ጥሩ ሰዎች ለምን መከራ ይደርስባቸዋል?
ዓመቱ 1914 ነበር፣ ዓለምም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ተውጣ ነበር። በሰርቢያ በሚገኝ የጦር እሥረኞች ሠፈር ውስጥ የተስቦ ወረርሽኝ በድንገት ተነሳ። ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በዚህ የእስረኞች ሠፈር ብቻ አልተወሰነም ነበር። አስፈሪው በሽታ ወደ ሲቪሎችም ተዛመተና በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ለ150,000 ሰዎች መሞት ምክንያት ሆነ። ሩሲያ በጦርነቱና ከጦርነቱ በኋላ በተጀመረው አብዮት መሃል ተውጣ እንዳለች ሦስት ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በተስቦ ወረርሽኝ ሞቱ። በበሽታው ከተገደሉትና ቤተሰቦቻቸው በመሞታቸው ምክንያት ካዘኑት ሰዎች መካከል ብዙ ጥሩ ሰዎች እንደነበሩ የታወቀ ነው።
ይህ በሰው ልጆች ላይ ከደረሱት አሳዛኝ ሁኔታዎች አንዱ ብቻ ነው። የምትወዷቸው ሰዎች በበሽታ፣ በአደጋ፣ እንዲሁም በአንዱ ወይም በሌላው ዓይነት መከራ የሚያደርሰው ሥቃይ በራሳችሁ ላይ ደርሶ ቀምሳችሁት ይሆናል። አንድ ጻድቅ ሰው ሊድን በማይችል ሕመም ሲሠቃይ አይታችሁ ሳታዝኑ አትቀሩም። አንድ ጥሩ፣ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚሯሯጥ ታታሪ ሠራተኛ የሆነ ሰው በድንገተኛ አደጋ ሲሞት በጣም ሳታዝኑ አትቀሩም። በቤተሰባቸው አባል መሞት ምክንያት ያዘኑ ሰዎች ኀዘናቸው ልባችሁን በጣም ሊነካው ይችላል።
ብዙ ሰዎች ጥሩ የሚሠራ ሰው ምንም ዓይነት መከራ ሊደርስበት አይገባም ብለው ያስባሉ። እንዲያውም በአንድ ሰው ላይ መከራ መድረሱ ሰውየው በደለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ከ3,600 ዓመታት ገደማ በፊት ይኖሩ የነበሩ ሦስት ሰዎች ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች ኢዮብ የተባለው ጥሩ ሰው ይኖር በነበረበት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው። በጥሩ ሰዎች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት በምናደርገው ፍለጋ እነዚህ ሰዎች ይኖሩ ወደነበረበት ዘመን እንመለስ።
በኢዮብ ላይ የደረሱት መከራዎች
ሦስቱ የኢዮብ ወዳጅ ተብዬዎች ኢዮብን ሊጠይቁት በመጡ ጊዜ በደረሰበት ህመም ከመጠን በላይ ይሠቃይ ነበር። አሥር ልጆቹ ሞተውበታል። ንብረቱ በሙሉ ጠፍቶበታል። ኢዮብን ያከብሩት የነበሩ ሰዎች ተጸይፈውታል። ሚስቱ እንኳን ሳትቀር እርሱን በመቃወም አምላክን ሰድቦ እንዲሞት አጥብቃ ጠየቀችው።—ኢዮብ 1:1–2:13፤ 19:13-19
ኢዮብን ሊጠይቁ የመጡት እንግዶች ለሰባት ቀንና ሌሊት ዝም ብለው ሥቃዩን ሲመለከቱ ቆዩ። ከዚያም ከመካከላቸው አንዱ ኢዮብ በኃጢአተኝነት ተግባሩ እየተቀጣ እንደሆነ በመግለጽ ወቀሰው። ኤልፋዝ የተባለው ሰው “እባክህ አስብ፣ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅኖችስ የተደመሰሰ ማን ነው? እኔ እንዳየሁ፣ ኃጢአትን የሚያርሱ፣ መከራንም የሚዘሩ ያንኑ ያጭዳሉ። በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፣ በቁጣውም መንፈስ ያልቃሉ” አለው።—ኢዮብ 4:7-9
ስለዚህ፣ አምላክ ኢዮብን በኃጢአቱ እየቀጣው ነው በማለት ኤልፋዝም ተከራከረ። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ሰዎች አሰቃቂ መከራዎች አምላክ ኃጢአተኛ ሰዎችን ለመቅጣት ብሎ የሚያመጣቸው ናቸው ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ኢዮብ ኃጢአተኛ በመሆኑ ምክንያት እየቀጣው አልነበረም። ይህንንም የምናውቀው በኋላ አምላክ ለኤልፋዝ “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል” በማለት ስለተናገረው ነው።—ኢዮብ 42:7
