ከሌሎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ዋነኛ የሆኑት ይሖዋና ክርስቶስ
“በእውነት [ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ (አዓት)] ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር አያደርግም”—አሞጽ 3:7
1. በዛሬው ጊዜ በሥራ ላይ የዋሉት ምን የመገናኛ ዘዴዎች ናቸው?
ዛሬ መገናኛ ብዙ ሚልዮን ብር የሚያንቀሳቅስ ንግድ ሆኗል። የሚታተሙት መጻሕፍት በሙሉ፣ በየጊዜው የሚወጡት ጋዜጦችና መጽሔቶች በሙሉ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡት ፕሮግራሞች በሙሉና እንዲሁም ሲኒማዎችና በመድረክ ላይ የሚቀርቡ ቲያትሮች ሁሉ የመገናኛ ክፍል ናቸው። ተጽፈው የሚላኩ ደብዳቤዎችና የስልክ ጥሪዎችም ቢሆኑ ለዚሁ ሲባል የሚደረጉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች ናቸው።
2. በመገናኛው መስክ ሰዎች ላደረጓቸው ቴክኒካዊ ዕድገቶች ምሳሌ የሚሆኑት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
2 ሰዎች በመገናኛው መስክ ያደረጉአቸው ቴክኒካዊ እድገቶች ከግምት በላይ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል ከመዳብ የሽቦ መሥመር በጣም ተሻሽለው የመጡት ፋይበር ኦፕቲክ የተባሉት ቀጫጭን ሽቦዎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የቴሌፎን ንግግሮችን በአንድ ጊዜ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ በኅዋ ውስጥ ምድርን የሚዞሩና የቴሌፎን፣ የቴሌግራፍ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የሚረዳ መሣሪያ ያላቸው የመገናኛ ሳተላይቶች አሉ። ከእነዚህ ሳተላይቶች ውስጥ አንዱ በአንድ ጊዜ 30,000 የቴሌፎን መልዕክቶችን ሊያስተናግድ ይችላል!
3. የሐሳብ ግንኙነት መቋረጥ ካለ ምን ነገር ይደርሳል?
3 ሆኖም እነዚህ ሁሉ የመገናኛ ዘዴዎች ቢኖሩም በግለሰቦች መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሊኖር ባለመቻሉ ምክንያት በዓለም ላይ ብዙ ችግር ይደርሳል። ስለዚህም “በገዥዎችና በተገዥዎች መካከል እያደገ የሚሄድ ገደል ማለትም—ሰፊ የሆነ ‘የግንኙነት ክፍተት’—አለ እየተባለ ይነገራል።” የትውልዶች መራራቅ እየተባለ የሚጠራውስ፣ ወላጆችና ልጆቻቸው እርስ በርሳቸው በተሳካ ሁኔታ በንግግር ሐሣባቸውን ለመገላለጥ አለመቻላቸው አይደለምን? የጋብቻ አማካሪዎች በጋብቻ ላይ ትልቁ ችግር በባልና በሚስት መካከል ሐሳብ ለሐሳብ አለመገናኘታቸው እንደሆነ ይዘግባሉ። የጥሩ ግንኙነት አለመኖር ሞት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታም አለ። በ1990 መጀመሪያ ላይ 73 ሰዎች በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን አጡ። ለዚህ አደጋ ዋነኛ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ምክንያት በአውሮፕላን አብራሪውና መሬት ላይ ባለው ተቆጣጣሪ መካከል ግንኙነት አለመኖሩ ነበር። አንድ የጋዜጣ ርዕስ “የግንኙነት መሰናክል ወደ አሰቃቂ አደጋ መራ” በማለት ገልጾ ነበር።
4. (ሀ) “የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ” ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች የሐሳብ ግንኙነት ሲያደርጉ ግባቸው ምንድን ነው?
