ላንተ የሚሆን አገልግሎት ነውን?
ይሖዋ ለጋስነቱን ምድርን ለሕይወት አስደሳች እንድትሆን አድርጎ በማዘጋጀት አሳይቷል። በለጋስነቱም እነዚህን ዝግጅቶቹን አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላም እንኳ ሳይቀር እንዲቀጥሉ አድርጓል። ከዚህም ሌላ የሚያምኑ የሰው ዘሮችን ከኃጢአት መከራ ለማዳን ብሎ ልጁን በመላክ የላቀ ፍቅሩን ገልጿል።—ማቴዎስ 5:45፤ ዮሐንስ 3:16
ለእንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ምላሽ የምንሰጠው እንዴት ነው? ኢየሱስ ይሖዋ አምላካችንን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ ሐሳባችንና በሙሉ ኃይላችን መውደድ እንዳለብን ተናግሯል። ይህም አምልኮታችንንና ታማኝነታችንን ልንሰጠው እንደሚገባና ከእርሱ ፈቃድ ጋር ተስማምተን መኖር እንዳለብን ያመለክታል።—ማርቆስ 12:30፤ 1 ጴጥሮስ 4:2
ነገር ግን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? ልናቀርብለት የምንችለው አገልግሎት፣ ማለትም ልንካፈልበት የሚገባን አገልግሎት አለን?
የአገልጋዮች አስፈላጊነት
አብያተ ክርስቲያናት አምላክ እንዴት ሊመለክና ሊገለገል እንደሚገባ እንዳያውቁ ሰዎችን አደናግረዋቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ብቻ እውነተኛ ሃይማኖት እንዳለና “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት፣ የሁሉም አባት የሚሆን አንድ አምላክ” እንዳለ ይገልጻል። ኢየሱስም “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት ይሰግዱለታል” ብሏል። ስለዚህ እውነተኛ አምላኪዎች “ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን . . .” ተብለው ተመክረዋል።—ኤፌሶን 4:3-6፤ ዮሐንስ 4:23፤ 1 ቆሮንቶስ 1:10
ስለ እውነተኛው ሃይማኖት ምንነት ግራ መጋባት የተጀመረው ሰይጣን በዔድን ገነት በአምላክ አገዛዝ ላይ ጥያቄ በማስነሣት የይሖዋን የበላይ ገዥነት በተገዳደረ ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-6, 13) ከዚያም ሰይጣን ተቃውሞውን “የጽድቅ አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን በሚለውጡ” አታላይ የሃይማኖት አስተማሪዎች አማካኝነት በተሰራጩ አስመሳይ ትምህርቶች አማካኝነት ቀጥሏል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጆች ሆይ፣ መንፈስን ሁሉ አትመኑ . . . ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 11:14, 15፤ 1 ዮሐንስ 4:1
ይሁን እንጂ አምላክ ለዚህ የአገዛዝ ክርክር እልባት ለማድረግ እርምጃ መውሰዱ ያስደስተናል። የሰው ልጆችን እንዲዋጅ ልጁን ከመላኩም በላይ ለኢየሱስ ሰይጣንንና የሰይጣንን ነቢያት ወይም አገልጋዮች ለማጥፋት የሚያስችል ሥልጣን ሰጥቶ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ አድርጐታል። ይህም ለታዛዥ ሰዎች ዘላለማዊ በረከት ሲባል የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ የሚፈጸም መሆኑን ያረጋግጣል።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ዕብራውያን 2:9
ሰይጣን እነዚህን እውነቶች እንዳይታወቁና ለመረዳት አስቸጋሪ እንዲሆኑ አደብዝዟቸዋል። ለእውነት በመመስከርና የሰይጣንን ውሸት በማጋለጥ የአምላክ አገልጋዮች መሆን የሚያስፈልገን በዚህ ምክንያት ነው። ይሖዋ እንድናገለግለው አያስገድደንም። እንደ ኢየሱስ ለይሖዋና ላደረገልን ነገር ባለን አድናቆት ተገፋፍተን በፈቃደኝነት ራሳችንን እንድናቀርብ ያስፈልጋል።—መዝሙር 110:3፤ ዕብራውያን 12:1-3
የክርስቲያን አገልግሎት
ኢየሱስ “እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር።” (ሉቃስ 8:1) ደቀ መዛሙርቱንም እንደሱ አገልጋዮች እንዲሆኑ በማሠልጠን እንዲሰብኩ ልኳቸዋል። (ማቴዎስ 10:1-14, 27) በኋላም አገልግሎታቸውን እስከ ምድር ዳርቻ እንዲቀጥሉበት ልኳቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8
ይህ ተልእኮ የተጣለው በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ነው። የአምላክ መንፈስም እንዲሰብኩ ይገፋፋቸዋል። በ33 እዘአ በጴንጤቆስጤ ዕለት እንደሆነው ሁሉ የምሥራቹን የሚቀበሉ ሁሉ እምነታቸውን ለሕዝብ የማሳወቅን ኃላፊነት ይቀበላሉ።—ሥራ 2:1-4, 16-21፤ ሮሜ 10:9, 13-15
