የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 11/1 ገጽ 25-29
  • ‘ይሖዋ የምታመንበት አምላኬ ነው’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ይሖዋ የምታመንበት አምላኬ ነው’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የወላጆቼ ምሳሌ የሚሆን ቅንዓት
  • የአባቴ የጥበብ ምክር
  • ከሰማይ የወረደ መልእክት!
  • ለማንኛውም የአገልግሎት መብት አመስጋኝ መሆን
  • በጦርነቱ ወቅት ንቁ ሆኖ መቆየት
  • ያልተጠበቁ ውጤቶችን ያመጣው ጉብኝት
  • ችግሮች ቢኖሩም መጽናት
  • ወንድም ኖር ተመለሰ
  • ያልታሰቡ አስደሳች ነገሮች
  • መለስ ብሎ ማሰብ
  • ባሳለፍኩት ሕይወት ፈጽሞ አልቆጭም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የከፈተልኝ ግሩም አጋጣሚዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 11/1 ገጽ 25-29

‘ይሖዋ የምታመንበት አምላኬ ነው’

በዊሊ ዲየል እንደተነገረው

“ቤቴል ለመሄድ የምትፈልገው ለምንድን ነው?” ይህ ጥያቄ በ1931 የፀደይ ወራት የቤቴል አገልግሎት ለመጀመር እንደምፈልግ ለአባቴ በነገርኩት ጊዜ የጠየቀኝ ጥያቄ ነበር። በዛርላንድ ይኖሩ የነበሩት ወላጆቼ ለአሥር ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ በእውነት ውስጥ የኖሩ ነበሩና ለእኛ ለሦስት ወንዶች ልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል። እውነት መላ ሕይወታቸው ነበር። እኔም እውነትን መላው ሕይወቴ ላደርገው ፈለግኩ።

ለመሆኑ ወላጆቼ ስለ ይሖዋና ስለ ቅዱስ ፈቃዱ እንዴት ሊማሩ ቻሉ? በታወቁት ሃይማኖቶች ስላልረኩ ለረጅም ጊዜ እውነትን ይፈልጉ ነበር። የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትንና እምነቶችን ሞክረው ሁሉም ሃይማኖት ትክክለኛ እንዳልሆነ ተገነዘቡ።

አንድ ቀን “ፎቶ ድራማ ኦፍ ክሪኤሽን” የተሰኘውን ስለ አምላክ ዓላማ በሥዕልና በፊልም የሚደረግ ንግግር የሚያስተዋውቅ የግብዣ ወረቀት በበራችን ላይ ተትቶ ተገኘ። ፎቶ ድራማው በሚታይበት ሰዓት አባቴ በሥራ ቦታው ተረኛ በመሆኑ ምክንያት ሊሄድ ስላልቻለ እናቴ እንድትሄድ አበረታታት። “ምናልባት አንድ ቁምነገር ይኖረው ይሆናል” አላት። በዚያ ምሽት አይታ ከመጣች በኋላ በአድናቆት ስሜት ተሞልታ ነበር። “በመጨረሻ አገኘሁት! ነገ ምሽት ና እንሂድና ራስህ እይ። ስንፈልገው የነበረው እውነት ነው” አለች። ይህ የሆነው በ1921 ነበር።

ወላጆቼ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በመሆን አባቴ በናዚዎች በተደጋጋሚ ከታሠረ በኋላ በ1944 እናቴ ደግሞ በ1970 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት ጸንተዋል። እናቴም በናዚ አገዛዝ ሥር በእሥር ቤት ረዘም ያለ ጊዜ አሳልፋለች።

