ይሖዋ ጥሩ እንክብካቤ አድርጎልኛል
ይሖዋን ማገልገል የጀመርኩት በጣም እንግዳ በሆነ መንገድ ነው። ያደግሁት እንደ እኔው ያሉ የማኦሪ ሕዝቦች በሚኖሩበት በኒው ዚላንድ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ በሚገኝ ውብ የገጠር አካባቢ ነው። አንድ ቀን በፈረስ ላይ ተቀምጬ ስሄድ ቤን የሚባል የአጎቴ ልጅ ወደ እኔ መጣ። ጊዜው 1942 የበልግ ወራት ነበር። በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ 27 የነበረ ሲሆን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ንቁ አባል ነበርኩ።
ቤን በዚያን ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን የጀጅ ራዘርፎርድን መጻሕፍት ማንበብ ከጀመረ ብዙ ዓመታት ሆኖት ነበር፥ አሁን ደግሞ ከኒው ዚላንዱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የጌታን ራት አንድ ላይ ሆነው ወደሚያከብሩበት ሥፍራ ሰዎችን እንዲጋብዝ የሚጠይቅ ደብዳቤ በእጁ ይዞ ነበር። በተጨማሪም ቤን የጌታን ራት ምሽት የአከባበር ሥርዓት የሚመራ ሰው ማዘጋጀት ነበረበት። ቤን እኔን ወደ ላይ አንጋጦ እየተመለከተ “የምሽቱን ሥርዓት እንድትመራ ያሰብኩት አንተን ነው” አለኝ። ብቃት እንዳለኝ በመቆጠሬ ኩራት እየተሰማኝና በቤተ ክርስቲያንም ቆራቢ ማለትም ከቂጣውና ከወይኑ የምካፈል በመሆኔ ላቀረበልኝ ግብዣ ተስማማሁ።
በጌታ ራት ምሽት ላይ የጌታን ሞት ለማክበር 40 የሚያህሉ ሰዎች በቤን ቤት የተሰበሰቡ ሲሆን አንዳቸውም የይሖዋ ምሥክር አልነበሩም። እኔ ስደርስ የአጎቴ ልጅ የንግግሩን አስተዋጽኦ ሰጠኝ። እንዲዘመር የታዘዘውን መዝሙር አስቀረሁና የቤንን እህት ባል በጸሎት እንዲከፍት ጠየቅሁት። ከዚያም ጥያቄዎችንና በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሠረቱ መልሶችን የያዘውን የንግግሩን አስተዋጽኦ ማቅረብ ጀመርኩ። በበዓሉ ላይ የተገኘ የአካባቢው ቄስ የተቃውሞ ጥያቄ አንስቶ አቋረጠኝ፣ ሆኖም ጥያቄዎቹ በአስተዋጽኦው ውስጥ ያሉትን የቅዱስ ጽሑፍ ማመሳከሪያዎች በማንበብ ተመለሱለት።
በአስተዋጽኦው ላይ ከነበሩት ጥያቄዎች አንዱ የጌታ ሞት ከዓመቱ ውስጥ በየትኛው ጊዜ መከበር እንዳለበት የሚመለከት ነበር። ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በመስኮት ወደ ውጭ ሲመለከቱና ጨረቃዋን ሙሉ ሆና ሲያዩአት በጣም ያስደስት ነበር። በዓሉ መከበር ያለበት ቀን ኒሳን 14 እንደነበረ ግልጽ ነበር።
ያ ምሽት በጣም አስደናቂ ምሽት ነበር! የበዓሉን ሥርዓት ለማክበር 4 ሰዓት ፈጀብን! ብዙ ጥያቄዎች ተነስተው በማኅበሩ አስተዋጽኦ ላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ተመለሱ። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ምንም እንኳን በዚያን ጊዜ ከይሖዋ ውስጥን ምሥክሮች አንዱ ባልሆንም የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ ባላገኝ ኖሮ ያን ተሞክሮ ለመቋቋም አልችልም ነበር። የሆነ ሆኖ በዚያ የማይረሳ የ1942 ምሽት የሕይወቴ ዓላማ ምን እንደሆነ አወቅሁ።
የቀድሞ ሕይወቴ
