ውድ የሆነውን የሕይወት ስጦታ ማድነቅ
ሕይወት እንዴት ያለ ውድ ሃብት ነው! ሕይወት ከሌለን ምንም ነገር መሥራት አንችልም። ሕይወት አንዴ ከጠፋ በምንም ዓይነት መንገድ በሰብዓዊ ሰው ሊተካ አይችልም። ሕይወታችን አደጋ ላይ ቢወድቅ ከአደጋው ለመትረፍ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። እንዲያውም አንዳንዶች በጭንቀት በሚያዙበት ጊዜ መለኮታዊ እርዳታ እንዲያገኙ ይጮሃሉ!
መጽሐፍ ቅዱስ በባሕር ላይ በታላቅ ማዕበል ተይዛ ስለነበረች አንድ መርከብ የሚናገረውን ታሪክ እናስታውሳለን። ለመሰበር በተቃረበችበት ጊዜ “መርከበኞቹ ፈሩ፣ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ።” ከዚያም ማንም ሳይቀር ወደ እውነተኛው አምላክ በመጮህ “አቤቱ፣ [ይሖዋ አዓት] . . . እንዳንጠፋ . . . እንለምንሃለን አሉ።” የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በመቀጠል “መርከቢቱም እንድትቀልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት” ይላል።—ዮናስ 1:4-6, 14፥ ከሥራ 27:18, 19 ጋር አወዳድር።
እነዚህ መርከበኞች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ብዙ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶቻቸውን መስዋዕት ለማድረግ እንኳን ዝግጁ ነበሩ። ቁሳዊ ንብረቶችን መተካት ይቻላል። ሕይወታችንን ግን መተካት አንችልም። ሕይወታችንን በደመ ነፍስ የመጠበቅ ችሎታ ስላለን ከአደጋ እንድናለን። አካላችንን እንመግበዋለን፣ እናለብሰዋለን እንዲሁም እንንከባከበዋለን። በምንታመምበት ጊዜ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት እንፈልጋለን።
ይሁን እንጂ ሕይወት ሰጪአችን ከተፈጥሮ ባገኘነው የደመ ነፍስ ባሕርይ ችሎታ ከመመራት የበለጠ ነገር እንድናደርግ ይፈልግብናል። ከሁሉም በላይ ሕይወት በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ነው። ስጦታውንም ያገኘነው በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ ከያዘው አካል ነው። ለሰጪውና ለስጦታው ባለን ልባዊ አድናቆት ተነሳስተን ሕይወትን መንከባከብ አይኖርብንም? ይህ አሳቢነታችን የሌሎች ሰዎችንም ሕይወት መጨመር አይገባውም?
ይሖዋ አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግ ውስጥ የሌሎችን ሕይወትና ጤንነት መጠበቅ የሚያጠቃልል ትዕዛዛት መስጠቱ ሊያስደንቀን አይገባም። (ዘጸአት 21:29፤ ዘዳግም 22:8) በዘመናችን ያሉት ክርስቲያኖችም የሌሎችን ሕይወትና ጤንነት በመጠበቅ ረገድ ንቁ መሆን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ በቤትህ ውስጥ ሕፃናት ልጆች ካሉህ አንዱ ሕፃን በየዋህነት ቢጫወትባቸው ወይም ቢውጣቸው አስከፊ ጉዳት ሊያመጡበት የሚችሉት እንደ ዶቃዎች፣ ስፒሎች ወይም ስለታም እቃዎች በቀላሉ ሊደረሱበት በሚችል ቦታ ላይ በግዴለሽነት ትተህ ትሄዳለህን? አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎችና መድኃኒቶች ሕፃናት ሊደርሱ በማይችሉበት ቦታ ተቀምጠዋልን? በወለል ላይ ውኃ ቢፈስስ አደጋ እንዳያደርስ በፍጥነት ታጸዳዋለህን? የተበላሹ መሣሪያዎችን በፍጥነት ለመጠገን ንቁ ነህን? መኪናህ የዘወትር ቁጥጥር ይደረግለታልን? ጠንቃቃ መኪና ነጂ ነህን? የሕይወትን ውድነት በሚገባ የምታደንቅ ከሆነ በእነዚህና በተመሳሳይ ክልሎች ምክንያታዊ የሆነ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ትገፋፋለህ።
የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች የራሳቸውን ሕይወት ለአደጋ አሳልፈው መስጠታቸው ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ሲጋራ ማጨስ ለጤና ጠንቅ መሆኑን የማያውቅ ማን አለ? ያም ሆኖ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለዚህ ሱስ ባሪያዎች ናቸው። ጤንነታቸው እየተቃወሰ ቢሄድም መርዛማውን ጭስ ወደ ሰውነታቸው ማስገባታቸውን አላቆሙም። ሌሎች በዕፅ ያለአግባብ ሲጠቀሙ ሌሎች ደግሞ በአልኮል መጠጥ በመስከር ራሳቸውን ይጎዳሉ። ኤድስ ፈውስ ያልተገኘለት ገዳይ በሽታ ነው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ከፆታ ብልግና፣ በዕፅ ያለአግባብ ከመጠቀምና ደምን በደም ሥር ከመውሰድ ቢርቁ ኖሮ በሽታው እንዳይተላለፍባቸው ማድረግ ይችሉ ነበር። ምንኛ የሚያሳዝን ለሕይወት አድናቆት ማጣት ነው!—ሮሜ 1:26, 27፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1
ለውጥ ማድረግ ይቻላል!
ታላቁ ፈጣሪያቸውን ይሖዋን የሚያደንቁ ሰዎች ሕይወትን እንደ ውድ ነገር አድርገው የሚመለከቱበት ጠንካራ ምክንያት አላቸው። ሕይወት የአምላክ ቅዱስ ስጦታ ነው። በዚህም ምክንያት ሕይወትን እንደ መለኮታዊ ስጦታ አድርገው ለመያዝ ማንኛውንም አስፈላጊ የሆነ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። በጋና ውስጥ የሚኖር ክዋኩ የተባለ የአንድ አስተማሪ ተሞክሮ እንመልከት። ሕይወቱን በግድ የለሽነት የሚመራ የአልኮል ሱሰኛ ነበር።
ክዋኩ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “በተለይ በምሰክርበት ጊዜ ባለቤቴ እንድታከብረኝ በኃይል ለማስገደድ እሞክር ነበር። ይህም አዘውትሮ ወደ ጦፈ ጭቅጭቅና ጥል ይመራናል። የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ ስለምጠጣ ብዙ ጊዜ ስብራት ደርሶብኛል። ለቤተሰብ መስጠት የሚገባኝን የወር ወጪ በተደጋጋሚ አቋርጥ ነበር። ይህም ባለቤቴን በጣም አድርጎ ያበሳጫት እንደነበረ መረዳት አያስቸግርም ነበር። ምን ጊዜም ገንዘብ ስጨርስ (ብዙ ጊዜ እንደሚያጋጥመኝ) ያለብኝን ሱስ ለማርካት ስል ማድረግ የምችለውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ አደርጋለሁ። በአንድ ወቅት ለሕዝብ ፈተና ምዝገባ ከተማሪዎች የሰበሰብኩትን ገንዘብ ለግል ጥቅም እስከማዋል ደርሻለሁ። ብዙ መጠጥ ከጠጣሁ በኋላ አብረውኝ ይጠጡ የነበሩትን ጓደኞቼን ጋበዝኳቸው። ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ገንዘቡን ማጥፋቴ ተደረሰብኝ። በዚያን ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በጉዳዩ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ከሥራ እባረር ነበር።
“ሕይወቴ የተመሰቃቀለ ነበር። የሠራሁት ሥራ ቢያሳፍረኝም ብዙም ሳይቆይ እረሳው ነበር። በሕይወት ውስጥ ምንም እንዳልተሳካልኝ ስለተሰማኝ ራሴን የማጥፋት ሐሳብ ማውጠንጠን ጀመርኩ። እንደዚህም ሆኖ ከአልኮል ሱሰኝነት ነፃ ለመሆን አልቻልኩም። እንዲያውም በአንድ ወቅት በአንድ ቡና ቤት ውስጥ በሰካራሞች መካከል በተነሳው ጥል ውስጥ እኔም በመግባቴ በጩቤ ተወጋሁ። ይህ ሁኔታ ለመጠጥ ያለኝ ፍቅር አንድ ቀን ሕይወቴን እንደሚያሳጣኝ እንድገነዘብ አደረገኝ።
“በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት እንዲኖረን ለማድረግ በየጊዜው ወደ ቤታችን እየመጡ ይጎበኙን ነበር። ባለቤቴና እኔ ከያዙ የማይለቁ ነዝናዞች ናቸው ብለን በማሰብ ሁልጊዜ ከቤት እንጠፋባቸው ነበር። ይሁንና በአንድ ወቅት ከልቤ በመነሳሳት እነርሱን ለማዳመጥ ወሰንኩ። ያደረግኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወዲያውኑ በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለሚኖረው አስደናቂ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ዓይኖቼን እንድከፍት አስቻለኝ። በይሖዋ ምሥክሮች ረዳትነት መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ እያጠናሁ በሄድኩ ቁጥር ሕይወት ሰጪአችን ለሆነው ለይሖዋና የእሱ ስጦታ ለሆነው ሕይወት ያለኝ አድናቆት የበለጠ ጥልቀት እያገኘ ሄደ። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊነት የበለጠ እየነካኝ መጣ። ይህም ሕይወቴን እንዳስተካክል ተጨማሪ ማበረታቻ ሰጠኝ። መጠጡንም ይሁን የጥንት ጓደኞቼን ያለማቋረጥ መቋቋም ቀላል አልነበረም። ጸሎት ሰሚ የሆነው ይሖዋ የልቤን ውሳኔ ተመልክቶ አደመጠኝ።a
“ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክር ባትሆንም በሕይወቴና በትዳራችን ግንኙነት ላይ ያደረግሁትን ትልቅ ለውጥ በማየቷ እኔንና ሃይማኖቴን በከፍተኛ አክብሮት ትመለከታለች። ጎረቤቶቻችን በባለቤቴና በእኔ መካከል ይነሳ በነበረው ጥል ገላጋይ መሆናቸው አብቅቶአል። አሁን ያገኘሁትን የአእምሮ ሰላም ከፍተኛ ዋጋ እሰጠዋለሁ። ብቸኛውና ጠቃሚው የሕይወት መንገድ ይሖዋ አምላክን እንደ ሕይወት ሰጪአችን አድርገን በማድነቅ ስለ ሕይወት ዋጋማነት ያለውን አመለካከት መያዝና እንዴት መኖር እንዳለብን የሰጠውን መመሪያ መታዘዝ ነው።”
አምላክ ያቀረበልን የዘላለም ሕይወት
የይሖዋ ምሥክሮች ክዋኩን የመሰሉ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” እንዲለብሱ ረድተዋል። (ኤፌሶን 4:24) እነርሱም አሁን ላላቸው ሕይወት ብቻ ሳይሆን ምድር ገነት ሆና ለሚያገኙት የዘላለም ሕይወት ተስፋም አድናቆት እንዳላቸው ይገልጻሉ። አምላክ በሚያዘጋጀው ገነት ውስጥ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ለሕዝብ ሁሉ . . . ያረጀ የወይን ጠጅ . . . ግብዣ ያደርጋል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስለገባ በምድር ላይ የሚኖር ማንም ሰው እንደገና በረሃብ አይሠቃይም።—ኢሳይያስ 25:6
በአሁኑ ጊዜ ያለን ሕይወት ትልቅ ስጦታ ቢሆንም ጊዜያዊ ነው። እያንዳንዱ ሰው ሞት ያጋጥመዋል። ሞት ደግሞ ከፍተኛ ሐዘን የሚያስከትል ትልቅ አደጋ ነው! በአጭሩ ለመናገር የምታፈቅረው ሰው ተነጥሎህ ፀጥታ በሰፈነበት መቃብር ውስጥ ሆኖ መመልከት በጣም የሚያሳዝን ነው። ነገር ግን በክርስቶስ በምትገዛው በአምላክ መንግሥት ሥር የይሖዋ ቃል ይፈጸማል፦ “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:4
በዚያን ጊዜ የሕይወት ስጦታ በሚያስደንቅ ሁኔታ ይራዘማል። በዚህ ምድር የመጨረሻውን ታላቅ ፈተና የሚያልፉት ወደተሟላ ሕይወት የመግባት አጋጣሚ አላቸው። ከዚያም በኋላ ይሖዋ አምላክ በትንሳኤ አማካኝነት በሞት ያንቀላፉትን ወደ ሕይወት በመመለስ በዋጋ የማይተመነውን የሕይወት ስጦታ ይሰጣቸዋል። (ዮሐንስ 5:24, 28, 29) ይህም የምናፈቅራቸው ሙታንና ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው የጥንት ሰዎች እንደገና ወደ ሕይወት ይመለሳሉ ማለት ነው።
ይህ ሁሉ ሊሆን የማይችል ነገር ነውን? “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር” ስለሌለ የማይቻል አይደለም።—ሉቃስ 1:37፤ ከኢዮብ 42:2 ጋር አወዳድር።
ከዚህም በላይ ይሖዋ አምላክ ራሱ ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ለሰው ዘሮች ዋስትና ሰጥቶአል። እንዴት? ከኃጢአትና ከሞት እንዲቤዠን በጣም የሚወደውን ውድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን መስዋዕት እንዲሆን በማድረግ ነው። ሮሜ 8:32 “ለገዛ ልጁ [ይሖዋ አምላክ] ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?” በማለት ያረጋግጥልናል። በሥነ ምግባር ብልሹ የሆኑትን የሰው ዘሮች እንደሚያነጻና የፍትሕ መጓደልን፣ ወንጀልንና ዓመፅን እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 11:9) ከዚያ በኋላ ሕይወት እንደ እርካሽ የሚታይበት ጊዜ በፍጹም አይኖርም።
አሁንም ቢሆን ፍጽምና በጎደለው ሁኔታዎች ሥር እንኳን እያለን ሕይወት አስደሳች ሊሆን ይችላል። በሚያስጎመጅ የምግብ ሽታ፣ በሞቃታማ ቀን በሚኖረው ለስለስ ያለ የንፋስ ሽውታ፣ ግርማ ሞገስ በተላበሰ ተራራ፣ ዕፁብ ድንቅ በሆነው የፀሐይ መጥለቅ፣ በጸጥታ በሚፈስ ጅረት፣ ልብን በሚመስጠው የአበቦች ቀለም፣ በጣፋጭ የሙዚቃ ድምፅ፣ ወይም በአእዋፍ ዝማሬ የማይደሰት ማን ነው? ለዘላለም እነዚህን በመሰሉ ነገሮች መደሰት ምን እንደሚመስል እስቲ አስበው?
የማይረባና ልቅ የሆነው በራስ የመመራት የሕይወት መንገድ ሊያስገኝ ለሚችለው ጊዜአዊ ደስታ ሲባል ለዘላለም የመኖርን ውድ መብት አሽቀንጥሮ መጣል ትርጉም አለውን? (ከዕብራውያን 11:25 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ በተሞላበት መንገድ “በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (1 ጴጥሮስ 4:2) የአምላክን ቃል በማጥናትና የተማርከውን በተግባር ላይ በማዋል እንደ አምላክ ፈቃድ እንድትኖር ከልብ እናበረታታሃለን፣ አጥብቀንም እናስገነዝብሃለን። (ዮሐንስ 13:17) እንዲህ ካደረግህ ጥሩነቱና ምህረቱ ከተትረፈረፈው አምላክና የዘላለም ሕይወት ሊሸልምህ ከሚችለው ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖርሃል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከአልኮል ሱሰኝነት በቀላሉ መላቀቅ አስቸጋሪ ነው። ብዙውን ጊዜ የባለሙያ እርዳታ ይጠይቃል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጠቃሚ መረጃ ለማግኘት የዚህ መጽሔት ጓደኛ የሆነውን የግንቦት 22, 1992 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አኗኗርህ ለሕይወት አድናቆት እንዳለህ ያሳያልን?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ አዲስ ዓለም ደስታ በሞላበት ሕይወት ለዘላለም እንድንደሰት ያስችለናል!