4 ከክርስትና አንፃር ሲታይ የሐሳብ ግንኙነት ምንድን ነው? አንድ መዝገበ ቃላት በገለጸው መሠረት “ኮሙኒኬሽን” (“የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ”) ማለት “አንድን ነገር በአጥጋቢ ሁኔታ ለመቀበል ወይም ለመረዳት ይቻል ዘንድ መልዕክትን፣ አሳብን፣ ወይም ስሜትን ማስተላለፍ” ማለት ነው። ሌላ መዝገበ ቃላትም “ሐሳቦችን ውጤታማ በሆነ መንገድ የማስተላለፉ ቴክኒክ ነው” ብሎአል። “ሐሳቦችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተላለፍ” የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። በተለይ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የሐሳብ ግንኙነት ውጤታማ መሆን ይገባዋል። ምክንያቱም ግቡ ሰዎች የተማሩትን ነገር በሥራ እንደሚያውሉት ተስፋ በማድረግ ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውነት ልባቸውን እንዲነካ ማድረግ ነው። በተለይም ራስን ባለ መውደድ ወይም በፍቅር ተነሣስቶ የሚደረግ ነገር ነው።
የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርገው ይሖዋ
5. ይሖዋ አምላክ ሐሳቡን ለሰው ከገለጸባቸው የመጀመሪያ መንገዶች ውስጥ አንዱ ምንድን ነው?
5 ከሁሉ የበለጠው የሐሳብ ግንኙነት አድራጊ ይሖዋ አምላክ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በመልኩ እንደ ምሳሌው ስለፈጠረን እርሱ ከእኛ ጋር የንግግር ግንኙነት ለማድረግ ይችላል፣ እኛም ስለ እርሱ ያለንን አሳብ ለሌሎች ለማስተላለፍ እንችላለን። ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ስለ ራሱ ለምድራዊ ፍጥረቶቹ አንዳንድ አሳቦችን አስተላልፎላቸዋል። ይህን ካደረገባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ በሚታየው ፍጥረቱ አማካኝነት ነው። ስለዚህም መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፣ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች።” (መዝሙር 19:1, 2) ሮሜ 1:20ም “የማይታየው [የአምላክ] ባሕርይ. . . ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና” በማለት ይነግረናል። “ግልጥ ሆኖ ይታያል” የሚለው አባባል ውጤታማ የሆነ ግንኙነትን ያመለክታል።
6. ይሖዋ ምድራዊ ፍጥረቶቹ በኤደን ገነት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ምን መልዕክት አስተላለፈላቸው?
6 በአምላክና በመለኮታዊ መግለጫው እምነት የሌላቸው ሰዎች ሰው ለምን እንደሚኖር ራሱ መርምሮ ማወቅ ይኖርበታል ብለን እንድናምን ሊያደርጉን ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ አምላክ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከሰው ጋር የሐሳብ ግንኙነት እንዳደረገ የአምላክ ቃል በግልጽ ይነግረናል። በዚህም ምክንያት አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት እንዲህ በማለት የመዋለድ መብት ሰጣቸው፦ “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ . . . የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ግዙአቸው።” በተጨማሪም አምላክ ከአንዱ በስተቀር በገነት ውስጥ ያለውን ፍሬ እስከሚበቃቸው እንዲበሉ ፈቅዶላቸው ነበር። አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ካፈረሱ በኋላም ይሖዋ ለሰው ልጅ የተስፋ ጭላንጭል በማሳየት የመጀመሪያውን መሲሐዊ ትንቢት ነገራቸው፦ “በአንተና [በእባቡና] በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።”—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:16, 17፤ 3:15
7. ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ስለማድረጉ የዘፍጥረት መጽሐፍ ምን ነገር ያሳየናል?