የወላጆቼ ምሳሌ የሚሆን ቅንዓት

ወላጆቼ ከመሞታቸው በፊት በመስክ አገልግሎት በጣም ትጉሆች ነበሩ። በተለይ እናቴ ከ1922-1928 በነበሩት ዓመታት በስብሰባ ላይ የወጡ ውሣኔዎችን በማሠራጨት በጣም ቀናተኛ ነበረች። አብያተ ክርስቲያናት ተወነጀሉ በሚል ርዕስ በ1924 ስብሰባ ላይ የወጣውን ውሣኔ የያዘው ጽሑፍ ቀሳውስትን የሚነቅፍ ነበር። ይህን ጽሑፍ ለማሠራጨት ትልቅ ድፍረት ይጠይቅ ነበር። አስፋፊዎቹ ጽሑፎቹን በየቤቶቹ በመዝጊያዎቹ ሥር ገፍተው ለማስገባት ከሌሊቱ በ10 ሰዓት ይነሡ ነበር። ያኔ የ12 ዓመት ልጅ ብሆንም ወላጆቼ እኔም እንድካፈል ፈቀዱልኝ። አብዛኛውን ጊዜ ራቅ ወዳሉ ቀበሌዎችም ለማዳረስ ከሦስት እስከ አራት ሰዓት በብስክሌት ለመሄድ ማለዳ በ11 ሰዓት እንጀምር ነበር። ብስክሌቶቻችንን በቁጥቋጦ ውስጥ እንደብቅና ሌሎቹ መንደሮቹን አዳርሰው እስኪመለሱ ድረስ እኔ ብስክሌቶቹን እጠብቅ ነበር። ከሰዓት በኋላ ወደቤታችን እንሄድና ምሽቱ ላይ ለአንድ ሰዓት ያህል ወደሚደረጉት ስብሰባዎቻችን እንሄድ ነበር።

ቆየት ብሎ ከእኔ የሚያንስ ሌላ ልጅ ብስክሌቶቹን እንዲጠብቅ ተደረገና ከአስፋፊዎቹ ጋር ሄድኩ። ነገር ግን እኔን ስለማመድ ማንም አላሰበም ነበር። ዝም ብለው ብቻ በየትኛው ጎዳና ልሠራ እንደሚገባኝ ነገሩኝ! ልቤ በኃይል እየደለቀ መጀመሪያው ቤት ቀረብኩና በቤት ማንም ሰው እንደማይኖር ተስፋ በማድረግ ቀስ ብዬ ተመለከትኩ። ጉዴ ፈላ፣ አንድ ሰው በሩን ከፈተ። መናገር አቃተኝ። ቦርሳዬን እየበረበርኩ በውስጡ ወዳለው መጽሐፍ አመለከትኩ። “ከጀጅ ራዘርፎርድ ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ተንተባትቤ መልስ ሰጠሁ። “ከአሁን በፊት ያላገኘሁት አዲስ ጽሑፍ ነው?” አለኝ። “አዎ አዲስ ነው” ብዬ አረጋገጥኩለት “እንግዲያውስ ልውሰደው፣ ዋጋው ምን ያህል ነው?” አለ። ይህ አጋጣሚ እንድቀጥል ድፍረት ሰጠኝ።

በ1924 በዕድሜ ከፍ ያሉት ስለ 1925 ብዙ ያወሩ ነበር። አንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሆኑ ቤተሰቦቼን ልንጠይቅ ሄደን ነበርና አንድ ወንድም “ጌታ እኛን ከወሰደን ልጆቻችን እንዴት ይሆናሉ?” ብሎ ሲጠይቅ ሰማሁት። እናቴ እንደማንኛውም ጊዜ እርግጠኛ ሆና “ጌታ ልጆቻችንን እንዴት እንደሚንከባከብ ያውቃል” ብላ መለሰች። የሚነጋገሩት ነገር መሰጠኝ። ምን ማለት ይሆን? 1925 መጣና አለፈ፤ ምንም ነገር አልተፈጸመም። ይሁን እንጂ ወላጆቼ ቅንዓታቸውን አላቀዘቀዙም።

