የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 4/15 ገጽ 7-11
  • ዜጋም ሆንክ ባዕድ አምላክ ይቀበልሃል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዜጋም ሆንክ ባዕድ አምላክ ይቀበልሃል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘የምድር ነገዶች ሁሉ ራሳቸውን ይባርካሉ’
  • ለባዕዳን የተደረገላቸው አቀባበል
  • ወደ ሰማይ የሚወሰዱ እሥራኤላውያን
  • በትንቢት የተነገረላቸው መጻተኞች
  • በእውነተኛው አምልኮ አንድ የሆኑ “ጊዜያዊ ነዋሪዎች”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • “የአምላክ እስራኤል” እና “እጅግ ብዙ ሰዎች”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • መጻተኞች ወደ አምላክ የጸሎት ቤት ተሰበሰቡ
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
  • ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ተራፊዎች
    በሕይወት ተርፎ ወደ አዲስ ምድር መግባት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 4/15 ገጽ 7-11

ዜጋም ሆንክ ባዕድ አምላክ ይቀበልሃል

“በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ።”​—ሥራ 17:26

1. በዛሬው ጊዜ ከባዕድ አገርና ባሕል የመጡ ሰዎችን በመቀበል ረገድ በብዙ ቦታዎች የሚያጋጥመው አስቸጋሪ ሁኔታ ምንድን ነው?

እንግዶችን፣ ስደተኞችንና ጥገኞችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በብዙ አገሮች አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የዜና ዘገባዎች ያመለክታሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስያ፣ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ አገሮች ለመውጣት በጣም ይፈልጋሉ። ለመውጣት የሚፈልጉት ከድህነት ቀንበር፣ ከእርስ በርስ ጦርነት ወይም ከስደት ለመሸሽ ሲሉ ይሆናል። ይሁንና በሚሄዱበት ቦታስ ጥሩ አቀባበል ያገኛሉን? ታይም መጽሔት “የአውሮፓ የዘር ስብጥር እየተለወጠ ሲሄድ አንዳንድ አገሮች ከዚህ በፊት ያስቡ እንደነበረው የባዕድ ባሕሎችን ችለው መኖር እያቃታቸው እንደሄደ ተገንዝበዋል” በማለት አትቷል። ታይም 18,000,000 ስለሚያክሉት “ያልተፈለጉ” ስደተኞች ሲናገር “ተደላድለው ለሚኖሩ ብሔራት የሚፈጥሩት ተፈታታኝ ሁኔታ በቀላሉ ለመላቀቅ የሚቻል አይደለም” ብሏል።

2, 3. (ሀ) ተቀባይነት በማግኘት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን የሚያጽናና ማረጋገጫ ይሰጣል? (ለ) አምላክ ከሕዝቦቹ ጋር ስላለው ግንኙነት ቅዱሳን ጽሑፎች የሚገልጹአቸውን ታሪኮች በመመርመር ልንጠቀም የምንችለው ለምንድን ነው?

2 በዚህ ረገድ የሚከሰተው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አንድ ሰው የአንድ አገር ተወላጅ የሆነ ዜጋም ይሁን ወይም መጤ ወይም ስደተኛ አምላክ የሁሉንም አገር ሕዝቦች እንደሚቀበል ይገልጻል። (ሥራ 10:34, 35) ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ‘እንዴት አምላክ የሁሉንም አገር ሕዝቦች ይቀበላል ልትሉ ትችላላችሁ? አምላክ ሌሎቹን ሕዝቦች በሙሉ አግልሎ የጥንቶቹን እሥራኤላውያን ብቻ ሕዝቦቹ አድርጎ አልመረጠምን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።

