የሕዝበ ክርስትና ፍሬ በአፍሪካ
ቻርልስ ላቬዥሪ አልጀሪያን “ክርስቲያን አገር” ለማድረግ የነበራቸው ሕልም እንዲያው ሕልም ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ዛሬ 99 በመቶ የሚሆነው የአልጀሪያ ሕዝብ እስላም ነው። ሕዝብ ክርስትና በአብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ አገሮች ተቀባይነት አጥታለች። በቀሩት የአህጉሪቱ ክፍሎችስ?
ዶክተር ጄ. ኤች. ኬይን የክርስቲያኑ ዓለም ሚስዮን አጭር ታሪክ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “ክርስትና በጥቁር አፍሪካ ውስጥ ያገኘው የአማኞች ቁጥር በቀሩት የሦስተኛ ዓለም አገሮች በሙሉ ካፈራቸው አማኞች ይበልጣል” ብለዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አማኞች እውነት ክርስቲያኖች ናቸውን? ዶክተር ኬይን “አፍሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያን የተደቀነባት ትልቅ አደጋ የክርስትናና የአረማዊነት አስተሳሰቦችና ተግባሮች መቀላቀል ነው” በማለት የእምነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። “አፍሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያን” የሚለው አገላለጻቸው ራሱ ትክክል አይደለም። በአፍሪካ ውስጥ እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን የአምልኮ መንገድ የሚከተሉ በሺህ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ለምን እንዲህ ሆነ?
የመከፋፈል ዘሮች መዘራት
የመከፋፈል ዘሮች መዘራት የጀመሩት ገና ሚስዮናውያን ወደ አፍሪካ ከመሳፈራቸው በፊት ነበር። የሎንደን ሚስዮናውያን ማኅበር አባሎቹን ያሰባሰበው ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ስለነበር ሚስዮናውያኑ ወደ ምድብ ቦታቸው በመጓዝ ላይ እንዳሉ በመካከላቸው በመሠረተ ትምህርቶች ረገድ የተጧጧፈ ክርክር ተፈጥሮ ነበር። በየሚስዮን ጣቢያዎቻቸው ከሠፈሩ በኋላም ቢሆን አለመስማማቱ የባሰ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበር።
ፕሮፌሰር ሮበርት ሮትበርግ ክርስቲያን ሚስዮናውያንና የሰሜናዊ ሮዴሺያ መፈጠር 1880-1924 በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “ሚስዮናውያን አብዛኛውን ጊዜ የወንጌላዊነት ዓላማቸው እስኪበደል ድረስ እርስ በርሳቸውና ባሕር ማዶ ከነበሩት ዲሬክተሮቻቸው ጋር መራራ ጥል ይጣሉ ነበር። ሚስዮናውያን ሰዎችን ወደ ሃይማኖታቸው ለመለወጥ ጥረት በማድረግ የሚያሳልፉትን ያህል ጊዜና ጉልበት እነዚህን አለመግባባቶች በወረቀት ላይ በማስፈር ያሳልፉ ነበር” በማለት ጽፈዋል።
አንዳንድ ጊዜ በሚስዮናውያኑ መካከል የተነሳው ጥል ለተፎካካሪ ሚስዮኖች መመሥረት ምክንያት ሆኖአል። የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ሚስዮኖች አማኞችን ለማግኘት የተካረረ ፉክክር ያደርጉ ነበር። በእነርሱ መካከል የታየው ይኸው የአንድነት መታጣት በአማኞቻቸውም ዘንድ እንደሚንጸባረቅ የታወቀ ነበር። ከጊዜ በኋላ በሚልዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን የሚስዮን አብያተ ክርስቲያናትን በመተው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያኖች መሠረቱ።
የሚስዮናዊያን ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ዶክተር ኬን “ነፃዎቹ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት በመላው አፍሪካ ይገኛሉ። . . . በጠቅላላው በዚህ ንቅናቄ ምክንያት የተፈጠሩ ሰባት ሺህ የሚያህሉ ተገንጣይ ቡድኖች አሉ” በማለት ጽፈዋል። ለዚህ ምክንያት የሆነው የሚቃረኑ እምነቶች ባሏቸው ሚስዮናውያን መካከል ይደረግ የነበረው ፉክክር ብቻ አልነበረም። ጂኦፍሬይ ሞርሃውስ ሚስዮናውያን በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ሌላውን “የጥቁሮች ተሐድሶ” እንቅስቃሴ ምክንያት ገልጸዋል። “የነጮችን የበላይነት መቃወም” እንደነበር ይገልጻሉ።
ሚስዮናውያን ክርስቲያኖች ነበሩ ወይስ አውሮፓውያን ዘረኞች?
