የ1914 ትውልድ ትልቅ ትርጉም የነበረው ለምንድን ነው?
“ከዓመታት በፊት ጀምሮ ይህ ትውልድ አሰቃቂ ወደ ሆነ የችግር ዘመን ውስጥ እንደሚገባ ጠብቀን እንደነበር አንባቢዎቻችን ያውቃሉ። ይህም ዘመን ከጥቅምት 1914 ብዙ ሳይርቅ በድንገት እንደሚፈነዳ እንጠብቃለን።”—መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነገሪ ግንቦት 15, 1911
በዚያን ጊዜ መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ይባል የነበረው መጽሔት (አሁን የአምላክን መንግሥት የሚያስታውቀው መጠበቂያ ግንብ የሚባለው) 1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ተለይቶ የሚታወቅ ዓመት መሆኑ በተደጋጋሚ ገልጾ ነበር። ይህ ዓመት በተቃረበ ጊዜም አሰቃቂ የሆነ የችግር ጊዜ እንደሚመጣ ለአንባቢዎች ተገልጾ ነበር።
ይህን የገለፁት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱት “ሰባት ዘመናት” እና “የአሕዛብ ዘመናት” ላይ በነበራቸው ግንዛቤ ላይ ተመስርተው ነው።a ይህ ዓመት ጥንት በኢየሩሳሌም የነበረው የዳዊት መንግሥት ከወደቀ ጀምሮና በ1914 በጥቅምት ወር ያበቃውን 2520 ዓመት የሚሸፍን እንደሆነ ተገንዝበዋል።b—ዳንኤል 4:16, 17፤ ሉቃስ 21:24, ኪንግ ጀምስ ቨርዥን
ጥቅምት 2 ቀን 1914 በጊዜው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማህበር ፕሬዚደንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በድፍረት “የአሕዛብ ዘመን ተፈጸመ፤ የተፈቀደው ጊዜ አከተመ” አስታውቋል። በእርግጥም የተናገራቸው ቃላት በትክክል ተፈጽመዋል። በጥቅምት ወር 1914 ዓለምን የሚያናውጥ ታላቅ ድርጊት በሰማይ ተከናውኗል። “የዳዊት ዙፋን” ቋሚ ወራሽ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በጠቅላላው የሰው ዘሮች ላይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል።—ሉቃስ 1:32, 33፤ ራእይ 11:15
ይሁን እንጂ ክርስቶስ መግዛት የጀመረው በ1914 ከሆነ በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎች ለምን እየባሱ ይሄዳሉ? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የሰው ዘሮች የማይታይ ጠላት የሆነው ሰይጣን አሁንም በሕይወት ስላለ ነው። እስከ 1914 ድረስ ሰይጣን ወደ ሰማይ መግባት ይችል ነበር። “የአምላክ መንግሥት በ1914 ስትቋቋም ግን ይህ ሁኔታ ተቀየረ። “በሰማይም ሰልፍ ሆነ።” (ራእይ 12:7) ሰይጣንና አጋንንቱ በጦርነቱ ተሸንፈው ወደ ምድር ተጣሉ። ይህም በሰው ዘሮች ላይ ብዙ እልቂት አስከተለ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለምድርና ለባህር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” በማለት ተንብዮአል።—ራእይ 12:12
በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን እዘአ ኢየሱስ የምድር አዲስ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ መንገድ መገኘቱ በሚታዩ ምልክቶች እንደሚታወቅ ተናግሮአል። “የመገኘትህና የሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት ምንድን ነው?” (አዓት) ተብሎ ተጠይቆ ነበር። ታዲያ ምን መልስ ሰጣቸው? “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፣ ራብም ቸነፈርም፣ የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።”—ማቴዎስ 24:3, 7, 8
በዚህ መሠረት በ1914 ከፈነዳው ጦርነት ቀጥሎ አሰቃቂ ራብ ሆነ። ይህም የሆነው የተለመደው የእህል የማምረት ሥራ ከአራት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ተቋርጦ ስለነበር ነው። “የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” የሚለው ትንቢትስ? ከ1914 በኋላ በነበሩት አስር ዓመታት 350,000 ሰዎችን የጨረሱ ከአስር ያላነሱ የምድር መንቀጥቀጦች ደርሰዋል። (ሳጥኑን ተመልከት) በእርግጥም በ1914 በነበረው ትውልድ ላይ “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ደርሶአል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተፈጥሮ አደጋ፣ ድርቅና በጣም ብዙ ጦርነቶች በተደጋጋሚ ከፍተኛ እልቂት ሲያስከትሉ ስለቆዩ የምጡ ጣር አልተቋረጠም።
