“ቸነፈር በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ይሆናል”
በመጠናቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው ቸነፈሮች በትንቢት የተነገሩት “የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘትና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” ገጽታዎች ሆነዋል። (ማቴዎስ 24:3) የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ በማቴዎስና በማርቆስ ወንጌሎች ላይ ያልተጠቀሱ ዝርዝሮችን ጨምሮበታል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ ማርቆስ ምዕራፍ 13) በመጨረሻው ቀኖች ተላላፊ በሽታዎች “በልዩ ልዩ ሥፍራ” እንደሚፈነዳ ተናግሯል። (ሉቃስ 1:3፤ 21:11) እነዚህ በሽታዎች የሚመጡት ከየት ይሆን?
ሳይንስ ኒውስ የተሰኘው መጽሔት ሲናገር “ሳይንቲስቶች በሞቃት አገሮች አድፍጠው የሚቆዩና ከተፈጥሮ እምብዛም እገዛ ሳያገኙ የኤድስ ወረርሽኝ ከሚያጠፋው ሕይወት ይልቅ እጅግ የሚበዛ ሕዝብ ሊፈጁ የሚችሉ አያሌ የቫይረስ ዓይነቶችን ያውቃሉ። የዓለም የቫይረስ ዝርዝር ሳይጨምር እንዳለ ቢኖርም እንኳ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሞቃት አካባቢዎች አሁንም እንኳ ከምድር ሕዝብ አብዛኛውን ክፍል ሊጠራርግ የሚችል በቂ የቫይረስ ‘ፈንጂ’ ይዘዋል” ይላል።
ዘመናችንን ይበልጥ በበሽታ ተጠቂ ያደረገው እያደገ ያለው የምድር ሕዝብ ብዛትና በኗሪዎቹ ብዛት የተጨናነቀው ዓለም ፍላጎት ከፍ እያለ መሄዱ ነው። ሳይንስ ኒውስ ሲናገር “ብዙውን ጊዜ ለሕይወት አስጊ የሆኑ ቫይረሶች የሚነሡት ሰዎች ከዚያ በፊት ወዳልተዳሰሰ ቦታ ሲዛወሩ ወይም የከተማ የኑሮ ይዞታ ተበላሽቶ አዳዲስ የቫይረስ መጠጊያ የሆኑ ነገሮችን በሚጋብዝበት ጊዜ እንደሆነ ታሪክ ያሳያል” ይላል። ሰዎች በፊት ወዳልተኖረባቸው በቫይረስ የተለከፉ ቦታዎች ሄደው መኖር ሲጀምሩ ብዙውን ጊዜ አዳዲስ የቫይረስ ወረርሽኝ በሽታዎች ይከሰታሉ። የመሬት የአየር ጠባይ በመለዋወጡ ምክንያት የነፍሳት መኖሪያ ስፍራ ሲሰፋም ይኸው ዓይነት ነገር ይደርሳል። “በተጨማሪ” ይላል መጽሔቱ “የአንዱን ሰው ደም ለሌላው መስጠትና የአንዱን አካል ለሌላው ሰው መትከል የመሳሰሉት ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች ቫይረሶች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉበት አዳዲስ መንገዶች አመቻችተዋል። በዓለም ላይ ከሚፈነጩት ሀብታሞችና ታዋቂ ሰዎች ጀምሮ መርፌ እስከሚዋዋሱት የዕፅ ሱሰኞች ድረስ የሚታየው ልዩ ልዩ ማህበራዊና የጠባይ ለውጥም የቫይረስ በሽታዎች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉበትን አዳዲስ መንገዶች አመቻችተዋል።”
ጽሑፉ በመቀጠል “በቅርብ ጊዜ ራቅ ባሉ ሥፍራዎች የታዩት አነስተኛ የቫይረስ ግጭቶች ለወደፊቱ በጣም በስፋት የቫይረስ ወረራ የሚደርስ ለመሆኑ ጥላነት ያላቸው ሕያው ምሳሌዎች ናቸው” ይላል። ምሳሌዎቹም የሚከተሉት ናቸው፦ ቀደም ብሎ የማይታወቅ የነበረው ማድበርግ ቫይረስ የተባለው በ1960ዎቹ ዓመታት በምዕራብ ጀርመን ብዙ ሳይንቲስቶችን ያጠቃው የሞቃት አገር ቫይረስ፤ በ1977 በግብፅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለክፎ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው የስምጥ ሸለቆ ትኩሳት የሚያስከትል ቫይረስ፤ በ1976 በዛየርና በሱዳን ከሺህ የሚበዙ ሰዎችን ለክፎ 500 ሰዎችን የገደለው የሞቃት አገር ኢቦላ ቫይረስ፤ ከሞቱት 500 ሰዎች መሃል የሚበዙት ሕሙማኑን የሚያክሙ ሐኪሞችና ነርሶች ነበሩ።
አውዳሚ የቫይረስ ጥቃቶች ከመከሰታቸው በፊት ሊተነብዩ አይችሉም። “ለምሳሌ ያህል በ1918 ለየት ያለ የመግደል ችሎታ ያለው ያልተለመደ ዲቃላ ኢንፍሉዌንዛ በምድር ዙሪያ ተዛምቶ ወደ 20 ሚሊዮን የሚገመቱ ሕዝቦችን ገደለ” ይላል። ቀጥሎም ሳይንስ ኒውስ እንዲህ አለ፦ “በጣም በቅርብ ጊዜ ደግሞ በአንድ ወቅት ምናልባት በአፍሪካ ዝንጀሮዎች ውስጥ ይኖር የነበረ ቫይረስ አለምንም የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በሰዎች ላይ ብቅ ብሎ ዓለምን በሙሉ ያጣድፈዋል። በዓለም የጤና ድርጅት በተገመተው መሠረት አሁን በ149 አገሮች ኤድስ ከ5 እስከ 10 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎችን ይዟቸዋል። ምንም እንኳ ይህ በቅርብ የመጣ መቅሰፍት ሙሉ ትኩረት የተደረገበት ቢሆንም ብዙ የቫይረስ ተመራማሪዎች ወደፊት ብዙ አስፈሪ ነገሮች ይጠብቁናል ብለው ይሰጋሉ።”
ቸነፈሮች አስጨናቂ የመሆናቸውን ያህል ጦርነት፣ ረሃብና ታላላቅ የመሬት መናወጦች ከመሳሰሉት ሁኔታዎች ጋር የኢየሱስን በመንግሥት ክብር መገኘት ከሚያመለክቱት የምልክቶቹ ቅንብር አንዱ ክፍል ናቸው። (ማርቆስ 13:8፤ ሉቃስ 21:10, 11) ሉቃስ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቧልና፣ አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሱ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ጨምሮ ስለሚነግረን ምልክቶቹ ለመደሰት ምክንያት ይሆኑናል።—ሉቃስ 21:28