ዶክተር ኬይን “ሚስዮናውያኑ የበላይነት ስሜት የሚያጠቃቸው ነበሩ” በማለት እውነቱን ሳይደብቁ ተናግረዋል። አድሬየን ሀስቲንግስ የአፍሪካ ክርስትና በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ሚስዮናውያን “የክርስትና ሃይማኖት ከአውሮፓውያን ባሕልና ከአውሮፓውያን አመራር ጋር አብሮ መሄድ አለበት ብለው ያምኑ ነበር” በማለት ተናግረዋል።
ፈረንሳዊው ቻርለስ ላቬዥሪ ይህን የመሰለ አመለካከት የነበራቸው ሚስዮናዊ መሪ ነበሩ። ሌላው ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የሎንደን ሚስዮናዊ ማኅበር ተቆጣጣሪ የነበሩት ጆን ፊሊፕ ነበሩ። በ1828 “የኛ ሚስዮናውያን . . . የብሪታኒያን ፍላጎቶች፣ የብሪታኒያን ተሰሚነትና የብሪታኒያን ግዛት የሚያስፋፉ ናቸው። ሚስዮናዊው ከአረመኔዎቹ ጎሣዎች መካከል አማኞችን ማፍራት ሲጀምር ጎሣዎቹ ለቅኝ ገዢው መንግሥት ያላቸው ተገቢ ያልሆነ ጥላቻ ይወገዳል፤ ሰው ሠራሽ ፍላጎቶች ስለሚፈጠሩ በቅኝ ገዢዎች ላይ ያላቸው ጥገኛነት ይጨምራል፤ . . . ኢንዱስትሪ፣ ንግድና እርሻ በፍጥነት ይስፋፋሉ፤ ስለዚህ ከእነርሱ መካከል የተገኘው እያንዳንዱ ሐቀኛ አዲስ አማኝ . . . የቅኝ ገዢው መንግሥት ተባባሪና ወዳጅ ይሆናል” በማለት በኩራት ተናግረዋል።
ታዲያ የአውሮፓ መንግሥታት እንዲህ ዓይነቶቹን ሚስዮናውያን ለቅኝ ግዛት ተስፋፊነታቸው ጠቃሚ መሣሪያዎች እንደሆኑ አድርገው ማየታቸው ያስደንቃልን? ሚስዮናውያኑም በበኩላቸው የአፍሪካን በቅኝ ገዢዎች ድል መደረግ በደስታ ተቀብለዋል። በ1910 በኤዲንበርግ በተደረገው የዓለም ሚስዮናውያን ስብሰባ እንዳወጣው መግለጫ ምንም ጊዜ ቢሆን “በሚስዮናውያን ዓላማና በመንግሥት ዓላማ መካከል ልዩነት ማግኘት አይቻልም።”
ሚስዮናውያኑ በአፍሪካ ውስጥ እንደ ነገሥታት ገዝተዋል
አንዳንድ ሚስዮናውያን በቅኝ ገዢዎች ወታደራዊ ኃይል አማካኝነት ሥልጣናቸውን አስከብረዋል። በባሕር ዳርቻ ላይ የነበሩ ከተሞች ነዋሪዎች ሚስዮናዊ ሥልጣንን ለመቀበል እምቢ በማለታቸው ምክንያት በብሪታኒያ የባሕር ኃይል ተኳሽ መርከቦች ተደምስሰዋል። በ1898 በምዕራብ አፍሪካ ተመድቦ የነበረው ዴኒስ ኬምፕ የተባለ የዌስሌያን ሚስዮናዊ “በአሁኑ ጊዜ የብሪታኒያ ጦር ሠራዊትና የባሕር ኃይል የአምላክን ዓላማ ለማከናወን መሣሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ መሆኑን በጽኑ እንደሚያምን” ገልጾ ነበር።
ሚስዮናውያን ተደላድለው መኖር ከጀመሩ በኋላ የጎሣ አለቆችን ሕዝባዊ ሥልጣን ይቃወሙ የነበረበት ጊዜ ነበር። ፕሮፌሰር ሮትበርግ ሲጽፉ “የለንደን ሚስዮናዊ ማኅበር የላካቸው ሚስዮናውያን ቲኦክራሲያዊ ሕጋቸውን ለማስከበር አዘውትረው በኃይል ይጠቀሙ ነበር። ደስ አለመሰኘታቸውን የሚያሳውቁበት ተወዳጅ መሣሪያ የጉማሬ አለንጋ ነበር። አፍሪካውያን በማንኛውም ጥቃቅን ሰበብ ያላንዳች ገደብ ይገረፉ ነበር” ብለዋል። ዴቪድ ላም አፍሪካውያን በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ “ኡጋንዳ ውስጥ ጌታ ቦትሬ የሚባል አንድ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊ አገልግሎት ከሚሰጥበት መድረክ ወርዶ ሰዓት አሳልፈው የመጡትን አፍሪካውያን በበትር ይማታ እንደነበረ አንድ አፍሪካዊ አማኝ ትዝ ይለዋል” በማለት ገልጸዋል።
