ይሖዋ፣ የማያዳላው “የምድር ሁሉ ፈራጅ”
“ለሰው ሁሉ ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት”—1 ጴጥሮስ 1:17
1, 2. (ሀ) ይሖዋ ታላቁ ፈራጅ መሆኑን ማሰባችን ሊያስፈራንም ሊያጽናናንም የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከአሕዛብ ጋር ባለው ክርክር ረገድ ምድራዊ አገልጋዮቹ ምን ድርሻ ያበረክታሉ?
ታላቁ “የምድር ሁሉ ፈራጅ” ይሖዋ ነው። (ዘፍጥረት 18:25) የመላው አጽናፈ ዓለም ፈጣሪና አምላክ እንደመሆኑ መጠን በፍጥረቶቹ ላይ ለመፍረድ ሙሉና ያልተገደበ መብት አለው። ይህን ማሰብ የሚያስፈራም የሚያጽናናም ነው። ሙሴ እርስ በርሱ የሚጻረር የሚመስለውን ይህን አስተሳሰብ እንደሚከተለው በማለት ለመግለጽ ተገፋፍቶ ነበር፦ “አምላካችሁ [ይሖዋ (አዓት)] የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፣ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፣ በፍርድ የማያደላ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና . . . ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፣ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል።”—ዘዳግም 10:17, 18
2 እንዴት ያለ የሚያስገርም ሚዛናዊነት ነው! ታላቅ፣ ኃያልና የሚያስፈራ አምላክ ሆኖ ሳለ የማያደላና አፍቃሪ ነው። ድሀ አደጎችን፣ መበለቶችንና ስደተኞችን ይወድዳል። ከይሖዋ የበለጠ አፍቃሪ ፈራጅ ከየት ሊገኝ ይችላል? ይሖዋ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር ሙግት እንዳለው ገልጾ በምድር የሚኖሩ አገልጋዮቹን ለምስክርነት ጠርቶአቸዋል። (ኢሳይያስ 34:8፤ 43:9-12) እርግጥ ነው፣ የይሖዋ አምላክነትና የሉዓላዊነቱ ገዥነቱ ሕጋዊነት መረጋገጥ ምድራዊ አገልጋዮቹ በሚሰጡት ምስክርነት ላይ የተመካ አይደለም። ሆኖም ምሥክሮቹ አምላክነቱንና ታላቅነቱን አምነው ስለመቀበላቸው በሰው ሁሉ ፊት እንዲመሰክሩ የሚያስችላቸውን ታላቅ መብት ሰጥቶአቸዋል። ምሥክሮቹ ራሳቸውን ትክክለኛ ለሆነው ሉዓላዊነቱ ከማስገዛታቸውም በላይ በሕዝባዊ አገልግሎታቸው አማካኝነት ሌሎች ሰዎች ራሳቸውን ለልዑሉ ፈራጅ ሥልጣን እንዲያስገዙ ያነቃቋቸዋል።
የይሖዋ ፍርድ አሰጣጥ
3. የይሖዋን የፍርድ አሰጣጥ እንዴት አጠቃልሎ መግለጽ ይቻላል? እነዚህስ በአዳምና በሔዋን በተፈጸመው ፍርድ ላይ የታዩት እንዴት ነበር?
