ቅዱሳን ጽሑፎች “ስለ ክርስቶስ መለኮትነት” ምን ይላሉ?
ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ የሆነ ኃይማኖታዊ ውጤት አስከትሏል። ይህንንም የምንልበት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የእሱ ተከታዮች እንደሆኑ ስለሚናገሩ ነው። ይሁን እንጂ ተከታዮቹ ነን የሚሉ ሁሉ በእሱ ማንነት ላይ አይስማሙም።
ኢየሱስ ያስተማረውን እንደሚቀበሉ ከሚናገሩት አንዳንዶቹ እሱን የሚመለከቱት ፈጣሪ እንደሆነ ሳይሆን የአምላክ ልጅ እንደሆነ አድርገው ነው። ሌሎች ደግሞ “በክርስቶስ መለኮትነት” ያምናሉ። እሱ ራሱ አምላክ እንደሆነም ያስባሉ። ኢየሱስ ምንጊዜም እንደኖረና በምድር ላይ ሳለም ከሰው በላይ እንደነበረ ያምናሉ። ታዲያ በዚህ ጉዳይ ትክክል ናቸውን? ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?
ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ያሳለፈው ሕልውና
ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ይኖር እንደነበረ ራሱ መስክሯል። “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 3:13) በተጨማሪም ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ። ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል። እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 6:51
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ይኖር እንደነበረ “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” ብሎ ከተናገራቸው ቃላት መረዳት ይቻላል። (ዮሐንስ 8:58) አብርሃም የኖረው ከ2018 እስከ 1843 ከዘአበ ድረስ ሲሆን የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት ግን የቆየው ከ2 ከዘአበ እስከ 33 እዘአ ድረስ ብቻ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ጥቂት ቀደም ብሎ “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” ብሎ ጸልዮ ነበር።—ዮሐንስ 17:5
የኢየሱስ ተከታዮችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የምሥክርነት ቃል ሰጥተዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ቃልም [አምላክ መሳይ (አዓት)]ነበረ። ሁሉ በእርሱ (በኩል) ሆነ፤ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። . . . ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትም ተመልቶ በእኛ አደረ። አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” በማለት ጽፏል። (ዮሐንስ 1:1, 3, 14) አዎን “ቃል” ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለ ሰው በመሆን “ሥጋ ሆነ።”
ሐዋርያው ጳውሎስም ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት የነበረውን ሕላዌ በመጥቀስ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም። ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:5-7) ጳውሎስ ኢየሱስን “የፍጥረት ሁሉ በኩር” በማለት ጠርቶታል። ምክንያቱም ሌሎች ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ አማካኝነት ስለሆነ ነው።—ቆላስይስ 1:13-16
በምድር በነበረ ጊዜ መለኮት አልነበረም
ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ሥጋዊ ሰው እንደነበረ ያረጋግጣሉ። ዮሐንስ ኢየሱስ ሥጋ የለበሰ ነው አላለም። “ሥጋ ሆነ” እንጂ ከፊል ሥጋ ከፊል አምላክ አልነበረም። ኢየሱስ በዚያ ጊዜ ሰውም አምላክም ቢሆን ኖሮ፣ ማለትም ከፊል ሰው ከፊል መለኮት ቢሆን ኖሮ ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው” ሊባልለት አይችልም ነበር።—ዕብራውያን 2:9፤ መዝሙር 8:4, 5
ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ሰውም አምላክም ቢሆን ኖሮ ለምን በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር? ጳውሎስ “(ክርስቶስ) በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ። እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 5:7
ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ በከፊል መንፈስ እንዳልነበረ ክርስቶስ “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” በሚለው የጴጥሮስ አነጋገር ተረጋግጧል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ኢየሱስ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የቀመሱትን መከራ ሊቀምስ የቻለውና የሚራራ ሊቀ ካህንም ሊሆን የቻለው ሙሉ በሙሉ ሰው ስለነበረ ብቻ ነበር። ጳውሎስ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 4:15
ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በመሆን “ራሱን ለሁሉ ቤዛ ሰጠ።” (ዮሐንስ 1:29፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:6) በዚህ መንገድም ኢየሱስ አዳም ያጠፋውን ፍጽምናና ዘላለማዊ ሰብአዊ ሕይወት መልሶ ገዝቷል። የአምላክ ፍትሕ “ነፍስ በነፍስ” የሚጠይቅ በመሆኑ ኢየሱስ አዳም መጀመሪያ በነበረበት ሁኔታ መገኘት ነበረበት። ይህም ማለት ፍጹም ሰው ነበር እንጂ አምላክም ሰውም አልነበረም ማለት ነው።—ዘዳግም 19:21፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ ያልተገለጸውን ነገር ለማንበብ አትሞክሩ
ኢየሱስ አምላክም ሰውም ነበር የሚሉ ሰዎች አሉ። ከአምላክ ጋር በባሕርይ፣ በሥልጣን፣ በክብርና በሕልውና እኩል የሆነ የሕዝበ ክርስትና ሥላሴ አባል መሆኑን ለማረጋገጥ በመሞከር የተለያዩ ጥቅሶችን በማስረጃነት ያቀርባሉ። እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶች በጥንቃቄ ስንመረምር ግን “ስለ ክርስቶስ መለኮትነት” የሚከራከሩ ሰዎች እነዚህ ጥቅሶች ከሚናገሩት የተለየ ነገር እንደሚናገሩ አድርገው እንደሚረዱ እንገነዘባለን።
አንዳንዶች አምላክ በዘፍጥረት 1:26 እና 11:7 ላይ “እንፍጠር” “እንውረድ” በሚሉት ጥቅሶች ላይ “እኛ” የሚለውን ተውላጠ ስም እንደተጠቀመ የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ኢየሱስ (ቃል) ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ከይሖዋ ጋር እኩል እንደነበረ ያረጋግጣሉ ይላሉ። ነገር ግን ይህን ተውላጠ ስም መጠቀሙ አምላክ ከእኩያው ጋር እንደሚነጋገር አያመለክትም። ግፋ ቢል የሚያመለክተው ከሰማያዊ ፍጡሮቹ መሃል አንዱ ከአምላክ ጋር ባለው ዝምድና ምክንያት የተመረጠ ቦታ እንደያዘ ነው። እንዲያውም ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት የነበረው ኢየሱስ ከአምላክ ጋር በቅርብ አብሮት በመሆን ዋና ሠራተኛና አፈ ንጉሥ ሆኖ ያገለግል ነበር።—ምሳሌ 8:30,31፤ ዮሐንስ 1:3
ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ የተፈጸሙ ሁኔታዎች አምላክ፣ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ እኩያዎች እንደሆኑ አያመለክቱም። ኢየሱስ ሰው ስለነበረ ለሰማያዊ አባቱ ራሱን ማቅረቡን ለማሳየት በውኃ ተጠምቋል። በዚያን ወቅት “ሰማያት ተከፈቱ” እና የአምላክ መንፈስ በእርግብ መልክ በኢየሱስ ላይ ወረደ። እንደዚሁም የይሖዋ ድምፅ “ከሰማያት” “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ተሰማ።—ማቴዎስ 3:13-17