ጄምስ መኪ የሚባል አንድ ሚስዮናዊ በእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በጣም ተሰቅቆ ለሎንደን ሚስዮናዊ ማኅበር ዲሬክተሮች ስሞታ አቅርቦ ነበር። “የአምላክን ፍቅር ምሥራች የምናደርስ ነጮች እንደሆንን ተደርገን በመታየት ፈንታ የታወቅንና የተፈራን ሰዎች ሆነናል” በማለት አስጠንቅቋል።
የዓለም ጦርነቶች
ሚስዮናውያን የተሰኘ መጽሐፍ “ለመቶ ዓመት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ [አፍሪካውያን] ውጊያና በውጊያ የሚገለጹት አረመኔያዊ የደመ ነፍስ ጠባዮች ፍሬ ቢስና ክፉ እንደሆኑ ባለማቋረጥና በኃይል ቃል ይነገራቸው ነበር” ይላል። በ1914 ክርስቲያን ተብለው በሚጠሩ የአውሮፓ መንግሥታት መካከል የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ፈነዳ።
ሙርሃውስ ሲያስረዱ “የማንኛውም አገር ዜጋ የሆኑ ሚስዮናውያን በታላቁ ጦርነት መግባት እንዳለባቸው አምነው ነበር” ብለዋል። የቅሌታቸው ብዛት ሚስዮናውያኑ አፍሪካውያን አማኞቻቸውም ከእነርሱ ጋር የአንዱ ወገን ደጋፊዎች እንዲሆኑ አጥብቀው ይመክሩአቸው ነበር። አንዳንድ ሚስዮናውያን አልፈው ተርፈው አፍሪካውያን ወታደሮችን ወደ ጦር ሜዳ መርተው ወስደዋል። ይህ ጦርነት ያስከተለውን ውጤት ፕሮፌሰር ስቴፈን ኔል የክርስትና ሚስዮኖች ታሪክ በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደሚከተለው በማለት በጥሩ ሁኔታ ገልጸዋል። “የአውሮፓ መንግሥታት የክርስትናና የሥልጣኔ ባለቤቶች እነርሱ ብቻ እንደሆኑ አድርገው በታላቅ ቃል እየተናገሩ ዓይናቸውን ጨፍነውና እየተደናበሩ በኢኮኖሚ ወዳደኸያቸውና ለዛቸውን አሟጦ ወደጨረሰው የእርስ በርስ ጦርነት ገቡ።” ኔል ቀጥለው “ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ቀደም ሲል የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የጀመረውን ሥራ አጠናቅቆ ጨረሰ። የምዕራባውያን የማስመሰያ ሥነ ምግባር ውሸት መሆኑ ተገለጠ፤ ‘ሕዝበ ክርስትና’ የምትናገረው ሁሉ ከተረት ያልተሻለ መሆኑ ታየ። ከዚያ ወዲህ ስለ ‘ክርስቲያኑ ምዕራብ’ ለመናገር የማይቻል ሆነ” ብለዋል።
የጥቁሮች ተሐድሶ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፋጠነበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። ይሁንና ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ሳይነጠሉ የቆዩት አፍሪካውያንስ ምን ሆኑ? ከዚያ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ ተደርጎአልን?
