለቤቴ ከተለቀቀ በኋላ ወደ ታይፔ ተዛወርን። አሁን ሁለቱ ወንድሞች ወደታሰሩበት መጠጋታችን በጣም ጥሩ ሆነ።
የታይፔ እስር ቤት ከባድ ጥበቃ የሚደረግበት ነበር። ልብስና ምግብ ይዤ ወንድሞችን ለመጠየቅ ሄድኩ። በመጀመሪያ ወንድም ኮሳካ ከአንድ ጠባቂና ወንጀል መርማሪ ጋር በመሆን 12 ኢንች ስኩኤር ከሆነች የሽቦ መስኮት በስተጀርባ ብቅ አለ። ፊቱ ገርጥቶና ከንፈሮቹም እንደ ትኩስ እንጆሪ ቀልተው ነበር። የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ይዞታል።
ከዚያም ወንድም ኦኢ በፊቱ ላይ ፈገግታ እያሳየ፣ በደስታ እየደጋገመ “ለመምጣት መቻልሽ ትልቅ ነገር ነው” እያለ መጣ። ፊቱ ቢጫና ያበጠ ስለነበር ስለ ጤንነቱ ጠየቅሁት። “ፍጹም ጤነኛ ነኝ” ብሎ መለሰልኝ። “ይህ በጣም ጥሩ ቦታ ነው። ቱሃን ወይም ቅማል የለበትም። በክዊት ከሚባል እህል የተዘጋጀ ቂጣ ለመብላት እችላለሁ። ልክ እንደ ቪላ ነው” አለኝ። ፖሊሱና ጠባቂው ሳቃቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፤ “ይህንን ኦኢ የተባለውን ሰው መደብደብ የለብንም” አሉ።
እንደገና ታሠርኩ
ኅዳር 30, 1941 ወንድሞችን ጠይቄ ወደ ቤት ከተመለስኩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ እኩለ ሌሊት አካባቢ በሩ በኃይል ተንኳኳ። መስታወት ባለው በር በኩል ተራራ የሚመስሉ የባርኔጣ ጥላዎችን አየሁ። ስምንቱን ቆጠርኳቸው። ፖሊሶች ነበሩ። ወደ ቤታችን ውስጥ በኃይል ከገቡ በኋላ በቤት ውስጥ ያለውን ዕቃ ሁሉ ገለባበጡ። ሆኖም በከንቱ ነበር። ቦታውን ለአንድ ሰዓት ያህል ካመሰቃቀሉ በኋላ ጥቂት የፎቶ አልበሞችን ወርሰው ከእርሱ ጋር እንድንሄድ ነገሩን። ኢየሱስም የታሰረው እኩለ ሌሊት ላይ እንደነበረ ትዝ አለኝ። (ማቴዎስ 26:31, 55-57፤ ዮሐንስ 18:3-12) ስምንት ሰዎች በሁለታችን ላይ ይህንን ያህል ችግር መፍጠራቸውን ሳስበው አስደነቀኝ።
ትልቅና ጨለማ ወደሆነ ወደ አንድ የማናውቀው ሕንፃ ተወሰድን በኋላም ይህ ቦታ የታይፔ ሂቺሴኢ ወኅኒ ቤት እንደሆነ አወቅን። ከአንድ ትልቅ ጠረጴዛ ፊት ተቀመጥንና ጥያቄው ተጀመረ። በተደጋጋሚም “ማንን ታውቃላችሁ?” ብለው ጠየቁን። እያንዳንዳችንም “ማንንም አላውቅም” እያልን መለስን። በዋናው የጃፓን ምድር ውስጥ ያሉትን እንዴት ለማወቅ እንችላለን? የምናውቀው ወንድም ኦኢን እና ኮሳካን ብቻ ነበር። በተዘዋዋሪም ቢሆን የሰማናቸውን ስሞች ላለመናገር ከንፈራችንን ዘጋን።
ወዲያውኑም ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ሆነ፤ ሁለቱ ወንጀል መርማሪዎች ወደ እስር ቤቱ ክፍሌ ወሰዱኝ። አዲሱን አካባቢ ለመልመድ ጊዜ ወሰደብኝ። በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቱሃኖች ጋር ትግል ገጠምኩ። እነዚህ በአዲስ መጪዎች ላይ ግብዣ ለማድረግ የሚፈልጉ ትንንሽ ነፍሳት በክፍሉ ውስጥ የነበሩትን ሌሎች ሁለት ሴቶች በመተው፣ ምንም እንኳን ወደ እኔ የመጡትን ብደፈጥጣቸውም ያለ ርህራሄ ጠቀጠቁኝ። በመጨረሻም ተሸንፌ ሥጋዬን እንዲመገቡ ተውኳቸው።
