የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 5/15 ገጽ 15-20
  • ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ እውነተኛ ደስታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ እውነተኛ ደስታ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተለየ የደስታ አመለካከት
  • እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት መሠረት
  • በየዘመናቱ የተለወጡ የደስታ ምክንያቶች
  • በጥንት ጊዜ ሳያገቡ ደስታ ያገኙ የአምላክ አገልጋዮች
  • በዘመናችን ነጠላ ሆነው ቢኖሩም ደስተኛ የሆኑ ሰዎች
  • በጋብቻ አለመታሰር የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
  • እውነተኛ ደስታ የተመካው በምን ላይ ነው?
  • ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ብቸኛ ቁልፍ ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ደስታ ስለሚገኝበት መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ‘ደስተኛውን አምላክ’ የሚያገለግሉ ደስተኞች ናቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 5/15 ገጽ 15-20

ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ እውነተኛ ደስታ

“የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ [በይሖዋ (አዓት)] የሆነ ሰው [ደስተኛ (አዓት)] ነው።”—መዝሙር 146:5

1, 2. ደስታ ለሚለው ቃል ምን ፍች ተሰጥቶአል? በዛሬው ጊዜ ላሉ ብዙ ሰዎች ደስታ ምን ትርጉም አለው?

ደስታ ምንድን ነው? የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች፣ ፈላስፋዎችና የሃይማኖት ሊቃውንት ለብዙ ዘመናት ለደስታ ፍች ለመስጠት ሲሞክሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያገኘ ፍች አላገኙለትም። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “‘ደስታ’ ለመፍታት በጣም አስቸጋሪ ከሆኑት ቃላት አንዱ ነው” በማለት ገልጾአል። ደስታ የተለያዩ ሰዎች ባላቸው የሕይወት አመለካከት ላይ የተመሠረተ የተለያየ ትርጉም አለው።

2 ለብዙ ሰዎች ደስታ የተመሰረተው በጥሩ ጤና፣ በቁሳዊ ሐብትና በአስደሳች ጓደኝነት ላይ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እያሏቸው ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች አሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ራሳቸውን ለይሖዋ ለወሰኑ ወንዶችና ሴቶች ዓለም ስለ ደስታ ካለው አጠቃላይ አስተያየት ፍጹም የተለየ ሐሳብ ይሰጣል።

የተለየ የደስታ አመለካከት

3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ደስተኞች ናቸው ያለው እነማንን ነው? (ለ) ኢየሱስ ከጠቀሳቸው ለደስታ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ነገሮች ምን ልብ ለማለት ይቻላል?

3 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ደስታ በጥሩ ጤና፣ በቁሳዊ ሐብትና በመሳሰሉት ላይ የተመካ ነው አላለም። “ለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ነገር ንቁዎች የሆኑ” እና “ጽድቅን የሚራቡ” በእውነት ደስተኞች ናቸው ብሏል። ከእነዚህ ከሁለቱ ጋር የሚዛመድ ነገር ግን እርስ በርሱ የሚቃረን የሚመስለው የኢየሱስ አገላለጽ “የሚያዝኑ [ደስተኞች (አዓት)] ናቸው፣ መጽናናትን ያገኛሉና” የሚለው ነው። (ማቴዎስ 5:3-6) ኢየሱስ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ሰዎች ወዲያውኑ ደስተኞች ይሆናሉ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ በኃጢአተኛ ሁኔታቸውና ኃጢአት ባስከተለባቸው ውጤት ከልብ ስለሚያዝኑ ሰዎች መናገሩ ነበር።

4 ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ፍጥረት “ከጥፋት ባርነት ነፃ” የሚወጣበትን ተስፋ እየጠበቀ በኃጢአት በመቃተት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል። (ሮሜ 8:21, 22) በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ኃጢአት የሚያስወግደውን የይሖዋ ዝግጅት የተቀበሉና የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች በእርግጥም እየተጽናኑ እና እየተደሰቱ ናቸው። (ሮሜ 4:6-8) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ “የዋሆች”፣ “የሚምሩ”፣ “ልበ ንጹሆች” እና “ሰላማውያን(አዓት)” ደስተኞች ናቸው በማለት ተናግሮአል። ኢየሱስ እነዚህ የዋሆች ሲያሳድዷቸው እንኳን ደስታቸውን እንደማያጡ ማረጋገጫ ሰጥቶአል። (ማቴዎስ 5:5-11) እነዚህ ከፍ ያሉት ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮች በሀብታምና በድሃ መካከል ልዩነት የማያደርጉ መሆናቸውን እናስተውል።

እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት መሠረት

5. የአምላክ ውስን አገልጋዮች ለሚያገኙት ደስታ መሠረቱ ምንድን ነው?

5 የእውነተኛ ደስታ ምንጭ ቁሳዊ ብልጽግና አይደለም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የይሖዋ (አዓት)] በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም” ሲል ገልጾአል። (ምሳሌ 10:22) የይሖዋን ፅንፈ ዓለማዊ ገዥነት አምነው ለተቀበሉ ፍጥረታት ሁሉ ደስታ ከአምላክ በረከት ተነጥሎ የማይታይ ነገር ነው። የይሖዋ በረከት ያለውና እንዳለው የሚሰማው ራሱን የወሰነ ሰው እውነተኛ ደስታ ያገኛል። ደስታ በመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት መሠረት የይሖዋን አገልግሎት በመፈጸም ከሚገኝ ደስታና እርካታ ጋር የሚዛመድ ነው።

6. የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛ ደስታ እንዲያገኙ ምን ነገር ይፈለግባቸዋል?

6 እውነተኛ ደስታ ከይሖዋ ጋር ትክክለኛ ዝምድና በመመስረት ላይ የተመካ ነው። አምላክን በማፍቀርና ለእርሱም ታማኝ በመሆን ላይ የተመሠረተ ነው። የይሖዋ ውስን አገልጋዮች በሙሉ የሚከተሉትን የጳውሎስ ቃላት በሙሉ ልባቸው ይቀበላሉ። “ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና . . .ለ[ይሖዋ (አዓት)] እንኖራለንና የ[ይሖዋ (አዓት)] ነን።” (ሮሜ 14:7, 8) ስለዚህ ለይሖዋ ከመታዘዝና በደስታ ለፈቃዱ ከመገዛት ውጭ እውነተኛ ደስታ ሊገኝ አይችልም። ኢየሱስ “[ደስተኞችስ (አዓት)] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ብሎአል።—ሉቃስ 11:28

በየዘመናቱ የተለወጡ የደስታ ምክንያቶች

7, 8. (ሀ) ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች በሁለት ሊከፈሉ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ስለ ማግባትና ልጅ ስለመውለድ ምን ሊባል ይቻላል?

7 ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው ደስታ የሚያስገኙ ምክንያቶች “መሠረታዊ” ወይም “ቋሚ” ደስታ የሚያስገኙ ምክንያቶች ሊባሉ ይቻላል። ምክንያቱም እነዚህ በማንኛውም ጊዜ ለይሖዋ ውስን አገልጋዮች ደስታ የሚያስገኙ ምክንያቶች ናቸው። በተጨማሪም በአንድ ወቅት ደስታ የሚያስገኙ በሌላ ጊዜ ግን ምንም ደስታ ያላስገኙ ምክንያቶች አሉ። በአበውና በቅድመ ክርስትና ዘመናት ደስታ ለማግኘት ማግባትና ልጅ መውለድ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ይህም ራሄል ለያዕቆብ ባቀረበችው በሚከተለው አቤቱታ ተገልጾአል፦ “ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው።” (ዘፍጥረት 30:1) ልጅ ስለመውለድ የነበረው ይህ ዝንባሌ ከወቅቱ የይሖዋ ዓላማ ጋር የሚስማማ ነበር።—ዘፍጥረት 13:14-16፤ 22:17

8 በጥንት የይሖዋ ሕዝቦች ዘንድ ጋብቻና ልጅ መውለድ ከአምላክ የሚገኙ በረከቶች ናቸው ተብሎ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ በታሪክ ዘመናቸው ባጋጠሙአቸው አስጨናቂ ጊዜያት በልጆቻቸው ምክንያት ብዙ ሐዘን ደርሶባቸዋል። (መዝሙር 127, 128⁠ን ከኤርምያስ 6:12፤ 11:22፤ ሰቆቃው 2:19፤ 4:4, 5 ጋር አወዳድር።) እንግዲያው ጋብቻና ልጅ መውለድ ቋሚ የሆኑ የደስታ ምክንያቶች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው።

በጥንት ጊዜ ሳያገቡ ደስታ ያገኙ የአምላክ አገልጋዮች

9. የዮፍታሔ ሴት ልጅ ዓመታዊ ምስጋናና ማበረታቻ ታገኝ የነበረው ለምንድን ነው?

9 ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ሳያገቡ ቢኖሩም እውነተኛ ደስታ አግኝተዋል። የዮፍታሔ ልጅ ለአባትዋ ስዕለት አክብሮት በማሳየት ነጠላ ሆና ኖራለች። እርስዋና ልጃገረድ ጓደኞቿ ለድንግልናዋ ያለቀሱበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ በይሖዋ ቤተ መቅደስ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመስጠቷና ምናልባትም “በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች” መካከል ሆና በማገልገሏ እንዴት ያለ ደስታ አግኝታ ነበር! (ዘጸአት 38:8) ይህን በማድረጓም ዓመታዊ ምሥጋናና ማበረታቻ ታገኝ ነበር።—መሳፍንት 11:37-40

10. ይሖዋ ኤርምያስን ምን እንዲያደርግ ጠይቆት ነበር? በዚህስ ምክንያት ደስታ የሌለበት ኑሩ ኖሮአልን?

10 ነቢዩ ኤርምያስ ታላቅ ለውጥ በሚመጣበት ዘመን ላይ ይኖር ስለነበረ ከጋብቻና ልጆችን ከመውለድ እንዲርቅ አምላክ አዝዞት ነበር። (ኤርምያስ 16:1-4) ይሁን እንጂ ኤርምያስ የሚከተሉት የአምላክ ቃላት እውነተኛ መሆናቸውን ከራሱ ተሞክሮ ሊማር ችሎ ነበር። በ“[ይሖዋ (አዓት)] የታመነ እምነቱም በ[ይሖዋ (አዓት)] የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።” (ኤርምያስ 17:7) ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ ባገለገለባቸው ከ40 የሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ነጠላ ሆኖ በመኖር ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። እኛ እስከምናውቀው ድረስ ሚስት አግብቶ ወይም ልጅ ወልዶ አያውቅም። ይሁን እንጂ በ“[ይሖዋ (አዓት)] በጐነት . . . ነፍሳቸው የረካች” እንደሆነችላቸው ታማኝ የአይሁድ ቀሪዎች በጣም ደስተኛ እንደነበረ ለአንድ አፍታ እንኳን ሊጠራጠር የሚችል ማን ሊኖር ይችላል?—ኤርምያስ 31:12

11. ሳያገቡ ቢኖሩም ደስተኞች የነበሩ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እነማን ናቸው?

11 ብዙ ሌሎች ሰዎችም የትዳር ጓደኛ ሳይኖራቸው ይሖዋን በደስታ አገልግለዋል። እነሱም ያላገቡ ወይም የትዳር ጓደኞቻቸው የሞቱባቸው ናቸው። ከእነሱም መካከል ነቢይቱ ሐና፣ ምናልባትም ዶርቃን ወይም ጣቢታን፣ ሐዋርያው ጳውሎስንና ከሁሉም የሚበልጠውን ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስን መጥቀስ ይቻላል።

በዘመናችን ነጠላ ሆነው ቢኖሩም ደስተኛ የሆኑ ሰዎች

12. አንዳንዶች ደስተኛ ውስን የይሖዋ አገልጋዮች የትኛውን ግብዣ እየተቀበሉ ነው? ለምንስ?

12 ዛሬም ቢሆን የትዳር ጓደኛ ሳይኖራቸው ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ በሺህ የሚቆጠሩ ራሳቸውን የወሰኑ ወንዶችና ሴቶች የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶች የነጠላነትን ስጦታ “ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” የሚለውን የኢየሱስ ግብዣ ተቀብለዋል። ይህንንም ያደረጉት “ስለ መንግሥተ ሰማያት” ብለው ነው። (ማቴዎስ 19:11, 12) ይህም ማለት አምላክ በሰጣቸው ነፃነት ተጠቅመው የበለጠ ጊዜና ጉልበት ለመንግሥቱ አገልግሎት ለማዋል ሲሉ ነው። ብዙዎች አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያን ወይም በመጠበቂያ ግንብ ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በቅርንጫፍ ቢሮዎች የቤቴል ቤተሰብ አባል በመሆን ያገለግላሉ።

13. አንድ ክርስቲያን ነጠላ ሆኖ ቢኖርም ደስተኛ እንደሚሆን ምን ምሳሌዎች ያሳያሉ?

13 አንዲት በጣም የተወደደች አሮጊት እህት “ነጠላ ሆኖ በአቅኚነት በደስታ ማገልገል” በሚል ርዕስ ስለ ሕይወት ታሪኳ ጽፋለች። (መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 1, 1985 ገጽ 23-6) ከ50 ዓመት በላይ በቤቴል ያገለገለች ሌላዋ ነጠላ እህት ደግሞ “በሕይወቴና በሥራዬ ሙሉ በሙሉ ረክቼአለሁ። ምንም የምጸጸትበት ነገር የለም። ወደ ኋላ መመለስ ቢቻል ኖሮ እንኳን ውሳኔዬን አልለውጠውም ነበር” ብላለች።—መጠበቂያ ግንብ ሰኔ 15, 1982 ገጽ 15

14, 15. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በተናገረው መሠረት ነጠላ ሆኖ ለመኖር ምን ነገር ያስፈልጋል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ነጠላ የሆነ ሰው “የተሻለ” አደረገ “ደስተኛም ነው” ያለው ለምንድን ነው?

14 “ውሳኔ” የሚለውን ቃል ልብ በሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ለማግባት የሚያስገድደው ነገር ከሌለ ላለማግባት ችሎታ ካለውና ላለማግባት ቁርጥ ውሳኔ ካደረገ አለማግባቱ መልካም ነው። ስለዚህ ሚስት የሚያገባ መልካም ያደርጋል፣ የማያገባ ግን የተሻለ ያደርጋል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:37, 38 የ1980 ትርጉም) “የተሻለ” የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አብራርቶታል፦ “ነገር ግን ያለአሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ . . . ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ . . . ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 7:32-35

15 “ሳይባክኑ በጌታ መጽናት” ከደስታ ጋር የሚዛመድ ነውን? ጳውሎስ እንደዚያ ብሎ ያሰበ ይመስላል። ባሏ ስለሞተባት ሴት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነፃነት አላት። እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።”—1 ቆሮንቶስ 7:39, 40

በጋብቻ አለመታሰር የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

16. ያላገቡ የይሖዋ ምሥክሮች የሚደሰቱባቸው አንዳንድ መብቶች ምንድን ናቸው?

16 አንድ ግለሰብ ያላገባው በራሱ ምርጫ ይሁን በሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ በጋብቻ ያልታሰረ ኑሮ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ነጠላ የሆኑ ሰዎች የአምላክ ቃል የሚያጠኑበትና የሚያሰላስሉበት የበለጠ ጊዜ አላቸው። በዚህ ጊዜ በሚገባ ከተጠቀሙበት መንፈሳዊነታቸው ጥልቀት ያገኛል። ችግራቸውን የሚካፈልላቸው የትዳር ጓደኛ ስለሌላቸው ብዙዎች በይሖዋ ላይ መታመንና በማንኛውም ሁኔታ የይሖዋን አመራር መፈለግ እንደሚኖርባቸው ተምረዋል። (መዝሙር 37:5) ይህም ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲኖራቸው አስችሎአቸዋል።

17, 18. (ሀ) ያላገቡ የይሖዋ አገልጋዮች ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት የሚያሰፉባቸው ምን ጥሩ አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል? (ለ) አንዳንድ ያላገቡ የይሖዋ አገልጋዮች ደስታቸውን የገለጹት እንዴት ነው?

17 ነጠላ የሆኑ ሰዎች ይሖዋን ለማመስገን ሠፊ የሆነ የአገልግሎት መብትና አጋጣሚ አላቸው። በአገልግሎት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ልዩ ማሰልጠኛ ላላገቡ ወይም ሚስቶቻቸው ለሞቱባቸው ወንድሞች ብቻ የተወሰነ ነው። ነጠላ የሆኑ እህቶችም ቢሆኑ ለብዙ የአገልግሎት መብቶች ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አሮጊት እህት ራሷ እንደተናገረችው፦ “50 ዓመት የሞላት ደካማ ሴት” በነበረችበት ጊዜ በአንድ የአፍሪካ አገር ለማገልገል ፈቃደኛ ሆና ነበር። በዚያ አገር የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ በዚያ የነበሩ ሚስዮናውያን ከተባረሩ በኋላ እንኳን እዚያው አገር ቆይታለች። በአሁኑ ጊዜ ከ80 ዓመት በላይ የሆናት ብትሆንም እዚያው አገር በአቅኚነት በማገልገል ላይ ነች። ታዲያ ደስተኛ ናትን? ስለ ሕይወት ታሪኳ በጻፈች ጊዜ እንዲህ ብላለች፦ “ነጠላነት በሚያስገኘው እንደልብ ወዲያ ወዲህ የመዘዋወር ተጨማሪ ነፃነት በመጠቀም በአገልግሎት ለመጠመድ ችዬ ነበር። ይህም ትልቅ ደስታ አምጥቶልኛል። . . . ባለፉት ዓመታት ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና በጣም ጥልቅ ሆኖአል። በአፍሪካ አገር ነጠላ ሴት ሆኜ ስኖር የይሖዋን ጥበቃ ተመልክቼአለሁ።”

18 በመጠበቂያ ግንብ ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ያገለገለ አንድ ወንድም የተናገራቸው ቃላትም ልብ ልንላቸው የሚገቡ ናቸው። ምንም እንኳን ያላገባ ቢሆንና ተስፋው ሰማያዊ ስለሆነ ወደፊት የማግባት ተስፋ ባይኖረውም ደስተኛ ነበር። የ79 ዓመት ሰው በነበረ ጊዜ እንዲህ ብሎ ጽፎአል፦ “የእሱን ቅዱስ ፈቃድ ማድረጌን መቀጠል እንድችል በመንፈሳዊም ሆነ በሰብአዊ ጤናማና ጠንካራ እንድሆን ጥበብና እርዳታ እንዲሰጠኝ የተወደደውን ሰማያዊ አባታችንን በየቀኑ በጸሎት እጠይቀዋለሁ። በእነዚህ ይሖዋን በማገልገል ባሳለፍኳቸው 49 ዓመታት አስደሳች በሆነ በሚያረካና በተባረከ ሕይወት ተደስቻለሁ። በይሖዋ የማይገባ ቸርነት ለእሱ ክብርና ለሕዝቦቹ በረከት በሚያስገኝ ሁኔታ ማገልገሌን ለመቀጠል እጓጓለሁ . . . መልካሙን የእምነት ገድል እንድጋደል የረዳኝ የይሖዋ ደስታ ነው። የይሖዋ ጠላቶች ከምድር ሙልጭ ብለው ሲጠፉና የይሖዋ ክብር ምድርን ሲሞላት ለማየት እጓጓለሁ።”—ዘኁልቁ 14:21፤ ነህምያ 8:10፤ መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 15, 1968 ገጽ 692-702

እውነተኛ ደስታ የተመካው በምን ላይ ነው?

19. ምንጊዜም ደስታችን የተመካው በምን ላይ ነው?

19 ከዘላለም እስከ ዘላለም እውነተኛ ደስታ የሚያመጡልን ነገሮች ከይሖዋ ጋር ያለን ውድ ዝምድና፣ የእሱን ሞገስና በረከት ማግኘት ናቸው። ያገቡ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳን እውነተኛ ደስታ ስለሚገኝበት ነገር ይህን የመሰለ ትክክለኛ አመለካከት ስላላቸው በሕይወታቸው ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዘው ጋብቻቸው እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። የሚከተለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ይከተላሉ፦ “ዳሩ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እናገራለሁ ዘመኑ አጭር ሆኖአል። ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 7:29) ይህም ሚስቶቻቸውን ፈጽሞ ቸል ይበሏቸው ማለት አይደለም። የጎለመሱ ክርስቲያን ባሎች የይሖዋን አገልግሎት ያስቀድማሉ። አምላካዊ፣ አፍቃሪና ደጋፊ የሆኑ ሚስቶቻቸውም እንደዚሁ ያደርጋሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከባሎቻቸው ጋር የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነዋል።—ምሳሌ 31:10-12, 28፤ ማቴዎስ 6:33

20. ብዙ ክርስቲያኖች ጋብቻቸው ስላስገኘላቸው መብቶች ምን ተገቢ ዝንባሌ አላቸው?

20 በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት፣ በቤቴል እና በጉባኤ ሽማግሌነት የሚያገለግሉ ያገቡ ወንድሞች የመንግሥቱን ፍላጎት የሚያስቀድሙ ያገቡ ክርስቲያኖች ስለሆኑ በዓለም ሙሉ በሙሉ አልተጠቀሙም። ጋብቻቸው ያስገኘላቸውን መብት ሕይወታቸውን ለወሰኑለት ለይሖዋ ከሚያቀርቡት አገልግሎት ጋር አስማምተው ይኖራሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:31) ቢሆንም ደስተኞች ናቸው። ለምን? ምክንያቱም የበለጠ ደስታ የሚያስገኝላቸው ጋብቻቸው ሳይሆን ይሖዋን ማገልገላቸው ነው። ብዙ ታማኝ ባሎችና ሚስቶች እንዲሁም ልጆቻቸው ይህን በመሰለ አኗኗር በመኖራቸው ደስተኞች ናቸው።

21, 22. (ሀ) በኤርምያስ 9:23, 24 መሠረት በደስታ እንድንሞላ የሚያደርገን ነገር ምንድን ነው? (ለ) በምሳሌ 3:13-18 ላይ ምን ለደስታ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ነገሮች ተዘርዝረዋል?

21 ነቢዩ ኤርምያስም እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “[ይሖዋ (አዓት)] እንዲህ ይላል ጠቢብ በጥበቡ አይመካ ኃይልም በኃይሉ አይመካ፣ ባለጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው ምሕረትንና ፍርድን፣ ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ [ይሖዋ (አዓት)] መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና ይላል [ይሖዋ (አዓት)]።”—ኤርምያስ 9:23, 24

22 ያገባንም ሆንን ያላገባን ትልቁ የደስታችን ምንጭ ይሖዋን ማወቃችንና የእሱን ፈቃድ ስለምናደርግ በረከቱን እንደምናገኝ እርግጠኛ መሆናችን መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ የሚደሰትባቸውን ነገሮች ጠለቅ ብለን ለማስተዋል በመቻላችን ደስተኞች ነን። ብዙ ሚስቶችን ያገባው ንጉሥ ሰለሞን ጋብቻ ለደስታ ብቸኛ ቁልፍ ነው ብሎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ብሏል፦ “ጥበብን የሚያገኝ ሰው [ደስተኛ (አዓት)] ነው፤ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፣ በብርና በወርቅ ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ከቀይ እንቁም ትከብራለች፣ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፣ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የተመረኮዛትም ሁሉ [ደስተኛ (አዓት)] ነው።”—ምሳሌ 3:13-18

23, 24. የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በሙሉ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ደስተኞች እንደሚሆኑ እርግጠኛ ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

23 እኛ ያገባነው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ዘላለማዊ ደስታ እናግኝ። በራሳቸው ምርጫም ይሁን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ነጠላ የሆኑ የተወደዱ ወንድሞችና እህቶችም የሚያጋጥሙአቸውን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁመው በመጽናትና አሁንና ለዘላለም ይሖዋን በማገልገል ደስታ ያግኙ። (ሉቃስ 18:29, 30፤ 2 ጴጥሮስ 3:11-13) በሚመጣው የአምላክ ሥርዓት ውስጥ የመጽሐፍ “ጥቅሎች” ይከፈታሉ። (ራዕይ 20:12) እነዚህም ጥቅሎች ታዛዥ ለሆኑት የሰው ዘሮች ደስታ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ አስደሳች አዲስ ትዕዛዞችንና ሕጐችን የያዙ ይሆናሉ።

24 ደስተኛው አምላካችን ደስታችንን የተሟላ የሚያደርጉልንን ብዙ ግሩም የሆኑ ነገሮችን እንዳዘጋጀልን ትምክህት ሊሰማን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) አምላክ ‘እጁን ከፍቶ ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን ማጥገቡን’ ይቀጥላል። (መዝሙር 145:16) ምንጊዜም ቢሆን አሁንም ሆነ ወደፊት እውነተኛ ደስታ ይሖዋን በማገልገል የሚገኝ መሆኑ አያስደንቅም።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ለይሖዋ ውስን አገልጋዮች ደስታ የሚያስገኝላቸው ነገር ምንድን ነው?

◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ያላገቡ ደስተኛ የይሖዋ አገልጋዮች እነማን ናቸው?

◻ ጳውሎስ ነጠላነትን ያበረታታ የነበረው ለምንድን ነው? አንዳንድ ክርስቲያኖች የነጠላነት ሕይወት አስደሳች ሕይወት ሆኖ ያገኙት እንዴት ነው?

◻ ደስታችን ሁልጊዜ የተመካው በምን ላይ ነው?

◻ በአዲሱ ሥርዓት ታማኞች የሆኑ ሁሉ ደስተኞች እንደሚሆኑ እርግጠኞች መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ነጠላ እህቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ይሖዋን በደስታ እያገለገሉ ናቸው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዋነኛው የደስታ ምንጭ ይሖዋን ማገልገል ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