አምላኪዎቹን መሰብሰብ
ሐዋርያው ዮሐንስ “በጌታ ቀን” ስለሚፈጸሙ ዓለምን የሚያናውጡ ሁኔታዎች የሚያሳይ ራእይ ተመልክቶ ነበር። ሰማያዊው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ድል ነሺ ሆኖ ከድል ወደ ድል ለመሄድ” በነጭ ፈረስ ወደተመሰለው የጽድቅ ጦርነት ሲጋልብ ተመልክቶታል። በመጀመሪያው የሚወስደው እርምጃ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነውን ሰይጣንን ከሰማይ አውጥቶ ወደ ምድር አቅራቢያ መወርወር ነው። ሰይጣንም የሰው ልጆችን በምሳሌያዊ ጋላቢዎችና በፈረሶቻቸው ማለትም በቀይ፣ በጥቁርና፣ በሐመር (ግራጫ) ፈረሶች እንደተመሰለው ከዚያ በፊት ታይቶ በማያውቅ መተራረድ፣ ረሀብና በሽታ በማጨራረስ አጸፋውን ይመልሳል። (ራእይ 1:10፤ 6:1-8፤ 12:9-12) እነዚህ ወዮታዎች በመጀመሪያ የፈነዱት በ1914 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየተባባሱ መጥተዋል። በቅርቡም ኢየሱስ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ ከእንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” ብሎ የገለጸው ሁኔታ ሲፈጸም ያከትማሉ።—ማቴዎስ 24:3-8, 21
የይሖዋ አምላኪዎችስ በዚያን ጊዜ እንዴት ይሆናሉ? ራእይ ምዕራፍ 7 ቁጥር 1 እስከ 10 እነዚህ አምላኪዎች እስኪሰበሰቡ ድረስ የጥፋት ነፋሶችን “አጥብቀው ስለያዙ” መላእክታዊ ኃይሎች ይናገራል። ከ1914 ጀምሮ ባለው ጊዜ ቁጥራቸው 144,000 የሆኑት የመጨረሻዎቹ የመንፈሳዊ እሥራኤላውያን ክፍሎች ተሰብስበዋል። ከዚያም “እነሆ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ታይተዋል። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አሁንም እንኳን ቢሆን ቁጥራቸው በሚልዮን የሚቆጠር ሆኗል። እንደ የዋህ በግ ሆኖ በታረደው በኢየሱስ ቤዛዊ ደም በማመናቸው ምክንያት ተቀባይነት አግኝተው በአምላክ ዙፋን ቆመዋል። “በታላቅ ድምጽ እየጮኹ ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው” ይላሉ። እነዚህ ቀናተኛ አምላኪዎች ሌሎች ሰዎችም ከታላቁ መከራ ለመዳን ይሰበሰቡ ዘንድ “ና” ማለታቸውን ቀጥለዋል።—ራእይ 7:14-17፤ 22:17
“በምድር ሁሉ ላይ”
ስለዚህ እነዚህ ታማኝ አምላኪዎች “ድምጻቸው በምድር ሁሉ ላይ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ” ሊባልላቸው ይችላል። (ሮሜ 10:18) ጠንክረው የሠሩት ሥራ አስደናቂ ፍሬ በማስገኘት ተባርኮላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፦
ሜክሲኮ በሦስት ዓመት ውስጥ ብቻ 100,000 የይሖዋ አምላኪዎች ጭማሪ በማግኘት ዛሬ 335,965 ንቁ የይሖዋ አምላኪዎች እንዳሉአት ሪፖርት አድርጋለች! ይህን የሚያህል ከፍተኛ ጭማሪ የተገኘው ለምንድን ነው? የሚቀጥለው ታሪክ ይገልጽልን ይሆናል። አውሬሊዮ የሚባል አንድ ወጣት ሰው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የንዋየ ቅድሳት ግምጃ ቤት ኃላፊ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ወደዚያ መንደር በመጡ ቁጥር ማንም ሰው እንዳይሰማቸው ለማድረግ የቤተክርስቲያን ደውሎችን ይደውልባቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ የካቶሊክ ጀሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ገዛና ማንበብ ጀመረ። ግን የሚያነበውን ሊረዳ አልቻለም። አንድ ቀን አንድ ወዳጁ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በክንዱ ሥር ይዞ አየው። የሱ (የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም)መጽሐፍ ቅዱስ ሐሰተኛ ነው በማለት አሾፈበትና የራሱን “እውነተኛ” መጽሐፍ ቅዱስ ሊያሳየው ወደቤቱ ወሰደው። ጓደኛውም “ዘጸአት 20ን አንብበው” አለውና ሄደ።