የአፍሪካ አባቶች እምነት
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን አፍሪካውያን የሞቱ ቅድመ አያቶቻቸውን ለመለማመን ሲሉ የሚያደርጉትን ጠንቋዮችን የመጠየቅና የመሳሰሉትን ሃይማኖታዊ ልማዶች አውግዘዋል። ቢሆንም ሰዎች ሁሉ የማትሞት ነፍስ አለቻቸው ብለው ማስተማራቸው አልቀረም። ለማርያምና ለቅዱሳን አምልኮታዊ አክብሮት የመስጠት ልማድ እንዲስፋፋ አድርገዋል። እነዚህ ትምህርቶች አፍሪካውያን የሞቱ ቅድመ አያቶቻቸው በሕይወት ስለመኖራቸው ያላቸውን እምነት ደግፎላቸዋል። በተጨማሪም ሚስዮናውያኑ እንደ መስቀል የመሳሰሉትን ሃይማኖታዊ ምስሎች በማክበር አፍሪካውያን በክፉ መንፈሶች መከላከያ እንዲሆኑአቸው በማሰብ በክታቦች መጠቀማቸው ትክክል ሆኖ እንዲታያቸው አድርጎአል።
ፕሮፌሰር ሲ. ጂ. ባኤታ ክርስትና በበረሃማዋ አፍሪካ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ “አንድ አፍሪካዊ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ ክታቡን እንዳሠረ ‘ከአንተ በቀር መጠጊያ የለኝም’ እያለ በተመስጦ ሲዘምር ወይም ከቤተ ክርስቲያን እንደወጣ በቀጥታ ወደ ጠንቋይ ቤት ሲሄድ ምንም ዓይነት ሥርዓት እንደጣሰ አይሰማውም” በማለት ይገልጻሉ።—ከዘዳግም 18:10-12 እና ከ1 ዮሐንስ 5:21 ጋር አወዳድሩት።
ብዙ ሚስዮናውያን የአፍሪካውያኑ ቅድመ አያቶች በእሳታማ ሲኦል በመሠቃየት ላይ እንዳሉና እነርሱም የሚስዮናውያኑን ትምህርት ካልተቀበሉ የዚሁ ዓይነት ዕጣ እንደሚደርስባቸው ነግረዋቸዋል። የዘላለማዊ ሥቃይ መሠረተ ትምህርት ግን ሚስዮናውያኑ ወደ አፍሪካውያን ቋንቋ ለመተርጎም ትልቅ ጥረት ባደረጉበት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው ቀላል መግለጫ የሚቃረን ነው።—ዘፍጥረት 3:19፤ ኤርምያስ 19:5፤ ሮሜ 6:23
እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአተኛ ሰዎች ነፍስ ትሞታለች፣ “ሙታን . . . አንዳች አያውቁም” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመስማት ዕድል ያላገኙ አፍሪካውያን ግን “ጻድቃንም ዓመፀኞችም” ከሚያገኙት ተስፋ ተካፋይ ይሆናሉ። (ሥራ 24:15) እነዚህ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች አምላክ ለደህንነት ስላደረገው ዝግጅት ይማራሉ። ከዚያ በኋላም የአምላክን ፍቅር በአድናቆት ከተቀበሉ በምድራዊት ገነት የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያገኛሉ።—መዝሙር 37:29፤ ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16
ሕዝበ ክርስትና እነዚህን አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በማስተማር ፈንታ በሀሰት ትምህርቶችና በሃይማኖታዊ ግብዝነት አፍሪካውያንን አሳስታለች። የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን አፍሪካ በቅኝ ግዛት እንድትያዝ በማድረግ ረገድ የተጫወቱት ሚና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌለው የተረጋገጠ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ በተቃራኒው መንግሥቱ “የዚህ ዓለም ክፍል” ያለመሆኗንና እውነተኛ ተከታዮቹም “ከዓለም” መሆን እንደማይገባቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19፤ 18:36) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የዓለማዊ መንግሥታት ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስ አምባሳደሮች ነበሩ።—2 ቆሮንቶስ 5:20
ስለዚህ በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስትና በአፍሪካ ያፈራችው ፍሬ የማያስደስትና አስከፊ በሆነ መከፋፈል፣ ባለመተማመንና “ክርስትናንና አረማዊነትን በመቀላቀል” የተሞላ ነው። በብዙዎቹ የአፍሪካ “ክርስቲያን” ክፍሎች ተስፋፍቶ የሚገኘው ዓመፅ “ከሰላሙ መስፍን” ትምህርቶች ጋር እንደማይስማማ ጥርጥር የለውም። (ኢሳይያስ 9:6) ሕዝበ ክርስትና በአፍሪካ ያፈራችው ፍሬ ኢየሱስ ስለ እውነተኛ ተከታዮቹ ከተናገረው ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው። ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ባደረገው ጸሎት “እነርሱም በፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም እኔን እንደላክኸኝና እኔን በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደወደድሃቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው” በማለት ልመና አቅርቧል።—ዮሐንስ 17:20, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 1:10
ታዲያ ይህ ማለት በአፍሪካ የተደረጉት ሚስዮናዊ ሥራዎች በሙሉ ውድቅ ሆነዋል ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። የእውነተኛው ክርስትና ሚስዮናዊ ሥራ በአፍሪካና በመላው ዓለም ያስገኘው መልካም ፍሬ በገጽ 10 ላይ ይገለጻል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ጆን ፊሊፕ ያሉት ያለፈው መቶ ዘመን ሚስዮናዊ መሪዎች የአውሮፓ ሥልጣኔና ክርስትና አንድና የማይነጣጠሉ እንደሆኑ ያምኑ ነበር
[ምንጭ]
Cape Archives M450
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ነፍስ አትሞትም እንደሚሉት ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶች በማስተማር የአፍሪካውያንን የቅድመ አያቶች እምነት አበረታትተዋል
[ምንጭ]
Courtesy Africana Museum, Johannesburg