አምላክ ተወቃሽ ሊሆን አይችልም
በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በመካከላቸው የሚገኙ ብዙ ጥሩ ሰዎች ጭምር፣ በድህነት ተጠቅተውና በረሃብ አዘቅት ላይ ወድቀው ይገኛሉ። አንዳንድ ግለሰቦችም ይማረሩና ለሚደርሰው መከራ አምላክን ይወቅሳሉ። ይሁን እንጂ ረሐብ በመድረሱ ምክንያት የሚወቀሰው እርሱ አይደለም። እንዲያውም ምግብ የሚሰጠን አምላክ ነው።—መዝሙር 65:9
ራስ ወዳድነትና ሌሎችም ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ለተራቡ ሰዎች ምግብ እንዳይደርስ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ከረሀብ መንስኤዎች አንዱ ጦርነት ነው። ለምሳሌ ያህል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደሚከተለው ይላል፦ “ብዙ ገበሬዎች እርሻቸውን ትተው ወደ ውትድርና ከገቡ ጦርነት ለረሀብ መንስኤ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎችም አንድ የጦር ሠራዊት ጠላቱን አንበርክኮ እጅ እንዲሰጥ ለማድረግ ሲል ሆን ብሎ እንዲራብ የሚያደርግበት ጊዜ አለ። ይህንንም ለማድረግ ሠራዊቱ የምግብ ክምችቶችንና በእርሻ ላይ ያለ ሰብልን ከማጥፋቱም በላይ ጠላት የምግብ አቅርቦት እንዳያገኝ በሮችን ይዘጋል። በናይጄሪያ (ከ1967-70) የተደረገው የእርስበርስ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ጊዜ የበሮች መዘጋት የምግብ ሸቀጦች ወደ ቢያፍራ እንዳይገቡ አግዶ ነበር። በዚህም ምክንያት በተነሳው ችጋር ምክንያት ከሚልዮን በላይ የሚሆኑ የቢያፍራ ሕዝቦች ሳይራቡ አልቀረም።
በተለይ ብዙ ጥሩ ሰዎች በተሠቃዩበትና በሞቱበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንዳንድ ሰዎች በስህተት አምላክን በጥፋተኝነት ወቅሰዋል። ሆኖም እርስበርሳቸው በመጠላላትና በመዋጋት የአምላክን ሕግ የሚያፈርሱት ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሁሉ ፊተኛይቱ” ትዕዛዝ የትኛይቱ እንደሆነች በተጠየቀ ጊዜ “ከትዕዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦‘እሥራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላካችን አንድ ጌታ [ይሖዋ አዓት] ነው፣ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክህን ውደድ’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትዕዛዝ ይህች ናት፣ ሁለተኛይቱም፦ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትዕዛዝ የለችም” በማለት መልስ ሰጥቷል።—ማርቆስ 12:28-31
ሰዎች የአምላክን ሕግ ጥሰው እርስበርስ በመጨፋጨፋቸው ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስባቸው አምላክን ማማረር ተገቢ ይሆናልን? አንድ ወላጅ ለልጆቹ እርስበርሳቸው እንዳይጣሉ ቢነግራቸውም ምክሩን ችላ ብለው ቢጣሉና ጉዳት ቢደርስባቸው አባትዬው ለደረሰው ጉዳይ ተጠያቂ ይሆናልን? አባትዬው ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ሰዎች መለኮታዊ ሕጎችን ሲጥሱ ለሚደርሰው የሰዎች መከራም ተወቃሹ አምላክ አይደለም።