3 አምላክ ከጥንቱ የእሥራኤል ሕዝብ ጋር የነበረውን ግንኙነት እስቲ እንመልከት። እግረ መንገዳችንንም በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን እውነተኛ አምላኪዎች የሚመለከቱ አንዳንድ ትንቢቶችን ልንመረምር እንችላለን። ይህን ትንቢት መመርመር በጣም አበረታች የሆነ የተሟላ ማስተዋል ሊያስገኝላችሁ ይችላል። በተጨማሪም አምላክ “ከሕዝብና ከነገድ፣ ከወገንም ከቋንቋም” ከተውጣጡ ግለሰቦች ጋር ከታላቁ መከራ በኋላ የሚኖረውን ግንኙነት ይጠቁማል።​—ራእይ 7:9, 14-17

‘የምድር ነገዶች ሁሉ ራሳቸውን ይባርካሉ’

4. የዜግነት ችግር የጀመረው እንዴት ነው? አምላክስ ምን እርምጃዎችን ወስዷል?

4 ከኖህ የጥፋት ውሃ እንዳበቃ በመላው ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩት የሰው ዘሮች የኖህ የቅርብ ቤተሰቦች ብቻ ነበሩ። ሁሉም የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች ነበሩ። ይሁንና ያ የአምልኮ አንድነት ወዲያውኑ ደፈረሰ። ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ችላ ብለው ግንብ መሥራት ጀመሩ። ይህም ድርጊት የሰው ልጆች በተለያዩ የቋንቋ ቡድኖች እንዲከፋፈሉ አደረገ። እነዚህም የቋንቋ ቡድኖች በመላው ምድር ተበታትነው የተለያዩ ሕዝቦችና ብሔሮች ሆኑ። (ዘፍጥረት 11:1-9) ቢሆንም እውነተኛው አምልኮ ወደ አብርሃም በሚያደርሰው የዘር ግንድ ቀጥሏል። አምላክ ታማኙን አብርሃምን ባረከውና ዘሩ ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን ቃል ገባለት። (ዘፍጥረት 12:1-3) ያም ታላቅ ሕዝብ የጥንቱ የእሥራኤል ሕዝብ ነው።

5. ሁላችንም አምላክ ለአብርሃም ካደረጋቸው ነገሮች ማበረታቻ ልናገኝ የምንችለው ለምንድን ነው?

5 ይሁን እንጂ የይሖዋ ዓላማ የሰው ልጆችን በሙሉ የሚያጠቃልል ስለነበረ እሥራኤልን መምረጡ የቀሩትን ሕዝቦች ገሸሽ ማድረጉ አልነበረም። ይህንንም አምላክ “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና” ሲል ለአብርሃም ከገባለት ቃል ለመረዳት እንችላለን። (ዘፍጥረት 22:18) ቢሆንም አምላክ ለብዙ መቶ ዘመናት ለእሥራኤል ሕዝብ ብሔራዊ ሕግና ደንብ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሥዋዕት የሚቀርብበትን የክህነት ሥርዓትና የሚኖሩበትን የተስፋይቱን ምድር በመስጠት ከእነርሱ ጋር የተለየ ግንኙነት ነበረው።

6. ከእሥራኤል ሕዝብ ጋር የተደረጉት ዝግጅቶች ለሁሉም የሰው ዘሮች የሚጠቅሙ የነበሩት እንዴት ነው?