የአባቴ የጥበብ ምክር

በመጨረሻም በ1931 በሕይወቴ ምን ልሠራበት እንደምፈልግ ለአባቴ ነገርኩት። በምላሹም አባቴ “ቤቴል መሄድ የምትፈልገው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። “ይሖዋን ለማገልገል ስለምፈልግ ነው” ብዬ መለስኩለት። አባቴ በመቀጠል “ለቤቴል አገልግሎት ተቀበሉህ እንበል። እዚያ ያሉት ወንድሞች መላእክት አለመሆናቸውን ትገነዘባለህ? ፍጹማን ስላልሆኑ ስሕተት ይሠራሉ። ይህም ከዚያ እንድትወጣና ምናልባትም እምነትህንም እንኳን ሳይቀር እንድትተው ያደርግሃል ብዬ እፈራለሁ። ስለዚህ ጉዳይ በጥንቃቄ አስብበት” አለኝ።

እንዲህ ዓይነት ነገር ስሰማ ደነገጥሁ። ነገር ግን ጉዳዩን ለጥቂት ቀናት አመዛዘንኩና ቤቴል ለመግባት ለማመልከት እንደምፈልግ ደጋግሜ ነገርኩት። “ለምን ለመሄድ እንደምትፈልግ እንደገና ንገረኝ” አለኝ። “ይሖዋን ለማገልገል ስለምፈልግ ነው” ብዬ በድጋሚ መለስኩለት። “የኔ ልጅ ይህን ፈጽሞ እንዳትረሳ። ከተጋበዝክ ለምን እንደምትሄድ አስታውስ። አንድ የተሳሳተ ነገር ካየህ ከልክ በላይ አትጨነቅ። መጥፎ ነገር ቢደረግብህም ትተህ አትውጣ። ይሖዋን ማገልገል ስለምትፈልግ ነውና በቤቴል ውስጥ የምትኖርበትን ምክንያት ፈጽሞ እንዳትረሳ። ሥራህን ብቻ ፈጽም፤ በይሖዋም ተማመን።”

ስለዚህ ኅዳር 17, 1931 ከሰዓት በኋላ በስዊዘርላንድ በርን ወደሚገኘው ቤቴል ስደርስ ገና ልጅ ነበርኩ። አንድ ክፍል ውስጥ አራት ሆነን እያደርን በእጅ የሚንቀሳቀስ አነስተኛ የማተሚያ መኪና ማሠራት እየተማርኩ በማተሚያው ክፍል እሠራ ነበር። በመጀመሪያ እንዳትም ከተሰጡኝ ጽሑፎች ውስጥ አንዱ በሩማንያኛ ቋንቋ የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ነበር።

ከሰማይ የወረደ መልእክት!

በ1933 ማህበሩ ወንድም ራዘርፎርድ በዩናይትድ ስቴትስ የሰጣቸውን ሦስት የሬዲዮ ንግግሮች የያዘ ዘ ክራይሲስ የተሰኘውን ትንሽ መጽሐፍ አወጣ። የቅርንጫፍ አገልጋይ የሆነው ወንድም ሀርቤክ አንድ ቀን ጧት በቁርስ ሰዓት ንዑስ መጽሐፉ የሚሠራጨው በተለየ መንገድ እንደሚሆን ለቤቴል ቤተሰብ ነገረ። አስተዋዋቂ ጽሑፎች በበርን ከተማ ሰማይ ላይ በምትበር ትንሽ የኪራይ አይሮፕላን እንደሚጣል በዚያኑ ሰዓት ወንድሞች በመንገድ ላይ ቆመው ለሕዝቡ ንዑስ መጽሐፉን እንዲያድሉ ተወሰነ። “ወጣቶች ከሆናችሁ ወንድሞች መሃል ማንኛችሁ ናችሁ በአይሮፕላኑ ለመሄድ የተዘጋጃችሁ?” ብሎ ጠየቀ። “ስማችሁን ቶሎ ስጡ” እኔ ስሜን ሰጠሁ፤ ወንድም ሀርቤክ እኔ እንደተመረጥኩ በኋላ አስታወቀ።