ምግባችን አንድ ኩባያ በደንብ ያልበሰለ ቀጭን የሩዝ ገንፎ ነበር፤ አፌ ላይ ግን ጨርሶ እንዳልበሰለ ጥሬ ሩዝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ከገንፎው ጋር ትንሽ ጨው የተጨመረባቸውና አሸዋ የሚታይባቸው የዳይኮን (የጃፓን ቀይ ሥር) ቅጠሎች ይቀርቡ ነበር። በመጀመሪያ ምግቡ መጥፎ ሽታ ስለነበረውና ቆሻሻም በመሆኑ ልውጠው አልቻልኩም ነበር። ስለዚህ ሌሎች እስረኞች መጥተው ይበሉት ነበር። በኋላ ግን ላለመሞት ስል ቀስ በቀስ ተለማመድኩት።
የእስር ቤቱ ኑሮ አሳዛኝ ነበር። ሰላይ ነው ተብሎ የተጠረጠረ አንድ ሰው ከመሠቃየቱ የተነሳ በየዕለቱ ሲጮህ እሰማ ነበር። በተጨማሪም በሚቀጥለው ክፍል ውስጥ አንድ ሰው ተሰቃይቶ ሲሞት ተመልክቻለሁ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች በፊቴ መፈጸማቸውን ስመለከት ይህ አሮጌ ሥርዓት መጥፋት እንዳለበት ይሰማኝ ነበር። በአምላክ ተስፋዎች ላይ የነበረኝ እምነትም ከምንጊዜውም የበለጠ ጠንካራ ሆነ።
የምርመራ ጥያቄ
ለአንድ ዓመት ያህል በእስር ቤት ውስጥ ቆየሁ። አምስት ጊዜም የምርመራ ጥያቄ ቀረበልኝ። አንድ ቀን ሕግ አስከባሪው ለመጀመሪያ ጊዜ መጣና ወደ አንዲት ጠባብ የምርመራ ክፍል ተወሰድኩ። እርሱ በመጀመሪያ የተናገረው ነገር፦ “የሚበልጠው ማን ነው፣ አማቴራሱ ኦሚካሚ [የፀሃይ የሴት አምላክ] ነች ወይስ ይሖዋ ነው? እስቲ ንገሪኝ” የሚል ነበር። እንዴት እንደምመልስ ጥቂት አሰብኩበት።
እርሱም “ማን ነው የሚበልጠው ንገሪኝ፣ አለዚያ ልመታሽ ነው” ብሎ በቁጣ ተመለከተኝ።
እኔም በረጋ መንፈስ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጀመሪያው ገጽ ላይ ‘በመጀመሪያ አምላክ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ’ ተብሎ ተጽፏል” ብዬ መለስኩለት። ሌላ ነገር መጨመር የሚያስፈልግ መስሎ አልተሰማኝም። ምንም ቃል ሳይናገር ፊቴን ትኩር ብሎ ተመለከተና አርዕስቱን ቀየረ።
በመሠረቱ በእሥር እንድቆይ የተደረገበት ምክንያንት ምን ነበር? የምርመራ መዝገቡ “ሕዝቡን በአነጋገርዋና በድርጊትዋ ልታሳስት ትችላለች የሚል ስጋት አለ” ይላል። ፍርድ ቤት ሳልቀርብ የታሰርኩት በዚህ ምክንያት ነበር።
ይህ ሁሉ ሲደርስብኝ ምንጊዜም ይሖዋ በአጠገቤ ነበር። በይሖዋ ቸርነት በኪስ ልትያዝ የምትችል የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መጽሐፍ ቅዱስ ተሰጠኝ። አንዱ ወንጀል መርማሪ አንድ ቀን “ይህን እንድትጠቀሚበት እሰጥሻለሁ” ብሎ ወደ ክፍሌ ውስጥ ወረወረልኝ። በየቀኑም የማነበውን ማስታወስ እስክችል ድረስ አነበው ነበር። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የድፍረት ምሳሌ የመበረታታት ምንጭ ሆኖልኛል። 14ቱ የጳውሎስ ደብዳቤዎችም አጠንክረውኛል። ጳውሎስ ከባድ ስደት ደርሶበታል። ቢሆንም ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይደግፈው ነበር። እንደዚህ ያለው የታሪክ መዝገብ አጠንክሮኛል።
