የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 10/1 ገጽ 20-22
  • ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ትክክለኛ የሆነ የሚገፋፋ ሐሳብ
  • ስስት በሌለበት ዓለም ውስጥ የሚኖር ፍቅር
  • በጉባኤ ውስጥ የሚታይ ፍቅር
  • እርስ በርስ ያለንን ፍቅር ማሳደግ
  • በፍቅር ታነጹ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • “በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • የሚወድህን አምላክ ውደደው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ፍቅር—ውድ የሆነ ባሕርይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 10/1 ገጽ 20-22

ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ምንድን ነው?

ዛሬ በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች ይበልጥ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የራሳቸውን የኑሮ ዘይቤ የሚከተሉ ክርስቲያኖች የያዟቸው እምነቶች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ናቸው። እነርሱም አንድነት የላቸውም፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እርስ በርሳቸው ይገዳደላሉ። በግልጽ እንደሚታየው አብዛኞቹ እውነተኛ ክርስቲያኖች አይደሉም። ኢየሱስ በዘመናችን ብዙዎች “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ” እንደሚሉት፣ በሌላ አነጋገር ክርስቲያን ነን እንደሚሉ፣ ሆኖም እርሱ “ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ” እንደሚላቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:21, 23) በእርግጥ ማናችንም ከእነዚህ ሰዎች መካከል መሆን አንፈልግም! ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች ነን ብለን ለመናገር የምንችለው እንዴት ነው?

እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን ብዙ ነገሮች ማስፈለጋቸው ሐቅ ነው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ጠንካራ እምነት ያስፈልገዋል። ምክንያቱም “ያለ እምነትም [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም።” (ዕብራውያን 11:6) ይህ ጠንካራ እምነት በትክክለኛ ሥራዎች መደገፍ ይኖርበታል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” በማለት አስጠንቅቋል። (ያዕቆብ 2:26) ከዚህም በላይ አንድ ክርስቲያን ‘የታማኝና ልባም ባሪያን’ ሥልጣን አምኖ መቀበል ይኖርበታል። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሁን እንጂ ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ከእነዚህ ነገሮች የተለየ አንድ ነገር ነው።

ቁልፉ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤው ላይ እንዲህ በማለት አብራርቷል፦ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ምሥጢርንም ሁሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።”​—1 ቆሮንቶስ 13:1-3

ስለዚህ ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ፍቅር ነው። እምነት፣ ሥራና፣ ከትክክለኛው ድርጅት ጋር መተባበር በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ሆኖም ያለ ፍቅር ዋጋ አይኖራቸውም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

ይህ የሆነው የምናመልከው አምላክ ባለው ጠባይ ምክንያት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ የእውነተኛ ክርስትና አምላክ የሆነውን ይሖዋን “አምላክ ፍቅር ነው” በሚሉት ቃላት ይገልጸዋል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ አምላክ እንደ ኃይል፣ ፍትሕና ጥበብ ያሉ ሌሎች ብዙ ጠባዮችም አሉት። ይሁን እንጂ እርሱ ከሁሉ በላይ የፍቅር አምላክ እንደመሆኑ አምላኪዎቹ ምን ዓይነት ሰዎች እንዲሆኑ ይፈልጋል? በእርግጥም እርሱን የሚመስሉ ግለሰቦች ሁሉ ፍቅርን ይኮተኩታሉ።​—ማቴዎስ 5:44, 45፤ 22:37-39

ትክክለኛ የሆነ የሚገፋፋ ሐሳብ

አዎን፣ ፍቅር ክርስቲያኖች የሚያመልኩትን አምላክ እንዲመስሉ ያደርጋቸዋል። ይህም ሲባል የሚገፋፋቸው የውስጥ ሐሳብ ከአምላክ የሚገፋፋ ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ማለት ነው። ከሁሉ በላይ ይሖዋ አምላክ ለእኛ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ዕድል ለመስጠት ኢየሱስን ወደ ምድር እንዲልክ የገፋፋው ሐሳብ ምንድን ነው? ፍቅር ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ታዲያ እንዲህ ከሆነ የአምላክን ፈቃድ ስለማድረግ ምን ዓይነት የሚገፋፋ ሐሳብ ሊኖረን ይገባል? “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና።”​—1 ዮሐንስ 5:3

በተሳሳተ የሚገፋፋ ሐሳብ ተነሳስቶ አምላክን ማገልገል ይቻላልን? አዎን ይቻላል። ጳውሎስ በቅንዓትና በክርክር ተነሳስተው የሚያገለግሉ ሰዎች በዘመኑ እንደነበሩ ጠቅሷል። (ፊልጵስዩስ 1:15-17) በእኛም ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሊደርስ ይችላል። ይህ ዓለም ፉክክር የበዛበት ዓለም ነው። ይህ የፉክክር መንፈስ እኛንም ሊበክለን ይችላል። ጥሩ ተናጋሪዎች እንደሆንን በማሰብ ወይም ለሌሎች ብዙ ጽሑፎችን ለማበርከት ስለቻልን እንኩራራ ይሆናል። የአገልግሎት መብቶቻችንን ሌሎች ካገኙአቸው መብቶች ጋር ልናወዳድርና ለራሳችን ከፍተኛ ግምት የምንሰጥ ወይም የምንቀና ልንሆን እንችላለን። አንድ ሽማግሌ ለያዘው የአገልግሎት ቦታ ቀንቶ አንድን ችሎታ ያለው ወጣት እድገት እንዳያደርግ እስከ መከልከል ሊደርስ ይችላል። ግላዊ ጥቅም ለማግኘት ያለን ጉጉት ድሆችን ችላ በማለት ሃብታም ከሆኑ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነትን እንድንኮተኩት ሊገፋፋን ይችላል።

ፍጽምና የሌለን ሰዎች ስለሆንን እነዚህ ነገሮች ሊደርሱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ይሖዋ ዋነኛው የሚገፋፋን ሐሳብ ፍቅር እንዲሆን ካደረግን እንደነዚህ ያሉትን ዝንባሌዎች መዋጋት እንችላለን። ራስ ወዳድነት፣ ራሳችንን ለማክበር ያለን ምኞት ወይም የማን አለብኝነት ትዕቢት በውስጣችን ያለውን ፍቅር ገፍተው ሊያስወጡት ይችላሉ። ከዚህ በኋላ ‘ምንም ጥቅም አናገኝም።’​—ምሳሌ 11:2፤ 1 ቆሮንቶስ 13:3

ስስት በሌለበት ዓለም ውስጥ የሚኖር ፍቅር

ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዚህ ዓለም ክፍል እንደማይሆኑ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:14) በዙሪያችን ባለው ዓለም ተጽዕኖ ከመዋጥ ለመራቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ የሚረዳን ፍቅር ነው። ለምሳሌ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ‘ከአምላክ ይልቅ ተድላን የሚወዱ’ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:4) ዮሐንስ እንደዚህ እንዳንሆን አስጠንቅቆናል። እንዲህ አለ፦ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”​—1 ዮሐንስ 2:15, 16

ይሁንና ‘በሥጋ ምኞት’ እና ‘በዓይን አምሮት’ ላይ ጀርባችንን ማዞር ቀላል ነገር አይደለም። እነዚህ ነገሮች የሚወደዱበት ምክንያት ለሥጋችን በጣም ማራኪ መሆናቸው ነው። ከዚህም በላይ በዛሬው ጊዜ በዮሐንስ ዘመን ከነበሩት የበለጡ የተለያዩ ተድላዎች (ደስታዎች) አሉ። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የዓይን አምሮት ችግር ከነበረ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የበለጠ የዓይን አምሮት ችግር መኖር አለበት ማለት ነው።