6 አምላክ ለእሥራኤል የሰጠው ሕግ የሰውን ኃጢአተኛነት ስለሚያጋልጥና የሰውን ኃጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ የሚሸፍን ፍጹም መሥዋዕት የሚያስፈልግ መሆኑን ስለሚያሳይ ለሁሉም ብሔር ሕዝቦች ጠቀሜታ ነበረው። (ገላትያ 3:19፤ ዕብራውያን 7:26-28፤ 9:9፤ 10:1-12) ሆኖም ሁሉም አሕዛብ ራሳቸውን የሚባርኩበት የአብርሃም ዘር እንደሚመጣና ተፈላጊዎቹን ብቃቶች እንደሚያሟላ ምን ዋስትና ነበር? በዚህም ረገድ ለእሥራኤል የተሰጠው ሕግ ጠቅሞአል። ሕጉ ከሥነ ምግባር ውጭ በሆኑ ልማዶች ከታወቁትና ልጆቻቸውን ከነሕይወታቸው የማቃጠልን የመሰሉ አረመኔያዊ የሃይማኖት ሥርዓቶችን ይፈጽሙ ከነበሩት የከነዓን ሕዝቦች ጋር መጋባትን ከልክሏል። (ዘሌዋውያን 18:6-24፤ 20:2, 3፤ ዘዳግም 12:29-31፤ 18:9-12) አምላክ እነዚህ ሕዝቦችና ልማዶቻቸው መጥፋት እንዳለባቸው ወሰነ። ይህም ዘሩ እንዳይበከል ስለሚከላከል የሰው ልጆችን በሙሉ መጻተኛውንም ጭምር የሚጠቅም ነበር።​—ዘሌዋውያን 18:24-28፤ ዘዳግም 7:1-5፤ 9:5፤ 20:15-18

7. አምላክ እንግዶችን እንደሚቀበል የሚያሳይ ምን የጥንት ምሳሌ አለ?

7 ሕጉ በሥራ ላይ በነበረበትና አምላክም እሥራኤልን እንደ ልዩ ሕዝብ ይመለከት በነበረበት ጊዜም እሥራኤላውያን ላልሆኑ ሰዎች ምህረት አሳይቷል። እሥራኤላውያን ላልሆኑ ሰዎች ምህረት አሳይቷል። እሥራኤላውያን ላልሆኑ ሰዎች ምህረት ለማሳየት የነበረው ፈቃደኛነት እሥራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ወጥተው ወደራሳቸው ምድር ለመሄድ በወጡበት ጊዜ ታይቷል። “ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ ከእነርሱ ጋር ወጡ።”(ዘጸአት 12:38) ፕሮፌሰር ሲ ኤፍ ኬይል እነዚህ ሕዝቦች “ብዙ ባዕዳን የሚገኙበት ጭፍራ . . . ከብዙ የተለያዩ ብሔሮች የተውጣጣ ብዙ ሠራዊት” እንደነበሩ ገልጸዋል። (ዘሌዋውያን 24:10፤ ዘኁልቁ 11:4) ብዙዎቹ እውነተኛውን አምላክ የተቀበሉ ግብፃውያን እንደነበሩ አያጠራጥርም።

ለባዕዳን የተደረገላቸው አቀባበል

8. ገባኦናውያን በአምላክ ሕዝቦች መሃል ቦታ ያገኙት እንዴት ነበር?

8 እሥራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ከወራዳዎቹ ብሔራት እንዲያነፁ አምላክ የሰጣቸውን ትዕዛዝ በሚፈጽሙበት ጊዜ አምላክ ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ይኖሩ ለነበሩት ገባኦናውያን የተባሉ ባዕዳን ልዩ ጥበቃ አድርጎአል። ገባኦናውያን ማንነታቸውን ሰውረው ከእሥራኤላውያን ጋር እርቀ ሰላም እንዲወርድ የሚለምኑ መልእክተኞች ወደ ኢያሱ ላኩ። የገባኦናውያን ዘዴ በታወቀ ጊዜ ኢያሱ “ለማህበሩና ለ[ይሖዋ (አዓት)] መሠዊያ እንጨት ለቃሚዎችና ውሃ ቀጂዎች አደረጋቸው።” (ኢያሱ 9:3-27) በዛሬው ጊዜ ብዙ ከሌላ አገር የመጡ ባዕዳን ሰዎች በአዲሱ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ዝቅተኛ የሆነ ሥራ ይቀበላሉ።

9. በእሥራኤል ምድር ይኖሩ የነበሩ እንግዶችን በሚመለከት የረአብና የቤተሰቧ ሁኔታ የሚያጽናና የሆነው ለምንድን ነው?