3 በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመሪያ ዘመናት ላይ ይሖዋ ራሱ አንዳንድ ሕግ ተላላፊዎችን ዳኝቶአል። የእርሱ ፍርድ አሰጣጥ በኋለኞቹ ዘመናት ሕዝቦቹን የመዳኘት ኃላፊነት ለሚሰጣቸው ሰዎች እንደ ምሳሌ ሆኖ አገልግሎአል። (መዝሙር 77:11, 12) ይሖዋ ይከተል የነበረውን የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ መሆንና በሚቻልበት ጊዜ ምሕረት ማድረግ ነው ብሎ ማጠቃለል ይቻላል። በገዛ ፈቃዳቸው ያመጹትንና ፍጹማን ሰብአዊ ፍጡሮች የነበሩት አዳምና ሔዋን ምንም ዓይነት ምህረት ሊደረግላቸው የሚገቡ አልነበሩም። ስለሆነም ይሖዋ የሞት ፍርድ በይኖባቸዋል። ይሁን እንጂ ለዘሮቻቸው ምህረት አሳይቶአል። በአዳምና በሔዋን ላይ የተበየነው የሞት ቅጣት የሚፈጸምበትን ጊዜ በማራዘሙ ልጆች ለመውለድ ችለዋል። ለተወላጆቻቸውም ከኃጢአትና ከሞት ባርነት የሚላቀቁበትን ተስፋ ሰጥቶአቸዋል።—ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 8:20, 21
4. ይሖዋ የቃየንን ጉዳይ የያዘው እንዴት ነበር? ይህስ በተለይ የእኛን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
4 በተለይ ይሖዋ በቃየን ላይ ያደረገው የፍርድ አፈጻጸም የተለየ ትኩረት ልናደርግበት የሚገባ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ፍርድ ‘ከኃጢአት በታች ሊሆን ለተሸጠ’ እና ፍጽምናውን ላጣ የአዳምና የሔዋን ዘር የተሰጠ የመጀመሪያ ፍርድ ስለሆነ ነው። (ሮሜ 7:14) ይሖዋስ የቃየንን አለፍጽምና ግምት ውስጥ በማስገባት የእርሱን ጉዳይ ከወላጆቹ በተለየ መንገድ ተመልክቶት ነበርን? ይህ ሁኔታስ ዛሬ ላሉት የበላይ ተመልካቾች ትምህርት ሊሰጥ ይችላልን? እስቲ እንመልከት። ቃየን መሥዋዕቱ ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ምክንያት ያደረበትን መጥፎ ዝንባሌ ይሖዋ አስተውሎ ከፊቱ ስለተደቀነበት አደገኛ ሁኔታ በፍቅር አስጠንቅቆት ነበር። “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚል አንድ ጥንታዊ አባባል አለ። ይሖዋም በቃየን ውስጥ የተፈጠረውን የኃጢአተኝነት ዝንባሌ እንዲያሸንፍ በሚቻለው መንገድ ሁሉ አስጠንቅቆታል። “መልካም እንዲያደርግ” ለመርዳት ጥረት አድርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 4:5-7) አምላክ ኃጢአተኛ የሆነው የሰው ልጅ ንስሐ እንዲገባ ጥሪ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነው። ቃየን ንስሐ የማይገባ መሆኑን ካረጋገጠና ወንድሙን በመግደል ከባድ ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ግን የሚያገኘው ሰው ሁሉ እንዳይገድለው ከሚከለክል የሐዘኔታ ድንጋጌ ጋር በምድር ላይ ተቅበዝባዥ እና ኮብላይ እንዲሆን ይሖዋ ፈረደበት።—ዘፍጥረት 4:8-15
5, 6. (ሀ) ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ትውልድ ላይ እርምጃ የወሰደው እንዴት ነበር? (ለ) ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ነዋሪዎች ላይ ፍርዱን ከማስፈጸሙ በፊት ምን አድርጎ ነበር?