የተወለድኩት በ1914 ነበር። አባቴ ከመወለዴ ከአራት ወር በፊት ሞተ። ስለዚህ ልጅ ሳለሁ የሚወዷቸው አባቶች ባሏቸው ልጆች እቀና እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህም ሁልጊዜ ይሰማኝ ነበር። እናቴም ያለባል መኖርዋ ከባድ ትግል ሆኖባት ነበር። ይኸው ኑሮዋ ዓለምን በሙሉ ባዳረሰው የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ውጤቶች ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኖባት ነበር።
ገና ወጣት እያለሁ አግነስ ኮፕ የምትባል ወጣት ልጅ አገባሁ። እርሷም ከ55 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ የኑሮ ጓደኛዬ ሆነች። በመጀመሪያ ኑሮአችንን ለማሳካት በአንድነት ታገልን። በከባድ ድርቅ ምክንያት የግብርና ሥራ ሳይሳካልን ቀረ። በስፖርት አማካኝነት ችግሬ ቢቀንስልኝም እስከ 1942ቱ የማይረሳ ተሞክሮ ድረስ በሕይወቴ ውስጥ እውነተኛ ዓላማ አልነበረኝም።
ለዘመዶች መመስከር
ከዚያ የመታሰቢያ በዓል በኋላ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ከአንዳንዶቹ የአጎቶቼ ልጆች ጋር በመወያየት መጽሐፍ ቅዱስን በቅንነት አጠናሁ። መስከረም 1943 ላይ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በገለልተኛ ሥፍራ የሚገኘውን ማህበረሰባችንን ለመጎብኘት ከተለያየ ቦታ መጡ። ጥልቅ የሆነ የአራት ሰዓት ውይይት አደረግን። ከዚያም በማግሥቱ ጧት እንደሚሄዱ ሳውቅ “አሁን እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁ። የአጎቴ ሁለት ልጆች ማለትም አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንዲሁም እንዴ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ ተጠመቅን።
ከዚያ በኋላ ለዘመዶቼ ለመመስከር በብዛት መጓዝ ጀመርኩ። አንዳንዶቹ ተቀባዮች ነበሩና እነርሱን ማቴዎስ 24ን መሠረት በማድረግ አወያያቸው ነበር። ሌሎች ደግሞ ተቀባይ አልነበሩም፤ በእነዚህ ጊዜያት በማቴዎስ 23 ላይ የተመዘገቡትን ኢየሱስ ለፈሪሳውያን የተናገራቸውን ቃላት እጠቀም ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ደጉንና አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችንን በመምሰል ይበልጥ በጥበብ ማነጋገርን ተማርኩ።—ማቴዎስ 5:43-45
መጀመሪያ ላይ ሚስቴ ይሖዋን ለማገልገል ያለኝን ፍላጎት ተቃውማ ነበር። ይሁን እንጂ ወዲያው ተባበረችኝና በ1943 በታህሣስ ወር ውስንና የተጠመቀች ረዳት ጓደኛዬ ሆነች። በዚያ የማይረሳ ቀን ዊማ ከምትባለው መንደራችን ከእርሷ ጋር አብረው የተጠመቁ አምስት ሰዎች ነበሩና በዚያ አካባቢ ያሉት የመንግሥት አስፋፊዎች ጠቅላላ ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ አለ።
ተቃውሞ ቢኖርም በረከት ማጨድ
በ1944 ከሌላ አካባቢ በመጡ ወንድሞች እንደገና ጉብኝት ተደረገልን፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ስለ መደበኛው የቤት ወደ ቤት አገልግሎት የሚያስፈልገውን ማሠልጠኛ ሰጡን። በማኅበረሰቡ ውስጥ መኖራችን በግልጽ እየታወቀ ሲመጣ ከሕዝበ ክርስትና ወኪሎች ተቃውሞ እየጨመረ መጣ። (ዮሐንስ 15:20) ከአካባቢው ቀሳውስት ጋር ተፋጥጠን በመሠረተ ትምህርት ጉዳዮች ላይ ረዥም ውይይቶችን በተደጋጋሚ አደረግን። ይሖዋ ድሉን ስለሰጠን እህቴን ጨምሮ ሌሎች የማኅበረሰቡ አባሎች ወደ ይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መጥተዋል።