9 አምላክ በዚያ የጥንት ዘመን ለባዕዳን ያደረገው አቀባበል በሕዝቦች ወይም በነገዶች ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን ማወቅ ሊያጽናናችሁ ይችላል። አንዳንድ ግለሰቦችም በተናጠል ተቀባይነት አግኝተዋል። በዛሬው ጊዜ አንዳንድ መንግሥታት የሚቀበሉት ከፍተኛ ማህበራዊ ደረጃ ወይም ሥልጣን፣ ሀብት ወይም ከፍተኛ ትምህርት ያላቸውን ስደተኞች ብቻ ነው። ከገባኦናውያን አጭር ታሪክ ቀደም ብሎ በተፈጸመ አንድ ሁኔታ እንደምንመለከተው ግን ይሖዋ ስደተኞችን የሚቀበለው እንደነዚህ ባሉት መሥፈርቶች መዝኖ አይደለም። ታሪኩ ከፍተኛ ማህበራዊ ደረጃ ያልነበራት ን አንዲት ከነዓናዊት ሴት የሚመለከት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ጋለሞታይቱ ረአብ” በማለት ይጠራታል። በእውነተኛው አምላክ በማመኗ ምክንያት እሷ ከነቤተሰቧ ከኢያሪኮ ጥፋት ድናለች። ረአብ ባዕድ ሴት ብትሆንም እሥራኤላውያን ተቀብለዋታል። እሷም ለሁላችንም ጥሩ የእምነት ምሳሌ ሆናለች። (ዕብራውያን 11:30, 31, 39, 40፤ ኢያሱ 2:1-21፤ 6:1-25) እንዲያውም የመሲሑ ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች።​—ማቴዎስ 1:5, 16

10. እሥራኤላውያን ለእንግዶች የሚያደርጉት አቀባበል በምን ላይ የተመካ ነበር?

10 እሥራኤላውያን ያልሆኑ ባዕዳን በተስፋይቱ ምድር ተቀባይነት የሚኖራቸው እውነተኛውን አምላክ ለማስደሰት በሚያደርጉት ጥረት መሠረት ነበር። እሥራኤላውያን ይሖዋን ከማያገለግሉ ባዕዳን ጋር እንዳይወዳጁ በተለይም ሃይማኖታዊ ቅርርቦሽ እንዳያደርጉ ተነግሯቸው ነበር። (ኢያሱ 23:6, 7, 12, 13፤ 1 ነገሥት 11:1-8፤ ምሳሌ 6:23-28) ያም ሆኖ እሥራኤላውያን ያልሆኑ ብዙ ሠፋሪዎች መሠረታዊ ሕጎችን ይታዘዙ ነበር። ሌሎች ደግሞ የተገረዙና አይሁዳዊነትን የተቀበሉ ሆነዋል። ይሖዋም የማህበሩ አባሎች አድርጎ ሙሉ በሙሉ ተቀብሏቸዋል።​—ዘሌዋውያን 20:2፤ 24:22፤ ዘኁልቁ 15:14-16፤ ሥራ 8:27a

11, 12. (ሀ) እሥራኤላውያን ከባዕዳን አገሮች የመጡ አምላኪዎችን እንዴት መያዝ ነበረባቸው? (ለ) የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ረገድ መሻሻል የሚያስፈልገን ለምን ሊሆን ይችላል?

11 እሥራኤላውያን ባዕዳን ለሆኑ አምላኪዎች ባላቸው አመለካከት ረገድ አምላክን የሚመስሉ እንዲሆኑ እንደሚከተለው በማለት አዟቸዋል፦ “በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ሆኖ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፤ እርሱንም እንደራስህ ውደድ።” (ዘሌዋውያን 19:33, 34፤ ዘዳግም 1:16፤ 10:12-19) እኛም በሕጉ ሥር የምንኖር ባንሆንም ከዚህ ትዕዛዝ ትምህርት እናገኛለን። ከሌላ ዘር፣ ብሔር ወይም ባሕል በመጡ ሰዎች ላይ አግባብ የሌለው ጥላቻ በማሳደር ስሜት ለመሸነፍ ቀላል ነው። ስለዚህ “የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ከእንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ ራሴን ለማላቀቅ እየጣርኩ ነውን?” ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ መልካም ነው።

12 እሥራኤላውያን አምላክ እሱን ለማምለክ የሚፈልጉ የባዕድ አገር ሰዎችን በሞቀ ስሜት እንደሚቀበል የሚያረጋግጥ የሚታይ ማስረጃ ነበራቸው። ንጉሥ ሰሎሞን “ከሕዝብህም ከእሥራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን . . . ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፣ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እሥራኤል ይፈሩህ ዘንድ . . . እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ” በማለት ጸልዮአል።​—1 ነገሥት 8:41-43፤ 2 ዜና መዋዕል 6:32, 33

13. አምላክ ከእሥራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመለወጥ ዝግጅት ያደረገው ለምንድን ነው?

13 በዚያ ዘመን ይሖዋ የመሲሑን የዘር መሥመር ለመጠበቅ ይጠቀም የነበረው በእሥራኤል ብሔር ቢሆንም ታላቅ ትርጉም የሚኖራቸው ለውጦች እንደሚመጡ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ቀደም ሲል እሥራኤላውያን ከአምላክ ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት በተስማሙ ጊዜ “የንጉሥ ካህናትና የተቀደሰ ሕዝብ” የሚያስገኙ ሕዝቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6) የእሥራኤል ሕዝብ ግን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት እምነተ ቢሶች ሆነዋል። ስለዚህ ይሖዋ “ለእሥራኤል ቤት” ከበደላቸውና ከኃጢአታቸው ይቅርታ የሚያስገኝ አዲስ ኪዳን እንደሚያቋቁም ተነበየ። (ኤርምያስ 31:33, 34) ይህ አዲስ ኪዳን የሚቋቋመው ብዙዎችን ከኃጢአታቸው የሚያነፃ መሥዋዕት የሚያቀርበው መሲሕ ሲመጣ ነው።​—ኢሳይያስ 53:5-7, 10-12

ወደ ሰማይ የሚወሰዱ እሥራኤላውያን

14. ይሖዋ የተቀበለው የትኛውን አዲስ “እሥራኤል” ነው? እንዴትስ?

14 ይህ ሁሉ እንዴት እንደተፈጸመ ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ለመረዳት እንችላለን። በመሥዋዕታዊ ሞቱ አማካኝነት ሕጉን የፈጸመውና የተሟላ የኃጢአት ይቅርታ የሚገኝበትን መሠረት የጣለው መሲሑ ኢየሱስ ነው። አንድ ሰው ከዚህ መስዋዕታዊ ሞት ተጠቃሚ ለመሆን በሥጋ የተገረዘ አይሁድ መሆን አያስፈልገውም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ “በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ” ሆኖ እንደሚቆጠርና “መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ” እንዳልሆነ ጽፏል። (ሮሜ 2:28, 29፤ 7:6) በኢየሱስ መሥዋዕት ያመኑ ሰዎች ይቅርታ አግኝተዋል። አምላክም “የእግዚአብሔር እሥራኤል” ተብሎ የሚጠራውን መንፈሳዊ ሕዝብ ያስገኙ ‘መንፈሳዊ አይሁድ’ አድርጎ ተቀብሎአቸዋል።​—ገላትያ 6:16

15. የመንፈሳዊ እሥራኤል አባል ለመሆን ሥጋዊ ዜግነት ወሳኝ ያልሆነው ለምንድን ነው?

15 አዎን፣ መንፈሳዊ እሥራኤል መሆን የአንድ ዓይነት ብሔር ወይም ጎሣ አባል በመሆን ላይ የተመካ አልነበረም። እንደ ኢየሱስ ሐዋርያት የመሰሉት አንዳንድ የመንፈሣዊ እስራኤል አባላት ሥጋዊ አይሁድ ነበሩ። እንደ መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ የመሳሰሉት ሌሎች መንፈሳዊ እስራኤላውያን ደግሞ ያልተገረዙ አሕዛብ ነበሩ። (ሥራ 10:34, 35, 44-48) ጳውሎስ መንፈሳዊ እሥራኤልን በሚመለከት “በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊ እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም” ሲል በትክክል ተናግሯል። (ቆላስይስ 3:11) በአምላክ መንፈስ የተቀቡት ሰዎች “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ሆኑ።​—1 ጴጥሮስ 2:9፤ ከዘጸአት 19:5, 6 ጋር አወዳድሩ

16, 17. (ሀ) መንፈሳዊ እሥራኤላውያን በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ እሥራኤል ክፍል ያልሆኑትን ሰዎች ሁኔታ መመልከት ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?

16 ታዲያ መንፈሳዊ እሥራኤላውያን በወደፊቱ የአምላክ ዓላማ ውስጥ ምን ድርሻ ይኖራቸዋል። ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ “አንተ ታናሽ መንጋ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ሉቃስ 12:32) ‘አገራቸው (ዜግነታቸው) በሰማይ የሆኑት’ ቅቡአን ከበጉ ጋር በመንግሥታዊ አገዛዙ ተባባሪ ወራሾች ይሆናሉ። (ፊልጵስዩስ 3:20፤ ዮሐንስ 14:2, 3፤ ራእይ 5:9, 10) እነሱ “ከእሥራኤል ልጆች የታተሙ”ና “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ” መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ቁጥራቸው 144,000 ነው። ይሁን እንጂ ዮሐንስ የእነዚህን የታተሙ ሰዎች ቁጥር ከገለጸ በኋላ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ከሚገኙበት የተለየ ቡድን ጋር ያስተዋውቀናል።​—ራእይ 7:4, 9፤ 14:1-4

17 አንዳንድ ሰዎች እንደሚከተለው ብለው ይጠይቁ ይሆናል፦ ‘የመንፈሳዊ እሥራኤል ክፍል ያልሆኑትና እጅግ ብዙ ሰዎች በመሆን ከታላቁ መከራ የሚያልፉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ? በዛሬው ጊዜ ካሉት ጥቂት የመንፈሳዊ እሥራኤል ቀሪዎች አንፃር ምን ድርሻ ይኖራቸዋል?’b

በትንቢት የተነገረላቸው መጻተኞች

18. እሥራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ እንዲመለሱ ያስቻላቸው ምንድን ነው?

18 እሥራኤላውያን በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ሳሉ ለቃል ኪዳኑ ታማኝ ወዳልሆኑበት ጊዜ መለስ ብለን ስንመለከት ባቢሎናውያን እሥራኤልን እንዲያጠፉ አምላክ የወሰነበት ጊዜ እንደነበረ እንገነዘባለን። በ607 ከዘአበ እሥራኤላውያን ለ70 ዓመታት ምርኮኞች ሆነው ወደኖሩበት ወደ ግዞት ተወሰዱ። ከዚያም አምላክ ሕዝቡን መልሶ ዋጃቸው። በገዢው በዘሩባቤል አመራር ሥር የሥጋዊ እሥራኤል ቀሪዎች ወደ አገራቸው ተመለሱ። ባቢሎንን የገለበጧት የሜዶንና የፋርስ መሪዎችም እንኳን ወደ አገራቸው የሚመለሱትን ምርኮኞች በአንዳንድ ዝግጅቶች ረድተዋቸዋል። የኢሳይያስ መጽሐፍ ስለእነዚህ ሁኔታዎች ተንብዮ ነበር። (ኢሳይያስ 1:1-9፤ 3:1-26፤ 14:1-5፤ 44:21-28፤ 47:1-4) ዕዝራም ስለተመለሱበት ሁኔታ ዝርዝር መግለጫ ሰጥቶናል።​—ዕዝራ 1:1-11፤ 2:1, 2

19. ከእሥራኤላውያን መመለስ ጋር በተያያዘ ጉዳይ እንግዶችም ተካፋይ እንደሚሆኑ የሚያመለክት ምን ትንቢታዊ ፍንጭ አለ?

19 ኢሳይያስ ስለአምላክ ሕዝቦች እንደገና መዋጀትና መመለስ “አሕዛብ ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ” የሚል አስገራሚ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 59:20፤ 60:3) ይህም አምላክ ከሰሎሞን ጸሎት ጋር በመስማማት የሚቀበላቸው ሰዎች ከግለሰብ እንግዶች ወይም መጻተኞች የሚበዙ ይሆናሉ ማለት ነው። ኢሳይያስ አንድ ያልተለመደ የሁኔታ ለውጥ እንደሚኖር ነበር። “አሕዛብ” ከእሥራኤል ልጆች ጋር ሆነው እንደሚያገለግሉ ሲያመለክት “በቁጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና መጻተኞች (እንግዶች) ቅጥርሽን ይሠራሉ፣ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል”​—ኢሳይያስ 60:10

20, 21. (ሀ) በዘመናችን እሥራኤላውያን ከምርኮ ከመመለሳቸው ጋር የሚመሳሰል ምን ሁኔታ እናገኛለን? (ለ) ከዚያ ወዲህ ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆች’ በመንፈሳዊ እሥራኤላውያን ላይ የተጨመሩት እንዴት ነው?

20 እሥራኤላውያን ወደ ምርኮ መወሰዳቸውና ከዚያም መመለሳቸው በብዙ መንገድ ከዘመናችን የመንፈሳዊ እሥራኤል ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት ቅቡአን ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ ከአምላክ ፈቃድ ጋር አልተስማሙም ነበር። ገና ያልተዉአቸው አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና አመለካከቶችና ልማዶች ነበሩ። ከዚያም የጦርነት መንፈስ በተፋፋመበት ጊዜ የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ግንባር ቀደም መሪዎች በቀሳውስት ቆስቋሽነት ፍትሕ በጎደለው ሁኔታ ታሠሩ። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በ1919 ቃል በቃል በእሥር ቤት የነበሩት እነዚያ ቅቡአን ክርስቲያኖች ከማንኛውም ወንጀል ነፃ ወጥተው ከእስር ቤት ተለቀቁ። ይህም የአምላክ ሕዝቦች ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ መውጣታቸውን የሚያመለክት ክንውን ነበር። የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ገነትን ለማስፋፋትና በዚህም መንፈሳዊ ገነት ለመኖር ከታላቂቱ ባቢሎን ወጡ።​—ኢሳይያስ 35:1-7፤ 65:13, 14

21 ይህም በሚቀጥለው የኢሳይያስ መግለጫ ላይ ተመልክቷል፦ “ዓይኖችሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፣ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ አይተሽ ደስ ይልሻል፣ ልብሽም ይደነቃል፣ ይሰፋማል።” (ኢሳይያስ 60:4, 5) ከ1919 ወዲህ በነበሩት አሥርተ ዓመታት “ወንዶችና ሴቶች ልጆች” በመምጣትና በመንፈስ በመቀባት በመንፈሳዊ እሥራኤል ውስጥ የቀሩትን የመጨረሻ ቦታዎች ሞልተዋል።

22. “እንግዶች” ከመንፈሳዊ እሥራኤላውያን ጋር አብረው ለመሥራት የመጡት እንዴት ነው?

