“ፍቅራዊ ደግነቱ አይላለች”
በጆሴ ቨርጋራ ኦሮዝኮ እንደተነገረው
በ70 ዓመት ዕድሜህ ሕይወትህ በትኩስ ኃይል ሊሞላ ይችላል ብለህ ታስባለህን? የእኔ ተሞልቷል። ይህም የሆነው ከዛሬ 35 ዓመት በፊት ነበር።
በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ከ1962 ጀምሮ በረዳት አቅኚነት አገልግያለሁ። ከ1972 ወዲህም በሜክሲኮ ጃሊስኮ ግዛት በኢል ካሪዛል የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል ቆይቻለሁ። ስለቀድሞ ሕይወቴ ጥቂት ልንገራችሁ።
በሜክሲኮ በሚቾአካን ግዛት ተወለድኩ። አባቴ ሜሰንስ የሚባሉት ሃይማኖታዊ ቡድኖች አባል ስለነበረ ቤተሰባችን ወደ ቤተክርስቲያን አይሄድም ነበር። በካቶሊክ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች አንካፈልም ነበር። በቤታችንም ውስጥ ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ምስሎች አልነበሩም።
ዕድሜዬ 16 ዓመት ሲሆን አባቴ ለሥራ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሄድ ለእኔ ግን አንድ ሰው የእጅ ሞያ እንዲያስተምረኝ ዝግጅት አደረገልኝ። ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሰውየው በወታደራዊ አካዳሚ እንድሰለጥን ወደ ሜክሲኮ ከተማ ይዞኝ ሄደ። ከዚያ በኋላ በሜክሲኮ ሠራዊት ውስጥ ሥራ ጀመርኩ።
በሠራዊቱ ውስጥና ከዚያ በኋላ
በ1910 ለጀመረው የሜክሲኮ አብዮት ተዋግቻለሁ። በአካዳሚው ውስጥ የነበርነው ወጣቶች በሙሉ የፖርፊሪዮ ዲያዝን አምባገነን አገዛዝ ይቃወም የነበረውን አብዮተኛ ፍራንሲስኮ አይ ማዴሮን ደገፍን። ማዴሮ በ1913 እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ደግፈነው ነበር። ከዚያ በኋላ ከ1915 እስከ 1920 ድረስ የሪፑብሊኩ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገለውን ቬኑስቲያኖ ካራንዛን ደገፍን። ካራንዚስታስ ተብለን ተጠራን።
በአራት የተለያዩ ወቅቶች ከሠራዊቱ ለመውጣት ወይም ለመሰናበት ሞክሬ ሳይሳካልኝ ቀርቶአል። በመጨረሻም ከድቼ ወጣሁና በየቦታው እየተባረርኩ መኖር ጀመርኩ። በዚህም ምክንያት ወደ ሜክሲኮ የተመለሰው አባቴ ታሠረ። አንድ ቀን አጐቴ ነው ብዬ እሥር ቤት ሄጄ ጠየቅሁት። ዘቦቹ እንዳይሰሙን የምንነጋገረው በትናንሽ ወረቀቶች ላይ በመጻጻፍ ነበር። ማንነቴ እንዳይታወቅ ወረቀቶቹን አኘክኋቸው።
አባቴ ከእሥር ቤት ሲለቀቅ ሊጠይቀኝ መጣና ለባለሥልጣኖች እጄን እንድሰጥ ለመነኝ። እኔም እጄን ሰጠሁ። ጉዳዩ የሚመለከተው ጄኔራል ይግረምህ ብሎ ሳያስረኝ ቀረ። ከዚህ ይልቅ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንድሄድ ሐሳብ አቀረበልኝ። እኔም ሐሳቡን ተቀብዬ ከ1916 እስከ 1926 ዩናይትድ ስቴትስ ሄጄ መኖር ጀመርኩ።
በ1923 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሜክሲካዊት ሴት አገባሁ። የሕንፃ ሥራ ተማርኩ። አንዲት ሕፃን ሴት ልጃችን አድርገን ማሳደግ ጀመርን። የ17 ወር ልጅ፤ ስትሆን ወደ ሜክሲኮ ተመለስን። መኖሪያችንን በጃልፓ ታባስኮ አደረግን። ከዚያም ‘የክርስቴሮ ዐመጽ’ ተነሣና ከ1926 እስከ ድረስ 1929 ቆየ።
የክሪስቴሮ ወገኖች እንድተባበራቸው ጠየቁኝ። ይሁን እንጂ ቤተሰቤና እኔ ወደ አጉዋስካሊየንትስ ግዛት ለመሸሽ መረጥን። በሜክሲኮ ሪፑብሊክ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ ከኖርኩ በኋላ በ1956 የሕንፃ ሥራዎችን መቆጣጠር በጀመርኩበት በማታሞሮስ ታማሊፖሊስ የተደላደለ ኑሮ ጀመርን።
ሕይወቴ ተለወጠ