በዚያ ታላቅ ቀን አስተዋዋቂ ጽሑፎቹን በካርቶኖች ጭነን ወደ አይሮፕላን ማረፊያው ሄድን። በፓይለቱ ጎን ተቀመጥኩና ጽሑፎቹን አጠገቤ ባለው መቀመጫ ላይ ከመርኳቸው። የተሰጠኝ ጥብቅ ትዕዛዝ ማስታወቂያዎቹን በመቶ መቶ ጠቅልዬ እያንዳንዱን ጥቅልል በመስኮት አዝልቄ ወደ አንድ ጎን ባለኝ ጉልበት ሁሉ እንድወረውር ነበር። ግድየለሽ ብሆን ወረቀቶቹ ከአይሮፕላኑ ጅራት ጋር ሊያያዙና ችግር ሊፈጥር ይችል ነበር። ነገር ግን ሁሉም ነገር ሠመረ። ወንድሞች በኋላ ይህን “ከሰማይ የወረደ መልእክት” ማየት እንዴት ያስደስት እንደነበረ ተናገሩ። አንዳንድ ሰዎች የአበባ መደቦቻቸው በወረቀቶቹ ተሸፈኑብን ብለው በማማረር ስልክ ቢደውሉም የተፈለገውን ውጤት አስገኝቶ ስለነበር ብዙ ንዑስ መጻሕፍት ተበረከቱ።

ለማንኛውም የአገልግሎት መብት አመስጋኝ መሆን

በቤቴል፣ አገልግሎት ላገኘሁት ደስታና እርካታ በየቀኑ ይሖዋን አመሰግን ነበር። በጉባኤው የመንግሥት አዳራሹን እንድከፍት፣ መቀመጫ ወንበሮችን እንዳስተካክልና በተናጋሪው መቆሚያ ንጹሕ ውሃ እንዳስቀምጥ ተመድቤ ነበር። ይህንንም እንደ ትልቅ ክብር እቆጥረው ነበር።

በቤቴል ዛሬ ንቁ! የሚባለውን ወርቃማው ዘመን መጽሔት በፖሊሽ ቋንቋ ለማተም በሚያገለግል ባለጠፍጣፋ መደብ ማተሚያ ላይ መሥራት ጀመርኩ። በ1934 በሸክላ ማጫወቻ መጠቀም ጀመርንና እኔም በመሣሪያው ዝግጅት አግዝ ነበር። በሸክላ ማጫወቻ ላይ የተቀዱ ንግግሮችን ይዤ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ትልቅ ደስታ አግኝቻለሁ። ብዙ ባለቤቶች ይህን አዲስ ዓይነት መሣሪያ ለማወቅ ይጓጉ ነበር። ስለዚህም አብዛኛውን ጊዜ መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ይሰበሰብ ነበር። በኋላ ግን አንድ አንድ እያሉ ጥለው ይሄዱ ነበር። ቤተሰቡ በሞላ ከሄዱ በኋላ እኔም ተነስቼ እሄድ ነበር።

በጦርነቱ ወቅት ንቁ ሆኖ መቆየት

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የትውልድ አገሬ ዛርላንድ ከጀርመን ተለይታ በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማህበር ሞግዚትነት ትተዳደር ነበር። ስለዚህ ዛርላንድ የራሷ የመታወቂያ ሰነድ አወጣች። በ1935 ዜጎቿ ከጀርመን ጋር መዋሃድ ይፈልጉ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲወስኑ የሕዝብ ምርጫ ተደርጎ ነበር። ዛርላንድ በናዚ ቁጥጥር ሥር ከሆነች ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ እንደማልችል ስላወቅሁ ከዚያ በፊት ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ አጋጣሚውን ተጠቀምኩበት። በእርግጥም ከዚያ በኋላ በነበሩት ብዙ ዓመታት ከቤተሰቦቼም ሆነ ከወንድሞች ስለደህንነታቸው ምንም ሳልሰማ ቆይቻለሁ።

ስዊዘርላንድ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ከመግባት ብትድንም ጀርመን ያጎራባች አገሮችን አንድ በአንድ ስትይዝ እሷ ብቻዋን ተለይታ ቆየች። ከጀርመን በስተቀር ለመላው አውሮፓ ጽሑፎችን እናትም ነበር። አሁን ግን የጽሑፎች ትእዛዝ ሊደርሰን አልቻለም። በዚያን ጊዜ የቅርንጫፍ አገልጋይ የነበረው ወንድም ዙርሸር ምንም ገንዘብ እንዳልቀረ ነገረኝና ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እስኪመለሱ ድረስ ከቤቴል ውጭ ሥራ እንድንፈልግ ነገረን። ይሁን እንጂ አንድ ሺህ ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች መታተም የነበረባቸው ጥቂት ጽሑፎች ስለነበሩ እኔ እንድቆይ ተፈቀደልኝ።

የቤቴል ቤተሰብ ሐምሌ 5, 1940ን ፈጽሞ አይረሷትም። ምሳ እንደበላን የወታደር መኪና መጣ። ወታደሮች እየዘለሉ ወጡና ቤቴልን ተሰገሰጉበት። ሳንንቀሳቀስ ባለንበት እንድንቆም ታዘዝን፤ እያንዳንዳችን በታጠቀ ወታደር እንጠበቅ ነበር። የቀረው የሕንፃው ክፍሎች እስኪፈተሹ ድረስ ወደ ምግብ አዳራሹ ተነዳን። ባለ ሥልጣኖቹ ሌሎች ወንድሞች ወታደራዊ አገልግሎት ለመቀበል እምቢ እንዲሉ ነግረዋቸዋል ብለው ጠርጥረውን ነበር። ግን ምንም ማስረጃ አላገኙም።

በጦርነቱ ዓመታት በቱንና በፍሩቲጀን በሁለቱም ጉባኤዎች የጉባኤ አገልጋይ ነበርኩ። በዚህም ምክንያት ቅዳሜና እሁድ በጣም ሥራ ይበዛብኝ ነበር። ሁልጊዜ ቅዳሜ ምሳ እንደበላሁ ምሽቱ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወደምመራበት 48 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ፍሩቲጂን በብስክሌት እበር ነበር። እሁድ ዕለት ጧት አስፋፊዎቹ ጋር ወደ መስክ አገልግሎት አብሬ እሄድ ነበር። ከዚያም እኩለ ቀን ላይ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ፕሮግራም ለመምራትና ከዚያ በኋላም በእስፒየዝ ለሚገኝ ቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት እሄድ ነበር። በቀኑ መጨረሻ በቱን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እመራ ነበር።

ማታ ሥራዎቼን ሁሉ ካጠናቀቅሁ በኋላ በጥልቅ ረክቼ እያፏጨሁ ወደ በርን እመለስ ነበር። መኪናዎች በጣም ጥቂትና በመንገዱ ላይ ተራርቀው የሚሄዱ ነበሩ። ኮረብታማው ምድር በጦርነት ጨለማ ተሸፍኖ ስለነበር የጨረቃ ብርሃን ከሚንጸባረቅበት በቀር ጸጥና ረጭ ያለ ነበር። እነዚያ የሳምንት መጨረሻ ቀናት ሕይወቴን በጣም አበልጽገውልኝና ኃይሌን አድሰውልኝ ነበር።

ያልተጠበቁ ውጤቶችን ያመጣው ጉብኝት

በ1945 የበልግ ወራት ወንድም ኖር ጎበኘን። አንድ ቀን ወደ ፋብሪካው ሲገባ በተሽከርካሪው ማተሚያ ላይ ቆሜ ነበር። “ውረድና ና” ብሎ ጠራኝ። “ጊሊያድ ትምህርት ቤት ብትከታተል ምን ይሰማሃል?” አለኝ። በጣም ተደነቅሁ። “ለዚያ የምበቃ ከመሰለህ ደስ ይለኛል” ብዬ መለስኩለት። ለወንድም ፍሬድ ቦሪስ፣ ለእህት አሊስ በርንርና ለእኔም ጥሪው በ1946 ጸደይ ወራት ደረሰን። ነገር ግን የዛርላንድ ተወላጅ በመሆኔ አሁን አገር አልባ ነበርኩና ልዩ ቪዛ እንዲሰጠኝ ለዋሽንግተን ዲሲ ዩ. ኤስ. ኤ. ማመልከት ነበረብኝ።

ሌሎቹ በጊዜው ሲሄዱ እኔ ግን የማመልከቻዬን መልስ መጠባበቅ ነበረብኝ። መስከረም 4 ትምህርቱ ሲጀምር እኔ ግን ገና በስዊዘርላንድ ስለነበርኩ የመሄድ ተስፋዬ ቀስ በቀስ እየጠፋ ሄደ። ከዚያም የዩ ኤስ ኤ ቆንስላ ጠራኝና ቪዛዬ እንደመጣ ነገረኝ። ወዲያውኑ የጉዞ ዝግጅት ለማድረግ ጣርኩና በመጨረሻ ከማርሴልስ ወደ ኒውዮርክ የሚሄድ የወታደር መርከብ ላይ መኝታ ክፍል አገኘሁ። እንዴት ዓይነት ተሞክሮ ነበር! አቶስ 2ኛ የተባለው መርከብ በተሳፋሪ ተጨናንቆ ነበር። በአንድ ባዶ ክፍል ውስጥ እንድተኛ መኝታ ተሰጠኝ። ጉዞ በጀመርን በሁለተኛው ቀን በሞተር ክፍሉ የደረሰ ፍንዳታ መርከቧ ቀጥ ብላ እንድትቆም አደረጋት። መንገደኞችና መርከበኞቹም እንሰጥም ይሆናል ብለው በመፍራት ተጨንቀው ነበር። ይህም ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለመመስከር ግሩም አጋጣሚ ሰጠኝ።

መርከቧን ለመጠገን ሁለት ቀን ፈጀ። ከዚያ በኋላ ባነሰ ፍጥነት ጉዞ ቀጠልን። ኒውዮርክ 18 ቀናት ዘግይተን ደረስን። እዚያም የወደብ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ስለነበረ ባሕር ላይ ለመቆየት ተገደድን። የስምምነት ንግግር ከተደረገ በኋላ በመጨረሻ መርከቧን ለቀን ለመሄድ ቻልን። ስለ ሁኔታው ለማህበሩ በቴሌግራፍ አስታወቅሁና የጉምሩክና የኢምግሬሽኑን መቆጣጠሪያ እንዳለፍኩ አንድ ሰው “ሚስተር ዲያል ነህ?” ብሎ ጠየቀኝ። ከወንድም ኖር ረዳቶች አንዱ ነበርና ከጊሊያድ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ወደምትገኘው ኢታካ የምትሄድ የማታ ባቡር ላይ አሳፈረኝና በማግሥቱ ጧት ሁለት ሰዓት አለፍ እንዳለ ደረስኩ። በመጨረሻ እዚያ በመድረሴና ከልዩ ልዩ አገሮች የመጡ ተማሪዎችን ባሰባሰበው የመጀመሪያው የጊልያድ ትምህርት ቤት ክፍል ለመካፈል በመብቃቴ እንዴት በደስታ ፈነደቅሁ!

