እየገነነ የመጣው በልሳን የመናገር ክስተት
“አንድ ኃይል አንደበቴን ተቆጣጠረውና ቃሎች ልክ እንደ ውኃ ይፈሱ ጀመር። ምንኛ ደስ የሚል ነገር ነበር! ከማንም በላይ ንጹሕ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ከዚያ ወዲህ እንደቀድሞው አልሆንኩም” በማለት “በማይታወቅ ልሳን” የመናገር እንግዳ ተሞክሮ ያጋጠመው ሰው በደስታ ተናገረ።”
አንድ ሰው “በማይታወቅ ልሳን” የተናገረበትን የመጀመሪያ ተሞክሮውን የገለጸው ከላይ እንዳነበባችሁት በማለት ነበር። አንዳንድ ሰዎች ‘በማይታወቅ ልሳን መናገር ምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቁ ተገቢ ጥያቄ ነው። “በማይታወቅ ልሳን” መናገር የሚያመለክተው በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በማያውቁት የውጭ ወይም ባልተለመደ ቋንቋ እንድንናገር በአምላክ መንፈስ ተነዳን ስለሚሉ ወንዶችና ሴቶች ነው።
ይህ ሁኔታ እየገነነ በመምጣት ላይ ያለ ሃይማኖታዊ ክስተት ነው። በአንድ ወቅት ለጰንጠቆስጤ አማኞች ብቻ የተወሰነ ተደርጎ ይታይ የነበረው በልሳን መናገር ዛሬ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የሃይማኖት ወገን ድንበር ጥሶ የባፕቲስትንና፣ የኤጲስቆጶሳውያንን፣ የሉተራንን፣ የሜቶዲስትን፣ የፕሬስቢቴሪያንንና የሮማን ካቶሊኮችን ሁሉ አጠቃሏል። አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ በደስታ መፈንደቅ፣ ኃይለኛ የዕብደት ዓይነት ስሜት፣ መፍዘዝና እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት እንደሆነ ይገለጻል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ይህን ሁኔታ በኃይለኛ የደስታ ወይም የፍርሃት ስሜት ምክንያት የሚመጣ ተሞክሮ ብለው ይጠሩታል። በልሳን ከመናገር ጋር ተያይዞ የሚታይ ረቂቅ ምስጢርና ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲባል ለግለሰቦች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ይሰጣል ተብሎ የሚታመን ነገር አለ።
በአሁኑ ጊዜ በልሳን የመናገር ስጦታ ለምን ተፈለገ?
ሲሪል ጂ ዊሊያምስ የመንፈስ ልሳናት በተሰኘ የእንግሊዝኛ መጽሐፋቸው ላይ “ነገሮች ሳይሳኩ ሲቀሩ በሚመጣው ስሜትና ‘በልሳን ለመናገር’ በመፈለግ መካከል ግንኙነት” ሊኖር እንደሚችል ያመለክታሉ። “የመንፈስ ጭንቀትን በመቀነስ የፈዋሽነት ጠቀሜታ” ያለውና “ለውስጣዊ ግጭት አስወጋጅነት” አላቃቂ መሣሪያ ነው በማለት ገልጸውታል። በቤተ ክርስቲያን ሥራ ውድቀት ሲያጋጥም፣ የስሜት ውጥረት፣ የሥራ አለመሳካት፣ ኀዘን፣ በቤት ውስጥ የተፈጠረ ጭንቀት፣ ወይም በቤተሰብ ውስጥ ሕመም ሲያጋጥም በስሜት ግንፋሎት ለሚደረጉ ለእንዲህ ዓይነት ንግግሮች ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል።
በተመሳሳይም ጆን. ፒ. ኪልዳህል በልሳን የመናገር የሥነ አእምሮ ጥናት በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ “በልሳን የመናገር ችሎታን ለማዳበር በቅድሚያ ጭንቀት እንደሚያስፈልግ” ይናገራሉ። በግል ምርምርና በጥንቃቄ በተደረገ ቃለ መጠይቅ አማካኝነት “ከልሳን ተናጋሪዎች ውስጥ 85 በመቶዎቹ በልሳን ከመናገራቸው በፊት የታወቀ የጭንቀት ችግር አጋጥሞአቸው እንደነበረ” ተደርሶበታል። ለምሳሌ ያህል አንዲት እናት ካንሰር ታሞ ለነበረው ልጅዋ ለመጸለይ እንድትችል በልሳን መናገር ትፈልግ ነበር። አንድ ሰው ደግሞ የሥራ ዕድገት ተሰጥቶት ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰን ባቃተው ሰዓት በልሳን መናገር ጀመረ። አንዲት ሴት ባሏ ከማታውቃቸው የጠጪዎች ጓድ ጋር መተባበር ከጀመረ ከሳምንት በኋላ በልሳን መናገር ጀመረች።
ልሳን ተናጋሪው የሚያጋጥመው ተሞክሮ ምንድን ነው?
ለመጀመሪያ ጊዜ በልሳን የተናገረ ሌላ ሰው “በውስጤ እንደ እሳት የሚያቃጥል ስሜት፣ ብርድ ብርድ የማለት ስሜትና ላብ ላብ የማለት ስሜት፣ የመንቀጥቀጥና በእጅና በእግሮቼ የድካም ስሜት ተሰማኝ” በማለት ሪፖርት አድርጓል። ብዙውን ጊዜ በልሳን ከመናገር ተሞክሮ ገጠመኝ ጋር ተያይዞ የሚመጣ አንዳንድ ሰዎች የሚረብሽ ሆኖ የሚያገኙት ያልተለመደ ጠባይ አለ። ለምሳሌ “አንዲት ልጃገረድ በወንበሯ ላይ ሆና አንገቷን በወንበሩ ጀርባ ላይ፣ ተረከዟን በወለሉ ላይ አድርጋ እግሯን ዘርግታ ስትንጠራራ ምራቋ ትን ብሏት ልትሞት ነበር።” በአንድ የጉባኤ ስብሰባ ወቅት “አንድ ሰው ከአንዱ የቤተ ክርስቲያን ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ መሬት ሳይነካ ይገለባበጥ ነበር።”
ፕሮፌሰር ዊሊያምስ ጄ ሳማሪን “ለአንዳንድ ሰዎች በልሳን መናገር በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ሁኔታ ነው” በማለት ጽፈዋል። በልሳን ካልተናገሩ “የጎደላቸው ነገር እንዳለ ሆኖ ተሰምቷቸዋል።” በልሳን መናገር “ለጸሎት መልስ እንደማግኘት፣ መለኮታዊ ፍቅርና ተቀባይነት እንደማግኘትም” ይቆጠራል። ሌሎችም “ከከፍተኛ የኃይል ስሜት” ጋርና “ከጠንካራ የማንነት ስሜት ጋር” ውስጣዊ ስምምነት፣ ደስታና ሰላም ትቶላቸው እንደሚሄድ ተናግረዋል።
በስሜት ፍንደቃ መናገር በእርግጥ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ማስረጃ ነውን? ይህን የማድረግ ተሞክሮውስ አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን መሆኑ ተለይቶ የሚታወቅበት ነውን? በዘመናችን በልሳን መናገር ተቀባይነት ያለው አምልኮ ክፍል ነውን? እነዚህ ጥያቄዎች በችኮላ ሳይሆን በእርጋታ መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም አምልኮታችን የአምላክ ድጋፍና በረከት እንዲኖረው ስለምንፈልግ ነው።