የአንባብያን ጥያቄዎች
ኖህ በመጀመሪያ ቁራ፣ በኋላም ርግብ ከመርከቡ የላከው ለምን ነበረ?
መጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር ማብራሪያ አይሰጠንም። ይሁን እንጂ ኖህ ያደረገው ነገር በቂ ምክንያት ያለው ይመስላል።
ለአርባ ቀንና ለአርባ ሌሊት ከፍተኛ ዝናብ ሲዘንብ በመቆየቱ ምድር በሙሉ፣ ረዥም ተራሮች እንኳን ሳይቀሩ አምስት ወራት ለሚያክል ጊዜ በውሃ ተሸፍነው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን መርከቢቱ “በአራራት ተራራ ላይ አረፈች።” (ዘፍጥረት 7:6 እስከ 8:4) ከጥቂት ወራት በኋላ “የተራሮች ራሶች ተገለጡ። ቁራንም ሰደደው፣ እርሱም ወጣ። . . . ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።”—ዘፍጥረት 8:5, 7
ቁራን የላከው ለምን ነበር? ይህ ወፍ ከፍተኛ የሆነ የመብረር ችሎታ አለው። በተጨማሪም የተለያዩ ምግቦችን፣ የሞቱ እንስሳትን ሥጋ ጭምር ሊበላ ይችላል። ኖህ ቁራን የላከው ተመልሶ ወደ መርከቡ ይመጣ እንደሆነ ወይም ውሃው እየጎደለ ሲሄድ መሬት ላይ የሚታዩትን በድኖች እየበላ እዚያው ይቀር እንደሆነ ለማየት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቁራው በዚያው አልቀረም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደተመለሰ ይናገራል። ወደ ኖህ እንደተመለሰ ግን አይናገርም። ምናልባት በውሃው ላይ የሚንሳፈፍ ምግብ ለማግኘት ሲበርር ከቆየ በኋላ ለማረፍ ወደ መርከቡ ይመለስ ይሆናል።
በኋላ ግን ኖህ ርግብ ለመላክ መረጠ። እንዲህ እናነባለን፦ “ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም። ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች።” (ዘፍጥረት 8:9) ይህም ርግቢቱ የጥፋቱ ውሃ ምን ያህል እንደጎደለ ለማመልከት ልታገለግል የምትችል መሆንዋን ያመለክታል። ርግቦች በሰዎች የመተማመንና የመመካት ባሕርይ አላቸው። ርግቢቱ በመርከቡ ላይ ለማረፍ ብቻ ሳይሆን ወደ ኖህ ወደ ራሱ እንደምትመለስ ኖህ እርግጠኛ ሊሆን ይችል ነበር።
ርግቦች የሚያርፉት በደረቅ መሬት ላይ ብቻ እንደሆነ፣ የሚበሩትም ዝቅ ባሉ ሸለቋማ አካባቢዎች እንደሆነና ዕፀዋትንና አዝርዕትን ብቻ እንደሚመገቡ ታውቆአል። (ሕዝቅኤል 7:16) የግርዝሚክ አኒማል ላይፍ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “ርግቦች የሚመገቡት ጥራጥሬዎችንና አዝርዕትን ብቻ በመሆኑና ምግባቸው በአብዛኛው የሚገኘው በመሬት ላይ በመሆኑ መሬቱ ከአንድ ቀን በላይ በውሃ ወይም በበረዶ ሲሸፈን ችግር ይደርስባቸዋል።” ስለዚህ ርግቢቱ ደረቅ ምድር ወይም በማቆጥቆጥ ላይ የሚገኝ ተክል እንዳገኘች የሚያሳይ ማስረጃ ለኖህ ልታመጣለት ትችላለች። ርግቢቱ ለሁለተኛ ጊዜ ስትላክ የወይራ ቅጠል አመጣችለት። ለሦስተኛ ጊዜ ስትላክ ግን ሳትመለስ በዚያው ስለቀረች ኖህ ከመርከቡ ሊወጣ እንደሚችል ለማወቅ ቻለ።—ዘፍጥረት 8:8-12
አንዳንዶች እነዚህን ዝርዝር ሁኔታዎች ከቁምነገር አስገብተው የማይመለከቱ ቢሆንም ታሪኩ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሳይሰጥ እነዚህን ልዩ ሁኔታዎች ማብራራቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሊታመንበት የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን ያመለክታል። ታሪኩ ልብ ወለድ ወይም ሐሳብ ወለድ ሳይሆን ትክክለኛ መሆኑን እንድንቀበል የሚያስችለን ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል። ዝርዝር ማብራሪያዎችና መግለጫዎች አለመሰጠታቸው ደግሞ ታማኝ ክርስቲያኖች ኖህ ከሙታን ሲነሣ የሚጠይቁት ብዙ ጥያቄዎች እንዳሉና በዚያ ጊዜ ያደረጋቸውን ነገሮች ምክንያትና አስፈላጊነት እንደሚገልጽላቸው ያመለክታል።—ዕብራውያን 11:7, 39