የዘመናችን የሐሰት ነቢያት
ኤርምያስ በኢየሩሳሌም የአምላክ ነቢይ ሆኖ ያገለገለው ከተማይቱ በጣኦት አምልኮ፣ በብልግና፣ በፍትሕ ማጉደልና የንጹሐንን ደም በማፍሰስ ተሞልታ በነበረበት ጊዜ ነበር። (ኤርምያስ 7:8-11) በዚያ ጊዜ በነቢይነት ያገለግል የነበረው ኤርምያስ ብቻ ባይሆንም አብዛኞቹ ሌሎች ነቢያት ራሳቸውን የሚያገለግሉና ምግባረ ብልሹዎች ነበሩ። በምን መንገድ? ይሖዋ “ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና። ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኮል ያደርጋሉና። የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ። ሰላም ሳይሆን ሰላም ሰላም ይላሉ” በማለት ተናግሯል።—ኤርምያስ 6:13, 14
በምድሪቱ ብዙ ምግባረ ብልሹነት ቢኖርም ሐሰተኞቹ ነቢያት ግን ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉና ሕዝቡም ከአምላክ ጋር ሰላም እንደሆነ ለማስመሰል ጥረዋል። ይሁን እንጂ ሁኔታው ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነበር። ኤርምያስ ያለ ፍርሐት እንዳስታወቀው የአምላክ ፍርድ ከፊታቸው ተደቅኖ ይጠብቃቸው ነበር። በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ወታደሮች ስትደመሰስ፣ ቤተመቅደሷ ሲጠፋና ሕዝቡም ሲገደሉ ወይም ተማርከው ወደ ባቢሎን በግዞት ሲወሰዱ እውነተኛ መሆኑ የተረጋገጠው እውነተኛው ነቢይ ኤርምያስ እንጂ ሐሰተኞቹ ነቢያት አልነበሩም። በምድሪቱ የተተዉት ጥቂት ምስኪን ሰዎች ወደ ግብጽ ሸሽተው ሄዱ።—ኤርምያስ 39:6-9፤ 43:4-7
የሐሰት ነቢያቱ ያደረጉት ነገር ምን ነበር? “እነሆ እያንዳንዱ በባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ ይላል ይሖዋ።” (ኤርምያስ 23:30) የሐሰት ነቢያቱ ሰዎች ወደ አምላክ እውነተኛ ማስጠንቀቂያ እንዲያዳምጡ በማድረግ ፈንታ ሐሰትን እንዲያዳምጡ በማበረታታት የአምላክን ቃል ያለውን ኃይልና ውጤት ሰርቀዋል። ይናገሩ የነበረው “የአምላክን ታላቅ ሥራ” ሳይሆን የራሳቸውን ሐሳብና ሰዎች ሊሰሙ የሚፈልጉትን ነገር ብቻ ነበር። የኤርምያስ መልእክት በእርግጥ ከአምላክ የተገኘ ነበር። እሥራኤላውያን የኤርምያስን ቃል ሰምተው ቢሆን ኖሮ ከጥፋቱ ይተርፉ ነበር። ሐሰተኞቹ ነቢያት “የአምላክን ቃል ሰርቀው” ሕዝቡን ወደ ጥፋት መርተዋል። የደረሰው ነገር ኢየሱስ በዘመኑ ስለነበሩት የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች “ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ” በማለት እንደተናገረው ነበር።—ሥራ 2:11፤ ማቴዎስ 15:14
ዛሬም በኤርምያስ ዘመን እንደነበረው የመጽሐፍ ቅዱስን አምላክ እንወክላለን የሚሉ የሐሰት ነቢያት አሉ። እነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ከሚናገረው እርግጠኛ ነገር የሰዎችን ሐሳብ በመውሰድ ወይም አዛብተው በመስበክ የአምላክን ቃል ይሰርቃሉ። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርት የሆነውን መንግሥቱን እንደ መፈተኛ ወይም እንደ መመዘኛ እንጠቀማለን።
ስለ መንግሥቱ የሚናገረው እውነት
የክርስቶስ ትምህርት ዋነኛ መልእክት የአምላክ መንግሥት ነበር። በወንጌሎቹም ውስጥ ከመቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ “ስለዚህ ተልኬያለሁና የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” ብሏል። ደቀ መዛሙርቱንም “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል።—ሉቃስ 4:43፤ 11:2
ታዲያ ይህች መንግሥት ምንድን ናት? በዘ ኒው ታየርስ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክሲኮን መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንግሥት” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ በመጀመሪያ “ንጉሣዊ ሥልጣን፣ ንግሥና፣ ግዛት፣ አገዛዝ” ማለት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “በአንድ ንጉሥ አገዛዝ ሥር የሚተዳደር አገር ወይም የግዛት ክልል” ማለት ነው። ከዚህም ልንገነዘብ የምንችለው የአምላክ መንግሥት በንጉሥ የምትተዳደር እውነተኛ መንግሥት ወይም መስተዳድር እንደሆነች ነው። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ትክክል ነውን?