የንዋየቅድሳቱ ግምጃ ቤቱ ኃላፊም ዘጸአትን ከምዕራፍ 1 ጀምሮ ምዕራፍ 20:4,5 እስኪደርስ ድረስ አነበበው። የራሱ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ስለምስሎች በሚናገረው ነገር ደነገጠ። በሚቀጥለው እሁድ ከቅዳሴ በኋላ ቄሱን ስለምስሎች በሚናገረው ጥቅስ አፋጠጠው። መጀመሪያ ላይ ቄሱ እሱ ራሱ ምስሎችን እንደሚያከብር እንጂ እንደማያመልካቸው ተናገረ። ይህ መልስ አውሬሊዮን እንዳላረካው ሲመለከት ግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እያጠናህ ነው ብሎ ወቀሰው። አውሬሊዮም የማያጠና መሆኑን ገለጸለትና “አሁን ግን አጠናለሁ!” አለው።
በሚቀጥለው ጊዜ ምሥክሮቹ ወደመንደሩ ሲመጡ አውሬሊዮ ተገናኛቸውና ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። በቤተክርስቲያን ውስጥ መሥራቱን አቆመና በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በሕዝባዊ አገልግሎት ለመካፈል ብቁ ሆነ። በመጀመሪያ የሄደው ወደቄሱ ቤት ነበር። ቄሱም የቀድሞውን የንዋየ ቅድሳት ግምጃ ቤት ኃላፊ የመንግሥት ሰባኪ ሆኖ ሲያየው ዓይኑን ማመን አቃተው። እገዝትሃለሁ ብሎ አስፈራራው። አውሬሊዮ ግን ቀደም ሲል ቤተክርስቲያኑን ስለተወ መገዘት እንደማያስፈልገው ነገረው። እሱ የወሰደው የድፍረት እርምጃ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እያጠኑ የነበሩትን መንደረተኞች አበረታታቸው። አውሬሊዮና ሌሎች 21 ሰዎች በወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቁ። በዚያ አካባቢ ዕድገቱ በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሣ ለእነዚህ የጥምቀት ዕጩዎች ቡድን የክለሳ ጥያቄዎቹን ያደረገላቸው አንድ ሽማግሌ ብቻ ነበር።
“ቃላቸው ወጣ”
ከመንግሥቱ ስብከት ሸሽቶ ማምለጥ አይቻልም። አንድ ኢጣሊያዊ ካቶሊክ የይሖዋ ምሥክሮች ሊያነጋግሩት በመጡ ቁጥር ይናደድ ነበር። ኩባንያው ወደ ሲንጋፑር ባዛወረው ጊዜ ከዚያ በኋላ እንደማያስቸግሩት ተሰምቶት ነበር። ግን ይግረምህ ብሎ ምሥክሮቹ እዚያም አገኙት። ስለዚህ ምሥክሮቹን የሚያባርሩ ሁለት ተናካሽ ውሾች አዘጋጀ። ሁለት ምሥክሮች ሊያነጋግሩት ወደ ቤቱ ሲመጡ እነዚያ ውሾች ዘለሉባቸውና ሴቶቹ ፈርተው በተለያዩ አቅጣጫዎች እግሬ አውጭኝ ብለው ሮጡ። አንደኛው ውሻ በአንደኛዋ ላይ ሲደርስባት የምታደርገው ጠፋትና ከቦርሳዋ ሁለት ብሮሹሮች አውጥታ ሊነክሳት በተከፈተው አፉ ውስጥ ወተፈችው። በዚህ ጊዜ ውሻው እሷን ማባረር ትቶ ወደ ቤቱ እየሮጠ ተመለሰ።
በሚቀጥለው ሳምንት እነዚያው ምሥክሮች በዚያው መንገድ በስተማዶ ላለ ቤት ተመላልሶ መጠየቅ ያደርጉ ነበር። የውሾቹ ባለቤት በአትክልቱ ውስጥ ነበርና ይግረማችሁ ብሎ ሴቶቹን ሰላምታ ሰጣቸውና ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዛቸው። የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግሮ ወይም ጽሑፎቻቸውን አንብቦ እንደማያውቅ ነገራቸው። ነገር ግን በውሻው አፍ ብሮሹር በማግኘቱ ተገርሞ ያንኑ ዕለት ማታ ብሮሹሩን ስላነበበ በጣም ተመስጧል። ዕድሜውን በሙሉ ካቶሊክ የነበረ ቢሆንም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።
ሰውየው ተዛውሮ ወደ ኢጣሊያ ስለተመለሰ ስለነበር የይሖዋ ምሥክሮች እንዲያስጠኑት ዝግጅት ተደረገ። እሱና ሚስቱ በስብሰባዎች መገኘት ሲጀምሩ የሰበካው ቄስ በንዴት ዛተባቸው። በአትክልታቸው ላይ እሳት ሲለኮስባቸው ባልና ሚስቱ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ሁሉ አቋረጡ። ይህ ሰው ዛሬ “የቤተሰቦቼ አባሎች በሙሉ ብቸኛውና እውነተኛው አምላክ ይሖዋ መሆኑን እንዲያውቁ ስለምፈልግ ለብዙዎቹ መስክሬላቸዋለሁ” ይላል።
“እስከ ምድር ዳርቻ”
ከምድር ዳርቻ የመጣ ሌላ ተሞክሮ የመንግሥቱ መልእክት ምን ያህል እንደተደነቀና አኗኗርን ለመለወጥ እንደረዳ ይገልጻል። በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት ምሥክር ለነፍሰጡሮች የሚሰጥ ትምህርት በምትከታተልበት ጊዜ አንዲት ብዙ መጥፎ ልማዶች ያሏትና በእርግዝናዋ ወቅት ማጨስ ለማቆም እምቢ ያለች ሴት አገኘች። ምሥክሯ በሴትየዋ መጥፎ ዝንባሌ በጣም ተረበሸች። እንዳጋጣሚ የሚወልዱበት ጊዜና ክፍል አንድ ሆኖ ተገኘ። ስለዚህ የሚነጋገሩበት አጋጣሚ አገኘች። ሴትየዋ በልጅነቷ ብዙ ችግሮች የደረሱባት ስትሆን አሁንም ጋብቻዋ ሊፈርስ ምንም ያልቀረው ይመስል ነበር። ስለዚህ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ምሥክሯ ሴትዮዋን ልትጠይቃት ሄደችና የቤተሰብ ሕይወታችሁን ደስተኛ ማድረግ በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረችላት።
