የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 4/15 ገጽ 23-25
  • በፍቅር ላይ የተመሠረተ ጥብቅ ምክር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በፍቅር ላይ የተመሠረተ ጥብቅ ምክር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኮብልሎ የነበረው ተመለሰ
  • ነገሮችን በፍቅር መፍታት
  • የዘመናችን ክርስቲያኖች የሚያገኙአቸው ትምህርቶች
  • የወንድማማች ፍቅር አንቀሳቃሽ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ፊልሞና እና አናሲሞስ በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተስማሙ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ጳውሎስ በሮም
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • ፊልሞና የመጽሐፉ ይዘት
    አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 4/15 ገጽ 23-25

በፍቅር ላይ የተመሠረተ ጥብቅ ምክር

በ60-61 እዘአ ገደማ አንድ ከጌታው ዘንድ ኰብልሎ የነበረ ባሪያ ሮምን ትቶ በትንሿ እስያ ደቡባዊ ምዕራብ ወደምትገኘውና የትውልድ ከተማው ወደሆነችው ወደ ቆላስይስ ለመመለስ የ900 ማይል (1440 ኪሎሜትር)ጉዞ ጀመረ። ለጌታው የሚሰጥ በእጅ የተጻፈ መልእክት ይዟል። መልእክቱ ጳውሎስ ራሱ የጻፈው ነው። ዛሬ ይህ ደብዳቤ የደብዳቤው ተቀባይ በሆነው በፊልሞና ስም የሚጠራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆኖአል።

በፊልሞና የተጻፈው ደብዳቤ ሰውን በብልሃት በማግባባትና በማሳመን ረገድ አይነተኛ ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። የፊልሞናን መልእክት በጣም ተፈላጊ የሚያደርገው ግን በዛሬ ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች የሚጠቅሙ በርከት ያሉ ተግባራዊ ትምህርቶች መያዙ ነው። ከእነዚህም ትምህርቶች አንዱ እርስ በርስ በክርስቲያናዊ ፍቅር መከባበር አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል። እስቲ ይህን አጭር፣ ነገር ግን በጣም ኃይለኛ የሆነ መልእክት የያዘውን ደብዳቤ ቀረብ ብለን እንመልከት።

ኮብልሎ የነበረው ተመለሰ

ፊልሞና በጣም ተወዳጅ የቆላስይስ ጉባኤ አባል የሆነ ክርስቲያን ነበር። (ፊልሞና 4, 5) እንዲያውም ጉባኤው ቤቱን ለመሰብሰቢያነት ይገለገል ነበር። (ቁጥር 2) በተጨማሪም ፊልሞና ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የግል ትውውቅ ነበረው። ምናልባትም ፊልሞናን ወደ ክርስትና ያመጣው ሐዋርያው ጳውሎስ ሳይሆን አይቀርም። እርግጥ፣ ጳውሎስ ራሱ ቆላስይስ ድረስ ሄዶ እንዳልሰበከ አመልክቷል። (ቆላስይስ 2:1) ይሁን እንጂ “በእስያ የኖሩት ሁሉ [ቆላስይስን ጨምሮ] የጌታን ቃል እስኪሰሙ” ድረስ ሁለት ዓመት ሙሉ በኤፌሶን በመስበክ ምሥራቹን ሰፋ ባለ አካባቢ አዳርሶአል። (ሥራ 19:10) ፊልሞናም በዚህ ጊዜ ምሥራቹን ሰምተው ከተቀበሉት ሰዎች አንዱ ሳይሆን አይቀርም።