በጣም ቀጭንና ደካማ ሆኛለሁ፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ብዙውን ጊዜ በማይጠበቁ መንገዶች ደግፎ አቁሞኛል። አንድ እሁድ ቀን በፍጹም አይቼው የማላውቀው አንድ መርማሪ በአንድ ቁራጭ ጨርቅ የተጠቀለለ ነገር ይዞ መጣ። የእስር ቤቱን በር ከፈተና ወደ ግቢው ወሰደኝ። ወደ አንድ ትልቅ የካምፖር ዛፍ ስንደርስ የተጠቀለለውን ጨርቅ ፈታው። በውስጡ ሙዝና ስስ ቂጣ ነበረበት። እዚያው እንድበላቸው ነገረኝ። ወንጀል መርማሪው እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሁላችሁም ጥሩ ሰዎች ናችሁ። ቢሆንም እንዲህ አድርገን አሰቃይተናችኋል። በቅርቡ ከዚህ ሥራ ውስጥ ለመላቀቅ እፈልጋለሁ።” ከዚህ በኋላ ጠባቂዎቹና ወንጀል መርማሪዎቹ በደግነት ይይዙኝ ጀመር። እኔን ስለሚያምኑኝም ክፍሎቻቸውን እንዳጸዳላቸው ያደርጉኝ ነበር። እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት የሥራ መብቶችን ይሰጡኝ ነበር።
በመጀመሪያ ቤታችን መጥተው ካሰሩን ወንጀል መርማሪዎች አንዱ በ1942 መጨረሻ ላይ ወደ ቢሮው ጠራን። “የሞት ፍርድ የሚገባችሁ ቢሆንም ዛሬ ትለቀቃላችሁ” ብሎ ተናገረ። ባለቤቴ እኔ ከመለቀቄ ከአንድ ወር በፊት ወደ ቤቱ ተመልሶ ነበር።
ከምሥክሮቹ ጋር የነበረንን ግንኙነት ማደስ
እኛ እስር ቤት ውስጥ እያለን ጃፓን ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገባች። ከዚያም በ1945 ጃፓን በጦርነቱ እንደተሸነፈች ሰማን። በጋዜጦችም ላይ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚለቀቁ አነበብን። ወንድም ኮሳካ በእስር ቤት ውስጥ እያለ ታሞ መሞቱን አወቅን። ሆኖም እኔ በታይፔ ሲንቹና በሌሎች ከተሞች ወደሚገኙ እስር ቤቶች ደብዳቤዎችን በመጻፍ ወንድም ኦኢ የሚገኝበትን ቦታ ጠየቅሁ። ይሁን እንጂ ምንም መልስ አላገኘሁም። በኋላም ወንድም ኦኢ በአፋኝ ጓዶች መረሸኑን ሰማን።
በ1948 ከሻንጋይ አንድ ያልተጠበቀ ደብዳቤ ደረሰን። ይህም ደብዳቤ በይሖዋ ምስክሮች አዲስ ከተቋቋመው የጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ወደ ቻይና ተልኮ ከነበረው ከወንድም ስታንሊ ጆንስ የተላከ ነበር። ይሖዋ እንደገና አስታወሰን። ከይሖዋ ድርጅት ጋር በዚህ ዓይነት በመገናኘታችን ከመጠን ያለፈ ተደስቼ ነበር። ወንድም ኦኢን ካየነው ሰባት ዓመታት አለፉ። በዚያን ጊዜ ከማንም ወንድም ጋር ግንኙነት ባይኖረንም እንኳ ለሌሎች ስለ ምሥራቹ እነግራቸው ነበር።
ወንድም ጆንስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኘን የደስታ ጊዜ ነበር። እርሱ ተግባቢ ሰው ነበር። ከዚያ በፊት በፍጹም ተገናኝተን የማናውቅ ቢሆንም እንኳ በጣም የቅርብ ዘመዳችንን እንግድነት እንደተቀበልን ሆኖ ተሰማን። ብዙም ሳይቆይ ወንድም ጆንስ ባለቤቴን እንደ አስተርጓሚ አድርጎ ከተራሮቹ ባሻገር ወደሚገኘው ወደ ታይቱንግ ሄደ። ከአንድ ሣምንት በኋላ ተመለሱ፤ በዚሁ ጊዜም የአንድ ቀን ስብሰባ አድርገው በምሥራቃዊ ዳርቻ የሚገኘው የአሚስ ጎሣ አባላት የሆኑ 300 ሰዎችን አጥምቀዋል።