22 “ቅጥርሽን ይሠራሉ” የተባለላቸው መጻተኞችና እንግዶችስ? ይህም በዘመናችን ተፈጽሟል። የ144,000ዎቹ ጥሪ ወደማብቃቱ ሲቃረብ ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ከመንፈሳዊ እሥራኤል ጋር ለማምለክ መጉረፍ ጀመሩ። እነዚህ አዳዲስ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። ወደፊት የታማኝነት አገልግሎት የሚያቀርቡበት ቦታ ቅቡአኑ ከሚያገለግሉበት ቦታ የተለየ ቢሆንም የመንግሥቲቱን የምሥራች በመስበክ ሥራ ቅቡአን ቀሪዎችን ለመርዳት ደስተኞች ናቸው።​—ማቴዎስ 24:14

23. “እንግዶች” ቅቡአኑን የረዱአቸው ምን ያህል ነው?

23 በዛሬው ጊዜ ከ4,000,000 በላይ የሚሆኑ “መጻተኞች” “አገራቸው (ዜግነታቸው) በሰማይ” ከሆኑት ቀሪዎች ጋር ሆነው ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው። ከመካከላቸውም ብዙዎቹ የጾታና የዕድሜ ልዩነት ሳያግዳቸው የሙሉ ጊዜ አቅኚዎች በመሆን እያገለገሉ ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ መጻተኞች ከ66,000 በላይ ከሚሆኑት ጉባኤዎች በአብዛኞቹ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በመሆን በሐላፊነት በማገልገል ላይ ናቸው። ቀሪዎቹ የሚቀጥሉት የኢሳይያስ ቃላት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ በማየታቸው ይደሰታሉ፦ “መጻተኞች ቆመው በጎቻችሁን ያሠማራሉ፣ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል።”​—ኢሳይያስ 61:5

24. አምላክ በቀድሞ ዘመን ይኖሩ ለነበሩት እስራኤላውያንና ለሌሎችም ባደረገው አያያዝ ልንጽናና የምንችለው እንዴት ነው?

24 ስለዚህ በየትኛውም ምድራዊ ብሔር የምትኖር ዜጋ፣ ስደተኛ ወይም ጥገኛ ብትሆን ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ልባዊ አቀባበል የሚያደርግልህ መንፈሳዊ መጻተኛ የመሆን ታላቅ አጋጣሚ አለህ። አምላክ የሚያደርግልህ አቀባበል በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት በእሱ አገልግሎት ውስጥ ዘላለማዊ መብት የማግኘት አጋጣሚ ይከፍትልሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a “በመጻተኛ”፣ “በሠፋሪ”፣ “በእንግዳ”ና “በባዕድ” መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ መመርመር የተሰኘውን በኒውዮርክ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር የተዘጋጀውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 72-5፣ 849-51 ተመልከት።

b የይሖዋ ምስክሮች በ1991 ባከበሩት የጌታ ራት ዓመታዊ መታሰቢያ ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር ከ10,600,000 በላይ ሲሆን የመንፈሳዊ እሥራኤል ቀሪዎች እንደሆኑ የተገለጹት ግን 8,850 ብቻ ነበሩ።

ይህን ተገንዝበሃልን?

◻ አምላክ ከማንኛውም ብሔር የተውጣጡ ሰዎች በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ቃል የገባው እንዴት ነበር?

◻ የአምላክ ልዩ ሕዝቦች ከነበሩት ከእሥራኤላውያን በቀር ሌሎች ሰዎችም አምላክን ሊቀርቡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

◻ እንግዶች ከእስራኤላውያን ጋር እንደሚተባበሩ በትንቢት የተገለጸው እንዴት ነው?

◻ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ከመመለሳቸው ጋር የሚመሳሰል ምን አይነት ሁኔታ ተፈጽሞአል? በዚህስ ጉዳይ “እንግዶች” የተካፈሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ሰሎሞን ወደፊት ይሖዋን ለማምለክ ስለሚመጡ እንግዶች ጸልዮአል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