ይሁንና ብዙ ሰዎች አገልጋዮች ሊሆኑ የሚችሉ መስሎ አይታያቸውም። ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ የሆነው ፒተር እንዲህ ብሏል፦ “የጀርመን ሰዎች ስለ ሃይማኖት ለሰዎች መናገር ክብራቸውን ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። “ይህ የቀሳውስት ሥራ ነው” ይላሉ። ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ቶኒ እንዳለው በእንግሊዝ አገር ያሉ ሰዎች “የምትናገረው ነገር ጥሩ ነው። የይሖዋ ምስክሮችም ጥሩ ሰዎች ይመስሉኛል። ነገር ግን ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ልሰብክ አልችልም” ይላሉ። ቤን ለትንሽ ጊዜ ከአንድ ናይጄሪያዊ ሰው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ሰውየውም “ከቤት ወደ ቤት ስሰብክ በሰው መታየት በፍጹም አልችልም። ግን ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑትን ለመርዳት ለጉባኤያችሁ ገንዘብ ልሰጥ እችላለሁ” አለው። አዎን ብዙ ሰዎች ለክርስቲያን አገልግሎት የሚያስፈልገው ጠንካራ እምነት ይጐድላቸዋል።
ይሁን እንጂ ሕዝባዊ ስብከት ጾታና ዕድሜ የማይለይ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ ኃላፊነት ነው። ስብከት ግምባር ቀደም ለሆኑት ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ብቻ የተተወ ሥራ ሳይሆን ሁሉም ክርስቲያኖች መሥራት ያለባቸው ሥራ ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ እናቅርብለት። . . . . ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ” በማለት ተመክረዋል።—ዕብራውያን 13:15, 17
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ለተለያዩ ዓይነት ሰዎች ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” በሌላ ወቅትም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለማያምኑ ሰዎች መስበክን እንደሚጨምር ገልጿል። ደቀ መዛሙርቱ ለሳምራውያን መስበኩን ትቶ ምግብ እንዲበላ ሲለምኑት “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል።—ማቴዎስ 7:21፤ ዮሐንስ 4:27-38
ያንተስ ቋሚ ሥራ መሆን ይኖርበታልን?
ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሥጋዊ ምግብንና ብልጥግናን ማሳደድ ይመርጣሉ። ኢየሱስ ግን በተራራው ስብከቱ ላይ አድማጮቹን ሥጋዊ ነገሮችን ለማሳደድ ከመጨነቅ እንዲጠነቀቁ መክሯቸዋል። “ነገር ግን በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ . . . አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 6:20, 33
መንግሥቱን አስቀድሞ መፈለግ ማለት ሌሎች ፍላጎቶች ለአገልግሎታችን ጊዜ እንዲያሳጡን አለመፍቀድ ማለት ነው። ይሁን እንጂ መንግሥቱን ማስቀደም ሲባል ሌላውን ነገር ሁሉ መተው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ የሆኑ የቤተሰብ ግዴታዎችን ችላ እንዳንል ያበረታታናል። እነዚህ ግዴታዎቻችን በሌሎች ሰዎች ሁሉ ላይ ያሉ ግዴታዎች ናቸው። እነሱን ችላ ማለት ከክርስትና እምነት ተቃራኒ ነገር ማድረግ ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይሁን እንጂ ሌሎች ኃላፊነቶቻችንን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እያከናወንን በአገልግሎቱም የሚቻለንን ያህል መሥራት ይኖርብናል።
ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል። በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) በዚህ ትንቢት ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች የትንቢቱ ፍጻሜ በእኛ ዘመን መሆኑን ያመለክታሉ። ከ1914 ወዲህ የሚነገረው ምሥራች መንግሥቲቱ ለይሖዋ የበላይ ገዥነት መረጋገጥና ሰይጣንንና የሱን ዓለም ለማጥፋት እርምጃ እንድትወስድ ሥልጣን የተሰጣት መሆኑን የሚገልጽ ነው። (ራእይ 11:15-18) ይህ ነገር ምን ትርጉም እንደሚኖረው በጥሞና ማሰብ ይኖርብናል። ፍጻሜው ይመጣል፤ ከዚያ በፊት ግን እኛ የስብከቱን ሥራ ማከናወን አለብን። የሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ወድቋል። ብዙዎች እንዲድኑ ልንረዳ እንችላለን።
ለተሟላ አገልግሎት ራሳችሁን ብቁ አድርጉ