የወንድም ጆንስ ጉብኝት ለእኔ በሌላም በኩል ትርጉም ያለው ነበር። እስከዚያን ጊዜ ድረስ የምሰብከው ብቻዬን ነበር። እስከዚያን ጊዜ ድረስ የምሰብከው ብቻዬን ነበር። አሁን ግን አንድ ባልና ሚስት በወንድም ጆንስ ጉብኝት ወቅት ተጠምቀው ነበር። (ባልየው መሬት የነበረው ሰው ነው) ከዚያን ጊዜ ወዲህ ለብዙ ጊዜ መንግሥቱን በማወጅ ከሚገኘው ደስታ በተጨማሪ ደቀመዛሙርት በማድረግ የሚገኘውንም ደስታ ቀምሻለሁ። ከዚያ ቆየት ብሎ ወደ ሲንቹ ተዛወርን፤ በዚህም ወንድም ጆንስ ለሦስት ጊዜ ማለትም በእያንዳንዱ ጉብኝት ለሁለት ሣምንት እየቆየ ጎብኝቶናል። በዚህ ጠቃሚ ግንኙነት በጣም ተደስቼበታለሁ። በመጨረሻው ጉብኝቱ ላይ “በሚቀጥለው ጊዜ ጓደኛዬን ሃሮልድ ኪንግን ይዤ እመጣለሁ” አለን። ሆኖም እንዳሰበው ሊመጣ አልቻለም፤ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ሁለቱም በቻይና ውስጥ ታሠሩ።
በ1949 11ኛውን የጊልያድ ኮርስ የተካፈሉት ጆሴፍ ማክጋርትና ሳይሪል ቻርልስ የተባሉት ሚሲዮናውያን ወደ ታይዋን መጡ። እነርሱም መኖሪያ ቤታችንን ማዕከል አድርገው በመጠቀም በታይዋን ውስጥ ሥራውን አስፋፉት። ምሳሌያቸው በእርግጥ አበረታቶኛል። ይሁን እንጂ የፖለቲካው ሁኔታ ወደ ሆንግ ኮንግ እንዲሄዱ አስገደዳቸው። ከፖሊስ ጋር አገሩን ለቀው ሲሄዱ እንባዬን ለመቆጣጠር አልቻልኩም ነበር። “ሚዮ አታልቅሺ” አለኝ ጆ። ጨምሮም “አመሰግናለሁ” አለኝና እንደ ማስታወሻ አድርጎ ብዕሩን ሰጠኝ።
ልጅን የማሳደጉን ሥራ መወጣት
ባሌና እኔ ልጅ አልነበረንም፤ ስለዚህ የባለቤቴን የእህት ልጅ ገና አራት ወር ሲሆናት ወስደን ማሳደግ ጀመርን። የእናትዋ ሕይወት በአስም ምክንያት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር።
በ1952 በጃፓን ውስጥ ሚሲዮናዊ ሆኖ ያገለግል የነበረው ወንድም ሎይድ ባሪ የይሖዋ ምስክሮች ለሚያከናውኑት ሥራ ሕጋዊ እውቅናን ለማግኘት ወደ ታይዋን መጥቶ ነበር። እርሱም ከእኛ ጋር ቆይቶ በጣም አጽናንቶናል። በዚያን ጊዜ ልጃችን 18 ወር ሆኗት ነበር። ወደ ላይ ብድግ አድርጎ ካነሳት በኋላ “የአምላክ ስም ማን ነው?” ብሎ ጠየቃት። በዚህን ጊዜ እኔ በመገረም “ገና ከትንሽነትዋ ጀምረን ልናስተምራት ይገባናል ማለትህ ነውን?” ብዬ ጠየቅሁት። ጠበቅ ባለ አነጋገር “አዎን” ብሎ መለሰልኝ። ከዚያም ልጅን ከሕፃንነት ጀምሮ የማሰልጠኑን አስፈላጊነት ነገረኝ። እርሱ የተናገራቸው “ይሖዋ መጽናኛ እንድትሆናችሁ የሰጣችሁ ስጦታ ነች” የሚሉት ቃላት በአእምሮዬ ውስጥ ተቀርፀዋል።
ወዲያውኑ ሴት ልጄን አኬሚን ይሖዋን እንድታውቅና እንድትወድ አገልጋዩም እንድትሆን ማሰልጠን ጀመርኩ። “ኢሆባ” ወይም በጃፓንኛ ይሖዋ የሚለውን ስም ከሚፃፍባቸው ኢ፣ ሆ፣ ባ ከሚሉት ሦስት ፊደሎች በመጀመር ፊደሎችን አስተማርኳት። ሁለት ዓመት ሲሆናት የምነግራትን ነገር ሁሉ ለመረዳት ቻለች። ስለዚህ ወደ መኝታዋ ከመሄድዋ በፊት በየምሽቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እነግራት ነበር። በጥሩ ስሜት ታዳምጣቸውና ታስታውሳቸውም ነበር።
ሦስት ዓመት ተኩል ሲሆናት ወንድም ባሪ እንደገና ጉብኝት አደረገልንና ለአኬሚ በጃፓንኛ ተራ የንግግር ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ሰጣት። “የአኪሜ መጽሐፍ ቅዱስ! የአኪሜ መጽሐፍ ቅዱስ!” እያለች እቤት ውስጥ ትዞር ነበር ከዚያም ጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ “የአኬሚ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ስም የለበትም! ይህን አልፈልገውም” ብላ ተናገረች። ወረወረችውም። በነገሩ ግራ ተጋብቼ የመጽሐፉን ይዘት ተመለከትኩት። በመጀመሪያ ኢሳይያስ ምዕራፍ 42 ቁጥር 8ን አወጣሁ። እዚያ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም “ጌታ” በሚለው ቃል ተተክቷል። ሌሎች ጥቅሶችንም ተመለከትኩ፤ ሆኖም ይሖዋ የተሰኘውን መለኮታዊ ስም ላገኝ አልቻልኩም። የይሖዋን ስም በጥንታዊ የጃፓንኛ ቋንቋ ከተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱሴ አውጥቼ እንደገና ሳሳያት አኬሚ ተረጋጋች።
ወደ ጃፓን መመለስ
በ1958 ወደ ጃፓን ተመለስንና በኮቤ ከሚገኘው የሳኖሚያ ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመርን። ይሖዋን የማመሰግንበት ብዙ ምክንያት ስለነበረኝ ይህንን አመስጋኝነት አቅኚ ማለትም የይሖዋ ምስክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ለመግለጽ ፈለግሁ። በአቅኚነቱ አገልግሎት የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አደረግሁ። በዚህም ምክንያት ብዙ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት ችያለሁ፤ እንዲሁም ከ70 እስከ 80 የሚሆኑ ሰዎች ወደ እውነት እንዲመጡ በመርዳት የሚገኘውን ደስታ ቀምሻለሁ። ለጊዜውም ቢሆን ለባለቤቴና ለሴት ልጄ የሚያስፈልገውን እያሟላሁ በየወሩ በመስክ ከ150 ሰዓት በላይ በማገልገል ልዩ አቅኚ የመሆንም መብት አግኝቻለሁ።
ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በታይዋን ውስጥ የኖርን እንደ መሆናችን በጃፓን ውስጥ ያለው ባሕል አስደንጋጭ ሆኖብኝ ነበር። በአያሌ ፈታኝ ሁኔታዎችም ውስጥ አልፌአለሁ። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ልክ ወንድም ባሪ ከብዙ ዓመታት በፊት እንደነገረኝ አኬሚ ማጽናኛና ደጋፊ ሆናልኛለች። ጭንቀት በሚያጋጥመኝ ጊዜ “እማዬ አይዞሽ ይሖዋ መፍትሔውን ያዘጋጃል” ትለኛለች። እኔም “አዎን ያዘጋጃል፤ አይደለም እንዴ?” ብዬ እመልስላትና አጥብቄ አቅፋታለሁ። እንዴት ጥሩ አጽናኝ አገኘሁ! ይሖዋን ከማመስገን ሌላ ምን ላደርግ እችላለሁ!