5 ከውኃ ጥፋት በፊት ‘የሰው ክፋት በምድር ላይ መብዛቱን ሲመለከት ይሖዋ በልቡ አዘነ።’ (ዘፍጥረት 6:5, 6) ከውኃ ጥፋት በፊት የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ነፃ ምርጫ የማድረግ ችሎታቸውን አግባብ ባልሆነ መንገድ ስለ ተጠቀሙበትና በእነርሱ ላይም የቅጣት ፍርድ ለማስፈጸም ስለተገደደ “ተጸጸተ”። ሆኖም “የጽድቅ ሰባኪ” በነበረው በኖኅ አማካኝነት ለብዙ ዓመታት በቂ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ይሖዋ አምላካዊ ባልሆነው ‘ኃጢአተኛ ዓለም’ ውስጥ የሚኖሩትን እነዚህን ሰዎች ከመቅጣት ወደ ኋላ የሚልበት አንዳች ምክንያት አልነበረውም።—2 ጴጥሮስ 2:5
6 በተመሳሳይም ይሖዋ ምግባረ ብልሹ በነበሩት በሰዶምና በገሞራ ነዋሪዎች ላይ ፍርዱን ለማስፈጸም ተገዶ ነበር። ይሁን እንጂ ፍርዱን ከማስፈጸሙ በፊት ምን እንዳደረገ ተመልከቱ። በጻድቁ ሰው በሎጥ ጸሎት አማካኝነት ብቻ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች ይፈጽሙ ስለነበረው አሳዛኝ ሥነ ምግባር ‘የአቤቱታ ጩኸት’ ሰምቶ ነበር። (ዘፍጥረት 18:20፤ 2 ጴጥሮስ 2:7, 8) ይሁን እንጂ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ነገሩን ለማረጋገጥ በመላእክት አማካኝነት ወደ ምድር ‘ወርዶ’ ተመልክቶአል። (ዘፍጥረት 18:21, 22፤ 19:1) በተጨማሪም ፍትሐዊ ያልሆነ የፍርድ እርምጃ እንደማይወስድ ለአብርሃም አረጋግጦለታል።—ዘፍጥረት 18:23-32
7. የፍርድ ኮሚቴ አባሎች በመሆን የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ከይሖዋ የፍርድ አሰጣጥ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
7 በዛሬው ጊዜ ያሉት ሽማግሌዎች ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ሊማሩ ይችላሉ? ይሖዋ ከአዳምና ከሔዋን ጋር ዝምድና ቢኖራቸውም በቀጥታ ጥፋት ላልሠሩት ዘሮቻቸው ፍቅራዊ አሳቢነቱን አሳይቶአል። ለአዳምና ለሔዋን ልጆች ምሕረት አሳይቶአቸዋል። የቃየንን ጉዳይ ስንመለከት፣ ይሖዋ በቃየን ፊት የተደቀነውን አደጋ ተመልክቶ ኃጢአት ከመሥራት እንዲርቅ በደግነት አነጋግሮታል። ተቅበዝባዥ ሆኖ እንዲኖር ከፈረደበት በኋላ እንኳን ቢሆን ለቃየን አሳቢነት ማሳየቱን አላቋረጠም። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ትውልድ ላይ ፍርዱን ያስፈጸመው በብዙ ትዕግስት ከቻለ በኋላ ነበር። ሰዎች ከክፋታቸው አለመመለሳቸውን ሲመለከት ይሖዋ “በልቡ አዘነ።” ሰዎች በጽድቅ ሕጉ ላይ በማመጻቸውና የቅጣት ፍርድ እንዲፈርድባቸው በመገደዱ አዝኖ ነበር። (ዘፍጥረት 6:6፤ ከሕዝቅኤል 18:31፤ 2 ጴጥሮስ 3:9 ጋር አወዳድር።) ሰዶምና ገሞራንም በሚመለከት ይሖዋ እርምጃ የወሰደው ነገሩን ካረጋገጠ በኋላ ነበር። ይህ በአሁኑ ጊዜ ላሉት የፍርድ ጉዳይ ለሚመለከቱ ሰዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
በአበው ዘመን የነበሩት ሰብዓዊ ፈራጆች
8. አባቶች የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩባቸው ዘመናት የትኞቹ የይሖዋ መሠረታዊ ሕጎች ይታወቁ ነበር?