ብዙዎቹ የይሖዋ ምስክሮች ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች በማካፈል በየወሩ አሥር ወይም ከዚያ በላይ ሰዓቶች ያሳልፋሉ። በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በረዳት አቅኚነት በመካፈል ለስብከቱ ሥራ በየቀኑ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሰዓቶች ያሳልፋሉ። ሌሎችም በዘወትር ወይም በልዩ አቅኚነት ያለማቋረጥ ያገለግላሉ። የዚህን ሥራ አጣዳፊነት ይገነዘባሉ። ስለዚህ በኀዘን የተሞላ ዓለም ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት ስብከቱ እንዲከናወን የተቻላቸውን ያህል የተሟላ ድርሻ ለማበርከት ይፈልጋሉ።
አንተስ የይሖዋ ንቁ ምስክር ነህን? እንግዲያውስ በአገልግሎቱ የተሟላ ድርሻ እንዲኖርህ ተጣጣር። በአገልግሎቱ የበለጠ ሥራ ለማከናወን በመጣር በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ያለህን ችሎታ አሻሽል። አቅኚ ለመሆን በሚያስችልህ ሁኔታ ላይ ካለህ አቅኚ ሁን። ሁኔታዎችህ አቅኚ እንድትሆን የማይፈቅዱልህ ከሆነ አቅኚዎች መሆን የሚችሉ ሌሎች ለዚህ አገልግሎት እንዲጣጣሩ አበረታታቸው።
ሕይወትህን የወሰንክ የይሖዋ ምስክር ካልሆንክ በዚህ አገልግሎት ልካፈል አልችልም አትበል። አንድ ፒተር የሚባል መካኒካል መሐንዲስ (በዚህ ርዕሰ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ከተጠቀሰው ፒተር የተለየ ነው) ሚስቱ የምሥራቹን ከሌሎች ጋር መካፈሏን በጥብቅ ይቃወም ነበር። “ሚስቴ ከቤት ወደ ቤት እየሄደች እንድትሰብክ እንዴት እፈቅድላታለሁ?” ይል ነበር። በአምላክ ቃል እውነት ላይ ያላትን ጽኑ እምነት ለዓመታት ከተመለከተ በኋላ ግን እሱም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰነ። አሁን እሱም እንደ ሚስቱ ሕይወቱን የሰጠና የተጠመቀ የምሥራቹ አገልጋይ ሆኖአል።
ስለዚህ ይሖዋን ከማገልገሉ መብት ራስህን አታግድ። መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠናና ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር በጉባኤዎቻቸው እንድትጐዳኝ እናበረታታሃለን። ይህም ከአምላክ ጽድቅ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወትህን እንድታስተካክልና በዓላማዎቹ ላይ ጽኑ እምነት እንድትገነባ ይረዳሃል። በዚህ ረገድ መሻሻል ካደረግህ የአምላክ አገልጋይ ለመሆንም ብቁ ትሆናለህ። ከዚያም “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን የኢየሱስን ትእዛዝ በመፈጸሙ ሥራ ለመካፈል ባለመብት ትሆናለህ።—ማቴዎስ 28:19, 20
አዎን፣ አንተ የምትካፈልበት አገልግሎት አለ። ይህን ማድረግም ከምን ጊዜውም የበለጠ አጣዳፊ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የእርሷን እንክብካቤ የሚፈልግ ቤተሰብ ያላት አንዲት ነርስ እንዲህ ትላለች፦ “ወደምሠራበት ሆስፒታል ለመድረስ በየቀኑ ከአንድ ሰዓት የሚበልጥ ጊዜ በጉዞ አሳልፋለሁ። በዚህም ምክንያት ረዳት አቅኚ ለመሆን አልችልም ብዬ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ ሥራዬን በጥንቃቄ አደራጀሁና ማለዳ ከመሄዴ በፊት፣ በዕረፍት ጊዜና ሥራ በማይኖረኝ ቀናት በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ወሰንኩ። በወሩ መጨረሻ ላይ 117 ሰዓት በስብከቱ ሥራ እንዳሳለፍኩ ሪፖርት ሳደርግ የተሰማኝን ደስታ ልትገምቱ ትችላላችሁ። 263 መጽሔቶች ላበረክት 22 የመጽሔት ኰንትራት አግኝቻለሁ። በተጨማሪም ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ችያለሁ።”
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሚካኤል ሰባት ወጣት ልጆች ሲኖሩት በአንድ የናይጄሪያ ኮሌጅ ውስጥ በኃላፊነት ሥራ ላይ ተመድቦ ይሠራል። በተጨማሪም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። የእርሱም አስተሳሰብ በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምስክሮች ካላቸው አስተሳሰብ የተለየ አይደለም፦
“ሁልጊዜም ቢሆን እንደ ዋና ሥራዬ አድርጌ የምመለከተው አገልግሎትን ነው። ‘እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ፣ የሚያሳድግ ግን አምላክ ነበር’ የሚለውን የጳውሎስን ቃል ዘወትር አስታውሳለሁ። እኔና ባለቤቴ ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎታችን ስለ ምሥራቹ ከሰዎች ጋር በመወያየት ‘እንተክላለን።’ ኢየሱስ እንደተናገረው ፍላጐት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰን ከመጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር ‘እናጠጣለን።’ በየሳምንቱ የሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ብዙ ሰዎች እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ቤተሰቦች እውነትን እንዲያውቁ ረድቷል።”