ልጄን ለይሖዋ ሰጠሁ
አኬሚ 7 ዓመት ሲሆናት አስፋፊ ሆነች፤ በ1963 በጋ ላይ 12 ዓመት ሲሞላት ተጠመቀች። የምችለውን ያህል ብዙውን ጊዜ አብሬያት ለማሳለፍ ሞክሬአለሁ። (ዘዳግም 6:6, 7) በጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበረችበት ጊዜ አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ ወደ ጉባኤያችን ከተላኩ ልዩ አቅኚዎች ባገኘቻቸው መልካም ምሳሌዎችና ማበረታቻ እያደር አኬሚ በአዳዲስ ክልሎች ውስጥ አቅኚ ሆኖ ማገልገልን ግቧ አደረገች።
በ1968 በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ በቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ላይ እንደ ዮፍታሄ ሴት ልጅ ሆና ሠርታለች። ድራማውን እየተከታተልኩ እያለሁ ልክ ዮፍታሄ እንዳደረገው እስከዚያን ጊዜ ድረስ ስንከባከባት የነበረችውን አንዷን ሴት ልጄን ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለይሖዋ ለመስጠት ወሰንኩ። ልጄ ከአጠገቤ ተለይታ ሕይወቴ ምን ይመስል ይሆን? በጣም ፈታኝ ነበር፤ ምክንያቱም ከ60 ዓመት አልፌ ነበር።
በ1970 ልጃችን ትታን የምትሄድበት ጊዜ ደረሰ። ከባለቤቴ ፈቃድ ካገኘች በኋላ አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ወደ ኪዮቶ ሄደች። የተሰማንን ስሜት ስለተረዳች ጥላን ስትሄድ ልቧ በጣም ያዘነ ይመስላል። እንደ መለያያ ጥቅስ በማድረግ መዝሙር 126: 5,6ን ጠቀስኩላት። “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ። በሄዱ ጊዜ፣ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ።” እነዚህ ቃላት እኔንም ጭምር አበርትተውኛል።
በኋላም አኬሚ አግብታ ከባልዋ ጋር በልዩ አቅኚነቱ አገልግሎት ቀጠለች። ባልዋ የክልል የበላይ ተመልካች ሆኖ ከተሾመበት ከ1977 ጀምሮ በተጓዥነት ሥራ አገልግለዋል። ዘወትር ካርታዬን እከፍትና በካርታው ላይ በሐሳቤ ከልጄ ጋር “እጓዝ ነበር።” ብዙ ተሞክሮዎቻቸውን በመስማቴና በልጄም አማካኝነት ከብዙ እህቶች ጋር በመተዋወቄ ተደስቻለሁ።
አሁን 86 ዓመት ሆኖኛል። ያለፉት ጊዜያት በአንድ ሌሊት እንዳለፈ ጊዜ ብቻ መስለው ይታዩኛል። የበፊቱን ያህል ለመሥራት አልችልም፤ ቢሆንም የመስክ አገልግሎቱ አሁንም ደስታን ይሰጠኛል። እውነትን ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ ያለፉትን 60 ዓመታት ሳስብ የሚያበረታው የአምላክ ተስፋ ልቤን ይሞላዋል። አዎን፣ ከታማኞቹ ጋር ታማኝ ሆኖ የሚገኘው ይሖዋ የተትረፈረፈ የደስታ ሰብል እንድናጭድ ያደርገናል።—መዝሙር 18:25