የይሖዋ ሕጎች ችላ ሲባሉ መከራ የሚከተል ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ አደጋዎች አምላክ ክፉዎችን ለመቅጣት የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መሆናቸውን አያመለክትም። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ የአምላክን ልዩ በረከትና ጥበቃ አጡ። የይሖዋን ዓላማዎች ለማስፈጸም ሲባል ከተደረጉት የመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ድርጊቶች በስተቀር በሰው ልጅ ላይ በየዕለቱ ሲደርሱበት የቆዩት ሁኔታዎች “ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና ዕድል [ያልታሰበ አጋጣሚ አዓት] ሁሉን ይገናኛቸዋል” በሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ደንብ መሠረት የመጡ ናቸው።—መክብብ 9:11
ጥሩ ሰዎችም ሆኑ መጥፎ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል
እንደ እውነቱ ከሆነ በተወረሰው ኃጢአትና አለፍጽምና ምክንያት ጥሩ ሰዎችም ሆኑ መጥፎ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። (ሮሜ 5:12) ለምሳሌ ያህል ጻድቃንም ሆኑ ክፉ ሰዎች እኩል በበሽታ ይሠቃያሉ። ታማኝ ክርስቲያን የነበረው ጢሞቴዎስ “በዘወትር ደዌ” ይሠቃይ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:23 የ1980 ትርጉም) ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ ስለነበረው “የሥጋ መውጊያ” ሲጠቅስ ስለ አንድ ዓይነት የአካል ሥቃይ መናገሩ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-9) አምላክ በአሁኑ ጊዜ ታማኝ አገልጋዮቹን እንኳን በውርሻ ካገኙአቸው ድካሞች ነፃ አያደርጋቸውም ወይም ከመታመም አይጠብቃቸውም።
አምላካዊ የሆኑ ሰዎች በአስተዋይነት ጉድለት ምክንያት ወይም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን በተግባር ላይ ሳያውሉ በመቅረታቸው መከራ ሊደርስባቸው ይችላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የአምላክን ትዕዛዝ ጥሶ የማያምን ሰው የሚያገባ ሰው እንዲህ ዓይነቱ የጋብቻ ቁርኝት ውስጥ ባይገባ ኖሮ ሊያስወግዳቸው ከሚችላቸው የጋብቻ ችግሮች ውስጥ ገብቶ ሊሠቃይ አይችልም ነበር። (ዘዳግም 7:3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 7:39) አንድ ክርስቲያን የተመጣጠነ ምግብ ባይበላና በቂ ዕረፍት ባያገኝ ጤንነቱ ይጎዳና ሊሠቃይ ይችላል።
ለድካማችን ተሸንፈን የኃጢአት ድርጊት ብንፈጽም የስሜት ሥቃይ ሊደርስብን ይችላል። ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር መፈጸሙ ትልቅ መከራ አስከትሎበት ነበር። (መዝሙር 51) ኃጢአቱን ሊደብቅ ሲሞክር ከባድ ጭንቀት ደርሶበታል። “ቀኑን ሙሉ ከመጮኼ የተነሳ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ . . . እርጥበቴም ለበጋ ትኩሳት ተለወጠ” ብሏል። (መዝሙር 32:3, 4) አንድ ዛፍ በድርቅ ወይም በበጋ ደረቅ ትኩሳት ምክንያት ሕይወት ሰጪ እርጥበቱን ሊያጣ እንደሚችል ሁሉ ዳዊትም በጥፋተኛነት ስሜት መጨነቁ ኃይል አሳጥቶታል። በግልጽ እንደሚታየው የአእምሮም ሆነ የአካል መከራ ደርሶበታል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ መከራ ንስሐ ገብቶ ኃጢአትን በመናዘዝና የአምላክን ይቅርታ በማግኘት ሊወገድ እንደሚችል መዝሙር 32 ይገልጻል።—ምሳሌ 28:13