7 የአዳም ልጅ ቃየል እስከ ግድያ የሚያደርስ ትልቅ የቅንዓት ስሜት ባደረበት ጊዜ ይሖዋ አምላክ ከእርሱ ጋር የንግግር ግንኙነት በማድረግ፦ ‘ተጠንቀቅ ወደ ችግር ውስጥ እየገባህ ነው’ ብሎት ነበር። ሆኖም ቃየል ይህንን ማስጠንቀቂያ ለመቀበል እምቢ በማለት ወንድሙን ገደለው። (ዘፍጥረት 4:6-8) ከዚህም ቆየት ብሎ ምድር በክፋትና በአመጽ በተሞላችበት ጊዜ ይሖዋ ጻድቅ ሰው ለነበረው ለኖኅ ምድርን ያበላሻት ከነበረው ነገር ለማጽዳት ዓላማ እንዳለው ሐሳቡን ገልጾለት ነበር። (ዘፍጥረት 6:13 እስከ 7:5) የጥፋት ውሃው ከመጣ በኋላም ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቡ ሲወጡ ይሖዋ ስለ ሕይወትና ስለ ደም ቅድስና ያለውን ዓላማ ገለጸላቸው። በቀስተ ዳመና አማካኝነትም ወደፊት ሕያዋን ፍጥረታትን ጨርሶ እንደገና በጎርፍ እንደማያጠፋ ማረጋገጫ ሰጣቸው። ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላም ይሖዋ ለአብርሃም የምድርን ነገዶች በሙሉ በአብርሃም ዘር አማካኝነት ለመባረክ ዓላማ እንዳለው ገለጸለት። (ዘፍጥረት 9:1-17፤ 12:1-3፤ 22:11, 12, 16-18) አምላክ በሰዶምና በጎሞራ የነበሩትን ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ለማጥፋት በወሰነበት ጊዜ ይህንን ውሳኔውን “እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን?” በማለት በፍቅር ለአብርሃም ገልጾለት ነበር። —ዘፍጥረት 18:17
8. ይሖዋ በምድር ላይ ካሉት አገልጋዮቹ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ያደረገባቸው አራት መንገዶች ምንድን ናቸው?
8 ይሖዋ ከእስራኤል ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ከሙሴ ጀምሮ በተከታታይ በተነሡ ነቢያት ለረጅም ጊዜ ተጠቅሟል። (ዕብራውያን 1:1) አንዳንድ ጊዜ ቃል በቃል በመናገር ሐሳቡን ያጽፍ ነበር፤ ለምሳሌ ለሙሴ “እነዚህን ቃሎች ጻፍ” ብሎት ነበር። (ዘፀዓት 34:27) አልፎ አልፎም ይሖዋ ቀደም ሲል ለአብርሃም አድርጎት እንደነበረው ከቃል አቀባዮቹ ጋር በራእይ አማካኝነት ሐሳቡን ያስተላልፍ ነበር።a በተጨማሪም ይሖዋ ከሰዎች ጋር ለመገናኘትና ሐሳቡን ለመግለጥ በሕልሞች ተጠቅሟል። ይህንን ያደረገው ከአገልጋዮቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ሰዎችም ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ታስረው የነበሩትን ሁለት ሰዎች ሕልም እንዲያዩና ዮሴፍ እንዲተረጉምላቸው አድርጓል። (ዘፍጥረት 40:8–41:32፤ ዳንኤል ምዕራፍ 2 እና 4) እንዲሁም በሌሎች ብዙ አጋጣሚዎች ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ሐሳቡን ለማስተላለፍ በመላእክታዊ መልዕክተኞች ተጠቅሟል።—ዘፀአት 3:2፤ መሳፍንት 6:11፤ ማቴዎስ 1:20፤ ሉቃስ 1:26
9. እርሱ በተናገረው ንግግር እንደታየው ይሖዋ ለሕዝቦቹ ለእስራኤላውያን ሐሳቡን እንዲገልጥ ያነሳሳው ምንድን ነው?
9 ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት ያደረገው ይህ የሐሳብ ግንኙነት ሁሉ እርሱ ለሕዝቡ ለእስራኤል የነበረውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነው። በዚህም ምክንያት በነቢዩ ሕዝቅኤል በኩል እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፣ ይላል ጌታ [ይሖዋ (አዓት)]፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ተመለሱ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?” (ሕዝቅኤል 33:11) ከ2 ዜና መዋዕል 36:15, 16 ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ከጥንት አመጸኛ ሕዝቡ ጋር ከነበረው ግንኙነት ታጋሽና ቻይ ነበር። “የአባቶቻቸውም አምላክ [ይሖዋ (አዓት)] ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነስቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን . . . ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ . . . ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።”
10. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ከሕዝቦቹ ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርገው እንዴት ነው? እርሱስ ሐሳቡን ገላጭ አምላክ የሆነው እስከ ምን ድረስ ነው?