8 በጊዜው በጽሑፍ የሠፈረ ሕግ እንዳልነበረ ግልጽ ቢሆንም አባቶች የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩበት ዘመን የነበረው ኅብረተሰብ የይሖዋን መሠረታዊ ሕጎች ያውቅ ነበር። የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑትም እነዚህን ሕጎች የመጠበቅ ግዴታ ነበረባቸው። (ከዘፍጥረት 26:5 ጋር አወዳድር።) በኤደን የታየው ድራማ የመታዘዝንና ለይሖዋ ሉዓላዊነት የመገዛትን አስፈላጊነት አሳይቶአል። የቃየል ጉዳይም ነፍስ መግደል በይሖዋ ዘንድ የተከለከለ ድርጊት መሆኑን ግልጽ አድርጎአል። ከጥፋት ውኃ በኋላ አምላክ ወዲያውኑ ስለ ሕይወት ቅድስና፣ ስለ መግደል፣ ወንጀለኞችን በሞት ስለ መቅጣትና ደም ስለ መብላት የሚገልጹ ሕጎችን ለሰው ልጆች ሰጥቶአል። (ዘፍጥረት 9:3-6) አብርሃምን፣ ሣራንና በጋዛ አጠገብ ይኖር የነበረውን የጌራራን ንጉሥ አቤሜሌክን የሚመለከት አንድ ሁኔታ በደረሰ ጊዜ ይሖዋ ምንዝርን አጥብቆ አውግዞአል።—ዘፍጥረት 20:1-7
9, 10. አባቶች የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩባቸው ዘመን በነበረው ኅብረተሰብ ውስጥ አንድ ዓይነት የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት እንደነበረ የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
9 በእነዚህ ዘመናት እንደ ዳኞች በመሆን ሕግ ነክ ጉዳዮችን ይመለከቱ የነበሩት የቤተሰብ ራሶች ነበሩ። አብርሃምን በሚመለከት ይሖዋ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የይሖዋን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝ ከአብርሃም ጋር ተዋውቄአለሁ።” (ዘፍጥረት 18:19 አዓት) አብርሃም በእርሱና በሎጥ እረኞች መካከል የተነሳውን ጥል ራስ ወዳድነት በሌለበትና አስተዋይነት በተሞላበት መንገድ አስወግዶአል። (ዘፍጥረት 13:7-11) ይሁዳ የቤተሰቡ ራስና ፈራጅ በመሆን ምራቱ የነበረችው ትዕማር ምንዝር እንደፈጸመች ስላመነ ተወግራ እንድትገደልና በእሳት እንድትቃጠል ፈርዶባታል። (ዘፍጥረት 38:11, 24፤ ከኢያሱ 7:25 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ትክክለኛውን ሁኔታ ባወቀ ጊዜ ከእርሱ ይልቅ እርሷ ጻድቅ እንደሆነች ተናገረ። (ዘፍጥረት 38:25, 26) አንድን የፍርድ ውሳኔ ከማስተላለፍ በፊት ሁኔታውን በሙሉ አጣርቶ ማወቅ ምንኛ አስፈላጊ ነው!
10 የኢዮብ መጽሐፍ ስለ አንድ የዳኝነት ሥርዓት ከመጠቆሙም ሌላ አድልዎ የሌለበት ፍርድ መስጠት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል። (ኢዮብ 13:8, 10፤ 31:11፤ 32:21) ኢዮብ ራሱ የተከበረ ፈራጅ በመሆን በከተማው በር ላይ ተቀምጦ ፍትሕን በማስፈጸም ስለ መበለቲቱና ስለ ድሀ አደጉ ይሟገት ስለነበረበት ጊዜ ተናግሮአል። (ኢዮብ 29:7-16) ስለዚህ እሥራኤላውያን ከግብፅ እስከወጡበትና አምላክ ለእስራኤል ብሔር የመተዳደሪያ ሕገ መንግሥት እስከሰጠበት ጊዜ ድረስ አባቶች የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ “ሽማግሌዎች” የአብርሃም ዘሮች ፈራጆችና ዳኞች ሆነው ያገለግሉ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ አለ። (ዘጸአት 3:16, 18) በሙሴ አማካኝነት የቀረበው የሕጉ ቃል ኪዳን ውል የተደረገውም ሕዝቡን ይወክሉ ከነበሩት “ሽማግሌዎች” ወይም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ነበር።—ዘጸአት 19:3-7
የእስራኤል ሕዝብ የፍርድ ሥርዓት
11, 12. ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በሰጡት አስተያየት መሠረት የእስራኤልን የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት ከሌሎች ብሔራት የፍርድ ሥርዓቶች ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
11 በእስራኤል ምድር የነበረው የፍትህ አስተዳደር በአካባቢያቸው ይኖሩ የነበሩት አሕዛብ ይከተሉት ከነበረው የሕግ ሥርዓት ወይም አፈጻጸም የተለየ ነበር። በፍትሐ ብሔርና በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መካከል የሚደረግ ልዩነት አልነበረም። ሁለቱም ከሥነ ምግባርና ከሃይማኖታዊ ሕጎች ጋር የተሳሰሩ ነበሩ። በባልንጀራ ላይ የሚፈጸም ወንጀል በይሖዋ ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል ተደርጎ ይቆጠር ነበር። አንድሬ ሹራኪ የተባሉት ደራሲ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት እና ሕዝቦች በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የዕብራውያን የዳኝነትና የፍርድ ልማድ በአካባቢአቸው ከሚገኙት የጎረቤት አገሮች ልማድ የተለየ ነው። ልዩነቱ ወንጀሎችንና ቅጣቶችን በመተርጎም ረገድ ብቻ ሳይሆን ሕጎቹ ባላቸው መንፈስ ጭምር ነው። . . . ቶራህ (ሕጉ) ከዕለታዊ አኗኗር የተለየ አልነበረም። በረከት ወይም እርግማን በማስተላለፍ የአንድን ሰው ዕለታዊ አኗኗር ባሕርይና ሁኔታ ይቆጣጠራል። . . . በእስራኤል ምድር ውስጥ የከተማውን የሕግ አፈጻጸም ሥርዓት ለይቶ ለማወቅ አይቻልም። ሕያው የሆነውን አምላክ ፈቃድ በመፈጸም ላይ ሙሉ በሙሉ ባተኮረው አኗኗር የተዋጠ ነበር።”
12 ይህ ልዩ ሁኔታ የእስራኤላውያንን የፍትሕ አስተዳደር በዚያን ዘመን ይኖሩ ከነበሩት አሕዛብ በጣም በላቀ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችሎታል። ይህን በሚመለከት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ኖናል ደ ቮ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የእስራኤላውያን ሕግ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሕጎች ጋር የቅርጽና የይዘት ተመሳሳይነት ቢኖረውም በአገላለጹና በአንቀጾቹ ረገድ ግን ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህ ሃይማኖታዊ ሕግ ነው። . . . ማንኛውም የመካከለኛው ምሥራቅ ሕግ ከዚህ በአምላክ እንደተዘጋጀ ከሚነገርለት ከዚህ ሕግ ጋር ሊተካከል አይችልም። ሥነ ምግባርንና የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚመለከቱ ደንቦችን አጣምሮ መያዝ የቻለው መላውን የመለኮታዊ ቃል ኪዳን መስኮች የሚያጠቃልል በመሆኑና ይህም ቃል ኪዳን ሰዎች እርስ በርሳቸውና ከአምላክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚይዝ በመሆኑ ነው።” ስለዚህ ሙሴ በአድናቆት “በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው?” ሲል መጠየቁ ሊያስደንቀን አይገባም።—ዘዳግም 4:8
በእስራኤል የነበሩት ፈራጆች
13. ሙሴ በአሁኑ ጊዜ ላሉት ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በምን ረገድ ነው?
13 እንዲህ ባለው ከፍተኛ የሕግና የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ በዳኝነት እንዲያገለግል የሚፈለገው ምን ዓይነት ሰው ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በእስራኤላውያን ላይ ፈራጅ እንዲሆን ስለ ተሾመው የመጀመሪያ ሰው እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።” (ዘኁልቁ 12:3) ሙሴ ስለ ራሱ ችሎታ ከመጠን በላይ የሚመካ ሰው አልነበረም። (ዘጸአት 4:10) ሙሴ በሕዝቡ ላይ የመፍረድ ኃላፊነት ቢኖርበትም አንዳንድ ጊዜ በይሖዋ ፊት ለሕዝቦቹ ጠበቃ በመሆን ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር እንዲላቸው ይለምንና ስለ እነርሱ መሥዋዕት ለመሆን ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾ ነበር። (ዘጸአት 32:11, 30-32) ሙሴ እንደሚከተለው በማለት ተቀኝቶአል፦ “ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈሳለች፣ ነገሬም እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፣ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ።” (ዘዳግም 32:2) በራሱ ጥበብ ላይ ተመርኩዞ ሕዝቡን ከመዳኘት ይልቅ “ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፣ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፣ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ” ብሎ ነበር። (ዘጸአት 18:16) ግራ የሚያጋባ ጉዳይ በሚያጋጥመው ጊዜ ይሖዋን ይጠይቅ ነበር። (ዘኁልቁ 9:6-8፤ 15:32-36፤ 27:1-11) ሙሴ በዛሬው ጊዜ ‘የአምላክን መንጋ በእረኝነት ለሚጠብቁና’ የፍርድ ውሳኔዎችን ለሚያደርጉ ሽማግሌዎች በጣም ጥሩ አርዓያ ይሆናል። (ሥራ 20:28) ከወንድሞቻቸው ጋር ያላቸው ዝምድና እንደ ሙሴ ‘በሣር ላይ እንደሚወርድ ካፊያ’ ይሁን።
14. በእስራኤል ሕዝብ ላይ እንዲፈርዱ ሙሴ የመረጣቸው ሰዎች ምን ዓይነት መንፈሳዊ ብቃቶች ነበሩአቸው?
14 ከጊዜ በኋላ ሙሴ የዳኝነቱን ሥራ ብቻውን መሸከም አቃተው። (ዘጸአት 18:13, 18) ሙሴ የአማቱን ምክር በመቀበል የሚረዱትን ሰዎች መረጠ። የተመረጡት እንዴት ያሉ ሰዎች ነበሩ? “አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ። . . . ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፣ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፣ የመቶም አለቆች፣ የአምሳም አለቆች፣ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበዳቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፣ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ።”—ዘጸአት 18:21-26
15. በእስራኤል ሕዝብ መካከል ፈራጅ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ሰዎች ምን ዓይነት ብቃቶች ነበሩአቸው?
15 በዳኝነት እንዲያገለግሉ ከሚመረጡት ሰዎች የሚፈለገው ብቃት ዕድሜ ብቻ እንዳልነበረ ማስተዋል ይቻላል። ሙሴ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፦ “ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮችም አዋቂዎችም [ተሞክሮ ያላቸው (አዓት)]” የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፣ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ።” (ዘዳግም 1:13) ሙሴ ከብዙ ዓመታት በፊት ወጣቱ ኤሊሁ የተናገረውን ቃል በሚገባ ያውቅ ነበር፦ “በዕድሜ ማርጀታቸው ብቻ ጠቢባን አያደርጋቸውም፣ በመሸምገላቸው ብቻ ፍርድን አያስተውሉም።” (ኢዮብ 32:9 አዓት) የሚሾሙት ሰዎች “ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች” መሆን ነበረባቸው። ከሁሉ በላይ ግን ችሎታ ያላቸው፣ አምላክን የሚፈሩ፣ የታመኑ፣ የግፍን ረብ የማይወዱ፣ ጥበበኞችና አስተዋዮች መሆን ነበረባቸው። ስለዚህ በኢያሱ 23:2 እና 24:1 ላይ የተጠቀሱት “አለቆች” እና “ፈራጆች” በእነዚህ ቁጥሮች ላይ ከተጠቀሱት “ሽማግሌዎች” የተለዩ ሰዎች ሳይሆኑ ከመካከላቸው የተመረጡ እንደሆኑ ግልጽ ነው።—ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 549 ተመልከት።
ፍትሕን ማስፈጸም
16. ሙሴ አዲስ ለተሾሙት ፈራጆች ስለሰጣቸው መመሪያዎች ምን ነገሮችን ልብ ማለት ይኖርብናል?
16 ሙሴ ፈራጆች እንዲሆኑ ለተሾሙት ለእነዚህ ሰዎች መመሪያ ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፤ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፤ ታላቁን እንደምትሰሙ፣ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፤ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፤ ከነገርም አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ [ወደ ሙሴ] አምጡት፣ እኔም እሰማዋለሁ’ ብዬ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው።”—ዘዳግም 1:16, 17
17. ፈራጆች እንዲሆኑ የተሾሙት እነማን ነበሩ? ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአቸው ነበር?