ያም ሆነ ይህ ፊልሞና በዘመኑ እንደነበሩት ባለጸጋ ሰዎች ባሪያ ነበረው። በጥንት ጊዜ ባሪያ ሆኖ ማገልገል እንደ ውርደት አይቆጠርም ነበር። በአይሁዶችም መካከል ራስን ወይም አንድን የቤተሰብ አባል ለባርነት መሸጥ እዳ ከፍሎ ለመጨረስ የሚያስችል ተቀባይነት ያገኘ መንገድ ነበር። (ዘሌ. 25:39, 40) ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ስለ ሮማውያን ዘመን አስተያየቱን ሲሰጥ “ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ለባርነት ይሸጡ ነበር። ከሁሉ በላይ ግን ድሃ ሆኖ ከመኖር ቀላልና ዋስትና ያለው ኑሮ ለመኖር ሲሉ ራሳቸውን ባሪያ ያደርጉ ነበር። ከባሪያ ያልተወለዱ ነፃ ሰዎችም ቢሆኑ ጥሩ ሥራ ለማግኘትና ማኅበራዊ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ሲሉ ራሳቸውን ለባርነት ይሸጡ ነበር። ብዙ ሮማውያን ያልሆኑ ሰዎች የሮማውያን ሕግ በሚደነግገው መሠረት ከባርነት ነፃ በሚወጡበት ጊዜ የሮማ ዜጎች ለመሆን እንደሚችሉ ስለሚያስቡ ራሳቸውን ለሮማ ዜጎች ይሸጡ ነበር” ብሏል።

ይሁን እንጂ ከፊልሞና ባሪያዎች አንዱ የነበረው አናሲሞስ ጌታውን ከድቶ ወደ ሮም በሸሸ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጠረ። እንዲያውም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው ገንዘብ ሰርቆ ሳይሄድ አልቀረም። (ቁጥር 8) አናሲሞስም ሮማ ሳለ እስረኛ ከነበረው ከጳውሎስ ጋር ተገናኘ። “ቀድሞ ጥቅም የሌለውና ’ከአገልጋይነቱ ኰብልሎ የነበረው አናሲሞስ አሁን ክርስቲያን ሆነ። ጳውሎስንም ለመርዳት ፈቃደኛ ሆነ። በእስር ላይ የነበረውንም ሐዋርያ በሚገባ አገለገለው። አናሲሞስ የጳውሎስን የጠለቀ ፍቅር ለማግኘትና በሱም የተወደደ ወንድም ለመሆን መቻሉ አያስደንቅም!—ቁጥር 11, 12, 16

ሐዋርያው ጳውሎስ አናሲሞስ አብሮት እንዲሆን ቢያስቀረው ይፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ የአናሲሞስ ጌታ ለመሆን ሕጋዊ መብት ያለው ፊልሞና ነበር። ስለዚህ አናሲሞስ ተመልሶ ሕጋዊ ጌታውን የማገልገል ግዴታ አለበት።ታዲያ በሚመለስበት ጊዜ ፊልሞና እንዴት ይቀበለው ይሆን? በንዴት ተነሳስቶ ሕግ የሚፈቅድለትን ቅጣት ይፈጽምበት ይሆን? አናሲሞስ ክርስቲያን ሆኛለሁ የሚለው ከልቡ አይደለም ብሎ ያስብ ይሆን?

ነገሮችን በፍቅር መፍታት

ጳውሎስ ስለ አናሲሞስ ለፊልሞና ለመጻፍ ተነሣሣ። ደብዳቤውን የጻፈው በራሱ እጅ ነበር። ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው በሌላ ሰው አላስጻፈውም። (ቁጥር 19) ጥቂት ጊዜ ወስዳችሁ ለፊልሞና የተጻፈውን አጭር ደብዳቤ በሙሉ አንብቡ። ጳውሎስ ራሱን ካስተዋወቀና ለፊልሞናና ለቤተሰቡ የይሖዋንና የኢየሱስን ‘የማይገባ ቸርነትና ሰላም’ ከተመኘ በኋላ ፊልሞናን ለጌታ ለኢየሱስና ለቅዱሳን ስላሳየው ፍቅርና እምነት እንዳመሰገነው ልብ ልትሉ ትችላላችሁ።—ቁጥር 1-7

ጳውሎስ በቀላሉ በሐዋርያነት ስልጣኑ ተጠቅሞ ፊልሞና ‘የሚገባውን እንዲያደርግ ለማዘዝ’ ይችል ነበር። ሆኖም ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ‘በፍቅር ለመነው።’ በእርግጥም አናሲሞስ ክርስቲያን ወንድም መሆኑንና ለጳውሎስም በጣም ጠቃሚ አገልግሎት አበርክቶ እንደነበረ መስክሮለታል። እንዲያውም “እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ [አናሲሞስን] ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር። ነገር ግን በጐነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን ሳልማከርህ ምንም እንኳ ለማድረግ አልወደድሁም” ብሏል።—ቁጥር 8-14