10 ዛሬም ቢሆን ይሖዋ ስለ ራሱና ስለ ዓላማዎቹ እንዲሁም ለእኛ ስላለው ፈቃዱ ሐሳቡን የገለጸበት በመንፈስ አነሳሽነት የተፃፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ አለልን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እንዲያውም ይሖዋ ሐሳቡን በመግለጽ ረገድ ከሁሉ የበለጠ መሆኑን ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፦ “በእውነት ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።” (አሞጽ 3:7) ምን ለማድረግ ዓላማ እንዳለው ለአገልጋዮቹ ያሳውቃል።
የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ በኩል የአምላክ ልጅ ሁኔታ
11. ይሖዋ ከሰው ጋር ለመገናኘት ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበት ማን ነው? “ቃል” የሚለው ስያሜስ ለእርሱ ተገቢ የሚሆነው ለምንድ ነው?
11 ይሖዋ ፈቃዱን ለማስተላለፍ ከተጠቀመባቸው ወኪሎች መካከል ከሁሉ የሚበልጠው በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው ቃል ወይም ሎጎስ ነው። እርሱ ቃል፣ ወይም ሎጎስ ተብሎ መጠራቱ የሚያስተላልፍልን ሐሳብ ምንድን ነው? ዋነኛው የይሖዋ ቃል አቀባይ መሆኑን ነው። ቃል አቀባይ ማለትስ ምን ማለት ነው? አንዱ የሚናገረውን ሐሳብ ለሌላው የሚያስተላልፍ ተናጋሪ ነው። ስለዚህ ሎጎስ የይሖዋን ቃል የማሰብ ችሎታ ላላቸው ምድራዊ ፍጥረቶች የሚያስተላልፍ ቃል አቀባይ ሆነ። ይህ የተሰጠው የሥራ ድርሻ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ቃል ተብሎ ሊጠራ ችሎአል።—ዮሐንስ 1:1, 2, 14
12. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለምን ዓላማ ነው? (ለ) ይህንንስ ዓላማ በታማኝነት መፈጸሙን የሚመሠክረው ምንድን ነው?
12 ኢየሱስ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ዓላማ እውነትን ለሰው ዘር ለመናገር እንደሆነ ነግሮት ነበር፦ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ።” (ዮሐንስ 18:37) በወንጌሎች ውስጥ የሚገኘው ታሪክ ይህንን ሥራ እንዴት በሚገባ እንደተወጣው ይነግረናል። የተራራ ስብከቱም በየትኛውም ሰው ከተሰበከው ስብከት የሚበልጥ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ስብከት አማካኝነት እጅግ በጣም ጥሩ ሀሳብ አስተላላፊ መሆኑን አስመስክሮአል። “ኢየሱስም ይህን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ።” (ማቴዎስ 7:28) ስለ አንድ ሌላ አጋጣሚ ጊዜም “ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር” የሚል ቃል እናነባለን። (ማርቆስ 12:37) ኢየሱስን አስረው እንዲያመጡ ወታደሮቹ በተላኩ ጊዜ እርሱን ሳይዙት ተመለሱ። ለምን? ወታደሮቹ ለፈሪሳውያን፦ “እንደዚህ ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” ብለው መልስ ሰጡ።— ዮሐንስ 7:46
የክርስቶስ ደቀመዛሙርትም መልዕክት አስተላላፊ የመሆን ሥራ ተሰጥቷቸዋል
13. ክርስቶስ ብቸኛው መልዕክት አስተላላፊ በመሆን እንዳልረካ የሚያሳየው ምንድን ነው?