በ1944 ሰኔ ወር በዊባ ጉባኤ ተቋቋመ። ሃይማኖታዊ ስደትና ጥላቻ ጨመረ። የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢው የመቃብር ሥፍራ እንዳይቀበሩ ተከለከሉ። ተቃውሞው አንዳንድ ጊዜ በጣም ይጠነክር ነበር። አካላዊ ጥቃት የማድረስ ድርጊቶች ማለትም ድብደባዎች ይፈጸሙ ነበር። መኪናዬና የጋራጅ ቤቴ ተቃጠሉ። ይሁን እንጂ ከሦስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከይሖዋ በረከት ጋር የጭነት መኪና ለመግዛት ቻልን። ቁጥሩ እየጨመረ የሄደውን ቤተሰቤን ወደ ስብሰባዎች ለማጓጓዝ በፈረስ የሚጎተት ሠረገላ እጠቀም ነበር።
የተሰብሳቢዎች ቁጥር በመጨመሩ ከበፊቱ የሚበልጥ ትልቅ የመሰብሰቢያ ቦታ በአስቸኳይ ማግኘት አስፈለገን። ስለዚህ በዊማ የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ወሰንን። እርሱም በኒው ዚላንድ የተሠራ የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሽ ሆነ። ታህሣስ 1, 1949 የመጀመሪያዎቹ ዛፎች ከተቆረጡ ከአራት ወር በኋላ 260-መቀመጫ ባለው አዲስ አዳራሽ ውስጥ ትልቅ ስብሰባና የምረቃ ፕሮግራም በአንድነት ተካሄደ። ይህ ለዚያ ዘመን በይሖዋ እርዳታ የተገኘ ትልቅ ክንዋኔ ነበር።
የይሖዋ እንክብካቤ ተጨማሪ ማስረጃዎች
በኒው ዚላንድ ሰሜናዊ ክፍል የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ማደጉን ስለቀጠለ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ይበልጥ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ስለማገልገል ማበረታቻ ሰጡ። በምላሹም በ1956 ከኦክላንድ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ፑኬኮሆ ቤተሰቤን አዛወርኩ። እዚያም ለ13 ዓመታት አገለገልን።—ከሥራ 16:9 ጋር አወዳድሩ።
በዚህ ጊዜ ያጋጠሙኝ የይሖዋን እንክብካቤ የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎች በትዝታዬ ውስጥ ከሌሎቹ ሁሉ ጎልተው የሚታዩ ናቸው። የአገር አስተዳደር ምክር ቤቱ በጭነት መኪና ነጂነትና በማሽን አንቀሳቃሽነት በቀጠረኝ ጊዜ በኦክላንድ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ለአራት ሳምንት ኮርስ እንድካፈል ተጋብዤ ነበር። ለዚህ ጉዳይ የአራት ሳምንት ፈቃድ ስጠይቅ ዋናው ኤንጂነር “በሚገባ ይፈቀድልሃል። ብዙ ሰዎች እንደ አንተ ቢሆኑ ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር። ስትመለስ ወደ ቢሮዬ መጥተህ አነጋግረኝ” አለኝ። ከተመለስሁ በኋላ ቢሮው ሄጄ ስጠይቀው ፈቃድ ወስጄ የነበርኩበትን የአራት ሳምንት ደመወዝ ተቀበልኩ። ስለዚህ የቤተሰቤ ሥጋዊ ፍላጎት አልተጓደለም።—ማቴዎስ 6:33
ይህ የመጀመሪያው የይሖዋ እንክብካቤ ምሳሌ ነው። ሁለተኛው የተፈጸመው ደግሞ እኔና ባለቤቴ በ1968 ወደ ዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ከገባን በኋላ ነበር። አሁንም እንዲደግፈን በይሖዋ ላይ ተማመንን፤ እርሱም ዋጋችንን ሰጥቶናል። አንድ ቀን ጧት ከቁርስ በኋላ ባለቤቴ ማቀዝቀዣውን ስትከፍት ግማሽ ፓውንድ ከሚሆን ቅቤ በቀር ምንም እንደሌለ ተገነዘበች። “ሳርን፣ ምንም የሚበላ የለንም። ዛሬም አገልግሎት ልንሄድ ነው?” አለችኝ። መልሴ ምን ነበር? “አዎ!” አልኳት።
መጀመሪያ ባንኳኳንበት ቤት ባለቤቷ የሰጠናትን ጽሑፎች ተቀበለችና በለጋስነት ብዛት ያለው ዕንቁላል በእርዳታ ሰጠችን። ያነጋገርነው ሁለተኛው ሰው ኩማራ (ስኳር ድንች)፣ የአበባ ጎመንና ካሮት ሰጠን። “ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” በማለት የተናገራቸው የኢየሱስ ቃላት በእኛ ላይ ምንኛ በትክክል ተፈጸሙ!—ማቴዎስ 6:26
በውጭ አገር ለማገልገል ምድብ መቀበል
በኩክ ደሴቶች ያለችው ራሮቶንጋ! ይህች ሥፍራ በ1970 ልዩ የአቅኚነት ምድባችን ነበረች። ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ቤታችን ነበረች። እዚህ ያጋጠመን የመጀመሪያው አስቸጋሪ ነገር አዲስ ቋንቋ መማር ነበር። ይሁን እንጂ በኒው ዚላንዱ ማኦሪኛ ቋንቋና በኩክ ደሴቱ ማኦሪኛ መካከል ተመሳሳይነት በመኖሩ ከደረስኩ ከአምስት ሳምንት በኋላ የመጀመሪያውን የሕዝብ ንግግሬን ለመስጠት ችዬ ነበር።
በኩክ ደሴቶች የነበሩት የመንግሥት አስፋፊዎች በቁጥር ጥቂቶች ነበር፣ የምንሰበሰብበት ቦታም አልነበረንም። እንደገና ለጸሎታችን መልስ በመስጠት ይሖዋ ፍላጎታችንን አሟላልን። ከአንድ ባለሱቅ ጋር የተደረገ ድንገተኛ ጭውውት አንድ ተስማሚ መሬት ላይ እንድንኮናተር አስቻለንና በአንድ ዓመት ውስጥ አንዲት አነስተኛ ቤትና 140 ሰዎች የሚያስቀምጥ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ሠራን። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና በረከት በበረከት ሆንን።
በተለይ የሚደነቀው የደሴት ነዋሪዎች የሚያደርጉልን መስተንግዶ ነበር። በአገልግሎት ላይ ስንሰማራ ብዙ ጊዜ ለሞቃቱና ለሚወብቀው የአየር ጠባይ በጣም ተስማሚ የሆነ ቀዝቃዛ መጠጥ ያቀርቡልን ነበር። ብዙውን ጊዜም እቤት ስንደርስ የማናውቃቸው ሰዎች ያስቀመጡልንን ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና ብርቱካን በደጃፋችን ላይ እናገኝ ነበር።
በ1971 ባለቤቴና እኔ ከሌሎች ሦስት የራሮቶንጋ አስፋፊዎች ጋር ሆነን በሚያምር ሐይቋ ወደታወቀችው ወደ ኢተታኬ ደሴት ተጓዝን። እንግዳ ተቀባይ በሆኑት ነዋሪዎቿ መካከል የአምላክ ቃል አፍቃሪዎች አገኘንና ከአራት ሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን፤ ወደ ራሮቶንጋ ከተመለስን በኋላም ጥናታችንን ደብዳቤ በመጻጻፍ ቀጠልን። ከጊዜ በኋላ እነዚያ የኢተታኬ ተማሪዎች ተጠምቀው ጉባኤ ተቋቁሟል። በ1978 በኩክ ደሴት ሁለተኛው የመንግሥት አዳራሽ የተሠራው እዚህ ነበር። ይሖዋ ያከናወነውን የመትከልና የማጠጣት ሥራ ያሳድግ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7
ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሆንም ከኩክ ደሴቶች ውስጥ አሥሩን ለመጎብኘት መብት አግኝቼ ነበር። በከባድ ንፋስና በሞገደኛ ባሕር ምክንያት አንዲት ጀልባ 180 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው አቴዩ ለመድረስ ከስድስት ቀኞች በላይ ፈጀብን። (ከ2 ቆሮንቶስ 11:26 ጋር አወዳድሩ።) ምንም እንኳን የምግብ አቅርቦቱ በጣም ውስጥ የነበረና በዙሪያዬ የነበሩት ሁሉ ቢያስመልሳቸውም ወደ መድረሻዬ በደህና እንድደርስ ላስቻለኝ ለይሖዋ እንክብካቤ አመስጋኝ ነበርኩ።