መጥፎ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሥቃይና መከራ የሚደርስባቸው በመለኮታዊ ቅጣት ምክንያት ሳይሆን መረን የተለቀቀ ተግባራቸው በሚያስከትልባቸው ውጤት ምክንያት ነው። ታላቁ ሄሮድስ መጥፎ ልማዶች ስለነበሩት በሽተኛ ሆኖአል። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ ሄሮድስ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ “የሚዘገንን ሥቃይ ደርሶበት ነበር” ብሏል። “ሰውነቱን አክኮ አይበቃውም ነበር። አንጀቱ ቆስሎ፣ ብልቱ በስብሶና ተልቶ ነበር። ያቃትተውና ያንቀጠቅጠው የነበረውን በሽታውን በካሌሮዋ በሚገኙት ፍል ውኃዎች ለማስታገሥ ሞክሮ አልሆነለትም። . . . በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ይህን በመሰለ አሰቃቂ መከራ ከመሰቃየቱ የተነሳ የአጎቱ ልጅ ባይከለክለው ኖሮ ራሱን በጩቤ ወግቶ ለመግደል ሞክሮ ነበር፣ . . . ቤተ መንግሥቱ በእርሱ ጩኸት ተሞልቷል።”—ጆሴፈስ፦ በጣም አስፈላጊ ጽሑፎች በፖል ኤል ማየር ተተርጉሞ የተዘጋጀ
የአምላክን ሕጎች መከተል በፆታ ግንኙነት እንደሚተላለፉት ካሉት የአባለ ዘር በሽታዎች ችግሮች ይጠብቃል። ይሁን እንጂ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ጥሩ ሰዎች ከመጥፎ ሰዎች ይበልጥ መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
አምላካዊ የሆኑ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
አምላካዊ የሆኑ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ዋናው ምክንያት ጻድቃን ስለሆኑ ነው። ለዚህም የእስራኤላውያን አባት በሆነው በያዕቆብ ልጅ በዮሴፍ ላይ የደረሰው ነገር ምሳሌ ይሆነናል። የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍ ከእርሷ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ባለማቋረጥ ብትጎተጉተውም እርሱ ግን “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔርስ ፊት እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” በማለት ጠይቋል። (ዘፍጥረት 39:9) ይህም ዮሴፍን ተገቢ ላልሆነ እሥራት ያበቃው ሲሆን ይህ መከራ የደረሰበት ጻድቅ በመሆኑ ምክንያት ነበር።
ይሁን እንጂ አምላክ በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ መከራ እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? መልሱ የሚገኘው በዓመፀኛው መልአክ በሰይጣን ዲያብሎስ ከተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ነው። ይህ አከራካሪ ጉዳይ ለአምላክ ፍጹም አቋም መጠበቅን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ቀደም ሲል በተጠቀሰው በጻድቁ ሰው በኢዮብ ረገድ የተገለጸ ስለሆነ ነው።
የአምላክ መላእክታዊ ልጆች አድርገውት በነበረው ስብሰባ ላይ ይሖዋ ሰይጣንን “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” ብሎታል። የዲያብሎስ መልስ ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው ለይሖዋ ያላቸውን ፍጹም አቋም ስለመጠበቃቸውና ስላለመጠበቃቸው የተነሣ ክርክር መኖሩን ያሳያል። ሰይጣን ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በፍቅር ተነሳስቶ ሳይሆን ከአምላክ በሚያገኛቸው ቁሳዊ በረከቶች ምክንያት ነው አለ። ቀጥሎም ሰይጣን እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ [ኢዮብ] ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” ይሖዋም “እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፣ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ” ብሎ መለሰለት።—ኢዮብ 1:6-12
ሰይጣን የተቻለውን ሁሉ ቢያደርግበትም ኢዮብ የጽድቅ አካሄዱን ጠብቋል፣ ይሖዋን የሚያገለግለውም በፍቅር ተገፋፍቶ መሆኑን አረጋግጧል። በእርግጥም ኢዮብ ለከሳሾቹ “እናንተ የተናገራችