የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 6/15 ገጽ 22-27
  • በዓለም ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን ማጥመድ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በዓለም ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን ማጥመድ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰዎችን ማጥመድ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ከባድ ሥራ ነው
  • በዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ የተገኙ እድገቶች
  • ሁሉም የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው
  • ለእድገቱ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች
  • እኛስ ልናሻሽል እንችላለንን?
  • የሰዎች አጥማጅ ሆኖ ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ማስገር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • መረቡና ዓሦቹ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 6/15 ገጽ 22-27

በዓለም ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን ማጥመድ

“ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፣ ግድ ደርሶብኝ ነውና፣ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ”—1 ቆሮንቶስ 9:16

1, 2. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 9:16 ላይ የሠፈሩትን ቃላት ፈጽመው የተገኙት እነማን ብቻ ናቸው? እንዲህ ብለህ የመለስከውስ ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የትኛውን ኃላፊነት ተቀብለዋል?

በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ጳውሎስ በተናገራቸው በእነዚህ ቃላት የተገለጸውን ከባድ ሥራ ፈጽመው የተገኙት እነማን ናቸው? ‘ስለ መንፈሣዊ ፍላጎታቸው የሚያስቡ’ ወንዶችንና ሴቶችን ለማጥመድ በሚሊዮን በሚቆጠር ብዛት በዓለም ላይ የተሠማሩት እነማን ናቸው? (ማቴዎስ 5:3 (አዓት)) በማቴዎስ 24:14 ላይ ያለውን የክርስቶስ ትዕዛዝ ለመፈጸም ሲሉ በብዙ አገሮች እስራት፣ ሞትና የመሳሰሉት ሥቃዮች የደረሱባቸው እነማን ናቸው?

2 የታሪክ መዝገብ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው በማለት መልሱን ይሰጠናል። ባለፈው ዓመት ብቻ ከአራት ሚሊዮን የሚበልጡ ምሥክሮች በ211 አገሮችና ቀበሌዎች ከ200 በላይ በሚሆን ቋንቋ ምሥራቹን አውጀዋል። እነዚህ ሰዎች ተመርጠው የሠለጠኑ ሚሲዮናውያን ብቻ አልነበሩም። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤትና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የመስበክ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እምነታቸውን ለሌሎች ማካፈል እንደሚያስፈልጋቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ዕውቀት ኃላፊነት እንደሚያስከትል ስለሚገነዘቡ ነው።—ሕዝቅኤል 33:8, 9፤ ሮሜ 10:14, 15፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16, 17

ሰዎችን ማጥመድ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ከባድ ሥራ ነው

3. ዓሣ የማጥመዱ ሥራ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል?

3 ይህ ታላቅ ዓሣ የማጥመድ ሥራ በአንድ ወንዝ ወይም ሐይቅ ወይም በአንድ ውቅያኖስ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ኢየሱስ እንዳዘዘው “ለአሕዛብ ሁሉ” የሚዳረስ ነው። (ማርቆስ 13:10) ኢየሱስ ወደ አባቱ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፣ እነሆም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏቸው ነበር።—ማቴዎስ 28:19, 20

4. (ሀ) የመጀመሪያዎቹን የኢየሱስ አይሁዳውያን ተከታዮች ሳያስደነግጣቸው ያልቀረው ነገር ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራቸውን ስፋት የሚመለከቱት እንዴት አድርገው ነው?

4 ይህ ትዕዛዝ አይሁዳውያን ለነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች የሚያስደነግጥ ትዕዛዝ ነበር። ኢየሱስ አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት “ንጹሕ ወዳልሆኑት” የአሕዛብ ወገኖች ሄደው እንዲያስተምሯቸው መንገሩ ነበር። ይህ ሥራ የሚያስከትለውን ለውጥ ለመቀበልና ሥራውን ለመፈጸም ራሳቸውን ማስተካከል አስፈልጎአቸው ነበር። (ሥራ 10:9-35) ከዚህ ሥራ ለመሸሽ አይችሉም ነበር። ኢየሱስ ከምሳሌዎቹ በአንዱ ላይ እንደተናገረው “እርሻውም ዓለም” እንደሆነ ነግሮአቸው ነበር። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በጠቅላላው ዓለም ላይ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከአምላክ የተሰጣቸውን ተልእኮ የሚፈጽሙበትን ባሕር የሚወስንባቸው ‘የባሕር ግዛት ድንበር’ የለም። የሃይማኖት ነፃነት በሌለባቸው አካባቢዎች ሥራቸውን በጥንቃቄና በጥበብ ለማከናወን ሊገደዱ ይችላሉ። ቢሆንም ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን በታላቅ ጥድፊያ ያከናውናሉ። አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? የዓለም ሁኔታዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜዎች ዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ዘመን እንደምንኖር ስለሚያመለክቱ ነው።—ማቴዎስ 13:38፤ ሉቃስ 21:28-33

በዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ የተገኙ እድገቶች

5. ለዓለም አቀፉ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ምላሽ እየሰጡ ያሉት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

5 አብዛኞቹ የመንግሥቱ ወራሾች ከአሕዛብ የተሰበሰቡት ከ1935 በፊት ነው። የመንግሥቱ ወራሾች ቁጥር ሞልቶአል ማለት ነው። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ ከ1935 ጀምሮ “ምድርን የሚወርሱትን” “ገሮች” ተብለው የተጠሩትን ትሑት ሰዎች ሲፈልጉ ቆይተዋል። (መዝሙር 37:11, 29) እነዚህ ሰዎች በዓለም ላይ “ስለተሠራው ርኩሰት ሁሉ የሚያለቅሱና የሚተክዙ” ሰዎች ናቸው። “ታላቁ መከራ” መጥቶ ብልሹና ወራዳ የሆነው የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ከመጥፋቱና የሰይጣን አምላኪዎች የመጨረሻ ጥፋት ምሳሌ በሆነው “የእቶን እሳት” ውስጥ ከመጣላቸው በፊት ከአምላክ መንግሥት ጎን የሚያሰልፋቸውን እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው።—ሕዝቅኤል 9:4፤ ማቴዎስ 13:47-50፤ 24:21

6, 7. (ሀ) የስብከቱን ሥራ በሚመለከት በ1943 ምን እርምጃ ተወሰደ? (ለ) ምን ውጤትስ ተገኘ?

6 ዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ እስከ አሁን የተሳካ ውጤት አስገኝቶአልን? የተፈጸሙት ሁኔታዎች መልሱን ይንገሩን። ወደ 1943 መለስ ስንል ገና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያላቆመ ቢሆንም በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙት ታማኝ ቅቡአን ወንድሞች ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፍ የማጥመድ ሥራ መከናወን እንደሚኖርበት ቀደም ብለው ተገንዝበው ነበር። ታዲያ ምን ዓይነት እርምጃዎች ተወሰዱ?a—ራእይ 12:16, 17

7 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በ1943 በየስድስት ወሩ አንድ መቶ ሚሲዮናውያንን እያሠለጠነ የሚልክ ጊሊያድ (በዕብራይስጥ “የምሥክሮች ክምር” ማለት ነው፣ ዘፍጥረት 31:47, 48) የሚባል የሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት አቋቋመ። ከዚህ ትምህርት ቤት የሚመረቁት ሚሲዮናውያን ምሳሌያዊ ዓሣ አጥማጆች በመሆን በምድር በሙሉ የሚላኩ ናቸው። በዚያ ጊዜ ሰዎችን የማጥመዱን ሥራ በ54 አገሮች ውስጥ በትጋት የሚያከናውኑ 126,329 ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። በአሥር ዓመት ውስጥ ይህ ቁጥር በጣም አድጎ በ143 አገሮች የሚያገለግሉ 519,982 ምሥክሮች ተገኙ። በእርግጥ የጊሊያድ ትምህርት ቤት ባህሉን ወደማያውቁት አገር ለመሄድና ከአዲስ የማጥመጃ ውኃዎች ጋር ለመለማመድ ፈቃደኛ የሆኑ ደፋር ወንድና ሴት ምሳሌያዊ ዓሣ አጥማጆችን አስገኝቶአል። በዚህም የተነሳ ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን ተቀብለዋል። እነዚህ ሚሲዮናውያን አብረዋቸው ያገለግሉ የነበሩት የየአገሩ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ ለሚታየው ከፍተኛ ጭማሪ መሠረት ጥለዋል።

8, 9. (ሀ) ስለ ሚሲዮናዊነት አገልግሎት የትኞቹን ታላላቅ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል? (ለ) ሚሲዮናውያን በአገልግሎት መስካቸው ትልቅ ዕድገት ያገኙት እንዴት ነው? (በተጨማሪም የይሖዋ ምስክሮችን የ1992 የዓመት መጽሐፍ ተመልከቱ)

8 ቀደም ካሉት የጊሊያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች መካከል በአሁኑ ጊዜ በ70 ወይም በ80 ዓመት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም አሁንም በተመደቡባቸው ባዕድ አገሮች በማገልገል ላይ የሚገኙ አሉ። በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን የ82 ዓመቱ ኤሪክ ብሪተንና ባለቤቱ ክርስቲና ናቸው። በ1950 ከ15ኛው የጊሊያድ ኮርስ የተመረቁት እነዚህ ባልና ሚስት እስከ አሁን ድረስ በብራዚል አገር በማገልገል ላይ ናቸው። ኤሪክና ክሪስቲና በብራዚል አገር ለማገልገል ሲሄዱ በአገሩ የነበሩት ምሥክሮች ከ3,000 ያነሱ ነበሩ። አሁን ግን ከ300,000 የሚበልጡ ምሥክሮች አሉ! በእርግጥም በብራዚል አገር የተከናወነው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ጥሩ ውጤት በማስገኘቱ “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ” ሆኗል።—ኢሳይያስ 60:22

9 በአፍሪካ ውስጥ ስለሚያገለግሉት ሚሲዮናውያንስ ምን ለማለት እንችላለን? አብዛኞቹ ከማያውቁት ባህል ጋር በመለማመዳቸው የአፍሪካን ሕዝቦች ወደዋቸዋል። በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ በማገልገል ላይ ያሉት ወንድማማቾቹ ዮሐንስና ኤሪክ ኩክ፣ እንዲሁም ሚስቶቻቸው ካተሊንና መርትል ናቸው። ዮሐንስና ኤሪክ በ1947 የተደረገው የጊሊያድ ስምንተኛ ኮርስ ተመራቂዎች ናቸው። በአንድነት ወይም በተናጠል በአንጎላ፣ በዚምባብዌ፣ በሞዛምቢክና በደቡብ አፍሪካ አገልግለዋል። በአፍሪካ ውስጥ አንዳንድ ሚሲዮናውያን በበሽታ ምክንያት ሌሎች ደግሞ በጦርነትና በስደት ምክንያት ሞተዋል። ለምሳሌ አለን ባቴና አርተር ሎውሰን በቅርቡ በላይቤሪያ ይደረግ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ሞተዋል። ይሁን እንጂ ከአፍሪካ ውኃዎችም ብዙ ውጤት ተገኝቶባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ400,000 የሚበልጡ ምሥክሮች በዚህ ሰፊ አህጉር ውስጥ ተሰራጭተው ይገኛሉ።

ሁሉም የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው

10. አቅኚዎች የሚመሰገን ሥራ በማከናወን ላይ የሚገኙት ለምንና በምን መንገድ ነው?

10 ከባዕድ አገሮች የተላኩት ሚሲዮናውያን በሺዎች የሚቆጠሩ ቢሆኑም በየጉባኤዎች ያሉት የአገሩ ተወላጅ አስፋፊዎችና አቅኚዎችb ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በምድር ዙሪያ የሚደረገውን የስብከት ሥራ አብዛኛውን ክፍል የሚሠሩት እነሱ ናቸው። በ1991 በአማካይ ከ550,000 የሚበልጡ አቅኚዎችና ተጓዥ አገልጋዮች ነበሩ። እነዚህ ታማኝ ምሥክሮች በሙሉ በየወሩ ከ60 እስከ 140 ሰዓት የሚያክል ጊዜ በስብከቱ ሥራ በማሳለፍ በታላቁ የማጥመድ ሥራ ለመሳተፍ ልዩ ጥረት የሚያደርጉ መሆናቸውን ስናስብ ይህ ቁጥር ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን እንገነዘባለን። አብዛኞቹ ይህን ሥራ ለማከናወን ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕትነትና ወጪ ይከፍላሉ። ግን ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላካቸውን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ሐሳባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም ኃይላቸው ስለሚወዱና ጎረቤቶቻቸውንም እንደራሳቸው ስለሚወዱ ነው።—ማቴዎስ 22:37-39

11. የይሖዋ መንፈስ በሕዝቦቹ መካከል እየሠራ እንዳለ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?

11 የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ያልሆኑ ነገር ግን ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን በይሖዋ አገልግሎት ባለ ኃይላቸው በሙሉ ስለሚሳተፉት ሦስት ተኩል ሚልዮን የሚያክሉ ምሥክሮችስ ምን ለማለት ይቻላል? አንዳንዶች ሚስቶችና የሚያሳድጉአቸው ትናንሽ ልጆች ያሉአቸው ሲሆኑ ውድ ከሆነው ጊዜያቸው ከፊሉን ለዓለም አቀፉ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ያውላሉ። ብዙዎቹ ደግሞ የሙሉ ጊዜ ሥጋዊ ሥራ ያላቸው ቢሆኑም በሣምንቱ የመጨረሻ ቀኖችና በምሽቶች ለአዳዲስ ሰዎች እውነትን ያስተምራሉ። ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ በስብከቱ ሥራ የሚካፈሉና በመልካም ጠባያቸው እውነትን የሚያስመሰግን እጅግ ብዙ ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በዕድሜ አነስተኛ የሆኑ ወጣቶች አሉ። ምንም ዓይነት ገንዘብ ሳይከፈላቸው በፈቃደኝነት በየወሩ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩ ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ አባሎች ያሉት ሌላ የሃይማኖት ድርጅት ይገኛልን? በእርግጥም ይህ የይሖዋ መንፈስ እየሠራ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው!—መዝሙር 68:11፤ ሥራ 2:16-18፤ ከዘካርያስ 4:6 ጋር አወዳድር።

ለእድገቱ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች

12. ሰዎች እውነትን በመቀበል ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው? ብዛታቸውስ ምን ያህል ነው?

12 ይህ ሰፊ የስብከት ሥራ በየዓመቱ የሚያስደንቅ ውጤት እያስገኘ ነው። በ1991 ከ300,000 የሚበልጡ አዲስ ምሥክሮች ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመጥለቅ ተጠምቀዋል። ይህ ማለት እያንዳንዳቸው 100 ምሥክሮች ያሉአቸው 3,000 አዳዲስ ጉባኤዎች ተመስርተዋል ማለት ነው። ይህን የሚያክል እድገት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የተናገረውን እናስታውስ፦ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፣ . . . ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።” ስለዚህ አንድ ሰው ለዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ ጥሩ ምላሽ የሚሰጠው በሰው ጥረት ብቻ አይደለም። ይሖዋ የሰዎች የልብ ሁኔታ ስለሚገነዘብ የሚገባቸውን ሰዎች ወደ እርሱ ይስባቸዋል።—ዮሐንስ 6:44, 45፤ ማቴዎስ 10:11-13፤ ሥራ 13:48

13, 14. ብዙ ምሥክሮች ምን ዓይነት ጥሩ ዝንባሌ አሳይተዋል?

13 ይሁን እንጂ ይሖዋ ሰዎችን ወደ ራሱ ለመሳብ የሚጠቀመው በሰብአዊ ዓሣ አጥማጆች ነው። ስለዚህ ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ለሚያከናውኑበት ክልልና ለሰዎች ያላቸው ዝንባሌ በጣም አስፈላጊ ነው። አብዛኞቹ አጥማጆች ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የጻፋቸውን ቃላት ከልብ ሲፈጽሙ መመልከት እንዴት የሚያበረታታ ነው። “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”—ገላትያ 6:9

14 ብዙ ታማኝ ምሥክሮች ለብዙ አሥርተ ዓመታት በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች በቅርብ እየተከታተሉ ሲሰብኩ ቆይተዋል። እነዚህ ታማኝ ምሥክሮች ናዚዝም፣ ፋሺዝምና ሌሎች አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሲነሱና ሲወድቁ ተመልክተዋል። አንዳንዶች ከ1914 ጀምሮ ለተደረጉት ብዙ ጦርነቶች የዓይን ምሥክሮች ሆነዋል። የዓለም መሪዎች ተስፋቸውን በመጀመሪያ በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በኋላ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ላይ ሲጥሉ ተመልክተዋል። የይሖዋ ሥራ በብዙ አገሮች ሲታገድና በኋላ ደግሞ ሕጋዊ እውቅና ሲያገኝ ተመልክተዋል። እነዚህ ሁኔታዎች በተፈራረቁባቸው ጊዜያት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ማጥመድን የሚጨምረውን ለሰዎች መልካም የማድረግ ሥራቸውን አቁመው አያውቁም። በጣም ታላቅ የሆነ የፍጹም አቋም ጠባቂነት ምሳሌ ነው።—ማቴዎስ 24:13

15. (ሀ) በዓለም አቀፉ ክልላችን ከሚያጋጥሙን የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ለመስማማት የሚያስችለን ምን ዓይነት እርዳታ አግኝተናል? (ለ) እነዚህ ጽሑፎች በተመደባችሁባቸው ክልሎች የረዱአችሁ እንዴት ነው?

15 ለዚህ ዓለም አቀፍ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሌሎች ነገሮችም አሉ። አንደኛው የአጥማጆቹ ዝንባሌ እንደ ክልሉ ሁኔታ የሚለዋወጥ መሆኑ ነው። የተለያየ ባህል፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ያላቸው ሰዎች ወደ ተለያዩ አገሮች ይፈልሳሉ። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮችም እነዚህ የተለያዩ ሰዎች ላሏቸው አመለካከቶች ያላቸውን ግንዛቤ አስፍተዋል። ዓለም አቀፉ ጉባኤም መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስነ ጽሑፎችን ከ200 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ብዙ ረድቷል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በአሁኑ ጊዜ ቼክንና ስሎቫክን ጨምሮ በ13 ቋንቋዎች በሙሉ ወይም በከፊል ተተርጉሞ ይገኛል። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር በአሁኑ ጊዜ በ198 ቋንቋዎች ታትሞአል። ከሀውሳ እስከ ፖርቱጊዝ በተለያዩ ብዙ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ 72 ሚልዮን በሚያክሉ ቅጂዎች ተሠራጭቶአል። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ደግሞ በ69 ቋንቋዎች ተዘጋጅቶአል። በ29 ቋንቋዎች የተተረጎመው የሰው ልጆች አምላክን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ የተባለው መጽሐፍም ስለ ዋና ዋናዎቹ ሃይማኖቶች አመሠራረትና እምነቶች ለማስተዋል ከማስቻሉም በላይ ለዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ ከፍተኛ ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል።

16. አንዳንዶች በሌላ አገሮች ለቀረበው ጥሪ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?

16 ለዓለም አቀፉ የማጥመድ ሥራ አስተዋጽኦ ያደረገው ሌላ ነገር ምንድን ነው? በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ለመቄዶንያ ጥሪ’ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች ሆነዋል። ጳውሎስ አምላክ ያቀረበለትን ጥሪ በመቀበል ከታናሿ እስያ ተነስቶ በአውሮፓ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈቃደኛ እንደሆነ ሁሉ ብዙ ምሥክሮችም ብዙ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደሚፈለጉባቸው፣ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ይበልጥ አስፈላጊ ወደሆኑባቸው አገሮችና ቀበሌዎች ሄደዋል። እውነተኛ ዓሣ አጥማጆች በአካባቢያቸው ባለው ባሕር ውስጥ ብዙ ጊዜ ደጋግመው ዓሣ ካጠመዱ ብዙ ጀልባዎች ወዳልተሰማሩባቸውና ብዙ ዓሣዎች ወደሚገኙባቸው ባሕሮች የሚዛወሩበትን ሁኔታ የሚመስል እርምጃ ወስደዋል።—ሥራ 16:9-12፤ ሉቃስ 5:4-10

17. ‘ለመቄዶንያው ጥሪ’ ምላሽ የሰጡ ምን ጥሩ ምሳሌዎች አሉን?

17 በቅርቡ በተደረጉት የጊሊያድ ሚሲዮናውያን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ኮርሶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተምረው በሌሎች አገሮችና ባሕሎች ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የተውጣጡ ብዙ ተማሪዎች ተካፍለዋል። በተመሳሳይም ብዙ ነጠላ ወንድሞች በአገልግሎት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አማካኝነት የሁለት ወር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ጉባኤዎችንና ክልሎችን እንዲያጠናክሩ ወደ ሌሎች አገሮች ተልከዋል። ሌሎች ልዩ የሆኑ የዓሣ ማጥመጃ ክልሎች ደግሞ በምሥራቅ አውሮፓ አገሮችና በቀድሞ ሶቪየት ኅብረት ሪፑብሊክ በመከፈት ላይ ናቸው።—ከሮሜ 15:20, 21 ጋር አወዳድር።

18. (ሀ) አቅኚዎች ውጤታማ አገልጋዮች የሚሆኑት ለምንድን ነው? (ለ) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎችንስ እንዴት ሊረዱ ይችላሉ?

18 ለዓለም አቀፉ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ተጨማሪ እርዳታ በማበርከት ላይ የሚገኘው ሌላ ዝግጅት ደግሞ የዘወትር አቅኚዎች የሚካፈሉበት የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ነው። በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለአቅኚዎች ብቻ የተዘጋጀውን በዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን ማብራት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት “የፍቅርን መንገድ መከታተል”፣ “የኢየሱስን አርአያ መከተል”፣ “የማስተማር ችሎታን ማሳደግና” የመሳሰሉትን ርዕሰ ጉዳዮች ስለሚመረምሩ የአገልጋይነት ችሎታቸውን ያሻሽላሉ። ጉባኤዎች እነዚህን ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ዓሣ የሚያጠምዱና ሌሎችን በዚህ ትልቅ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ሊያሰለጥኑ የሚችሉ ብቃት ያላቸው አገልጋዮች በማግኘታቸው ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባቸዋል!—ማቴዎስ 5:14-16፤ ፊልጵስዩስ 2:15፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:1, 2

እኛስ ልናሻሽል እንችላለንን?

19. እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

19 እኛም እንደ ጳውሎስ ሁልጊዜ ወደ ፊት የሚመለከትና ይሆናል የሚል ዝንባሌ እንዲኖረን እንፈልጋለን። (ፊልጵስዩስ 3:13, 14) ጳውሎስ ከሁሉም ዓይነት ሰዎችና ሁኔታዎች ጋር ይስማማ ነበር። የጋራ መወያያ ነጥብ እንዴት ማግኘት እንደሚችልና ከአካባቢው ዝንባሌና ባህል ጋር የሚስማማ ምክንያት እያቀረበ እንዴት ከሰዎች ጋር እንደሚወያይ ያውቅ ነበር። የቤቱ ባለቤት ለመንግሥቱ መልእክት የሚያሳየውን ዝንባሌ በንቃት በመከታተልና መልእክታችንን ከሰውየው ፍላጎት ጋር በማስማማት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንችላለን። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚረዱ ብዙ ዓይነት ጽሑፎች ስላሉን ከግለሰቡ አመለካከት ጋር የሚስማማውን መጽሐፍ መርጠን ልናበረክትለት እንችላለን። በተጨማሪም ራሳችንን ከሁኔታዎች ጋር በማስማማት ረገድ ያለን ችሎታና ንቃታችን በዓሣ ማጥመድ ሥራችን ጥሩ ውጤት እንድናገኝ ያስችለናል።—ሥራ 17:1-4, 22-28, 34፤ 1 ቆሮንቶስ 9:19-23

20. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ የማጥመድ ሥራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አሁን በግለሰብ ደረጃ ያለብን ኃላፊነት ምንድን ነው?

20 ይህ ልዩ የሆነ ዓለም አቀፍ ዓሣ የማጥመድ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሰይጣን ዓለም ሥርዓት የሚያከትምበት ጊዜ በጣም ቅርብ መሆኑን ቀደም ብለው ከተፈጸሙትም ሆነ አሁን በመፈጸም ላይ ከሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስለምንረዳ ነው። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? በዚህ መጽሔት ሦስት ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች በዓለም አቀፍ ውኃዎች በምናከናውነው ዓሣ የማጥመድ ሥራችን ትጉሆችና ቀናተኞች የመሆን ኃላፊነት እንዳለብን ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ይሖዋ በትጋት የምናከናውነውን የማጥመድ ሥራ እንደማይረሳ መጽሐፍ ቅዱስ ጠንካራ ዋስትና ይሰጠናል። ጳውሎስ እንዲህ ብሎአል፦ “እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ አመፀኛ አይደለምና። በእምነትና በትዕግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፣ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻው እንድታሳዩ እንመኛለን።”—ዕብራውያን 6:10-12

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በተጨማሪም በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማኅበር ኒው ዮርክ የታተመውን ራእይ፣ ታላቁ መደምደሚያ ቀርቧል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 185 እና 186 ተመልከት

b “አቅኚ አስፋፊ . . . የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ”—ዌብስተርስ ሰርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ

ታስታውሳለህን?

◻ የይሖዋ ምሥክሮች መላውን ዓለም ዓሣ እንደሚያጠምዱበት ባሕር የሚቆጥሩት ለምንድን ነው?

◻ የጊሊያድ ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ዓሣ ለማጥመዱ ሥራ ምን በረከት አስገኝቶአል?

◻ የይሖዋ ምሥክሮች ከዓሣ ማጥመድ ሥራቸው የተሳካ ውጤት እንዲያገኙ ካስቻሉአቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

◻ በግለሰብ ደረጃ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ልናሻሽል የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]

ዓለም አቀፉ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ያስገኛቸው ውጤቶች

ዓመት አገሮች ምሥክሮች

1939 61 71,509

1943 54 126,329

1953 143 519,982

1973 208 1,758,429

1983 205 2,652,323

1991 211 4,278,820

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምስክርነቱ ሥራ አሁንም በገሊላ ዓሣ አጥማጆች መካከል በመከናወን ላይ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