ሆኖም የአምላክ መንግሥት በ1914 የመመሥረቷ ዜና የምሥራች ነው። ምክንያቱም ይህ መንግሥት ይህችን ምድር ከጥፋት ያድናታል። እንዴት? መንግሥቲቱ ግብዝ የሆኑትን ሐሰተኛ ሐይማኖቶች፣ ምግባረ ብልሹ መንግሥታትንና ክፉ የሆነውን የሰይጣን ተጽዕኖ ታስወግዳለች። (ዳንኤል 2:44፤ ሮሜ 16:20፤ ራእይ 11:18፤ 18:4-8, 24) ከዚህም በላይ መንግሥቲቱ “ጽድቅ የሚኖርባትን” አዲስ ዓለም ታመጣለች።—2 ጴጥሮስ 3:13
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወዲያው በዚያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ስለሚገኝበት ጊዜ ከተናገራቸው ምልክቶች በአንዱ ረገድ ሊኖራቸው የሚችለውን መብት መረዳት ጀመሩ። ኢየሱስ ክርስቶስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:14
የይሖዋ ምሥክሮች በ1919 በጣም አነስተኛ ከነበረ ጅምር ተነስተው ምስራቹን ያለማቋረጥ ሲያሰራጩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ከ200 አገሮች በላይ የተውጣጡ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ተገዥ ለመሆን እየተሰበሰቡ ናቸው። ለነዚህ ተገዢዎች ምን አይነት በረከቶች ይመጣላቸው ይሆን! መንግሥቲቱ ጦርነትን፣ ራብን፣ ወንጀልንና ጭቆናን ታስቀራለች። በሽታንና ሞትን ታስወግዳለች።—መዝሙር 46:9፤ 72:7, 12-14, 16፤ ምሳሌ 2:21, 22፤ ራእይ 21:3, 4
የ1914 ትውልድ ከማለፉ በፊት የመንግስቱ ስብከት ሥራ ዓላማ ይፈጸማል። ኢየሱስ እንደተነበየው “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ ከእንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር። ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።”—ማቴዎስ 24:21, 22
ከ1914 በፊት የነበረው ትውልድ የሠራውን ስህተት አትድገም። አሁን ያሉት ሁኔታዎች እንዲሁ እንዳሉ አይቀጥሉም። አስደናቂ ለውጦች ከፊታችን ተደቅነዋል። በጥበብ የሚመላለሱ ሁሉ በጣም ግሩም የሆነ ተስፋ ይጠብቃቸዋል።
እንግዲያው የጥንቱን ነቢይ ቃላት በጥሞና አዳምጥ፦ “እናንተ የምድር ትሁታን ሁሉ፦ [ይሖዋን (አዓት)] ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ ምናልባት [በይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል። (ሶፎንያስ 2:3) ይህንን ምክር እንዴት በሥራ ላይ ልናውል እንችላለን? የሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የዜናርዮ ኦፍ ዘ ፎቶ-ድራማ ኦፍ ክርኤሽን አርእስተ ገፅ፣ 1914
b ለተጨማሪ ማብራሪያ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማህበር ኒው ዮርክ የታተመውን በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
ከ1914 በኋላ በነበሩት አስር ዓመታት ውስጥ የተከሰቱት የመሬት መንቀጥቀጦች
ቀን፦ ቦታ፦ የሞቱ ሰዎች
ጥር 13, 1915 አቭዛኖ፣ ጣልያን 32,600
ጥር 21, 1917 ባሊ፣ ኢንዶኔዢያ 15,000
የካቲት 13, 1918 ዋንግታግ ክፍለ ሐገር፣ ቻይና 10,000
ጥቅምት 11, 1918 (ምዕራባዊ) ፖርቶ ቶሪኮ 116
ጥር 3, 1920 ቬራክሩዝ፣ ሜክሲኮ 648
መስከረም 7, 1920 ሬጂዮ ዲ ካላብሪያ፣ ጣልያን 1,400
ታህሳስ 16, 1920 ኒግሲያን ክፍለ ሐገር፣ ቻይና 200,000
መጋቢት 24, 1923 ዜቸዋን ክፍለ ሐገር፣ ቻይና 5,000
ግንቦት 26, 1923 (ሰሜን ምስራቅ) ኢራን 2,200
መስከረም 1, 1923 ቶክዮ-ዮከሃማ፣ ጃፓን 99,300
ቴራ ኖን ፊርማ ከተባለው መጽሐፍ፣ በጄምስ ኤም ጌራ እና ሐርሽ ሲ ሻህ የተዘጋጀ “የዓለም የመሬት መንቀጥቀጦች” ከሚለው ሰንጠረዥ የተወሰደ