ታዲያ ኢየሱስ ተከታዮቹ “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ደቀመዛሙርትን እንዲያጠምቁ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?” (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ እሱ፣ አባቱና መንፈስ ቅዱስ እኩያዎች ናቸው ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የሚጠመቁ ሰዎች ሁሉ ሕይወታቸውን የሚወስኑለት ይሖዋ ሕይወት ሰጪና ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ይገነዘባሉ። ኢየሱስንም አምላክን ለሚያምኑ ሰዎች ቤዛ ሆኖ የቀረበ መሲሕ መሆኑን ይቀበላሉ። መንፈስ ቅዱስም ሊገዙለት የሚገባ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን ይገነዘባሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የጥምቀት ዕጩዎች ይሖዋን፣ ኢየሱስንና መንፈስ ቅዱስን እንደ አንድ ሥላሴያዊ አምላክ አድርገው ሊመለከቷቸው አይገባም።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተአምራትን ያደርግ የነበረ መሆኑ አምላክም ሰውም እንደነበረ አያረጋግጥምን? አያረጋግጥም። ምክንያቱም ሙሴ፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና ሌሎችም አምላክና ሰው ሳይሆኑ ተአምራት ፈጽመዋል። (ዘጸአት 14:15-31፤ 1 ነገሥት 18:18-40፤ 2 ነገሥት 4:17-37፤ ሥራ 9:36-42፤ 19:11, 12) ኢየሱስ እንደ እነሱ በአምላክ በተሰጠው ኃይል ተአምራትን የፈጸመ ፍጹም ሰው ነበር።—ሉቃስ 11:14-19
ኢሳይያስ በትንቢት መሲሑን ኢየሱስን “ኃያል አምላክ” በማለት ጠርቶታል። (ኢሳይያስ 9:6) በኢሳይያስ 10:21 ላይ ይኸው ነቢይ ይሖዋ “ኃያል አምላክ” እንደሆነ ተናግሯል። አንዳንድ ሰዎች ይህን የቃላት መመሳሰል ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ለማረጋገጥ ይጠቀሙበታል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ያልተጻፈ ወይም ያልተባለ ነገር እንዳናነብ ጠንቃቆች መሆን ያስፈልገናል። “ኃያል አምላክ” ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል “ሁሉን ቻይ አምላክ” እንደሚለው አባባል ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አይደለም። (ዘፍጥረት 17:1) በእርግጥ ኃያል አምላክ በመሆንና የበላይ የማይገኝለት ሁሉን ቻይ አምላክ በመሆን መሃል ልዩነት አለ።
በኢሳይያስ 43:10 መሠረት ይሖዋ “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይሆንም” ብሏል። እነዚህ ቃላት ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አያረጋግጡም። ፍሬ ነገሩ ይሖዋ ዘላለማዊ ስለሆነ ቀዳሚ የለውም፤ ከእሱም በፊት አምላክ አልነበረም ማለት ነው። ከእሱም በኋላ አምላክ የማይኖረው እሱ ምን ጊዜም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር ልዑል ጌታ በመሆን የሚተካው አምላክ አይኖርም ማለት ነው። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች አንዳንድ ሰዎችን በሚመለከት “እኔ ግን አማልክት ናችሁ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ። ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ” እንደሚሉት ይሖዋ ራሱ አማልክት ብሎ የጠራቸውን ሌሎች ፍጥረታት ፈጥሯል። (መዝሙር 82:6, 7) በተመሳሳይም “ቃል” በይሖዋ የተፈጠረ አምላክ (a god) ነበር። ይህ ግን በማንኛውም ጊዜ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል አድርጎት አያውቅም።
የኢየሱስ እውነተኛ ደረጃ
ይሖዋ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ ሰብዓዊ ሕልውና ወስዷል የሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደነበረ አድርጎ ራሱን እንደተመለከተ የሚያመለክት ቅንጣት ፍንጭ የማይሰጥ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ምንጊዜም ከአባቱ ያነሰ መሆኑን ያለማወላወል ይገልጻል። ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ የአምላክ ልጅ ከመሆን የበለጠ ደረጃ እንዳለው ተናግሮ አያውቅም። ከዚህም በላይ ክርስቶስ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ብሏል።—ዮሐንስ 14:28