ሕይወቴ መለወጥ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ያገባችው ልጄ ከምትኖርበት ከዩናይትድ ስቴትስ ብራውንስቪል ቴክሳስ ዘወትር እየመጣች ትጠይቀን ነበር። አንድ ቀን እንዲህ አለች፦ “አባዬ በአሁኑ ጊዜ በሕብረት አዳራሽ ብዙ ሰዎች ተሰብስበዋል። እንሂድና ምን አይነት ስብሰባ እንደሆነ እንይ” አለችኝ። የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ነበር። ሴት ልጄ፣ ባሏ፣ የልጅ ልጄ፣ ሚስቴና እኔ በሁሉም የአራት ቀን ስብሰባ ላይ ተገኘን።
ከዚያ ዓመት ጀምሮ በይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘት ጀመርን። ልጄ በዩናይትድ ስቴትስ መንፈሣዊ መሻሻል ስታደርግ እኔም በሜክሲኮ መንፈሳዊ ዕድገት ሳደርግ ቆየሁ። ወዲያውኑ ስለምማራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለሥራ ባልደረቦቼ መናገር ጀመርኩ። ከእያንዳንዱ እትም አሥር አሥር የመጠበቂያ ግንብና ንቁ! የመጽሔቶችን እወስድና ለሥራ ባልደረቦቼ አድል ነበር። በቢሮአችን ውስጥ ከሚሰሩት ሰዎች መካከል አምስት ሰዎች እንዲሁም ሦስት መሐንዲሶችና ሌሎች ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።
ታህሣሥ 19, 1959 ወንዝ ውስጥ በተጠመቅሁ ዕለት በጣም ይበርድ ነበር! ያን ዕለት የተጠመቁ ሁሉ በከፍተኛው ብርዳም የአየር ጠባይ ምክንያት ታመሙ። ልጄ የተጠመቀችው እኔ ከመጠመቄ በፊት ነበር። ሚስቴም ባትጠመቅም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ወደማወቅ ደረጃ ደርሳ ስለነበር በጣም ትተባበረኝ ነበር።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
ለፍቅራዊ ደግነቱ የአምላክ ባለዕዳ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ስለዚህ የካቲት 1962 በ75 ዓመት ዕድሜዬ አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1968 ሚስቴ ሞተች። በዚህ ጊዜ ሌላ አገር ሄጄ ለማገልገል ፈልጌ ነበር። ወንድሞች ግን በዕድሜዬ መግፋት ምክንያት የኔ መሄድ ተገቢ አልመሰላቸውም። ይሁን እንጂ በ1970 አንድ አነስተኛ ጉባኤ ባለበት በጃሊስኮ ግዛት በኮሎትላን አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ።
መስከረም 1972 የክልል የበላይ ተመልካቹ በኮሎትላን አቅራቢያ ወደምትገኘው ኢልካሪዛ የምትባል ትንሽ ከተማ እንድዛወር ሐሳብ አቀረበልኝ። በዚያ ዓመት በህዳር ወር ውስጥ እዚያች ከተማ ውስጥ ጉባኤ ተቋቋመና እኔም ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ። ፈንጠር ብላ የምትገኝ ከተማ ብትሆንም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እስከ 31 ሰዎች ይገኙ ነበር።
እርጅና ቢጫነኝም እንኳ ሰዎች እምነታቸውን በምክንያታዊነት እንዲመረምሩ በመርዳት አሁንም በአገልግሎት በንቃት እካፈላለሁ። ለምሳሌ ያህል ቅን የሆኑ ካቶሊኮች መቁጠሪያቸውን እየቆጠሩ “ፀጋ የሞላብሽ ማርያም ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” እያሉ “እመቤቴ ማርያም ሆይ” የሚባለውን ጸሎት ይደግማሉ። ጸሎቱ በመቀጠል “ቅድስት ማርያም የአምላክ እናት” ይላል። እኔም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አምላክ ማርያምን የሚያድናት ከሆነ እንዴት ልጇ ሊሆን ይችላል?” ብዬ እጠይቃቸዋለሁ።
አሁን 105 ዓመቴ ነው። በኤል ካሪዛል ጃሊስኮ ወደ ሃያ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የዘወትር አቅኚና ሽማግሌ ሆኜ አገልግያለሁ። እነዚህን ሁሉ ዓመታት በሕይወት የቆየሁት ሳላገለግል ላጠፋሁት ጊዜ ማካካሻ እንዲሆን የይሖዋ ፈቃድ ሆኖ ነው ብዬ አስባለሁ።
አንድ የተማርኩት ነገር ቢኖር ታላቁ ዳኛችን ከጻድቅ ዙፋኑ ላይ ሆኖ እየተመለከተን እንዳለና የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያቀርብልን ትምክህት ሊኖረን እንደሚገባ ነው። መዝሙር 117:2 እንደሚለው “ምሕረቱ (ፍቅራዊ ደግነቱ) በእኛ ላይ ጸንታለች (አይላለች)።”