13 ኢየሱስ እርሱ ብቻውን መልዕክት አስተላላፊ በመሆኑ ስላልረካ በመጀመሪያ 12 ሐዋርያቱን በኋላም 70 ወንጌላውያንን የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያሰሙ ላካቸው። (ሉቃስ 9:1፤ 10:1) ከዚያም ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ደቀመዛሙርቱ አንድ ልዩ ሥራ እንዲሠሩ ኃላፊነት ሰጣቸው። ምን ሥራ? በማቴዎስ 28: 19,20 ላይ እንደምናነበው መልዕክት አስተላላፊዎች እንዲሆኑ መመሪያ ሰጣቸው። ሌሎችም እንደ እነርሱ መልዕክት አስተላላፊዎች እንዲሆኑ ማስተማር ነበረባቸው።
14. የጥንቶቹ መልዕክት አስተላላፊ ክርስቲያኖች ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ?
14 ደቀመዛሙርት ጥሩ መልዕክት አስተላላፊዎች ነበሩን? በእርግጥ ነበሩ! በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ቀን ባደረጉት ስብከት አዲስ በተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ 3,000 ነፍሳት ተጨምረው ነበር። ብዙም ሳይቆይ የወንዶቹ ቁጥር 5,000 ደርሷል። (ሥራ 2:41፤ 4:4) አይሁዳውያን ጠላቶቻቸው ኢየሩሳሌምን በሙሉ በትምህርታቸው ሞልተዋታል በማለት መክሰሳቸውና በኋላም ምድርን በስብከታቸው እንደገለበጧት መነገሩ አያስደንቅም።—ሥራ 5:28፤ 17:6
15. ይሖዋ በዘመናችን ከሰዎች ጋር ግንኙነት ለማድረግ በየትኛው መሣሪያ ተጠቅሟል?
15 በዘመናችንስ ያለው ሁኔታ እንዴት ነው? በማቴዎስ 24:3, 45-47 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው ጌታው ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በሚገኝበት ዘመን በምድር ያለውን ንብረቱን በሙሉ እንዲንከባከብ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አባል የሆኑበትን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። ይህ ታማኝና ልባም ባሪያ የተወከለው በይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል ሲሆን የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበርን የማስታወቂያ መሣሪያው አድርጎ ይጠቀምበታል። ታማኝና ልባም ባሪያ የአምላክ መገናኛ መሥመር ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። እርሱም በተራው ጥሩ መልዕክት አስተላላፊዎች እንድንሆን ያበረታታናል። እንዲያውም የጽዮን የመጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አብሳሪ የመጀመሪያ ዕትም አንባቢዎቹን እንዲህ በማለት መክሮ ነበር፦ “[በዚህ መጽሔት] ላይ ያሉትን መመሪያዎች ለማወቅ ይፈልጋል ወይም ቢያውቃቸው ይጠቀማል ብላችሁ የምታስቡት ጎረቤት ወይም ጓደኛ ካላችሁ ልታሳዩት ትችላላችሁ። ይህን ስታደርጉ ባላችሁ አጋጣሚ ለሰው ሁሉ ቃሉን ለመስበክና መልካም ለማድረግ ትችላላችሁ።”
16. አምላክ ከምድራዊ አገልጋዮቹ ጋር ይበልጥ ውጤት ባለው መንገድ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ ሌላም ነገር እንደሚያስፈልግ የሚያሳየው ምንድን ነው?
16 ይሁን እንጂ አንድን ሰው በሕይወት መንገድ እንዲጓዝ የሚያስችለውን ትክክለኛውን እውቀት ለማግኘት የአምላክን ቃል ማወቅና በግል ማንበብ ብቻ በቂ አይሆንም። የኢሳይያስን ትንቢት ያነብ የነበረውንና ግን ያነበበውን ያልተረዳውን ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን አስታውስ። ወንጌላዊው ፊልጶስ ትንቢቱን አብራራለት፤ ከዚያም የክርስቶስ ደቀመዝሙር በመሆን ለመጠመቅ ዝግጁ ሆነ። (ሥራ 8:27-38) ለብቻ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ በተጨማሪ ሌላም ነገር የሚያስፈልግ መሆኑን ከኤፌሶን 4:11-13 ለመረዳት ይቻላል። በዚህም ላይ ክርስቶስ ስጦታ አድርጎ የሰጠው አንዳንድ በመንፈስ አነሳሽነትና መሪነት የሚናገሩ ሐዋርያትንና ነቢያትን ብቻ ሳይሆን “ሌሎቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ” እንደሰጠ ጳውሎስ ገልጾአል። ይህም የሆነው “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፣ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ” ነው።
17. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ዓላማዎቹን ለሰው ዘር ለማስተላለፍ የሚጠቀምበትን መሣሪያ በምን መለያ ምልክቶች ለይተን ለማወቅ እንችላለን?