ሐዋርያው ፊልሞና የቀድሞ አገልጋዩን እንደ ወንድሙ አድርጎ እንዲቀበለው ለመነው። “እንግዲህ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው”ሲል ጳውሎስ ጻፈለት። ይህ ማለት አናሲሞስ ከባርነት አገልግሎቱ ነፃ ሆኗል ማለት አልነበረም። ጳውሎስ በጊዜው የነበረውን ማኅበራዊ ሥርዓት ለመበጥበጥ ቅስቀሳ ማካሄዱ አልነበረም። (ከኤፌሶን 6:9፤ ቆላስይስ 4:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:2 ጋር አወዳድር) በአናሲሞስና በፊልሞና መካከል የነበረው የጌታና የባሪያ ግንኙነት አሁን በተፈጠረው ግንኙነት ይለዝባል ማለት ነው። ፊልሞና አናሲሞስን ‘እንደባሪያ ሳይሆን እንደተወደደ ወንድም’ ያየዋል።—ቁጥር 15-17

ሆኖም አናሲሞስ ምናልባትም በስርቆቱ ምክንያት የገባበት እዳስ? ጳውሎስ አሁንም ፊልሞናን በመካከላቸው ያለውን ወዳጅነት በማሳሰብ እንዲህ በማለት ለምኖታል፦ “በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ ይህን በእኔ ላይ ቁጠር።”ፊልሞና ጳውሎስ ከጠየቀው በላይ የይቅር ባይነት መንፈስ እንደሚያሳይ ተስፋ ስለነበረው በቅርቡ ፊልሞና ቤት ለመስተናገድ ማሰቡን እንኳ ገልጾለታል። ለጥቂት ሰዎች ሰላምታ ካቀረበና ፊልሞና “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ” እንዲሰጠው ከተመኘ በኋላ ጳውሎስ ደብዳቤውን አጠቃልሏል።—ቁጥር 18-25

የዘመናችን ክርስቲያኖች የሚያገኙአቸው ትምህርቶች

የፊልሞና መጽሐፍ ለዘመናችን ክርስቲያኖች የሚጠቅሙ ብዙ ትምህርቶች ይዞአል። አንደኛ ነገር አማኝ ጓደኛችን ከባድ በደል ቢፈጽምብን እንኳ ይቅር ባይ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ያስታውሰናል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋል” ብሏል።—ማቴዎስ 6:14

በተለይ በዛሬው ጊዜ ባሉ ክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚሠሩ ወንድሞች ከፊልሞና መጽሐፍ ብዙ ይጠቀማሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚገባውን እንዲያደርግ ፊልሞናን ለማዘዝ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ከመጠቀም መቆጠቡን ልብ ልንል ይገባል። በተጨማሪም አናሲሞስ ሮም ቀርቶ እሱን እንዲያገለግለው እንዲፈቅድለት ፊልሞናን አልጠየቀም። ጳውሎስ የሌሎችን የባለቤትነት መብት ያከብር ነበር። በተጨማሪም በባለሥልጣንነት ቢያዝዘው ፊልሞና ትዕዛዙን እንደሚፈጽምለት ቢያውቅም ከልቡ በመነጨ ስሜት ተገፋፍቶ ቢያደርግ የተሻለ እንደሚሆን ተገንዝቦአል። ከልቡ በመነጨ ስሜት ተገፋፍቶ መልካም እንዲያደርግ ስለፈለገ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ጥያቄ አቅርቦለታል።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ከመንጋው ጋር ባላቸው ግንኙነት ‘ማህበሮቻቸውን በኃይል በመግዛት’ ወይም በሻካራ ቃል በመናገርና ፈላጭ ቆራጭ በመሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት አለአግባብ መጠቀም የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:1-3) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆችም በላያቸው እንዲሰለጥኑ ታውቃላችሁ በእናንተስ እንዲህ አይደለም።” (ማቴዎስ 20:25, 26) የመንጋው አባሎች ትዕዛዝ ከሚሰጣቸው ይልቅ በፍቅር ሲጠየቁ የበለጠ እንደሚሠሩ የበላይ ተመልካቾች ተገንዝበዋል። የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸውና የተከዙ የመንጋው አባሎች ረጋ ብለው ችግሮቻቸውን የሚያዳምጡትንና ተገቢ የሆነ ምክር የሚሰጧቸውን የበላይ ተመልካቾች ያደንቃሉ።