17 እርግጥ ነው፣ ሙሴ የፍርድ ጉዳዮችን ሊሰማ የሚችለው በሕይወት እስከቆየ ድረስ ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት ከበድ ያሉ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ወደ ካህናት፣ ወደ ሌዋውያን እና በልዩ ሁኔታ ወደ ተሾሙ ፈራጆች የሚያቀርቡባቸው ዝግጅቶች ተደርገዋል። (ዘዳግም 17:8-12፤ 1 ዜና 23:1-4፤ 2 ዜና 19:5, 8) ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ለሾማቸው ፈራጆች እንዲህ ብሎ ነበር፦ “[ለይሖዋ አዓት] እንጂ ለሰው አትፈርዱምና ፣ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ። . . . እንዲሁ [ይሖዋን አዓት] በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ . . . [ይሖዋን አዓት] እንዳይበድሉ፣ ቁጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም።”—2 ዜና 19:6-10
18. (ሀ) በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፈራጆች የሚሆኑት ሰዎች መከተል ከሚገባቸው መሠረታዊ ሕጎች አንዳንዶቹ ምን ነበሩ? (ለ) ፈራጆቹ በአእምሮአቸው መያዝ የነበረባቸው ምን ነገር ነበር? ይህን በመርሳታቸው ምክንያት የመጡባቸውን ውጤቶች የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
18 የእስራኤል ፈራጆች ሊከተሉአቸው ከሚገቡት መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙ ነበር፦ በድሃውና በሀብታሙ መካከል በእኩልነት መፍረድ (ዘጸአት 23:3, 6፤ ዘሌዋውያን 19:15)፤ አለአንዳች አድልዎ መፍረድና (ዘዳግም 1:17)፤ ጉቦ አለመቀበል። (ዘዳግም 16:18-20) ፈራጆች የሚፈርዱት በይሖዋ በጎች ላይ መሆኑን ዘወትር ማስታወስ ነበረባቸው። (መዝሙር 100:3) ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ከተወባቸው ምክንያቶች አንዱ ካህናቶቻቸውና እረኞቻቸው ሕዝቡን በጽድቅ ከመፍረድ ማቆማቸውና መጨቆናቸው ነበር።—ኤርምያስ 22:3, 5, 25፤ 23:1, 2፤ ሕዝቅኤል 34:1-4፤ ሚልክያስ 2:8, 9
19. ከዘአበ የነበረውን የፍትሕ ሥርዓት መመርመራችን ምን ጥቅም አለው? በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርትስ የምንመለከተው ምን ይሆናል?
19 ዛሬም ቢሆን ይሖዋ አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) ይሖዋ በእስራኤላውያን መካከል እንዲከናወን ይፈልግ የነበረው የዳኝነት ሥርዓት እንዴት ያለ እንደነበረ ያደረግነው አጭር ክለሣ በዛሬው ጊዜ የፍርድ ውሣኔ የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ሽማግሌዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይገባል። ይሖዋ በፈራጅነት ረገድ ያሳየው ምሳሌና በእስራኤላውያን መካከል አቋቁሞት የነበረው የፍርድ ሥርዓት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚኖረው የፍትሕ አስተዳደር ለሚከተለው መሠረታዊ ሥርዓት በምሳሌነት ያገለግላሉ። ይህንንም በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እንመለከታለን።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የይሖዋን የፍርድ አሰጣጥ እንዴት ማጠቃለል ይቻላል?
◻ ይሖዋ ለቃየንና ከጥፋት ውኃ በፊት ለነበረው ትውልድ ያደረጋቸው ነገሮች ለይሖዋ ፍርድ አሰጣጥ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
◻ በጥንቱ አባቶች የቤተሰብ ራስና ሃይማኖታዊ መሪ በነበሩበት ዘመን እንደ ፈራጆች ሆነው ያገለግሉ የነበሩት እነማን ናቸው? እንዴትስ?
◻ የእስራኤልን የፍርድ ሥርዓት ሌሎች አሕዛብ ከነበራቸው የፍርድ ሥርዓት የሚለየው ነገር ምን ነበር?
◻ በእስራኤላውያን መካከል ፈራጆች እንዲሆኑ የተሾሙት ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ? ምን ሥርዓቶችንስ መከተል ነበረባቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንት የእምነት አባቶች ዘመንና በእስራኤል ሕዝብ መካከል የተሾሙት ሽማግሌዎች በከተማዋ በር ተቀምጠው ይፈርዱ ነበር