17 ሰዎች ሙሉ ሰው ወደ መሆን ደረጃ የደረሱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ለመርዳት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጠቀሙባቸውን ሰዎች ለይተን ለማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በገለጸው መሠረት ከመለያ ምልክቶቹ ውስጥ አንዱ ኢየሱስ ተከታዮቹን እንደወደዳቸው እነዚህም እርስ በርሳቸው መዋደዳቸው ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ሌላው መለያ ምልክት ኢየሱስ የዓለም ክፍል እንዳልነበር ሁሉ እነርሱም የዓለም ክፍል አለመሆናቸው ነው። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:16) አሁንም ሌላው ምልክት ልክ እንደ ኢየሱስ የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነ ያምናሉ፣ ለሚያስተምሩትም ሁሉ የአምላክን ቃል እንደ በላይ ባለሥልጣን አድርገው ሁል ጊዜ ይጠቅሱታል። (ማቴዎስ 22:29፤ ዮሐንስ 17:17) ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው የአምላክ ስም ከሁሉ በላይ ከፍ እንዲል ማድረጋቸውም ሌላው ምልክት ነው። (ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6) ሌላው ምልክት ደግሞ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የአምላክን መንግሥት መስበካቸው ነው። (ማቴዎስ 4:17፤ 24:14) እነዚህን ብቃቶች ሁሉ ሊያሟላ የሚችለው አንድ ቡድን ብቻ ነው። እነርሱም ክርስቲያን የይሖዋ ምስክሮች በመባል የሚታወቁት ዓለም አቀፉ መልዕክት አስተላላፊዎች ናቸው።
18. የሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች የሐሳብ ግንኙነት የሚደረግባቸው ምን ሦስት መስኮችን ያብራራሉ?
18 ይሁን እንጂ መልዕክት አስተላላፊ መሆን ለሌሎች ኃላፊነት ያለብን መሆኑን ያመለክታል። ክርስቲያኖች መልዕክት አስተላላፊ የመሆን ኃላፊነት ያለባቸው ለእነማን ነው? በመሠረቱ ክርስቲያኖች የሐሳብ መገናኛ መሥመሮችን ሁልጊዜ ክፍት ስለ ማድረግ ሊያስቡባቸው የሚገቡ ሦስት መስኮች አሉ። እነዚህም የቤተሰብ ክልል፣ የክርስቲያን ጉባኤና የክርስቲያን የመስክ አገልግሎት ናቸው። የሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች እነዚህን ጉዳዮች የሚያብራሩ ይሆናሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘፍጥረት 15:1፣ 46:2፣ ዘኁልቁ 8:4፣ 2 ሳሙኤል 7:17፣ 2 ዜና መዋዕል 9:29፣ ኢሳይያስ 1:1፣ ሕዝቅኤል 11:24፣ ዳንኤል 2:19፣ አብድዩ 1፣ ናሆም 1:1፣ ሥራ 16:9፣ ራእይ 9:17 ተመልከት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ካልተቻለ ምን ጉዳት ሊደርስ ይችላል?
◻ ሁለቱ ዋነኛ የሐሳብ ግንኙነት አድራጊዎች እነማን ናቸው?
◻ አምላክ ከሰው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ምን የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሟል?
◻ ኢየሱስ የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ከሌሎች ልቆ የሚታየው እንዴት ነው?
◻ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መልዕክት በማስተላለፍ ረገድ ምን ያህል የተሳካላቸው ነበሩ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ልክ እንደ ሰማያዊ አባቱ አዛኝ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት አድራጊ ነበር