የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉት የአጋጣሚ ምሥክርነት ጥሩ ውጤት ያስገኛል
አንድ የይሖዋ ምሥክር በአጋጣሚ ሰብኮላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የተዋወቁ ሰዎች ብዙ ናቸው። በዚህም የይሖዋ ምሥክሮች ውኃ ልትቀዳ ወደ ጉድጓድ ለመጣችው ሳምራዊት ሴት በአጋጣሚ የሰበከላትን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ። (ዮሐንስ ምዕራፍ 4) በምሥራቅ አፍሪቃ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለአንዲት የካቶሊክ መነኩሲት በአጋጣሚ ሰበከችላት። ምን ውጤት እንዳገኘት የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ ይነግረናል።
◻ አንድ ቀን ጧት ምሥክሯ ወደ ከተማ ስትሄድ አንዲት የካቶሊክ መነኩሲት አገኘች። “በጧት ወዴት እየሄድሽ ነው?” ብላ ጠየቀቻት። “ወደ አምላኬ ልጸልይ እየሄድኩ ነው” ስትል መለሰችላት። ከዚያም መነኩሲቷን “የአምላክሽን ስም ታውቂዋለሽ?” ብላ ጠየቀቻት። “ስሙ አምላክ አይደለም እንዴ?” ብላ መነኩሲቷ መለሰች። ምሥክሯ ከሰዓት በኋላ እቤትዋ ድረስ መጥታ ስለአምላክ ስም እንደምትነግራት ቃል ገባችላት። ይህን ከተነጋገሩ በኋላ መነኩሲቷ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደችና “ይሖዋ” ምን ማለት እንደሆነ ያውቅ እንደሆነ አንደኛውን ቄስ ጠየቀች። መልሱ “የአምላክ ስም ነው” የሚል ነበር። መነኩሲቷ ቄሱ ይህን ስም እያወቀ ሳያስተምራት በመቅረቱ ተገረመች።
ምሥክሯ መደዳውን ለዘጠኝ ቀናት ለመነኩሴይቱ ጉብኝት አደረገችላትና ስለ ሥላሴ፣ ስለ ነፍስ፣ ስለ ሲኦል እሳትና ስለ ሙታን ተስፋ እውነቱን አስተማረቻት። ሴትየዋ የተማረችውን ሁሉ ተቀበለችና እነዚህን አዳዲስ ትምህርቶች እንድታስብባቸው ጥቂት ጊዜ እንድትሰጣት ምሥክሯን ጠየቀቻት። ከሁለት ሳምንት በኋላ ምሥክሯን እንደገና አገኘቻትና ተጨማሪ ውይይት እንድታደርግላት ጠየቀቻት። በዚህ ጊዜ መነኩሲቱ ቤተክርስቲያኗን ለመተው ወስናና ምስሎቿን፣ መቁጠሪያዎቿንና መስቀሏን አቃጥላ ነበር። ቄሱ ተመልሳ እንድትመጣ ሊያሳምናት ሞክሮ ነበር። እሷ ግን እውነትን ለመከታተል ቆርጣ ነበር። በኋላም ተጠመቀችና የጤና ችግር ያለባትና በዕድሜ የገፋች ብትሆንም ለብዙ ወራት በዘወትር የረዳት አቅኚነት ሥራ ስትካፈል ቆይታለች።
ቤቷ ሰፊ ስለሆነ ጉባኤው በመንግሥት አዳራሽነት እንዲጠቀምበት እንደምትፈቅድ ገለጸች። ወንድሞች ያረጀውን ጣራ በአዲስ ተክተውና የውስጥ ግድግዳውን አፍርሰው የሕንፃውን አብዛኛውን ክፍል አንድ የሚያምር የስብሰባ ቦታ አድርገው አደሱት። ይህች የቀድሞ የካቶሊክ መነኩሲት አሁን ከአዳራሹ በስተጀርባ ባለ ክፍል ውስጥ ትኖራለች። ለይሖዋ አምልኮ ይህን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመቻሏ በጣም ደስተኛ ናት።
◻ የአጋጣሚ ምሥክርነት መስጠት ጥበብ መሆኑን የሚያሳይ ሌላው ተሞክሮ የመጣው ከካምፓላ ኡጋንዳ ነው። አንድ ሚስዮናዊ ምሥክር ወደ አንድ የመንግሥት ቢሮ ሲሄድ በሕንፃው ሊፍት ላይ አብረውት ለነበሩ ሰዎች የአጋጣሚ ምሥክርነት ሰጣቸው። ስሙ አቶ ለ———— የሆነ ሰው የቀረበለትን ጽሑፍ ለመውሰድ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ። ሆኖም በዚያን ሰዓት ሊወስደው አልቻለም። ስለዚህ ለሚሲዮናዊው ስሙንና የመሥሪያ ቤቱን አድራሻ ሰጠው። በኋላ ሚሲዮናዊው ወደ መሥሪያ ቤቱ ሄደና አቶ ለ————ን እንዲጠሩለት ጠየቀ። ተጠራ ግን የመጣው ሌላ ሰው ነበር። በዚያ መሥሪያ ቤት ስመ ሞክሼ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ለሁለተኛው አቶ ለ———— አጭር ምሥክርነት ተሰጠውና ሰውየው ከፍተኛ ፍላጎት አሳየ። የመጀመሪያው አቶ ለ———— የነበረው ፍላጎት ቢጠፋም ከሁለተኛው አቶ ለ———— ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። አሁን የተጠመቀ ምሥክር ነው። ሚስቱና ወንድ ልጁ ለመጠመቅ የሚያስችላቸውን ጥሩ መሻሻል እያደረጉ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኛ ስለሆነ ወደ ጽድቅ ያዘነበለ ልብ ያላቸውን በግ መሰል ሰዎች ያውቃቸዋል። እነዚህ ተሞክሮዎች ተከታዮቹን ወደ እነዚህ በግ መሰል ሰዎች እንደሚመራቸው ያሳያሉ። ያጋጣሚ ምሥክርነት ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።—ዮሐንስ 10:14