በተጨማሪም የጳውሎስ ደብዳቤ ሽማግሌዎች አመስጋኝና ብልሃተኛ መሆናቸው ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያሳስባቸዋል። ጳውሎስ ደብዳቤውን ‘የቅዱሳን ልብ በሱ ሥራ እንዳረፈ’ በመግለጽና ፊልሞናን በማመስገን ይጀምራል። (ቁጥር 7) ይህ ከልብ የመነጨ ምስጋና ፊልሞና አናሲሞስን ለመቀበል ይበልጥ ዝግጁ እንዲሆን እንዳደረገው አያጠራጥርም። ዛሬም በተመሳሳይ ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ከልብ የመነጨ ሞቅ ያለ ምሥጋና ማከል ይቻላል። እንደዚህ ያለው ምክር ብልሃት የጐደለው መሆን የለበትም። ነገር ግን ለሚሰማው ሰው እንዲጥም “በሚገባ በጨው የተቀመመ” መሆን አለበት።—ቆላስይስ 4:6

በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኛ መሆኑን ገልጾታል። እንዲህ አለ፦ “ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ።” (ቁጥር 21) ሽማግሌዎችስ በክርስቲያን ባልንጀሮቻችሁ ላይ እንዲህ ያለ ትምክህት እንዳላችሁ ትገልጻላችሁን? ይህን ማድረጋችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለማድረግ እንዲፈልጉ ይረዳቸው የለምን? ወላጆችም ይህን ዓይነት ትምክህት በልጆቻቸው ላይ ከኖራቸው ጥሩ ውጤት ያገኛሉ። ልጆቻቸው የሚታዘዙትን መፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን በፈቃደኝነት መታዘዛቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ልጆቻቸውን ማመንና ማክበር ይገባቸዋል። ወላጆች ልጆችን በሚያዙበት ወይም አንድ ነገር እንዲያደርጉላቸው በሚጠይቁበት ጊዜ የፍቅርንና የደግነትን ስሜት በሚገልጽ አነጋገር ቢጠይቋቸው ጥሩ ነው። ራሳቸውን በልጆቻቸው ቦታ አድርገው መመልከትና

ለሚሰጡት ትዕዛዝና ሕግ ምክንያት መስጠት ይገባቸዋል። ልጆች የሚያስመሰግን ነገር ሲያደርጉ ማመስገን ያስፈልጋል። ከመጠን በላይ ከመተቸትና በተለይም በሰዎች ፊት ከመውቀስ መቆጠብ አለባቸው።

በዚህ ረገድ ባሎችም ምክንያታዊና ደግ፣ ሚስቶቻቸውንም ለማመስገን ዝግጁ የመሆንን ባህሪ ሊያሳዩ ይችላሉ። ይህን ሲያደርጉ ሚስቶቻቸው በደስታ ይገዙላቸዋል። መገዛታቸውም እረፍትና ደስታ የሚያስገኝላቸው ይሆናል።—ምሳሌ 31:28፤ ኤፌሶን 5:28

ፊልሞና ለጳውሎስ ደብዳቤ ምን ምላሽ እንደሰጠ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ የጳውሎስ ትምክህት ከንቱ ሆኖአል ብለን ለመገመት አንችልም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ወላጆችና ባሎችም በተመሳሳይ በማስገደድ ወይም የግዴታ ትእዛዝ በመስጠት ሳይሆን በፍቅር በመምከር ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት የተሳካ ውጤት ሊያገኙ ይችላሉ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ፊልሞናን በሐዋርያነት ሥልጣኑ ተጠቅሞ ከማዘዝ ይልቅ በክርስቲያናዊ ፍቅር ለመነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