ጳውሎስ “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን። ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” በማለት በይሖዋና በኢየሱስ መሃል ልዩነት እንዳለ አመልክቷል። (1 ቆሮንቶስ 8:6) በተጨማሪም ጳውሎስ “እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፣ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 3:23) በእርግጥም ክርስቲያኖች የጌታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆኑ ሁሉ እሱም ራሱ የሆነው የይሖዋ አምላክ ነው።
ጳውሎስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፍሬ ነገር ሲያስገነዝብ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በአምላክና በክርስቶስ መሃል ያለው ይህ ዝምድና ለወደፊቱም የሚቀጥል ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ከሺህ ዓመት ግዛቱ በኋላ “መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ ስለሚሰጥና እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ስለሚገዛ” ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:24, 28፤ ራእይ 20:6
ሌሎች ጥቅሶችንም እንመልከት
የኢየሱስን ልደት በሚመለከት ማቴዎስ “በነቢይ [ኢሳይያስ 7:14] ከጌታ (ከይሖዋ) ዘንድ ‘እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ልጅንም ትወልዳለች። ስሙንም አማኑኤል ይሉታል’ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል። ትርጓሜውም ‘እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው’” በማለት ጽፏል። (ማቴዎስ 1:22, 23) አማኑኤል የሚለው ስም ለኢየሱስ መጠሪያ ስምነት አልተሰጠም። ሆኖም ሰው ሆኖ ያከናወነው ሥራ አማኑኤል የሚለውን ስም ትርጉም ፈጽሞታል። ኢየሱስ መሲሐዊው ዘርና የዳዊት ዙፋን ወራሽ በመሆን በምድር ላይ መገኘቱ ለይሖዋ አምላኪዎች አምላክ ከእነሱ ጋር ከጐናቸው እንደሆነና በውጥናቸው እንደሚደግፋቸው አረጋግጦላቸዋል።—ዘፍጥረት 28:15፤ ዘጸአት 3:11, 12፣ ኢያሱ 1:5, 9፤ መዝሙር 46:5-7፤ ኤርምያስ 1:19
ሐዋርያው ቶማስ ከሙታን ለተነሣው ኢየሱስ “ጌታዬ አምላኬም” በማለት በደስታ ተናግሯል። (ዮሐንስ 20:28) ይህም ሆነ ሌሎች ጥቅሶች “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ (እናምን) ዘንድ (አምነንም) በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ ተጽፈዋል። ቶማስም ኢየሱስ “ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ” በማለት ለደቀመዛሙርቱ የላከውን መልእክት ማስተባበሉ አልነበረም። (ዮሐንስ 20:17, 30, 31) ስለዚህ ቶማስ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ብሎ አላሰበም። ምንም እንኳ ኢየሱስ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” ባይሆንም ቶማስ “አምላኬ” ብሎ የጠራው ክርስቶስ አምላክ (a god) ከመሆኑ አንጻር ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 1:1፤ 17:1-3) ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ተልኮ የመጣ መልአክን ይሖዋ እንደሆነ አድርገው እንደተናገሩት ቶማስም “አምላኬ” ሲል ኢየሱስ የአምላክ ቃል አቀባይና ወኪል መሆኑን አምኖ መቀበሉ ሊሆንም ይችላል።—ከዘፍጥረት 18:1-5, 22-33፤ 31:11-13፤ 32:24-30፤ መሳፍንት 2:1-5፤ 6:11-15፤ 13:20-22 ጋር አወዳድር
እንግዲያውስ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት “ቃል” ሆኖ ይኖር ነበር። በምድር ሳለ መለኮት የሆነ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው አልነበረም። አዳም ኃጢአት ሳይሠራ በፊት እንደነበረው ዓይነት ፍጹም ሥጋዊ ሰው ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ከፍ ከፍ የተደረገ የማይሞት መንፈስ ሆኖ እንደ ምንጊዜውም የአምላክ የበታች ሆኗል። ስለዚህ በግልጽ እንደምናየው ቅዱሳን ጽሑፎች “የክርስቶስ መለኮትነት” የሚለውን ሐሳብ አይደግፍም።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መላእክት ኢየሱስን ያመልኩታልን?
አንዳንድ ትርጉሞች ዕብራውያን 1:6 ላይ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ለእርሱ (ለኢየሱስ) ይስገዱ” ወይም “ያምልኩት” ይላሉ። (የኪንግ ጀምስ ቨርሽን፣ የጀሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ) በግልጽ እንደሚታየው ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው “መላእክቱ ሁሉ (ለአምላክ) ስገዱለት” የሚለውን የመዝሙር 97:7ን የሰፕቱጀንት ትርጉም ነው።—ሲ ቶምፕሰን
በዕብራውያን 1:6 ላይ ማምለክ ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ፕሮስኪይኒዮ ሻካህ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል ተክቶ በሰፕቱጀንት ትርጉም ላይ በመዝሙር 97:7 ላይ ተሠርቶበታል። ሻካህ ትርጉሙ “ሰገደ”፣ “እጅ ነሣ” ማለት ነው። ይህም ተቀባይነት ያለው ለሰዎች አክብሮት የማሳየት ድርጊት ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 23:7፤ 1 ሳሙኤል 24:8፤ 2 ነገሥት 2:15) ወይም ደግሞ እውነተኛውን አምላክ ማምለክን ወይም ለሱ መስገድን ወይም ለሐሰት አማልክት የሚደረግ ስግደትን ወይም አምልኮትን ሊያመለክት ይችላል።—ዘጸአት 23:24፤ 24:1፤ 34:14፤ ዘዳግም 8:19
አብዛኛውን ጊዜ ለኢየሱስ የሚሰጠው ፕሮስኪይኒዮ ለነገሥታትና ለሌሎች የተከበሩ ሰዎች ከሚደረገው እጅ መንሳት ጋር ይመሳሰላል። (ማቴዎስ 2:2, 8፤ 8:2፤ 9:18፤ 15:25፤ 20:20ን ከ1 ሳሙኤል 25:23, 24፤ 2 ሳሙኤል 14:4-7፤ 1 ነገሥት 1:16፤ 2 ነገሥት 4:36, 37 ጋር አወዳድር) ለኢየሱስ ይሰግዱለት ወይም እጅ ይነሱለት የነበረው አምላክ (እግዚአብሔር) በመሆኑ ሳይሆን “የእግዚአብሔር ልጅ” ስለሆነ ወይም መሲሐዊው “የሰው ልጅ” በመሆኑ እንደሆነ ግልጽ ነው።—ማቴዎስ 14:32, 33፤ ሉቃስ 24:50-52፤ ዮሐንስ 9:35, 38
ዕብራውያን 1:6 ኢየሱስ ከአምላክ ሥር ስላለው ደረጃ ወይም ሥልጣን ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 2:9-11) እዚህ ላይ ፕሮስኪይኒዮን ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል “አክብሮት ማሳየት፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “እጅ መንሳት”፣ አን አሜሪካን ትራንስሌሽን ደግሞ “መጐንበስ” በማለት ተርጉመውታል። አንድ ሰው “ማምለክ” የሚለውን ትርጉም ከመረጠ ይህ አምልኮ አንጻራዊ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ኢየሱስ ለሰይጣን “ለጌታህ ለአምላክህ ብቻ ስገድ (የፕሮስካይኒዮ ዓይነት ቃል) እሱንም አምልክ” ብሎታል።—ማቴዎስ 4:8-10
ጳውሎስ አምላክን ስለ ማምለክ የሚናገረውን መዝሙር 97:7ን ጠቅሶ በዕብራውያን 1:6 ላይ ለኢየሱስ ቢጠቀምበትም ኢየሱስ የአምላክ “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” መሆኑንገልጿል። (ዕብራውያን 1:1-3) ስለዚህ መላእክት ለአምላክ ልጅ የሚያደርጉት ማንኛውም ዓይነት ስግደት አንጻራዊና በሱ በኩልም ወደ ይሖዋ እንዲያልፍ የሚቀርብ ነው።