አዎን ትክክል ነው፤ ንጉሡም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት መልአኩ ገብርኤል ለማርያም “እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል። ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 1:32) ኢየሱስ ዙፋን የሚቀበል መሆኑ ንጉሥና የአንድ መስተዳድር ገዥ ወይም መሪ እንደሚሆን ያረጋግጣል። መንግሥቲቱ ቃል በቃል መንግሥታዊ መስተዳድር መሆኗን “ሕፃን ተወልዶአልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና። መንግሥትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። . . . ለንጉሣዊ ሥልጣኑ ወሰን የለውም። መንግሥቱም ዘላለማዊ ሰላም የሠፈነበት ይሆናል” የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት ያረጋግጣል።—ኢሳይያስ 9:6, 7 (ቁጥር 7 ከ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም የተወሰደ ነው።)
ኢየሱስ የሚገዛው የት ሆኖ ነው? ኢየሩሳሌም ሆኖ ነው? አይደለም። ነቢዩ ዳንኤል ኢየሱስ ሰማይ ሆኖ መንግሥቱን ሲቀበል የሚያሳይ ራእይ ተመልክቶአል። (ዳንኤል 7:13, 14) ይህም ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ ከተናገረው ጋር ይስማማል። አብዛኛውን ጊዜ ይህችን መንግሥት “መንግሥተ ሰማያት”ብሎ ይጠራ ነበር። (ማቴዎስ 10:7፤ 11:11, 12) ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት ለፍርድ ቀርቦ ሳለ ከተናገራቸው ቃላት ጋርም ይስማማል። “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም መንግሥቴ ከዚህ ዓለም ብትሆን ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው።” (ዮሐንስ 18:36) የቤተ ክርስቲያንህ አገልጋይ ወይም ቄስ የኢየሱስ መንግሥት ከሰማይ ላይ ሆና የምትገዛ እውነተኛ መስተዳድር እንደሆነች ነግረውህ ያውቃሉን? ወይም መንግሥቲቱ በሰው ልብ ውስጥ ብቻ የምትኖር ነገር ነች ብለው ነው ያስተማሩህ? ከሆነ የአምላክን ቃል ሲሰርቁብህ ቆይተዋል ማለት ነው።
በዚህች መንግሥታዊ መስተዳድርና በተለያዩት ሰብዓዊ መንግሥታት መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? በሚርሲያ ኤሊያድ በተዘጋጀው ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ሪሊጅን መሠረት የተሐድሶ መሪ የነበረው ማርቲን ሉተር ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲናገር “ዓለማዊ መንግሥትም . . . የእግዚአብሔር መንግሥት ተብሎ ሊጠራ ይችላል” የሚል ሐሳብ አቅርቧል። ሰዎች በራሳቸው ጥረት ሰብዓዊ መንግሥታትን ወደ አምላክ መንግሥት ደረጃ ሊያደርሱ ይችላሉ ብለው የሚያስተምሩ ሰዎች አሉ። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ይህንን ሐሳብ በ1983 ሲያረጋግጥ “ልባዊ የሆነ የሰላም ፍላጎት እንዳለን እየመሰከርን የተቆረጠ እርምጃ ስንወስድ የዚህን ዓለም መንግሥታት የእግዚአብሔር መንግሥት ወደመሆን ልናደርሳቸው እንድንችል የእግዚአብሔር መንፈስ በደካማ ጥረቶቻችን ሊጠቀም ይችላል” ብሎአል።
ይሁንና በጌታ ጸሎት (“አባታችን ሆይ” በተባለው ጸሎት) ላይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ እንዲጸልዩ እንዳስተማራቸውና “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ የነገራቸው ስለመንግሥቲቱ ከጸለዩ በኋላ ብቻ መሆኑን አስተውሉ። (ማቴዎስ 6:10) በሌላ አነጋገር ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በማድረግ መንግሥቲቱን ሊያመጧት አይችሉም ማለት ነው። የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንድትሆን የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት መምጣት ነው።?
የዳንኤል ትንቢት በምዕራፍ 2 ቁጥር 44 ላይ የሚናገረውን አዳምጥ። “በእነዚያም ነገሥታት (በፍጻሜው ዘመን በሚኖሩ ሰብዓዊ መሪዎች) ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች፤ ታጠፋቸውማለች።” እንግዲያውስ ኢየሱስ መንግሥቲቱ የዚህችን ምድር መንግሥታትና መስተዳድሮች አጥፍታ የእነርሱን ቦታ በመውሰድ ሰዎችን ልትገዛ ነው። አምላክ ለሰው ልጆች የሰጣቸው መንግሥት ስለሆነች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲደረግ ታደርጋለች።
ይህን ዓለም የሚቆጣጠረው ማን መሆኑን ስንመለከት መንግሥቲቱ ይህን የመሰለ ሥር ነቀል እርምጃ የምትወስድበት ምክንያት ግልጽ ይሆንልናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለም በሞላው በክፉው ኃይል ተይዟል” በማለት ጽፎአል። (1 ዮሐንስ 5:19) “ክፉው” ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ሲል የጠራው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) አምላኩ ሰይጣን ዲያብሎስ በሆነለት በዚህ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ክፍል ሊሆን የሚችል አንድም ተቋም የለም።
ኢየሱስ በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ ካልገባበት ምክንያት አንዱ ይህ ነው። አይሁዳውያን ብሔረተኞች ሊያነግሡት በሞከሩ ጊዜ ከእነርሱ ሸሽቶአል። (ዮሐንስ 6:15) ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ለጲላጦስ በግልጽ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሎአል። ከዚህም ጋር በመስማማት ስለተከታዮቹ እኔ ከዓለም አይደለሁም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) ስለዚህ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የጥገናና የተሐድሶ ለውጦችን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ማፋጠን ይችላል ብለው የሚያስተምሩና ምዕመናኖቻቸውንም ለዚህ ዓለም እንዲታገሉ የሚያበረታቱ ሃይማኖታዊ መሪዎች የሐሰት ነቢያት ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያለውን ኃይልና ውጤት ሠርቀዋል።
ይህን ያህል አስፈላጊ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
ይህ ሁሉ ምክንያት የቀረበው የአእምሮ ዕውቀት ለማግኘት ሲባል ብቻ ነውን? ፈጽሞ አይደለም። ስለአምላክ መንግሥት የተሰጡት የተሳሳቱ ትምህርቶች ብዙ ሰዎችን አሳስተዋል። እንዲያውም የታሪክን አቅጣጫ ሳይቀር ለውጠዋል። ለምሳሌ ያህል የሮማ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ የሆነው ቲዮ የተሰኘ ጽሑፍ፦ “የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ምድር ላይ ኢየሱስ ወዳቋቋመው የእግዚአብሔር መንግሥት እየተንቀሳቀሱ ነው። . . . የዚህም መንግሥት ዘር ቤተክርስቲያን ናት” ይላል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር አንድ ሆና መታየቷ አጉል እምነት ሰፍኖበት በነበረው በመካከለኛው ዘመን ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሆነ ዓለማዊ ኃይል እንዲኖራት አስችሎአል። ዛሬም እንኳ ሳይቀር የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣኖች አንዳንድ ፖለቲካዊ ሥርዓቶችን በመደገፍና ሌሎቹን ደግሞ በመቃወም በዓለም ጉዳዮች አፈጻጸም ላይ ተጽእኖ ለማሳደር እየጣሩ ነው።
አንድ ተቺ “የአብዮት ወይም የለውጥ መንገድ የአምላክ መንግሥት ነው። ምክንያቱም አብዮቱ የእውነት መንገድ በሆነው በኢየሱስ . . . በጋንዲ፣ . . . በቤሪጋኖች በኩል የተሰጠና በእነሱ አነሳሽነት የተለኮሰ የሕዝቦች በአዲስ ሰብአዊነት መሰባሰብ ነው” ሲል ዛሬ በሠፊው ተዛምቶ የሚገኘውን ሌላ አመለካከት ገልጾአል። የአምላክን መንግሥት ዓላማዎች በፖለቲካ እንቅስቃሴ ማራመድ ይችላል ብሎ ማስተማርና የመንግሥቲቱን እርግጠኛ ሐቅ ችላ ማለት የሃይማኖት መሪዎች የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት እንዲሽቀዳደሙ አድርጎአቸዋል። ሌሎች ደግሞ በእርስ በርስ ብጥብጥ ውስጥ እንዲገቡና በሽምቅ ውጊያ እንዲካፈሉ አነሳስቶአቸዋል። ይህ ድርጊታቸው ደግሞ መንግሥቲቱ ከዚህ ዓለም ካለመሆኗ ጋር የሚስማማ አይደለም። ይህን ያህል በፖለቲካ ጉዳዮች የሚጠላለፉ የሃይማኖት መሪዎችም ኢየሱስ ስለ እውነተኛ ደቀመዛሙርቱ ሲናገር የዚህ ዓለም ክፍል አይደሉም ሲል ከተናገረው ቃል ጋር አይስማሙም። የአምላክ መንግሥት በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ትገኛለች ብለው የሚያስተምሩ ሁሉ የሐሰት ነቢያት ናቸው። የአምላክን ቃል ከሕዝቦች እየሰረቁ ነው።
በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የሚያስተምሩ ቢሆኑ ኖሮ መንጐቻቸው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ድህነት፣ በሽታ፣ የዘር መድልኦና ጭቆና ለመሳሰሉት ችግሮች መፍትሔ እንደምታመጣ ያውቁ ነበር። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ለመሳሰሉት ችግሮች መፍትሔ የሚገኘው አምላክ ራሱ በወሰነው ጊዜና በአምላክ መንገድ ነው እንጂ መንግሥቲቱ በምትመጣበት ጊዜ በሚያልፈው የፖለቲካዊ ሥርዓቶች የተሐድሶ ለውጥ አማካኝነት አይደለም። እነዚህ ቀሳውስት እውነተኛ ነቢያት ቢሆኑ ኖሮ የአምላክ መንግሥት መጥታ እርምጃ የምትወስድበትን ጊዜ እየተጠባበቁ የዚህ ዓለም የፍትሕ መዛባት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን እውነተኛና ተግባራዊ እርዳታ ከአምላክ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያስተምሩአቸው ነበር።
በመጨረሻም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት እውነተኛ ነቢያት ቢሆኑ ኖሮ በምድር ላይ ብዙ ጭንቀት ያስከተሉት እየተባባሱ የሚሄዱ ሁኔታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት የተነገሩና የአምላክ መንግሥት መምጫ መቅረቡን የሚያመለክቱ ምልክቶች መሆናቸውን ለመንጐቻቸው ያስተምሩ ነበር። አዎን የእግዚአብሔር መንግሥት በቅርቡ ጣልቃ ገብታ እርምጃ በመውሰድ አሁን ያሉትን ፖለቲካዊ መዋቅሮች ትተካለች። ይህም ለመላው የሰው ልጅ ታላቅ በረከት ይሆናል!—ማቴዎስ 24:21, 22, 36-39፤ 2 ጴጥሮስ 3:7፤ ራእይ 19:11-21
የሰው ዘር በአምላክ መንግሥት ሲገዛ
የአምላክ መንግሥት መምጣት ለሰው ልጅ ምን ማለት ይሆናል? ሁልጊዜ ጧት ጧት በሙሉ ኃይልና ብርታት ከእንቅልፍህ ስትነሣ በዓይነ ሕሊናህ ልታይ ትችላለህን? ማንም ሰው ታመመ ወይም ሞተ ሲባል አትሰማም። የምታፈቅራቸውና በሞት የተለዩህ ሰዎች እንኳን በትንሣኤ ተመልሰው አግኝተሃቸዋል። (ኢሳይያስ 35:5, 6፤ ዮሐንስ 5:28, 29) በንግድ ስግብግብነት ወይም በማይመጣጠን የኢኮኖሚ ሥርዓት የተነሣ የሚመጡ የኤኮኖሚ ጭንቀቶች የሉም። የራስህ የሆነ ምቹ ቤትና ቤተሰብህን ለመመገብ የሚያስፈልግህን ሁሉ ለማምረት የሚበቃ መሬት አለህ። (ኢሳይያስ 65:21-23) በቀንም ሆነ በማታ ጥቃት ይደርስብኛል ብለህ ሳትፈራ በማንኛውም ሰዓት መዘዋወር ትችላለህ። ጦርነቶችና ለደህንነት የሚያሰጋ ምንም ነገር የለም። እያንዳንዱ ሰው ስለ አንተ ጥቅምና ደህንነት የሚያስብ ነው። ክፉዎች የሉም። ፍቅርና ጽድቅ ሰፍኖአል። እንዲህ ዓይነቱ ጊዜ ይታይሃልን? መንግሥቲቱ የምታመጣው ይህን ዓይነቱን ዓለም ነው።—መዝሙር 37:10, 11፤ 85:10-13፤ ሚክያስ 4:3, 4
ይህ ሁሉ ሊፈጸም የማይችል ከንቱ ቅዠት ነውን? አይደለም። ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አንብብና የተባለው ነገር ሁሉ የአምላክን እርግጠኛ ተስፋ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ትገነዘባለህ። ከዚህ በፊት የእግዚአብሔር መንግሥት ለሰው ልጆች ልታደርግላቸው ስለምትችላቸውና ስለምታደርጋቸው ነገሮች የሚገልጸውን ይህን እውነተኛ መግለጫ አግኝተህ የማታውቅ ከነበረ የአምላክን ቃል የሰረቀብህ ሰው ነበር ማለት ነው።
ሁኔታዎቹ በዚሁ ዐይነት ለዘላለም የማይኖሩ መሆናቸው በጣም ያስደስተናል። ኢየሱስ በዘመናችን “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል። በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) አሁን የምታነበው መጽሔት የዚህ የስብከት ሥራ አንዱ ክፍል ነው። በሐሰት ነቢያት ከመታለል እንድትርቅ እናበረታታሃለን። ስለ አምላክ መንግሥት እውነቱን ለማወቅ የአምላክን ቃል ጠለቅ ብለህ መርምር። ከዚያም የታላቁ እረኛ የይሖዋ አምላክ ዝግጅት ለሆነችው ለዚህች መንግሥት ራስህን አስገዛ። በእውነትም የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት ናት። መምጣትዋም የማይቀር ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሉተር ሰብአዊ መንግሥታት እንደ አምላክ መንግሥት ሊታዩ እንደሚችሉ አስተምሯል
[የሥዕሉ ምንጭ]
Courtesy of the Trustees of the British Museum
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ እረኛ በመንግሥቱ አማካኝነት ማንም ሰው ሊያመጣ ያልቻላቸውን ጥሩ ሁኔታዎች ያመጣል