ችግሮች ቢኖሩም መጽናት

የስምንተኛው የጊልያድ ኮርስ ምረቃ የካቲት 9, 1947 ስለነበረ ልባችን ተሰቅሎ ነበር። ወዴት እንላክ ይሆን? ለእኔ ማህበሩ በዌስባዴን ጀርመን አዲስ በከፈተው ማተሚያ ቤት እንድሠራ “የዕጣ ገመድ ወደቀችልኝ።” (መዝሙር 16:6) አስፈላጊ ወረቀቶችን ለማግኘትና ማመልከቻ ለማቅረብ ወደ በርን ተመለስኩ። ነገር ግን ጀርመንን የያዙ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ የሚፈቅዱት ከጦርነቱ በፊት እዚያ ለነበሩት ብቻ ነበር። እኔ ከጦርነቱ በፊት እዚያ ስላልነበርኩ ከብሩክሊን ዋና ጽሕፈት ቤት አዲስ ምድብ መቀበል አስፈለገኝ። ምድቤ በስዊዘርላንድ የክልል ሥራ ሆነ። እኔም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ተቀበልኩት። ነገር ግን ምድቤን ገና ስጠባበቅ ሳለሁ የቤቴልን ግቢ ሊጎበኙ ለመጡት ሦስት እኅቶች እንዳሳይ ተጠየቅሁ። አንዷ ማርተ ሜሀል የምትባል አቅኚ እኅት ነበረች።

በ1949 ግንቦት ወር ለዋናው መሥሪያ ቤት ማርተን ለማግባት ማቀዴንና በሙሉ ጊዜ አገልግሎቱም ለመቀጠል የምንፈልግ መሆኑን ገለጽኩ። ምላሹስ ምን ነበር? ከዘወትር አቅኚነት በስተቀር ሌላው መብት ሁሉ ተወሰደብኝ። ይህንኑ የሥራ ምድቤን በሰኔ ወር 1949 ከተጋባን በኋላ በቢየል ጀመርን። ንግግር እንድሰጥ አልተፈቀደልኝም ነበር። ለመጪው ስብሰባ ለሚመጡ ልዑካን ማረፊያ የመፈለግ መብት እንዲሰጠኝ የክልል የበላይ ተመልካቹ ሐሳብ ቢያቀርብም ሊፈቀድልን አልቻለም። አቅኚዎች ብንሆንም ብዙዎች ከዚያ ወዲያ ልክ እንደተወገድን በመቁጠር ሰላም አይሉንም ነበር።

ይሁን እንጂ መጋባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ነገር አለመሆኑን እናውቅ ስለነበር ጸሎትን መሸሺያችን በማድረግ በይሖዋ ተማመንን። እርግጥ ስለተጋባን እንደተወገድን ያህል መታየታችን የማህበሩን አመለካከት አያንጸባርቅም ነበር። ድርጅታዊ መመሪያዎችን ያለቦታቸው መጠቀም ያመጣው ውጤት ነበር።

ወንድም ኖር ተመለሰ

በ1951 ወንድም ኖር እንደገና ስዊዘርላንድን ጎበኘ። ንግግር ካቀረበ በኋላ ሊያነጋግረኝ እንደፈለገ ተነገረኝ። በመጠኑ ስጋት ቢያድርብኝም ሊያየኝ በመፈለጉ ደስ አለኝ። በጀኔቫ ሊቋቋም በታሰበ የሚሲዮናውያን ቤት ለመመደብ ፈቃደኞች እንሆን እንደሆነ ጠየቀን። በጣም ደስ አለን። ሆኖም ቢየልን ለቆ መሄድም ቅር የሚያሰኝ ነገር ሆኖብን ነበር። በሚቀጥለው ቀን ከወንድም ኖር ተጨማሪ ጥያቄ ደረሰን። በስዊዘርላንድ ይደረግ የነበረው የክልል ሥራ ተጨማሪ ትኩረት ያስፈልገው ስለነበር ይህንን መብት እንቀበል እንደሆነ ጠየቀን። ወዲያውኑ ተስማማን። ምንጊዜም ዝንባሌዬ የቀረበልኝን ማንኛውንም ምድብ መቀበል ነበር።

በምሥራቅ ስዊዘርላንድ የክልል ሥራ እንቅስቃሴአችን በጣም ተባርኳል። ዕቃዎቻችንን በሙሉ በሁለት የልብስ ሻንጣዎች በመያዝ ከጉባኤ ወደ ጉባኤ በባቡር እንጓጓዝ ነበር። ወንድሞች ብዙ ጊዜ በባቡር ጣቢያው ብስክሌቶቻቸውን ይዘው ይጠብቁን ነበር። ምክንያቱም በዚያ ወቅት መኪና የነበራቸው በጣም ጥቂቶች ነበሩ። ዓመታት ካለፉ በኋላ አንድ ወንድም በምንፈልግበት ጊዜ የምንጠቀምበት መኪና ሰጠን። ይህም አገልግሎታችንን ይበልጥ ቀላል አደረገልን።

ያልታሰቡ አስደሳች ነገሮች

ሚስቴና እኔ በ1964 አሁን ወደ 8 ወር ያጠረውንና ያኔ አጠቃላይ የ10 ወር ኮርስ የነበረውን 40ኛ የጊልያድ የመጨረሻ ክፍል እንድንካፈል ስንጋበዝ እንዴት በደስታ ፈነደቅን! ማርተ እንግሊዝኛ በፍጥነት መማር ነበረባት። ይሁን እንጂ በሚደነቅ መንገድ ቻለች። የት እንደምንላክ ብዙ እናሰላስል ነበር። የኔ ዝንባሌ “ወንበር ላይ መቀመጥ አይሁን እንጂ የትም ብመደብ ግድ የለኝም” የሚል ነበር።

ነገር ግን የተሰጠኝ ምድብ ያው ወንበር ላይ መቀመጥ ሆነ! በመስከረም ወር 1965 በተደረገው የምረቃ ዕለት የስዊዘርላንድ የቅርንጫፍ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። ለማርተ ቤቴል አዲስ ገጠመኝ ሊሆንባት ነው። ለእኔ ግን “ወደ አምላክ ቤት” መመለስ ማለት ነበር። ነገር ግን ወደ ቢሮ እንጂ ከ1931 እስከ 1946 ወደሠራሁበት የሕትመት ክፍል አልነበረም። መማር ያለብኝ ብዙ ነገሮች ነበሩ። ነገር ግን በይሖዋ እርዳታ ችያለሁ።

መለስ ብሎ ማሰብ

በ60 ዓመታት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በሙሉ አባቴ እንደነገረኝ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ተማምኛለሁ። ይሖዋም ልዩ ልዩ በረከቶችን አፍስሶልኛል። ማርተ የከፍተኛ ብርታት ምንጭ ሆናኛለች። እውነትም በይሖዋ ፍጹም ትምክህት ያላት ታማኝ ጓደኛዬ ሆነች።

ላገኘኋቸው ብዙ የአገልግሎት መብቶች ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን! አሁንም በቱን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ ሆኜ አገለግላለሁ። ክልል የበላይ ተመልካች በመሆንም ለአያሌ ጊዜዎች ተጉዣለሁ። ምንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ስጠየቅ መመሪያ ለማግኘት ሁልጊዜ ወደ ይሖዋ እመለከታለሁ። ብዙ ስህተቶችና ድክመቶች ቢኖሩብኝም ይሖዋ በክርስቶስ በኩል ይቅር እንዳለኝ ከልብ አምናለሁ። የማስደስተው ሆኜ እንድቀጥል ያድርገኝ። “የምተማመንበት አምላኬ” እንደሆነ አድርጌ ያለማቋረጥ ወደሱ ስለምመለከት እርምጃዬን መምራቱን ይቀጥል።-​—መዝሙር 91:2

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ዲየል በመጀመሪያው የቤቴል ሥራው ላይ በነበረበት ጊዜ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