የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 10/1 ገጽ 29-31
  • “ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘እነርሱን ማበሳጨት’ ማለት ምን ማለት ነው?
  • ልጆችን በአምላክ ተግሣጽ ማሳደግ
  • ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት
    ንቁ!—2005
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችህን ለማሰልጠን ይረዳህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 10/1 ገጽ 29-31

“ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው”

“አባቶች ሆይ ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው።” ይህን ያለው ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር። (ኤፌሶን 6:4) የኢንዱስትሪው ማህበረሰብ ብዙ ጭንቀትና ውጥረት በወላጆች ላይ በሚጭንባቸው በምዕራብ አገሮች ልጆችን በፍቅርና በደግነት መያዝ ቀላል ነገር አይደለም። በማደግ ላይ በሚገኙት አገሮች ውስጥም ቢሆን ልጅ ማሳደግ ከዚህ ያላነሰ ፈታኝ ሆኗል። እርግጥ በእነዚህ አገሮች ያለው የኑሮ ሩጫ በምዕራቡ ካለው ዝግ ያለ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ባሕሎችና ልማዶች ልጆቻችሁን በሚያበሳጭና በሚያሳዝን ሁኔታ እንድታሳድጉአቸው ሊያደርጓችሁ ይችላሉ።

በአንዳንድ አዳጊ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ትንንሽ ልጆች የሚሰጣቸው እውቅናና አክብሮት በጣም አነስተኛ ነው። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ልጆች የግዴታ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል፣ ይዛትባቸዋል፣ ይጮኽባቸዋል ወይም ይሰደባሉ። አንድ ትልቅ ሰው ልጅን “እባክህ” እና “አመሰግናለሁ” በሚሉት የአክብሮት ቃላት መናገር ይቅርና በደግነት ቃል ሲናገረው የሚሰማው አልፎ አልፎ ብቻ ሊሆን ይችላል። አባቶች ሥልጣናቸውን በኃይል ማስጠበቅ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። በኃይለኛ ቃላት ላይ ዱላም ይጨመራል።

በአንዳንድ የአፍሪካ ባሕሎች አንድ ትንሽ ልጅ በራሱ ተነሳስቶ ለአንድ ትልቅ ሰው ሰላምታ ቢሰጥ እንደ ብልግና ይቆጠርበታል። በራሳቸው ላይ ከባድ ሸክም የተሸከሙ ወጣቶች ሌሎች ትልልቅ ሰዎችን ሰላም ለማለት እስከሚፈቀድላቸው ድረስ ሸክማቸውን ሳያወርዱ በትዕግሥት ሲጠባበቁ መመልከት ያልተለመደ ነገር አይደለም። በዕድሜ ትልቅ የሆኑት ሰላም እንዲሉ እስከሚፈቀድላቸው ድረስ ቆመው የሚጠባበቁትን ወጣቶች ችላ ብለው የስንፍና ወሬያቸውን ይቀጥላሉ። ልጆቹ ለማለፍ የሚፈቀድላቸው ሰላምታ ከሰጡ በኋላ ብቻ ነው።

ሌላው የልጆች እድገት ጠላት ድህነት ነው። ወጣቶች ገና በልጅነታቸው ተቀጣሪ ሠራተኞች በመሆን ጤንነታቸውንና ትምህርታቸውን ሰውተው ይበዘበዛሉ። በቤት ውስጥም ቢሆን ከአቅም በላይ የሆነ ከባድ የሥራ ጭነት በልጆች ላይ ሊጫን ይችላል። እንዲሁም በገጠር አካባቢ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት እንዲያገኙ በትልቅ ከተሞች ውስጥ ወደሚገኙ ዘመዶች ይልኳቸዋል፤ በዚያም አብዛኛውን ጊዜ ከባሪያ ባልተሻለ ሁኔታ ይያዛሉ። ይህ ሁሉ መጥፎ አያያዝ ልጆችን እንደሚያበሳጫቸው የተረጋገጠ ነው!

‘እነርሱን ማበሳጨት’ ማለት ምን ማለት ነው?

አንዳንድ ወላጆች የሚያስከትላቸውን ውጤቶች ሳያስቡ በአካባቢያቸው በተለመዱት ልጆችን የማሳደግ ልማዶች ተሸንፈው እንዲወሰዱ ፈቅደዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳያበሳጩአቸው ያሳሰበው አለበቂ ምክንያት አይደለም። እዚህ ላይ “አታበሳጩአቸው” ተብሎ የተተረጎመው የጥንቱ የግሪክኛ አባባል ቃል በቃል ሲተረጎም “ቁጣን የምትቀሰቅሱ አትሁኑ” ማለት ነው። (ኪንግደም ኢንተርሊኒየር) በሮሜ 10:19 ላይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ግሥ “ብርቱ ቁጣን ማነሳሳት” ተብሎ ተተርጉሟል።

በዚህ ምክንያት ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሺን እንዲህ ይላል፦ “ልጆችን በሚያስቆጣቸው መንገድ አትያዟቸው።” ዘ ጀሩሳሌም ባይብልም በተመሣሣይ “ልጆቻችሁን በፍጹም ቅር ወደሚሰኙበት ሁኔታ አትገፋፏቸው” ይላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ላይ የሚናገረው አንድ ወላጅ ባለፍጽምና ምክንያት ሳያውቀው ቀለል ባለ ሁኔታ ስለማስቆጣቱ አይደለም። ወይም በተገቢ መንገድ የተሰጠውን ተግሣጽ ማውገዙ አይደለም። ላንጅስ ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ እንደገለጸው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚናገረው “ልጆች በጥድፊያ፣ ስሜትን ባለመቆጣጠርና በጭካኔ በመያዝ ምክንያት . . . ከወላጆች እንዲርቁ፣ ወላጆቻቸውን በምሬትና በግትርነት እንዲቃወሙ ስለማነሳሳት ነው።”

የትምህርት አሰጣጥ ምሁር የሆኑት ጄ ኤስ ፋራንት እንደገለጹት “ልጆች ሰዎች ናቸው። ዕፅዋት ለአካባቢያቸው እንደሚያደርጉት የሚያጋጥማቸውን ተጽእኖ ሁሉ አለተቃውሞ በእሺታ አይቀበሉም። አፀፋዊ እርምጃ ይወስዳሉ።” ብዙውን ጊዜም ለሚሰጣቸው ፍትሕ የጎደለው አያያዝ የሚሰጡት ምላሽ መንፈሳዊና ስሜታዊ ውድቀት ያስከትልባቸዋል። መክብብ 7:7፦ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” ይላል።

ልጆችን በአምላክ ተግሣጽ ማሳደግ

ልጆቻቸው በእውነት እንዲመላለሱ የሚመኙ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው ባሕላዊ ሥርዓቶችና ልማዶች እንዲወስኑላቸው መፍቀድ የለባቸውም። (ከ3 ዮሐንስ 4 ጋር አወዳድር) ጳውሎስ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳያበሳጯቸው ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ጨምሮ፦ “በተግሣጽና በይሖዋ ምክር አሳድጓቸው” ብሏል። (ኤፌሶን 6:4) ስለዚህ የአካባቢ ልማዶችና አስተሳሰቦች በይሖዋ ሕጎችና ሥርዓቶች መተካት ይኖርባቸዋል።

በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ልጆች ዝቅተኞች እንደሆኑና እንደ ባሮች መታየታቸው የተለመደ ነገር ሊሆን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 127:3 ላይ “እነሆ፣ ልጆች [የይሖዋ (አዓት)] ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው” በማለት ይገልጻል። አንድ ወላጅ ስጦታውን አግባብ በሌለው መንገድ የሚይዝ ከሆነ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖረው ይችላልን? በፍጹም አይችልም። ወይም ልጆች የወላጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የሚኖሩ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ቦታ የለውም። በ2 ቆሮንቶስ 12:14 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውም” በማለት ያሳስበናል።

ልጆች በቤት ውስጥ ሥራዎችና ኃላፊነቶች መካፈል አይገባቸውም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የልጁ የግል ፍላጎቶች ትኩረት ሊሰጣቸው አይገባምን? ለምሳሌም ያህል አንዲት በአፍሪካ ውስጥ የምትገኝ ያአ የምትባል ክርስቲያን ልጃገረድ ወላጆችዋ ለእርስዋ ምን ቢያደርጉላት እንደምትፈልግ ተጠይቃ የሰጠችው መልስ፦ “በመስክ አገልግሎት በምሰማራባቸው ቀናት የቤት ውስጥ ሥራዬን ቢቀንሱልኝ በጣም ደስ ይለኛል” የሚል ነበር። ስለዚህ አንድ ልጅ የቤት ውስጥ ሥራዎች ስለበዙበት በጊዜው ትምህርት ቤት ለመድረስ ወይም በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ካልቻለ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ የተሻለ አይሆንምን?

ወጣቶች አስቸጋሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አይካድም። ቢሆንም ወላጆች ሳይሳደቡና ሳያበሳጩአቸው እንዴት ሊይዙአቸው ይችላሉ? ምሳሌ 19:11 “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቁጣ ያዘገየዋል” ይላል። አዎን፣ ልጅህ አንድ የተለየ ግለሰብ መሆኑን ለመረዳት መሞከር ይኖርብሃል። እያንዳንዱ ልጅ የራሱ ስሜቶች፣ ችሎታዎችና ፍላጎቶች ያሉት የተለየ ሰው ነው። እነዚህ ፍላጎቶቹ ምንድን ናቸው? ልጅህን በደንብ ለማወቅና ለዚህ ጥያቄ መልሱን ለማግኘት ጊዜ ወስደሃልን? አብሮ መሥራትና ማምለክ፣ በቤተሰብ መዝናኛ መሳተፍና እነዚህን የመሳሰሉት ነገሮች ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዲቀራረቡ አጋጣሚዎችን ይሰጧቸዋል።

በ2 ጢሞቴዎስ 2:22 ላይ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ” በማለት አንድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንዳለ ገልጾአል። አዎን፣ ጳውሎስ ወጣትነት አስቸጋሪ ወቅት ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቧል። አስገራሚ የሆኑ አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች ይከናወናሉ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚኖረው መሳሳብ ያድጋል። በዚህን ጊዜ ውስጥ ወጣቶች ከአደገኛ ወጥመድ ለመዳን እንዲችሉ የበሰለና ፍቅራዊ የሆነ መመሪያ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ባለጌ እንደሆኑ ተደርገው መታየት የለባቸውም። በጣም የተበሳጨች የአንድ ክርስቲያን ልጅ “ምንዝር ሳልፈጽም አባቴ እንደፈጸምኩ አድርጎ የሚመለከተኝ ከሆነ ሄጄ አመነዝራለሁ” ስትል በሐዘን ተናግራለች። ልጃችሁን ከመጠራጠርና መጥፎ ድርጊት እንደፈጸመ ከማሰብ ይልቅ በልጃችሁ ላይ እምነት እንዳላችሁ ግለጹ። (ከ2 ተሰሎንቄ 3:4 ጋር አወዳድር) ተቺዎች ከመሆን ይልቅ ራሳችሁን በልጃችሁ ቦታ የምታስቀምጡና አስተዋዮች እንዲሁም ሕጋችሁን በየጊዜው የማትለዋውጡ ሁኑ።

ይሁን እንጂ ወላጆች አንድን ልጅ ስለሚያጋጥሙት የመጥፎ ስነ ምግባር አደጋዎች አስቀድመው ቢያወያዩት ከብዙ ችግሮች ሊያድኑት ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን በአምላክ ቃል እንዲያሰለጥኗቸውና እንዲያስተምሯቸው አምላክ ግዴታ እንደጣለባቸው አስታውስ። (ዘዳግም 6:6, 7) ይህም ብዙ ጊዜንና ጥረትን ይጠይቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ወላጆች ትዕግሥት በማጣታቸው ምክንያት የማስተማር ሥራቸውን ሳይፈጽሙ ቀርተዋል። ሌሎች ወላጆች ደግሞ በአዳጊ አገሮች ከፍተኛ ችግር በሆነው በመሃይምነት ምክንያት ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተቸግረዋል።

አንዳንድ ጊዜ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ እንዲያደርጉ ሊጠሩ ይችላሉ። ይህም እርዳታ ብዙ ተሞክሮ ለሌለው ወላጅ ሐሳብ መስጠት ብቻ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 27:17) ወይም የቤተሰብ ጥናቱን በመምራት መርዳትን የሚጨምር ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ አይነቱ እርዳታ አንድ ወላጅ ልጁን የአምላክን ቃል እንዲያስተምር ከተሰጠው ኃላፊነት ነፃ አያደርገውም። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከልጆቹ ጋር በመስክ አገልግሎት አብሮ ለመሥራትና በምግብ ጊዜ ወይም አመቺ በሆኑ በሌላ ጊዜያት ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመወያየት ጥረት ማድረግ ይችላል።

አንድ ሙሉ ሰው ወደመሆን ደረጃ የደረሰ ወጣት የበለጠ ነፃነት ለማግኘት ይመኝ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ይህ ነገር እንደ አልገዛም ባይነት ወይም እንደ ብልግና ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል። ወላጆቹ ልክ እንደ ሕፃን አድርገው ቢቆጥሩትና በሚያደርጋቸው ነገሮች የሐሳብ ነፃነት ሊሰጡት ፈቃደኛ ባይሆኑ በጣም የሚያበሳጨው ነገር ይሆናል። ስለ ሁሉም የሕይወቱ ገጽታዎች ማለትም ስለ ትምህርቱ፣ ስለ ሥራው፣ ስለ ጋብቻው ጉዳዩን በተረጋጋና በአክብሮት መንገድ ከእርሱ ጋር ሳይነጋገሩበት ቢወስኑ ደግሞ በጣም የሚያበሳጨው ይሆናል። (ምሳሌ 15:22) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹን ‘በማስተዋል ኃይላቸው ሙሉ ሰው እንዲሆኑ’ አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:20) ወላጆች ልጆቻቸው በስሜትና በመንፈሳዊ እንዲያድጉላቸው መፈለግ የለባቸውምን? አዎን የአንድ ወጣት ‘የማስተዋል ኃይል’ ሊሰለጥን የሚችለው ‘ሲጠቀምበት’ ብቻ ነው። (ዕብራውያን 5:14) በማስተዋል ኃይሉ እንዲጠቀም የተወሰነ መጠን ያለው የመምረጥ ነፃነት ሊሰጠው ይገባል።

በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ልጆችን ማሳደግ ቀላል ነገር አይደለም። ሆኖ የአምላክን ቃል የሚከተሉ ወላጆች “ልባቸው እንዳይዝል” ልጆቻቸውን አያስቆጡአቸውም ወይም አያበሳጩአቸውም። (ቆላስይስ 3:21) ከዚህ ይልቅ በጋለ ፍቅር፣ በማስተዋልና በክብር ሊይዟቸው ይሞክራሉ። ልጆቻቸውን ማባረር ሳይሆን መምራት፣ ችላ ማለት ሳይሆን ማሳደግ፣ ለቁጣ ወይም ለብስጭት ማነሣሣት ሳይሆን ፍቅር ማሳየት ይገባቸዋል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጋና ውስጥ “ኦዋሪ” የተባለውን የቤት ውስጥ ጨዋታ መጫወቱ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አብረው እንዲሆኑ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