የይሖዋን ቀን በሐሳባችሁ አቅርባችሁ ተመልከቱ
“የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና።”—ኢዩኤል 3:14
1. በይሖዋ የሚታወጀው መጪ ቅዱስ ጦርነት ከሰው ልጆች “ቅዱስ” ጦርነት የሚለየው ለምንድን ነው?
“ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ፤ ለሰልፍ ተዘጋጁ [ጦርነትን ቀድሱ (አዓት)] (ኢዮኤል 3:9) ታዲያ ይህ ማለት ቅዱስ ጦርነት ይኖራል ማለት ነውን? ሕዝበ ክርስትና በግንባር ቀደምትነት የተሳተፈችባቸውን የመስቀል ጦርነቶች፣ ሃይማኖታዊ ውጊያዎችና ሁለቱን የዓለም ጦርነቶች መለስ ብለን በምንቃኝበት ጊዜ “ቅዱስ” ጦርነት የሚለው ሐሳብ ብቻውን ሊዘገንነን ይችላል። ይሁን እንጂ በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሰው ቅዱስ ጦርነት በመንግሥታት መካከል የሚደረግ ጦርነት አይደለም። በሃይማኖት ሰበብ አንድን ግዛት ወይም ንብረት ለመቀማት የሚደረግ ጥላቻ የተሞላበት ፍልሚያ አይደለም። ይህ ጦርነት የጽድቅ ጦርነት ነው። ምድርን ከስስት፣ ከጥል፣ ከሥልጣን ብልግናና ከጭቆና ለማላቀቅ የሚደረግ የአምላክ ጦርነት ነው። ይህ ጦርነት ይሖዋ በፍጥረቱ ሁሉ ላይ በሉዓላዊነት የመግዛት መብት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ጦርነት ይሆናል። ይህ ጦርነት የክርስቶስ መንግሥት የአምላክ ነቢያት በትንቢት የተናገሩለትን አጽናፈ ዓለማዊ ሰላም፣ ብልጽግናና ደስታ የሠፈነበት የሺህ ዓመት ግዛት ለሰው ልጆች እንዲያመጣ መንገድ የሚጠርግ ይሆናል።—መዝሙር 37:9-11፤ ኢሳይያስ 65:17, 18፤ ራዕይ 20:6
2, 3. (ሀ) በኢዩኤል 3:14 ላይ በትንቢት የተገለጸው “የይሖዋ ቀን” ምንድን ነው? (ለ) ብሔራት በዚያ ቀን የሚመጣባቸው መዓት ሁሉ የሚገባቸው ቅጣት የሆነው ለምንድን ነው?
2 ታዲያ ይህ በኢዩኤል 3:14 ላይ በትንቢት የተነገረለት “[የይሖዋ (አዓት) ቀን” ምንድን ነው? “የ[የይሖዋ (አዓት)] ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል” በማለት ይሖዋ ራሱ አስታውቋል። ጥፋት የሆነውስ እንዴት ነው? ነቢዩ ቆየት ብሎ “የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ” በማለት አብራርቶአል። (ኢዩኤል 1:15፤ 3:14) ይህ ቀን ይሖዋ በሰማይና በምድር ላይ በሉዓላዊነት የመግዛት መብቱን አንቀበልም በሚሉ አምላክ የለሽ የሰው ዘሮች ላይ የፍርድ ውሳኔውን የሚያስፈጽምበት ቀን ነው። ይሖዋ ይህን ለሚያህል ረዥም ዘመን የሰው ልጆችን በመዳፉ ጠፍሮ የያዘውን ሰይጣናዊ ሥርዓት ለማጥፋት ወስኖአል።—ኤርምያስ 17:5-7፤ 25:31-33
3 ይህ የጥፋት ፍርድ በምድር ላይ በሚገኘው በዚህ ብልሹ ሥርዓት ፊት ተደቅኖአል። ይሁን እንጂ ይህ ዘመናዊ ዓለም ይህን ዓይነት ፍርድ ሊያስፈርድበት የሚገባ ክፋት ሠርቶአልን? ዓለም የሚያደርጋቸውን ነገሮች ለአንድ አፍታ ብቻ መመልከት ይበቃል። ኢየሱስ በማቴዎስ 7:16 ላይ “በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። ታላላቆቹ የዓለም ከተሞች የአደንዛዥ ዕጽ፣ የወንጀል፣ የሽብር፣ የብልግናና የቆሻሻ ማከማቻ ኩሬዎች አልሆኑምን? በብዙ አገሮች ለነፃነት የሚደረገው ጩኸት በፖለቲካዊ ዝብርቅ፣ በምግብ እጥረትና በድህነት ታፍኖአል። ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ የምድር ነዋሪዎች የሚተዳደሩት ለረሀብተኞች በሚሰጥ የእርዳታ ራሽን ነው። በተጨማሪም በጎጂ ዕጾችና ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አኗኗር የተቀጣጠለው የኤድስ ወረርሽኝ በአብዛኛው የምድር ክፍል ላይ የጨለማ ደመና እንዲያጠላ በማድረግ ላይ ነው። በተለይ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከፈነዳበት ከ1914 ወዲህ ይህ ሃያኛው መቶ ዘመን በሁሉም የኑሮ ዘርፎች እያዘቀጠ መጥቷል።—ከ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ጋር አወዳድሩት
4. ይሖዋ ለብሔራት ምን የግጥሚያ ጥሪ አቅርቧል?
4 ይሁን እንጂ ይሖዋ ስለ መንገዶቹና በጎዳናዎቹ ስለመሄድ የሚሰጠውን መመሪያ በደስታ የሚቀበሉ ሕዝቦችን ከብሔራት በሙሉ እያሰባሰበ ነው። እነዚህ በምድር ዙሪያ የሚገኙ ሕዝቦች የዓለምን የዓመጽ መንገዶች በመካድ ሠይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ ቀጥቅጠዋል። (ኢሳይያስ 2:2-4) አዎን፣ ሠይፋቸውን ወደ ማረሻነት ቀይረዋል! ታዲያ ይህ ይሖዋ በኢዩኤል 3:9, 10 ላይ እንዲታወጅ የሚያደርገው ቃል ተቃራኒ አይደለምን? ኢዩኤል 3:9, 10 “በአሕዛብ መካከል አውጁ ለሰልፍ ተዘጋጁ ኃያላንን አስነሡ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። ማረሻችሁን ሰይፍ፣ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ” ይላል። እዚህ ላይ ይሖዋ የዓለም መሪዎች እሱን በመቃወም የትጥቅ ኃይላቸውን ሁሉ አስተባብረው ወደ አርማጌዶን እንዲያመጡና እንዲገጥሙት የጦርነት ጥሪ እያቀረበላቸው ነው። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ሊሳካላቸው አይችልም። ሙሉ በሙሉ ድል ተሸንፈው ይደመሰሳሉ።—ራዕይ 16:16
5. ኢየሱስ “የምድርን ወይን ሲያጭድ” ውጤቱ ምን ይሆናል?
5 ኃያላን መሪዎች ልዑሉን ጌታ ይሖዋን በንቀት በመገዳደር አስፈሪ የጦር መሣሪያዎችን በብዛት አከማችተዋል። ግን ልፋቱ ከንቱ ነው! ይሖዋ በኢዩኤል 3:13 ላይ “መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ ክፋታቸው በዝቶአልና መጥመቂያው ሁሉ ፈስሶአል” በማለት ትዕዛዝ ያስተላልፋል። እነዚህ ቃላት በራዕይ 14:18-20 ላይ መሢሐዊ ንጉሥ ለሆነው ለኢየሱስ “ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ላይ ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቁረጥ” ተብሎ ከታዘዘበት ቃላት ጋር ይመሳሰላሉ። ንጉሡ ስለታም ማጭዱን ዘርግቶ እነዚህን ትዕቢተኛ ብሔራት አጭዶ “ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቁጣ መጥመቂያ” ይጥላል። በዚህ ጊዜ በምሳሌያዊ አባባል “እስከ ፈረሶች ልጓም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ!” የ288 ኪሎ ሜትር ርቀት ይኖረዋል ማለት ነው። ይሖዋን የማያከብሩ ብሔራትን የሚጠብቃቸው ምንኛ አስፈሪ የሆነ የወደፊት ጊዜ ነው!
ሕግ አክባሪ ዜጎች
6. የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራትንና መሪዎቻቸውን የሚመለከቱአቸው እንዴት ነው?
6 ታዲያ ይህ ማለት የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራትንና ገዢዎቻቸውን አያከብሩም ወይም ያዋርዳሉ ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም! ለማንም ሰው ግልጽ ሆኖ በሚታየው ምግባረ ብልሹነት የሚሰማቸውን ቅሬታ በመግለጽ በፍጥነት እየቀረበ ስላለው አምላክ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ቀን ያስጠነቅቃሉ። ይህን እያደረጉም “ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣኖች ይገዛ” የሚለውን በሮሜ 13:1 ላይ የሚገኘውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር በትህትና ይታዘዛሉ። እነዚህን ባለሥልጣኖች ያከብራሉ፤ ግን አያመልኳቸውም። ሕግ አክባሪ ዜጎች በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ለሐቀኝነት፣ ለእውነተኛነትና ለንጽሕና ያወጣውን የአቋም ደረጃ ይከተላሉ፤ በቤተሰቦቻቸው ውስጥም ጥሩ ሥነ ምግባርን ይኮተኩታሉ። ሌሎች ይህን እንዴት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያስተምራሉ። ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር በሰላም ይኖራሉ እንጂ በማንኛውም አድማ ወይም የፖለቲካ ንቅናቄ ጣልቃ አይገቡም። የይሖዋ ምሥክሮች የመጨረሻው ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆነው የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ ይሖዋ በምድር ላይ ፍጹም ሰላምና ጻድቅ መንግሥት የሚያቋቁምበትን ጊዜ እየጠበቁ ‘የበላይ ባለሥልጣኖች’ን ሕጎች በመታዘዝ ረገድ ጥሩ ምሳሌዎች ለመሆን ይፈልጋሉ።
ፍርዱን ማስፈጸም
7, 8. (ሀ) ብሔራት የሚናወጡትና ጨለማ የሚከድናቸው በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢዩኤል በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩት ለእነማን ምሳሌ ሆኖአል? በኢዩኤል የተመሰሉትስ ሕዝቦች ከዓለም ጋር ሲነፃፀር የተባረኩት እንዴት ነው?
7 ይሖዋ ስለ ፍርዱ አፈጻጸም ሕያው በሆነ ምሳሌያዊ አነጋገር ተጨማሪ መግለጫ ይሰጠናል፦ “ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፣ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፣ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣ ለእሥራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።” (ኢዩኤል 3:15, 16) ብሩሕና የበለጸገ መስሎ ይታይ የነበረው የሰው ልጅ ሁኔታ የጨለመና አስፈሪ ይሆናል፤ እየተሸራረፈ ያለው ይህ ዓላማዊ ሥርዓትም በታላቅ የመሬት መናወጥ እንደተመታ ያህል ተሰባብሮ ይንኮታኮታል!—ሐጌ 2:20-22
8 ይሖዋ ለሕዝቡ መሸሸጊያና መጠጊያ እንደሚሆን የሰጠውን ዋስትና ልብ በሉ! ይህን ዋስትና የሰጠው ለምንድነው? ይሖዋ “እኔም አምላካችሁ [ይሖዋ (አዓት)] እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” በማለት የተናገረውን ቃል የተቀበሉ ዓለም አቀፍ አንድነት ያገኙ ሕዝቦች እነሱ ብቻ ስለሆኑ ነው። (ኢዩኤል 3:17) ኢዩኤል ማለት ትርጉሙ “ይሖዋ አምላክ ነው” ማለት በመሆኑ ይህ ነቢይ በዘመናችን የይሖዋን ሉዓላዊነት በድፍረት በማስታወቅ ለሚያገለግሉት የይሖዋ ቅቡአን ምሥክሮች ተገቢ ምሳሌ ነው። (ከሚልክያስ 1:11 ጋር አወዳድሩ) ወደ ኢዩኤል ትንቢት የመግቢያ ቃላት መለስ ብለን ስንመለከት በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች እንቅስቃሴ እንዴት ባለ ሕያው ቃል እንደተነበየ እንገነዘባለን።
የአንበጣ ሠራዊት
9, 10. (ሀ) በኢዩኤል የተተነበየው መቅሰፍት ምንድን ነው? (ለ) የራዕይ መጽሐፍ የኢዩኤልን ትንቢት መቅሰፍት የሚያስተጋባው እንዴት ነው? ይህስ መቅሰፍት በሕዝበ ክርስትና ላይ ምን ውጤት ያስከትላል?
9 “ለኢዩኤል የመጣለትን የ[ይሖዋ (አዓት)] ቃል . . . በምድር የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፣ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ። ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው ከደጎብያ የቀረውን ኩብኩባ፣ በላው።”—ኢዩኤል 1:1-4
10 በመጪዎቹ ዘመናት በሙሉ መታወስ የሚገባው ልዩ የሆነ ዘመቻ ነው። ምድሪቱ እየተከታተሉ በሚመጡ አጥፊ ነፍሳትና በተለይም በአንበጣ ሠራዊት ትጠፋለች። ታዲያ የዚህ ትርጉም ምንድን ነው? ራዕይ 9:1-12ም “የጥልቅ መልአክ በተባለ ንጉሥ” አዝማችነት ይሖዋ ስለላከው የአንበጣ መቅሰፍት ይናገራል። ይህ የጥልቅ መልአክም ከኢየሱስ በቀር ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክኛ ደግሞ አጶልዮን ሲሆን ትርጉሙ “ጥፋት” እና “አጥፊ” ማለት ነው። እነዚህ አንበጦች የሚያመለክቱት ባለንበት የጌታ ቀን ውስጥ የሐሰት ሃይማኖትን በማጋለጥና ከይሖዋ የሚመጣበትን በቀል በማወጅ የሕዝበ ክርስትናን ግጦሽ ለማውደም የወጡትን ክርስቲያን ቅቡዓን ቀሪዎች ነው።
11. ዘመናዊዎቹ አንበጦች የተጠናከሩት እንዴት ነው? የእነርሱ ጥቃት ኢላማ የሆኑትስ በተለይ እነማን ናቸው?
11 በራዕይ 9:13-21 ላይ እንደተገለጸው የአንበጣው ወረራ በጣም ትልቅ በሆነ የፈረሰኞች ጭፍራ ወረራ ተተክቷል። በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩት ቅቡዓን ቀሪ ክርስቲያኖች ከአራት ሚሊዮን በላይ በሆኑ “ሌሎች በጎች” ተጠናክረው ማንም ሊቋቋማቸው የማይችል ታላቅ የፈረሰኞች ሠራዊት ሆነዋል። (ዮሐንስ 10:16) በሕዝበ ክርስትና ጣኦት አምላኪዎች ላይና ‘ስለ መግደላቸውም ሆነ ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ ባልገቡ’ ሁሉ ላይ የይሖዋን ተናዳፊ የፍርድ መልእክት በማወጅ ተባብረዋል። እነዚህ የፍርድ መልእክቶች ከሚያነጣጥሩባቸው ሰዎች መሃል የዚህን መቶ ዘመን የእልቂት ጦርነቶች በሙሉ ልብ የደገፉ፣ በሕፃናት ላይ ነውር የሚፈጽሙ የካቶሊክም ሆነ የፕሮቴስታንት ቀሳውስትና ምግባረ ብልሹዎቹ የቴሌቪዥን ወንጌላውያን ይገኙበታል።
12. የሕዝበ ክርስትና መሪዎች የፍርድ መልእክት መቀበል የሚገባቸው ለምንድን ነው? እነርሱስ ከሁሉም የታላቂቱ ባቢሎን አባሎች ጋር ባንድነት ምን ይደርስባቸዋል?
12 ለእንዲህ ዓይነቶቹ በውጭ ብቻ ጨዋ መስለው የሚታዩ ወራዶች “በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፣ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፣ ዋይ በሉ” የሚለው የይሖዋ ጥሪ ይደውልባቸዋል። (ኢዩኤል 1:5) በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት በአምላክ ቃል የንጹሕ ሥነምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶች ምትክ ዓለማዊ ስድነትን ተቀብሎአል። የዓለም መንገድ ለሐሰት ሃይማኖትና ለምእመናኑ ጣፋጭ መስሎ ታይቷል፤ ይሁን እንጂ በጣም ብዙ የመንፈሳዊና የአካላዊ ሕመም ምርት አሳጭዷቸዋል! በራዕይ 17:16, 17 ላይ እንደተገለጸው በቅርቡ ፖለቲካዊ ኃይላት የመላው ዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲዞሩና ቦጫጭቀው እንዲበሉአት ያቀደው የአምላክ “አሳብ” ይፈጸማል። ከስካርዋ የምትነቃው የይሖዋ ፍርድ እየተፈጸመባት እንዳለ ስትመለከት ብቻ ይሆናል።
“ታላቅና ብርቱ ሕዝብ”
13. የአንበጣው ሠራዊት ለሕዝበ ክርስትና “ታላቅና ብርቱ” ሆኖ የሚታያት በምን መንገድ ነው?
13 የይሖዋ ነቢይ ቀጥሎ የአንበጣውን ጭፍራ “ታላቅና ብርቱ ሕዝብ” በማለት ይገልጸዋል። ይህ ጭፍራ ለታላቂቱ ባቢሎንም ቢሆን “ታላቅና ብርቱ ሕዝብ” ሆኖ ይታያታል። (ኢዩኤል 2:2) ለምሳሌ ያህል የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በቡድሂስቷ ጃፓን ሰዎችን ወደ ክርስትና ለመለወጥ ባለመቻላቸው ቀሳውስት በጣም ያዝናሉ። ሆኖም ባሁኑ ጊዜ በጃፓን አገር ከ160,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። ከ200,000 በሚበልጡ ቤቶች ውስጥ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራሉ። በኢጣሊያ 180,000 የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚገኙ በቁጥር ከካቶሊክ ሃይማኖት ቀጥሎ ሁለተኛውን ቦታ ይዘዋል። በኢጣሊያ የሚገኙት የሮማ ካቶሊክ አቡን የይሖዋ ምሥክሮች በያመቱ ‘ቢያንስ 10,000 ታማኝ ካቶሊኮችን’ እየወሰዱብን ነው ብለው ማማረራቸው ምንም ውጤት አላስገኘላቸውም።a ምሥክሮቹ እንዲህ ዓይነቶቹን ‘ታማኝ ካቶሊኮች’ ለመቀበል ደስተኞች ናቸው።—ኢሳይያስ 60:8, 22
14, 15. ኢዩኤል የአንበጣውን ሠራዊት የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ የተፈጸመው በምን መንገድ ነው?
14 ኢዩኤል 2:7-9 የቅቡዓን ምሥክሮችን የአንበጣ ጭፍራ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፣ እንደ ሠልፈኞችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፤ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፣ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም። አንዱ ከአንዱ ጋር አይጋፋም፣ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል።፤ በሠልፉ መካከል ያልፋሉ፣ እነርሱም አይቆስሉም። በከተማዋም ያኮበኩባሉ፣ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፣ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ።”
15 በእርግጥም ይህ አገላለጽ አሁን ከአራት ሚሊዮን በላይ የሆኑ “ሌሎች በጎች” ለተባበሩአቸው የቅቡዓን “አንበጦች” ሠራዊት የሚስማማ ሕያው የሆነ ሥዕላዊ መግለጫ ነው! እነርሱን ሊያግድ የሚችል ምንም ዓይነት የሃይማኖታዊ ጥላቻ “ቅጥር” የለም። በድፍረት ሕዝባዊ ምሥክርነት በመስጠትና በሌሎችም ክርስቲያናዊ ተግባሮች ‘በዚያው ልማድ በሥርዓት በመመላለስ ይቀጥላሉ።’ (ከፊልጵስዩስ 3:16 (አዓት) ጋር አወዳድር) እነዚህ በአንበጣ የተመሰለው ሠራዊት አባሎች የእምነት አቋማቸውን ከማላላት ይልቅ የናዚ ጀርመኑን ካቶሊካዊ ሂትለር ለማወደስ እምቢ በማለታቸው ምክንያት “በሚሳይሎች መሃል የወደቁት” በሺህ የሚቆጠሩ ምሥክሮች እንዳደረጉት ሞትን ለመጋፈጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። የአንበጣው ሠራዊት ማንኛውንም መሰናክል ጥሶ እንደ ሌላ በመስኮት እንደገባ ያህል ከቤት ወደ ቤት በሚያደርገው አገልግሎት በቢሊዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስላደለ በሕዝበ ክርስትና “ከተማ” ሠፊ ምሥክርነት ሰጥቶአል። ይህ ምሥክርነት እንዲሰጥ የይሖዋ ፈቃድ ስለሆነ በሰማይም ሆነ በምድር ይህን ሥራ ሊያቆመው የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል የለም።—ኢሳይያስ 55:11
“መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው”
16, 17. (ሀ) የኢዩኤል 2:28, 29 ቃላት ከፍተኛ ፍጻሜያቸውን ያገኙት መቼ ነበር? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ያላገኙት የትኞቹ የኢዩኤል ትንቢታዊ ቃላት ናቸው?
16 ይሖዋ ለምሥክሮቹ “እኔም [በመንፈሳዊ] እሥራኤል መካከል እንዳለሁ፣ እኔም አምላካችሁ [ይሖዋ (አዓት)] እንደሆንሁ፣ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ” በማለት ይነግራቸዋል። (ኢዩኤል 2:27) ሕዝቦቹ ወደዚህ ክቡር ግንዛቤ የመጡት ይሖዋ በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ” የሚለውን ትንቢት መፈጸም በጀመረ ጊዜ ነበር። ይህም የተፈጸመው በ33 እዘአ በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ተሰብስበው በነበሩት ደቀመዛሙርት ላይ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ በሞላባቸው” ጊዜ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ኃይልም ሰበኩና በአንድ ቀን “ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ።”—ሥራ 2:4, 16, 17, 41
17 በዚያ አስደሳች ወቅት ጴጥሮስ ኢዩኤል 2:30-32ን ጠቅሶ “በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፣ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። ታላቁና የሚያስፈራው የ[ይሖዋ (አዓት)] ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። እንዲህም ይሆናል፤ የ[ይሖዋ (አዓት)]ን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ብሎአል። እነዚህ ቃላት ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ በጠፋች ጊዜ በከፊል ተፈጽመዋል።
18. ኢዩኤል 2:28, 29 ከፍተኛ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው መቼ ነበር?
18 ይሁን እንጂ ኢዩኤል 2:28-32 ሌላ ተጨማሪ ፍጻሜ አለው። ይህ ትንቢት በተለይ ከመስከረም 1919 ወዲህ በአስደናቂ ሁኔታ ተፈጽሞአል። በዚያ ጊዜ በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ዩ.ኤስ.ኤ የይሖዋ ሕዝቦች የማይረሳ ስብሰባ አድርገው ነበር። በዚህ ጊዜ የአምላክ መንፈስ መግለጫ በግልጽ ታይቶ ነበር። ቅቡዓን አገልጋዮቹም እስከዛሬ ድረስ የተራዘመውን የስብከት ሥራ ለመጀመር ተነቃቅተው ነበር። በውጤቱም ትልቅ መስፋፋት ተገኝቷል! በዚህ በሴዳር ፖይንት ስብሰባ ላይ በተገኙ ከ7,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመገኘቱ መጋቢት 30, 1991 በተከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ 10,650,158 ተገኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መሆናቸውን የገለጹት 8,850 ብቻ ነበሩ። እነርሱም በይሖዋ ኃያል መንፈስ አማካኝነት በዓለም ዙሪያ ይህን የመሰለ ፍሬ መገኘቱን ሲመለከቱ በጣም ተደስተዋል።—ኢሳይያስ 40:29, 31
19. የይሖዋ ቀን በጣም በመቅረቡ ምክንያት የእያንዳንዳችን ዝንባሌ ምን መሆን ይኖርበታል?
19 በቅርቡ ከፊታችን የሚጠብቀን የሰይጣንን ሥርዓት የሚያወድመው “ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን መምጣት” ነው። (ኢዩኤል 2:31) “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ” ስለሚድን ደስ ሊለን ይገባል። (ሥራ 2:21) ይሁን እንጂ እንደ ኢየሱስ የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ የሚድነው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ “የይሖዋ ቀን ግን እንደሌባ ሆኖ ይመጣል” ካለ በኋላ በመቀጠል “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ የ[ይሖዋ (አዓት)]ን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል [ለአምላክ ያደራችሁ በመሆን (አዓት)] እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” ብሏል። የይሖዋን ቀን በሐሳባችን አቅርበን በማየት የይሖዋን የጽድቅ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ተስፋ ፍጻሜ በማየት እንደሰታለን።—2 ጴጥሮስ 3:10-13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a La Repubblica፣ ሮም፣ ኢጣሊያ፣ ህዳር 12፣ 1985 እና La rivista del clero italiano, ግንቦት 1985ን ተመልከቱ።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ “የይሖዋ ቀን” ምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ ‘የምድርን ወይን’ የሚያጭደው እንዴት ነው? ለምንስ?
◻ የአንበጦቹ መቅሰፍት ከ1919 ጀምሮ ሕዝበ ክርስትናን ያጠቃው በምን መንገድ ነው?
◻ የይሖዋ መንፈስ በ33 እዘአ እና እንደገናም በ1919 በሕዝቡ ላይ የፈሰሰው እንዴት ነበር?