አምላክ ጸሎቶችህን ይመልስልሃልን?
“ጸሎቴ እንደተሰማልኝ ተሰምቶኝ አያውቅም” አለች አንዲት በሆካይዶ ጃፓን የምትኖር ሴት። እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማት ይህች ሴት ብቻ አይደለችም። ብዙ ሰዎች ጸሎታቸው መልስ አግኝቶ እንደማያውቅ ይሰማቸዋል። አንተም ብትሆን እውነት አምላክ ጸሎቴን ይሰማልን? ብለህ ሳታስብ አትቀርም።
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው አማልክት ጸሎት ያቀርባሉ። ታዲያ ብዙ ጸሎቶች መልስ ያገኙ የማይመስለው ለምንድነው? የዚህን መልስ ለማግኘት መጀመሪያ ለአምላክ የሚቀርቡትን የጸሎት ዓይነቶች እንመርምር።
አንዳንዶች የሚጸልዩት ምን ለማግኘት ነው?
በአዲስ ዓመት ወራት ሁለት ሦስተኛው የጃፓን ሕዝብ ወይም 80 ሚልዮን ያህል ሕዝብ በሽንቶ ቅዱስ ሥፍራዎች ወይም በቡድሂስት ቤተመቅደሶች ይጸልያሉ። የሳንቲሞች ስጦታ እያቀረቡ ለመልካም ዕድልና ለቤተሰባቸው ደህንነት ይጸልያሉ።
ተማሪዎች በጥርና በየካቲት ወራት በጣም ከባድ ከሆነው የመግቢያ ፈተና ጥቂት ቀደም ብሎ በትምህርት አምላኩ እውቅ ወደሆነው በቶኪዮ የሚገኝ ቅዱስ ሥፍራና ወደመሳሰሉት የጸሎት ቦታዎች ይጐርፋሉ። ምኞታቸውን ከእንጨት በተሠራ የጸሎት ጣውላ ላይ ጽፈው በቅዱስ ሥፍራው መሬት ላይ እንጨት ተክለው ይሰቅሉታል። በ1990 የፈተና ወራት ቢያንስ ቢያንስ 100,000 የሚያህሉ ጣውላዎች አንዱን በቶኪዮ እውቅ የሆነ ቅዱስ ሥፍራ አጥር ግቢ አስጊጠው ነበር።
ጤንነትን የሚመለከቱ ብዙ ጸሎቶች ይቀርባሉ። በጃፓን አገር በከዋሳኪ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ሥፍራ ሰዎች ከኤድስ እንዲጠበቁ ይጸልያሉ። “ከኤድስ ለመዳን የመጸለይ ጠቀሜታ” ይላሉ የቅዱስ ሥፍራው ቄስ “ሰዎች በጠባያቸው ጥንቁቅ እንዲሆኑ ማድረጉ ነው።” ይሁን እንጂ ሰዎች የሚጸልዩት ስለእነዚህ ነገሮች ብቻ ነውን?
በሌላው ቤተመቅደስ በዕድሜ የገፉ አንዲት ሴት “ድንገተኛ ሞት” እንዲሞቱ ይጸልያሉ። ለምን? ለረዥም ጊዜ ታሞ ከመሰቃየትና ለቤተሰብ ሸክም ከመሆን ለመዳን ስለፈለጉ ነው።
አንድ የክርስቲያን አገር ነው በሚባል አገር የአንድ የእግር ኳስ ቡድን አምበል ቡድኑ ድል እንዲያደርግና ከአደጋ እንዲጠበቅ ጸልዮአል። በፖላንድ የሚኖሩ ካቶሊኰች ለግል ደህንነታቸው ይጸልያሉ። ጸሎታቸው እንደተሰማላቸው ሲሰማቸውም እመቤታቸውን በጌጣጌጥ ያስጌጧታል። ብዙ ሰዎች ሜክሲኰ ከተማ ያለውን ዝነኛውን ጓደሎፕና ፈረንሳይ አገር ያለውን ሉርድ ወደመሳሰሉ አብያተ ክርስቲያናት ተአምራዊ ፈውስ ለመለመን ይጐርፋሉ።
ሕዝቦች በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ለብዙና የተለያዩ የግል ምክንያቶች ጸሎት ያቀርባሉ። በእርግጥ ጸሎታቸው እንዲሰማላቸውና መልስ እንዲያገኝላቸው ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ጸሎቶች ተቀባይነት ባለው መንገድ ተሰሚነት ያገኛሉ ብሎ መጠበቅ ትክክል ነውን? ያንተ የራስህ ጸሎትስ መልስ ያገኛልን? ለመሆኑ አምላክ ለጸሎት መልስ ይሰጣልን?