በ1974 በኩክ ደሴቶች ለመቆየት ፈቃድ ስለተከለከልን ወድ ኒው ዚላንድ መመለስ ነበረብን። እስከዚያ ድረስ በደሴቶቹ ሦስት ጉባኤዎች ሊመሠረቱ ችለው ነበር።
ተጨማሪ የአገልግሎት መብትና ፈተና
ወደ ኒው ዚላንድ እንደተመለስን አዳዲስ የአጋጣሚ በሮች ተከፈቱ። (1 ቆሮንቶስ 16:9) ማኅበሩ መጠበቂያ ግንብንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ኩክ ደሴቱ የማኦሪ ቋንቋ መተርጎም የሚችል ሰው አስፈልጎት ነበር። ይህ መብት ለእኔ ተሰጠኝና እስካሁንም የእኔው ሆኖ ቀጥሏል። ከዚያም በኩክ ደሴቶች ያሉትን ወንድሞቼን በመጀመሪያ በክልል የበላይ ተመልካችነት፣ በኋላም በተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካችነት አዘውትሬ እንድጎበኛቸው መብት አግኝቼ ነበር።
ከእነዚያ ጉብኝቶች በአንዱ በራሮቶንጋ ልዩ አቅኚ የነበረው ወንድም አሊክስ ናፓ የሰሜናዊ ኩክ ደሴቶች ወደሆኑት ማናሂኪ ራከሀንጋ እና ፔንርሂን ለመሄድ የ23 ቀን የባሕር ጉዞ ከእኔ ጋር ተጉዞ ነበር። በእያንዳንዱ ደሴት ላይ ነዋሪዎቹ ማረፊያ እንዲያቀርቡልንና ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን እንዲቀበሉ ይሖዋ ልባቸውን ገፋፍቶት ነበር። (ከሥራ 6:15 ጋር አወዳድሩ) በእነዚህ ደሴቶች ዕንቁ የሚገኝባቸው የባሕር ፍጥረቶች ሞልተው ነበርና ብዙ ጊዜም ሕዝቡ ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ መደጎሚያ እንዲሆን ዕንቁዎችን ይሰጡን ነበር። ስለዚህ እኛ መንፈሳዊ ዕንቁ ስንሰጥ ቃል በቃል ዕንቁዎችን እንቀበል ነበር።—ከማቴዎስ 13:45, 46 ጋር አወዳድሩ።
ያ ገለልተኛ የሆነ የምድር ክፍል ምንኛ ውብ ነበር! ሌሎች ዓሦችን የሚበሉ ትላልቅ ዓሦች (ሰው የሚበሉት ዓይነቶች አይደሉም) በሐይቅ ላይ ከልጆች ጋር አብረው ሲዋኙ በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ! የማታው ሰማይ ምንኛ የሚያስደስት ድምቀት ይታይበት ነበር! “ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፣ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ምን ያህል እውነት ናቸው!—መዝሙር 19:2
ከዚያ በኋላ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከባድ የታማኝነት ፈተና አጋጠመኝ። ባለቤቴ አንጎልዋ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ሆስፒታል ገባች። ቀዶ ጥገና አስፈለገ፣ ሆኖም ሐኪሙ ያለ ደም ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ አልተስማማም ነበር። ባለቤቴና እኔ በህሊናችን ምክንያት የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ሕክምና እንዲደረግልን ልንስማማ አልቻልንም። የሐኪሙ ህሊና ግን ሕይወትን ለማዳን ደምን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ዘዴ እንዲጠቀም የሚያዝዘው ሆነ።
የባለቤቴ የጤንነት ሁኔታ እየተዳከመ ሄደና ገብቶ መጠየቅ በማይቻልበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ወደሚደረግበት ክፍል ገባች። በጆሮ ታምቡሯ ላይ ከፍተኛ ጭነት ስላጋጠማት የመስማት ችሎታዋ እየቀነሰ ሄደ። በጣም አስጊ ሁኔታ ሆነ። አንድ ጊዜ ጠይቄያት ስመለስ ሐኪሙ እስከ መኪናዬ ተከተለኝና ባለቤቴ ያላት ዕድል ደም ተጠቅሞ ቀዶ ጥገናውን ማከናወን እንደሆነና እኔም በዚህ እንድስማማ ለመነኝ። ሁኔታው እንዲህ ቢሆንም ባለቤቴና እኔ ይሖዋን መታዘዝ ከአሁኑ ሕይወት ጥቂት ዓመታት ማጣትን ቢያስከትልም እንኳን ከማንኛውም ሰው ይበልጥ ለዘለቄታው ሊያስብልን በሚችለው በይሖዋ ተማመንን።
በድንገት በባለቤቴ ሁኔታ ላይ ጉልህ መሻሻል ታየ። አንድ ቀን ልጠይቃት ስሄድ ቀና ብላ በአልጋዋ ላይ ተቀምጣ ስታነብ ደረስኩ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት ለበሽተኞችና ለነርሶች መመስከር ጀመረች። ከዚያ በኋላ ወደ ቀዶ ጥገና ሐኪሙ ቢሮ እንድሄድ ተጠራሁ። “ሚስተር ዋሬራኡ፣ በእውነት ዕድለኛ ሰው ነህ! የሚስትህ ሕመም ድኗል ብለን እናምናለን” አለኝ። ሳይታሰብ የደም ግፊቷ ተስተካከለ።
አሁን እንደገና በኩክ ደሴቶች ተመደብኩና እንደገና በራሮቶንጋ እያገለገልኩ ነው። ምን ዓይነት የተባረከ መብት ነው! ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስብ ባለቤቴና እኔ ከሃምሳ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ በአገልግሎቱ ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ላደረገልን እንክብካቤ አመስጋኞች ነን። በቁሳዊ ረገድ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን አጥተን አናውቅም። በመንፈሳዊ ረገድ በረከቶቹ ለቁጥር ይታክታሉ። ከእነዚህ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው እውነትን የተቀበሉት ዘመዶቼ ብዛት ነው። አሁን የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ከ200 በላይ መቁጠር እችላለሁ። ከእነዚህም ውስጥ 65ቱ በአንድ አካባቢ ተወልደን ያደግን ነን። አንደኛ የልጄ ልጅ የኒው ዚላንድ ቤቴል አባል ሲሆን ሴቷ ልጄ ደግሞ ከባሏና ከሁለት ወንድ ልጆቻቸው ጋር የቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመሥራት በሚደረገው የግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።—3 ዮሐንስ 4
ወደ ፊት ስመለከት ውበቱ በምድር ዙሪያ ከተወለድኩበት የሚያምር አረንጓዴ ሸለቆ በሚበልጠው ገነት የመኖርን ተስፋ በጉጉት እጠባበቃለሁ። አባቴንና እናቴን በትንሣኤ ተቀብዬ ስለ ቤዛው፣ ስለ መንግሥቱና ስለ ሌሎች የይሖዋ እንክብካቤ ማስረጃዎች ከእነርሱ መንገር ምን ዓይነት ታላቅ መብት ይሆናል!
አምላክ እንደሚያስብልኝ በማወቄ ተጠናክሮ የቆየው ቁርጥ ውሳኔዬ መዝሙራዊው በመዝሙር 104:33 ላይ የገለጸው ነው፦ “በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር [ለይሖዋ አዓት] እዘምራለሁ፤ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ።”—በሳርን ዋሬራኡ እንደተነገረው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1950 በኒው ዚላንድ የተሠራው የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሽ