ራስን የመግዛት ፍሬ መኮትኮት
“የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት ነው። እነዚህንም የሚከለክል ሕግ የለም።”—ገላትያ 5:22, 23
1. ራስን በመግዛት ረገድ ከሁሉ የበለጠ ምሳሌ የሚሆኑን እነማን ናቸው? ይህስ በየትኞቹ ቅዱስ ጽሑፎች ላይ ተገልጿል?
ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ራስን በመግዛት ረገድ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ምሳሌ ትተውልናል። ይሖዋ የሰው ልጅ በዔድን ገነት ውስጥ ትእዛዙን ከጣሰበት ጊዜ ጀምሮ ራስ የመግዛትን ባሕርይ ሲያሳይ ቆይቷል። (ከኢሳይያስ 42:14 ጋር አወዳድር) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑ ዘጠኝ ቦታዎች ላይ ተገልጿል። (ዘጸአት 34:6) “ለቁጣ የዘገዩ” ለመሆን ደግሞ ራስን መግዛት ያስፈልጋል። የአምላክ ልጅም ‘ሲሰድቡት መልሶ ስላልተሳደበ’ በእርግጥ ከፍተኛ የሆነ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። (1 ጴጥሮስ 2:23) ኢየሱስ አባቱን “ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት” ለእርዳታ እንዲልክለት መለመን ይችል ነበር።—ማቴዎስ 26:53
2. ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች የታየ ምን ጥሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ የራስ መግዛት ምሳሌዎች አሉ?
2 ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች የታዩ አንዳንድ የራስን መግዛት ምሳሌዎችም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጸዋል። ለምሳሌ የጥንት አበው የነበረው የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በአንድ ሊታወስ በሚገባው አጋጣሚ ይህን ጠባይ አሳይቷል። ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ልታባብለው ስትሞክር ከፍተኛ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። (ዘፍጥረት 39:7-9) አራቱ ዕብራውያን የሙሴ ሕግ በጣለባቸው እገዳ ምክንያት የባቢሎናዊውን ንጉሥ ጣፋጭ ምግብ ለመብላት እምቢ በማለት ከፍተኛ የሆነ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይተዋል።—ዳንኤል 1:8-17
3. በመልካም ጠባያቸው ሊጠቀሱ የሚገባቸው እነማን ናቸው? ይህስ በምን ማስረጃ ታይቷል?
3 የይሖዋ ምስክሮችም በአጠቃላይ ራስን በመግዛት ረገድ ለዘመናችን ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑን ይችላሉ። አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “በዓለም ካሉት ቡድኖች ሁሉ የበለጠ ጥሩ ምግባር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው” በማለት የሰጣቸው ምስጋና የሚገባቸው ነው። አንድ የፊሊፒንስ ዩኒቨርሲቲ መምህር “ምሥክሮቹ ከቅዱሳን ጽሑፎች የሚማሩትን ነገር በሃይማኖታቸው ተግባራዊ ያደርጉታል” በማለት ተናግሯል። አንድ የፖላንድ ዘጋቢ ምሥክሮቹ በዋርሶ ያደረጉትን ስብሰባ በሚመለከት “55,000 ሰዎች ለሦስት ቀን አንዲትም ሲጋራ አላጤሱም! . . . ይህ በነዚህ ሰዎች ላይ የታየው ከሰው በላይ የሆነ ሥነ ሥርዓታማነት በአድናቆትና በአክብሮት እንድመሰጥ አድርጎኛል” በማለት ጽፏል።
አምላክን መፍራትና ክፉ የሆነውን ነገር መጥላት
4. ራስ የመግዛትን ባሕርይ ለማሳየት ከሁሉ በላይ ከሆኑት እርዳታዎች አንዱ ምንድን ነው?
4 ራስን የመግዛትን ባሕርይ ለመኰትኰት ከፍተኛ እገዛ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ፈሪሐ አምላክ ነው። ፈሪሐ አምላክ ሲባል አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችንን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሐት ማሳየት ማለት ነው። አክብሮት የተሞላበት ፈሪሐ አምላክ ማሳየት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይህ ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ከመጠቀሱ ልንረዳ እንችላለን። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ሲል አምላክ “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ። አንዳችም አታድርግበት አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄያለሁ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 22:12) ስሜታዊ ጭንቀቱ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ስለማያጠራጥር የሚወደውን ልጁን ለማረድ ቢላዋውን እስከማንሳት ድረስ የአምላክን ትእዛዝ ለመፈጸም መዘጋጀቱ ከፍተኛ የሆነ ራስን የመግዛት ባሕርይ ሳይጠይቅበት አልቀረም። አዎን ፈሪሐ አምላክ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናሳይ ይረዳናል።
5. መጥፎ የሆነውን መጥላት ራስ የመግዛትን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?
5 ይሖዋን ከመፍራት ጋር በቅርብ የሚዛመደው ባሕርይ ክፉ የሆነውን ነገር መጥላት ነው። በምሳሌ 8:13 ላይ “ይሖዋን መፍራት ማለት ክፋትን መጥላት ነው” የሚል ቃል እናነባለን። ክፉ የሆነውን ነገር መጥላታችንም በምላሹ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናሳይ ይረዳናል። ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ክፋትን እንድንጠላና እንዲያውም እንድንጸየፈው ይነግሩናል። (መዝሙር 97:10፤ አሞጽ 5:14, 15፤ ሮሜ 12:9) ክፉ የሆነው ነገር ብዙውን ጊዜ በጣም የሚያስደስት፣ የሚያጓጓ፣ የሚያስጐመጅ በመሆኑ እንዲህ ካለው ድርጊት ለመጠበቅ የምንችለው ድርጊቱን በመጥላት ብቻ ነው። ይህ ዓይነቱ ክፋትን የመጥላት ባሕርይ ራሳችንን ለመግዛት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ስለሚያጠናክርልን ከመጥፎ ድርጊቶች ሊጠብቀን ይችላል።
ራስን መግዛት የጥበብ መንገድ ነው
6. ራሳችንን በመግዛት የስስት ዝንባሌያችንን መግታት የጥበብ መንገድ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ራሳችንን እንድንገዛ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ይህን ጠባይ ማሳየት ትልቅ የጥበብ መንገድ መሆኑን መገንዘብ ነው። ይሖዋ ራሳችንን እንድንገዛ የሚጠይቀን ለራሳችን ጥቅም ሲል ነው። (ከኢሳይያስ 48:17, 18 ጋር አወዳድሩ) የአምላክ ቃል ራሳችንን በመግዛት የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎቻችንን መግታት ምን ያህል ከፍተኛ ጥበብ እንደሆነ የሚገልጽ ብዙ ምክር ይዞልናል። የአምላክን የማይለዋወጡ ሕጐች መጣስ ከሚያስከትለው ቅጣት በቀላሉ ማምለጥ አንችልም። ቃሉ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳልና፤ በመንፈስ ግን የሚዘራ ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል” በማለት ይነግረናል። (ገላትያ 6:7, 8) በዚህ መንገድ ግልጽ ምሳሌ የሚሆነን የመብልና የመጠጥ ጉዳይ ነው። ሰዎች ያለመጠን በመብላታቸውና በመጠጣታቸው ብዙ ሕመም ይመጣባቸዋል። በዚህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት ስሜት መሸነፍ አንድ ሰው ለራሱ ያለውን አክብሮት እንዲያጣ ያደርገዋል። ከዚህም በላይ አንድ ሰው ለራስ ወዳድነት ስሜት መሸነፉ ከሌሎች ጋር ያለውን ዝምድና ሳያበላሽበት አይቀርም። ከሁሉ የከፋው ደግሞ ራስን የመግዛት ባሕርይ መጓደሉ ከሰማያዊ አባታችን ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል።
7. የምሳሌ መጽሐፍ ዋና መልእክት ምንድን ነው? ይህስ በየትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ተገልጿል?
7 ስለዚህ ራስ ወዳድነት ተመልሶ ራስን የሚጐዳ ነገር መሆኑን ለራሳችን ደጋግመን መንገር ይገባናል። ራስን ስለ መገሰጽ ጠበቅ አድርጎ የሚገልጸው የምሳሌ መጽሐፍ ዋነኛ መልእክት ራስ ወዳድነት ምንም ጥቅም እንደሌለውና ራስን የመግዛትን ባሕርይ ማሳየት የጥበብ መንገድ መሆኑን አጉልቶ ይገልጻል። (ምሳሌ 14:29፤ 16:32) ራስን መገሰጽ መጥፎ የሆነውን ነገር ከማስወገድ የበለጠ ነገርን እንደሚያጠቃልል መታወስ አለበት። ራስን የመገሰጽ ወይም ራስን የመግዛት ባሕርይ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግም አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ ከኃጢአተኛው ዝንባሌያችን ጋር ስለሚጋጭ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
8. ራስን መግዛት የማሳየትን ጥበብ የሚያጐላው ምን ተሞክሮ ነው?
8 ራስ መግዛትን ማሳየት ጥበብ መሆኑን የሚያሳይ የአንድ የይሖዋ ምስክር ምሳሌ እንውሰድ። ባንክ ቤት ተሰልፎ ተራውን እየጠበቀ ሳለ አንድ ሰው ገፍቶት ከፊቱ ቆመ። ምስክሩ ጥቂት ቢናደድም ራሱን ገዝቶ ዝም አለ። በዚያው ዕለት ለመንግሥት አዳራሽ መሥሪያ በሚያገለግል ፕላን ላይ ለማስፈረም አንድን መሐንዲስ ማነጋገር ነበረበት። ይህ መሐንዲስ ማን ሆነ? ባንክ ቤት ሠልፉ ላይ ገፍትሮ ከፊቱ የገባው ሰው ራሱ ሆኖ ተገኘ! መሐንዲሱ ለወንድም የወዳጅነት አቀባበል ከማሳየቱም በላይ ከተለመደው ክፍያ ከአንድ አሥረኛው ያነሰ ብቻ አስከፈለው። ያን ዕለት ጧት ጠብ ባለማንሣት የራስ መግዛትን ባሕርይ በማሳየቱ ይህ ምስክር በጣም ተደሰተ።
9. በአገልግሎት ላይ እንዳለን ሰዎች ሲሰድቡን መከተል የሚገባን የጥበብ መንገድ ምንድን ነው?
9 የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ከቤት ወደቤት ስንሄድ ወይም በመንገድ ላይ ቆመን ለመልእክታችን የመንገድ ተላላፊዎችን ትኩረት ለመሳብ በምንሞክርበት ጊዜ በተደጋጋሚ ስድብ ያጋጥመናል። በዚህ ጊዜ መከተል የሚገባን የጥበብ መንገድ ምንድን ነው? በምሳሌ 15:1 ላይ “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች” የሚል ጥበብ የሞላበት ቃል እናገኛለን። በሌላ አባባል ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል ማለት ነው። ይህ ቃል እውነት መሆኑን የተገነዘቡት የይሖዋ ምስክሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ናቸው። ራስን መግዛት ፈዋሽነት ያለው ባሕርይ መሆኑ በሕክምና መስክም የበለጠ ግንዛቤ አግኝቷል።
ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ይረዳል
10, 11. ፍቅር ራስን የመግዛት ባሕርይ በማሳየት ረገድ እውነተኛ እርዳታ የሆነው ለምንድን?
10 ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ ስለ ፍቅር የሰጠው መግለጫም የፍቅር ኃይል ራስ የመግዛትን ባሕርይ እንድናሳይ እንደሚረዳን ያሳያል። “ፍቅር ይታገሣል።” ታጋሽ ለመሆን ደግሞ ራስን የመግዛት ባሕርይ ያስፈልጋል። “ፍቅር አይቀናም። ፍቅር አይመካም። አይታበይም።” የፍቅር ጠባይ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ለመቆጣጠር ማንኛውንም የቅናት፣ የትምክህት፣ ወይም የመታበይ አዝማሚያ እንድንገታ ይረዳናል። ፍቅር እንደ ኢየሱስ ራሳችንን ዝቅ የምናደርግና ትሑቶች እንድንሆን ይገፋፋናል።—ማቴዎስ 11:28-30
11 ጳውሎስ በመቀጠል ፍቅር “የማይገባውን አያደርግም” ብሏል። በማንኛውም ጊዜ በጨዋነት ለመኖር ራስን የመግዛት ባሕርይ ያስፈልጋል። የፍቅር ጠባይ ከስስት “የራሳችንን ጥቅም ብቻ ከመፈለግ” ይቆጥበናል። ፍቅር “አይበሳጭም” (ወይም ለጠብ አይነሣሣም)። ሌሎች በሚናገሩት ወይም በሚያደርጉት ነገር ምክንያት ለጠብ መነሣሣት በጣም ቀላል ነው። ፍቅር ግን ራስን የመግዛትን ባሕርይ እንድናሳይ፣ በኋላ የምንጸጸትበትን ነገር እንዳንናገርና እንዳናደርግ ይረዳናል። ፍቅር “በደልን አይቆጥርም።” የሰው ተፈጥሮ ቂም ወደመያዝ ወይም ወደማኩረፍ ያዘነብላል። ፍቅር ግን እንዲህ ዓይነት ሐሳቦችን ከአእምሮአችን እንድንፍቅ ይረዳናል። ፍቅር “ክፋት በሆነ ነገር አይደሰትም።” (በ1980 ትርጉም) ክፋት በሆነ ነገር፣ ለምሳሌ እንደ ብልግና ሥዕሎች ወይም ስሜት በሚመስጡ የቴሌቪዥን የሬድዮ ፕሮግራሞችና በመሳሰሉት ላለመደሰት ራስን መግዛት ያስፈልጋል። ፍቅር “ሁሉን ይታገሣል።” እንዲሁም “በሁሉ ይጸናል።” ነገሮችን ለመታገሥ፣ ፈታኝ ወይም ከባድ የሆኑ ነገሮችን ለመቻልና ተስፋ እንዳያስቆርጡን ወይም በዓይነት በመመለስ እንድንበቀል ወይም ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንድንል እንዳያደርጉን ራስን መግዛት ያስፈልጋል።
12. ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረጉልን ሁሉ አድናቆታችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
12 ሰማያዊ አባታችንን በእውነት የምንወድ ከሆነና ግሩም ጠባዮቹንና ለእኛ ያደረገልንን ሁሉ የምናደንቅ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ ራስ የመግዛትን ባሕርይ በማሳየት ልናስደስተው እንፈልጋለን። እንደዚሁም ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት የምንወድና ያደረገልንን ሁሉ የምናደንቅ ከሆነ ‘የመከራውን እንጨት ተሸክመን ያለማቋረጥ እንድንከተለው’ የሰጠንን ትእዛዝ እንቀበላለን። (ማርቆስ 8:34) ይህም ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናሳይ ይጠይቅብናል። ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ያለን ፍቅርም በራስ ወዳድነት አካሄድ በመመራት እነሱን ከመጉዳት ይቆጥበናል።
እምነትና ትሕትና ይረዳሉ
13. እምነት ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናሳይ ሊረዳን የሚችለው ለምንድን ነው?
13 ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማሳየት ከፍተኛ እርዳታ የሚሰጠን ሌላው ነገር በአምላክና በተስፋዎቹ ማመን ነው። እምነት በይሖዋ እንድንታመንና እሱ ራሱ በወሰነው ጊዜ ነገሮችን እስኪያስተካክል ድረስ እንድንጠባበቅ ያስችለናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 12:19 ላይ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህንኑ ጉዳይ አመልክቷል፦ “ተወዳጆች ሆይ ራሳችሁ አትበቀሉ።. . . ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና” በዚህ ረገድ ትሕትናም ሊረዳን ይችላል። ትሑቶች ከሆንን ሰዎች እኛን ለመጉዳት ብለው አንድ ነገር ያደረጉብን መስሎ ሲታየንም ሆነ በእውነት ሲበድሉን ለመቀየም አንቸኩልም። በችኰላ በኃይላችን በመጠቀም ተበቃዮች ከመሆን ይልቅ ራስ የመግዛትን ባሕርይ በማሳየት ይሖዋን ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንሆናለን።—መዝሙር 37:1, 8
14. የራስ መግዛት ባሕርይ በጣም ያንሳቸው የነበሩ ሰዎችም እንኳ ይህን ባሕርይ ሊማሩ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ተሞክሮ አለ?
14 ራስ የመግዛትን ባሕርይ ለማሳየት ራሳችንን ለማሠልጠን የምንችል መሆኑን ከአንድ ኃይለኛና ጠበኛ ከነበረ ሰው ተሞክሮ መገንዘብ እንችላለን። በጣም ግልፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ እሱና አባቱ ሁከት በማስነሣታቸው ምክንያት ፖሊሶች ተጠርተው መጡ። ፖሊሶቹ ተረዳድተው እስኪያሸንፉት ድረስ ሦስቱን ፖሊሶች መትቶ ጣላቸው። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘና የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ከሆኑት አንዱ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት ተማረ። (ገላትያ 5:22, 23) ዛሬ ከ30 ዓመታት በኋላ ይህ ሰው አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገለ ነው።
ራስን መግዛት በቤተሰብ ክልል ውስጥ
15, 16. (ሀ) አንድ ባል ራስ የመግዛትን ባሕርይ እንዲያሳይ ምን ነገር ሊረዳው ይችላል? (ለ) ራስን መግዛት የሚያስፈልገው በተለይ በምን ሁኔታ ነው? ይህስ በምን ተሞክሮ ታይቷል? (ሐ) አንዲት ሚስትም ራስዋን መግዛት የሚያስፈልጋት ለምንድን ነው?
15 ራስን መግዛት በቤተሰብ ክልል ውስጥም አስፈላጊ ነው። ባል ሚስቱን እንደራሱ አድርጎ እንዲወድ ሐሳቡን፣ ቃሉንና ድርጊቱን መቆጣጠር ያስፈልገዋል። (ኤፌሶን 5:28, 29) አዎ ባሎች በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ ያሉትን “ባሎች ሆይ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ” የሚሉትን ቃላት ለመፈጸም ራሳቸውን መግዛት ያስፈልጋቸዋል። በተለይ ደግሞ ሚስቲቱ የማታምን በምትሆንበት ጊዜ አማኝ የሆነው ባል ራሱን መግዛት ይኖርበታል።
16 ለምሳሌ ያህል ግልፍተኛ የሆነች የማታምን ሚስት የነበረችው አንድ ሽማግሌ ነበር። ሆኖም የራስ መግዛትን ባሕርይ ያሳይ ነበር። ይህም በጣም ስለጠቀመው ሐኪሙ “አንድም በተፈጥሮህ በጣም በጣም ትዕግሥተኛ ሰው ነህ ወይም ኃይለኛ ሃይማኖት አለህ” ሊለው ችሏል። በእርግጥም ኃይለኛ ሃይማኖት አለን። ምክንያቱም “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።” ራሳችንንም እንድንገዛ ያስችለናል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7) በተጨማሪም ሚስትም በበኩሏ ለባልዋ ታዛዥ እንድትሆን በተለይም ባሏ የማያምን ከሆነ ራስዋን መግዛት ያስፈልጋታል።—1 ጴጥሮስ 3:1-4
17. ራስን የመግዛት ባሕርይ ለወላጅና ለልጅ ዝምድና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ራስን የመግዛት ባሕርይ በወላጅና በልጅ ዝምድና ረገድም አስፈላጊ ነው። ወላጆች ራሳቸውን የሚገዙ ልጆች እንዲኖሩአቸው ከፈለጉ እነርሱ ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን አለባቸው። ልጆችም የተለያየ ዓይነት ተግሣጽ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ተግሣጹ ሁልጊዜ በእርጋታና በፍቅር መሰጠት ይኖርበታል። ይህም እውነተኛ ራስን የመግዛት ባሕርይ የሚጠይቅ ነው። (ኤፌሶን 6:4፤ ቆላስይስ 3:21) ልጆችም ወላጆቻቸውን በእርግጥ እንደሚወዱ የሚያሳዩት በመታዘዝ ሲሆን ለመታዘዝ ደግሞ ራስን መግዛት ያስፈልጋል።—ኤፌሶን 6:1-3፤ ከ1 ዮሐንስ 5:3 ጋር አወዳድሩ።
አምላክ በሚሰጠው እርዳታ መጠቀም
18-20. ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማሳየት የሚረዱንን ጠባዮች ለመኰትኰት ልንጠቀምባቸው የሚገቡን ምን ሦስት መንፈሳዊ ዝግጅቶች አሉ?
18 በፈሪሐ አምላክ፣ ራስ ወዳድነት በሌለበት ፍቅር፣ በእምነት፣ መጥፎ የሆነውን በመጥላትና ራስን በመግዛት ረገድ ለማደግ ይሖዋ አምላክ ባቀረበው እርዳታ በሙሉ መጠቀም ያስፈልገናል። ራሳችንን እንድንገዛ ሊረዱን የሚችሉ ሦስት መንፈሳዊ ዝግጅቶችን እንመልከት። ከሁሉ አስቀድሞ ውድ የሆነው የጸሎት መብት አለ። ለመጸለይ ጊዜ እስክናጣ ድረስ ሥራ እንዲበዛብን ፈጽሞ አንፈልግም። አዎ “ሳናቋርጥ ለመጸለይ”ና “በጸሎት ለመጽናት” መፈለግ ይኖርብናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ሮሜ 12:12) ራስን የመግዛትን ባሕርይ የመኰትኰቱን ጉዳይ የጸሎታችን ርዕስ እናድርገው። ነገር ግን ራስን የመግዛትን ባሕርይ ሳናሳይ ስንቀር እንጸጸትና ሰማያዊ አባታችንን ምሕረት እንጠይቀው።
19 የራስ መግዛትን ባሕርይ ለማሳየት እርዳታ የምናገኝበት ሁለተኛው ዘርፍ የአምላክን ቃልና ቅዱሳን ጽሑፎችን እንድንረዳና በሥራ እንድናውላቸው የሚያስችለንን ጽሑፍ በመመገብ የሚገኘውን እርዳታ ማግኘት ነው። የቅዱስ አገልግሎታችን አንዱ ክፍል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የመመገብ አስፈላጊነት ችላ ለማለት በጣም ቀላል ነው! የራስ መግዛትን ባሕርይ ማሳየትና ከመጽሐፍ ቅዱስና “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ከሚቀርበው ጽሑፍ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ የሚነበብ ጽሑፍ የሌለ መሆኑን ለራሳችን ደጋግመን ማሳሰብና ለዚህም ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት አለብን። (ማቴዎስ 24:45-47) ኑሮ ይህ እና ያ ሳይሆን ይህ ወይም ያ ነው የሚል ጥሩ አባባል አለ። በእውነት መንፈሳውያን የሆንን ወንዶችና ሴቶች ነንን? መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የምናውቅ ከሆነ ቴሌቪዥን ለማጥፋት የሚያስፈልገውን ራስ የመግዛት ባሕርይ በማሳየት ለስብሰባዎቻችን እንዘጋጃለን ወይም አሁን የደረሰንን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እናነባለን።
20 ሦስተኛው ደግሞ ለጉባኤ ስብሰባዎቻችንና ለታላላቅ ስብሰባዎቻችን ተገቢ የሆነ ቦታ የመስጠት ጉዳይ ነው። እነዚህ ስብሰባዎች በሙሉ በጣም እንደሚያስፈልጉን ይሰማናልን? በስብሰባዎቹ ለመሳተፍ ተዘጋጅተን በመምጣት አጋጣሚው ሲሰጠን እንሳተፋለንን? በማንኛውም ሁኔታ ራሳችንን ለመግዛት የምናደርገው ውሳኔ ጥንካሬ ለስብሰባዎቻችን በምንሰጠው አስፈላጊነት ላይ የተመካ ነው።
21. የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይ በመኮትኮታችን የምናገኛቸው አንዳንድ ሽልማቶች ምንድን ናቸው?
21 በማንኛውም ጊዜ ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማሳየት ስንጥር ምን ሽልማት ለማግኘት ልንጠባበቅ እንችላለን? መጀመሪያ ነገር የራስ ወዳድነትን መራራ ፍሬ አናጭድም። የራሳችንን ክብርና ንጹሕ ሕሊና ጠብቀን እንኖራለን። ራሳችንን ከብዙ ችግር ጠብቀን በሕይወት ጐዳና ላይ ጸንተን እንኖራለን። በተጨማሪም በተቻለን መጠን ለሌሎች መልካም ለማድረግ እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ምሳሌ 27:11ን ለመፈጸም እንችላለን፦ “ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን ልቤንም ደስ አሰኘው። ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።” አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችን የሆነውን የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት ደግሞ ልናገኘው ከምንችለው ከማንኛውም ሽልማት ሁሉ የበለጠ ነው!
ታስታውሳላችሁን?
◻ ፈሪሐ አምላክ ራስ የመግዛትን ባሕርይ ለማሳየት የሚረዳን እንዴት ነው?
◻ ፍቅር ራስ የመግዛትን ባሕርይ እንድናሳይ የሚረዳን ለምንድን ነው?
◻ ራስን መግዛት ለቤተሰብ ዝምድና የሚረዳው እንዴት ነው?
◻ ራስ የመግዛትን ባሕርይ እንድንኰተኩት በምን ዝግጅቶች መጠቀም ይገባናል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሴፍ በተፈተነ ጊዜ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል 17]
ልጆችን በእርጋታና በፍቅር ለመገሠጽ ራስን የመግዛት ባሕርይ ያስፈልጋል