የሴትየዋ ባል “የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ብቻ አይሁን እንጂ” የሚለውን ቅድመ ሁኔታ በማከል እውነተኛውን ሃይማኖት እንዲያገኝ ወደ አምላክ ይጸልይ ነበር! ይሁንና ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እያጠናች እንዳለች ሲያውቅ ጥያቄ መጠየቅ ጀመረና በጥናቱ ላይ እንዲገኝ ተጋበዘ። በጥናቱም ላይ መገኘት ጀምሮ ወዲያውኑ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። አሁን ሁለቱም ባልና ሚስት ተጠምቀዋል፤ የትዳራቸውም ሁኔታ ተሻሽሏል።
በእንዲህ ዓይነቱ ጽሑፍ አማካኝነት የሚደረጉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዙ አዳዲስ አምላኪዎችን አስገኝተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች አብዮቶችን፣ የእርስ በርስ ጦርነትን፣ ወይም መንግሥታዊ እገዳዎችን ለመቋቋም በተገደዱባቸው አገሮች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥራ ጨምሯል። የእርስ በርስ ጦርነት በአንጎላ ውስጥ ለብዙ ዓመት ተጧጡፎ ነበር። ምሥክሮቹም ብዙ ስደትና መከራ አጋጥሟቸዋል። ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ ከ14,000 በላይ የሚሆኑ አስፋፊዎች ከ40,000 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳላቸው ሪፖርት አድርገዋል። ያላቸው ጽሑፍ ግን በጣም ጥቂት ነበር። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ቀን የመስክ አገልግሎት ማታ ማታ ደግሞ ስብሰባ በማዘጋጀት ትናንሽ ቡድኖችን በየቀኑ ያገለግሉ ነበር። ጦርነቱ አብቅቶ ከደቡብ አፍሪካ 420 ኩንታል የሚያክል በጣም የሚያስፈልጋቸው ጽሑፍ ሲመጣላቸው በጣም ተደስተው ነበር። በእርግጥ እነዚህ ወንድሞች አሁን “የሚሻለውን ነገር ፈትነው ሊወዱ ስለሚችሉ ፍቅራቸው በዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ ይበዛላቸዋል።” (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) ይህም ብዙ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች ያላቸው ሁሉ ይሖዋ በልግስና ያደረገላቸውን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት የሚያነቃቃ ነው!—1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16
የእነዚህ ታማኝ አምላኪዎች ደስታ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። . . . ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹአን (ደስተኞች) ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና . . . ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 5:3-12) እስከ አሁን እንኳን በአንጐላ በጣም ብዙ ምርት ተሰብስቦአል።
በሌሎች የዓለም አካባቢዎችም በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ ተጥለው የነበሩ እገዳዎች እየላሉ ወይም እየተወገዱ ነው። ኢየሱስ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 9:37) ይህ ቃል አሁንም ቢሆን እውነት ነው! ምንጊዜም ተጨማሪ ሠራተኞች ማስፈለጋቸው አልቀረም። አምልኮታችን ምርቱን መሰብሰብን የሚያጠቃልል በመሆኑ ደስ ይለናል። በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ አምላክ ፍሬያማና ለሱ የተወሰነ አገልግሎት ከማቅረብ የበለጠ ደስታ በምድር ላይ አይገኝም።
ይሁንና የይሖዋ አምላኪዎች እንዲህ ዓይነቱን ደስታና ቅንዓት እንዲያሳዩ የሚያነሣሣቸው ነገር ምንድን ነው? እስቲ እንመልከት።