የሚያስገርመው ነገር ዓለም የሚያቀርባቸው ብዙዎቹ ዘመናዊ መደሰቻዎች በራሳቸው ስህተት የሌለባቸው መሆናቸው ነው። ትልቅ ቤት፣ ቆንጆ መኪና፣ ቴሌቪዥን ወይም ስቴሪዮ ማጫወቻ ቢኖረን ምንም ስህተት የለበትም። ወይም ረጅምና አስደሳች ጉዞዎችን ማድረግና አስደናቂ የሆኑ የእረፍት ጊዜዎች ብናሳልፍ የትኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ አንጥስም። ታዲያ ዮሐንስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ የሚገልጸው ነጥብ ምንድን ነው? አንዱ፣ እንደነዚህ ያሉት ነገሮች በሕይወታችን በጣም ከፍተኛውን ቦታ ከያዙ በውስጣችን የራስ ወዳድነትን፣ የፍቅረ ነዋይንና የኩራትን መንፈስ ሊያሳድጉብን ይችላሉ። እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ስንል ገንዘብ ለማጠራቀም የምናደርገው ጥረትም ለይሖዋ ለምናቀርበው አገልግሎት እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። እነዚህን ነገሮች ማግኘት ጊዜ ይወስዳል። ሚዛናዊ የሆነ መዝናኛ እረፍትን ሊያመጣልን የሚችል ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ለአምልኮ የመሰብሰብና የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ግዴታ ስላለብን ያለን ጊዜ በጣም የተወሰነ ነው።​—መዝሙር 1:1-3፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 10:24, 25

በዚህ የፍቅረ ነዋይ ዘመን ‘የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም’ እና ‘በዚህ ዓለም ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም’ ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል። (ማቴዎስ 6:33፤ 1 ቆሮንቶስ 7:31) ይህን ለማድረግ ጠንካራ እምነት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ በተለይ ለይሖዋና ለጎረቤታችን ያለን እውነተኛ ፍቅር በራሳቸው ስህተት ያልሆኑ፣ ነገር ግን ‘አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለማከናወን’ እንዳንችል የሚያደርጉንን ዘዴዎች ለመቃወም ያጠነክረናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) እንደዚህ ያለ ፍቅር ከሌለን አገልግሎታችን በቀላሉ ለይስሙላ ብቻ የሚደረግ ሥራ ወደመሆን ደረጃ ዝቅ ይላል።

በጉባኤ ውስጥ የሚታይ ፍቅር

ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ በተናገረበት ጊዜ የፍቅርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጾአል። (ዮሐንስ 13:35) ሽማግሌዎች ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን የማያፈቅሯቸው ቢሆኑ ኖሮ እነርሱን በእረኝነት ለመጠየቅና ለመርዳት ይህን ያህል ጊዜ ያጠፉ ነበርን? የጉባኤው አባላት የእምነት ጓደኞቻቸውን ድካሞች የሽማግሌዎችንም ጭምር የሚታገሡበት ከፍቅር ሌላ ምን ምክንያት አላቸው? ክርስቲያኖች ሌሎች ችግር እንደደረሰባቸው ሲሰሙ በሥጋዊ በኩል እርዳታ እንዲያደርጉ ፍቅር ያነሳሳቸዋል። (ሥራ 2:44, 45) ስደት በሚኖርበት ጊዜም አንዱ ክርስቲያን ሌላውን አያጋልጥም፤ ለሌላው ሲል ለመሞት ፈቃደኛ ነው። ለምን? በፍቅር ምክንያት ነው።​—ዮሐንስ 15:13

አንዳንድ ጊዜ ፍቅር በትንንሽ መንገዶች ሊፈተን ይችላል። አንድ ሽማግሌ ከባድ የሥራ ጭነት በዝቶበት እያለ አንድ ክርስቲያን ለእርሱ ያን ያህል ጠቃሚ መስሎ የማይታይ ሌላ ችግር ይዞ ወደ እርሱ ይመጣ ይሆናል። ሽማግሌው መቆጣት ይኖርበታልን? ይህ ነገር ለመከፋፈል መነሾ እንዲሆን ከመፍቀድ ይልቅ ከወንድሙ ጋር በትዕግሥትና በደግነት ይነጋገራል። ጉዳዩን አብረው ይወያዩበታል፣ ወዳጅነታቸውንም ያጠናክረዋል። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15-17) እያንዳንዱ ሰው መብቴ ነው ብሎ ከሚከራከር ይልቅ ሁሉም ኢየሱስ እንዳበረታታው ልበ ሰፊ የመሆንን ማለትም ወንድሞቻቸውን “ሰባ ሰባት ጊዜ” ይቅር ለማለት ዝግጁ የመሆንን ችሎታ ለማዳበር መሞከር አለባቸው። (ማቴዎስ 18:21, 22) በዚህ መንገድ ክርስቲያኖች ፍቅርን ለመልበስ ጠንክረው ይሞክራሉ፤ ምክንያቱም ፍቅር “ፍጹም የአንድነት ማሠሪያ” ነው።​—ቆላስይስ 3:14

እርስ በርስ ያለንን ፍቅር ማሳደግ

አዎን ይሖዋን ለማገልገል የሚረዳው ትክክለኛው የሚገፋፋ ሐሳብ ፍቅር ነው። ፍቅር ከዓለም የተለየን እንድንሆን ያጠነክረናል። ፍቅር ጉባኤው እውነተኛ የክርስቲያን ጉባኤ ሆኖ እንዲቀጥል ዋስትና ይሰጣል። ሥልጣን ያላቸው ወንድሞች በተቀላጠፈ ሁኔታ ብዙ ሥራ ለማከናወን በማሰብ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ደግነትና ትሕትና የማሳየትን አስፈላጊነት መርሳት አይኖርባቸውም። ፍቅር ሁላችንም ‘የመሪነቱን ቦታ ለያዙ ወንድሞች እንድንታዘዝና እንድንገዛ’ ይረዳናል።”​—ዕብራውያን 13:17

ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ስለሚሸፍን’ እርስ በርሳችን ’የጠለቀ ፍቅር’ እንዲኖረን አሳስቦናል። (1 ጴጥሮስ 4:8) ይህን ለማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሰው የተፈጠረው በአምላክ ምሳሌ ስለሆነ ሌላውን የማፍቀር ተፈጥሮአዊ ችሎታ ይኖርሃል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የምንናገርለት የፍቅር ዓይነት አንድ ተጨማሪ ነገር ያስፈልገዋል። ፍቅር ዋነኛው የአምላክ የመንፈስ ፍሬ መሆኑ እውነት ነው። (ገላትያ 5:22) ስለዚህ ፍቅርን ለመኮትኮት ራሳችንን ለአምላክ መንፈስ ክፍት ማድረግ ይኖርብናል። እንዴት? በይሖዋ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን በመጸለይ ነው። መንፈሱ በነፃ ከሚፈስበት ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር በመሰብሰብ ነው።

በተጨማሪም ፍቅር የጎደላቸው ድርጊቶች ወይም አስተሳሰቦች እንዳሉብን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። ፍቅር የልብ ጠባይ መሆኑንና “ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ” መሆኑን አስታውሱ። (ኤርምያስ 17:9) ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት እርዳታ የሚሰጠን ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ፍቅር በጎደለው መንገድ ልንመላለስ እንችላለን። ክርስቲያን ጓደኞቻችንን አስፈላጊ ባልሆነ ኃይለኛ ቃል ልንናገራቸው እንችላለን፤ ወይም በአንድ በተነገረ ቃል ልንቆጣና ልንጎዳ እንችላለን። እንደዚህ ከሆነ የሚከተለውን የዳዊትን ጸሎት ደግመን እንጸልይ፦ “አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።”​—መዝሙር 139:23, 24

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘ፍቅር በፍጹም አይወድቅም።’ (1 ቆሮንቶስ 13:8) እርስ በርሳችን የምንፋቀር ከሆነ በፈተና ጊዜ በፍጹም ቀልለን አንታይም። በአምላክ ሕዝብ መካከል የሚገኘው ፍቅር በዛሬው ጊዜ ላለው መንፈሳዊ ገነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚችሉት እርስ በርሳቸው ከልብ አጥብቀው የሚዋደዱት ብቻ ናቸው። እንግዲያው እንደዚህ ያለውን ፍቅር ለማሳየትና የአንድነትን ማሠሪያ ለማጠናከር ይሖዋን ምሰሉት። ፍቅርን ኮትኩቱ፤ የእውነተኛ ክርስትናን ቁልፍ አግኙ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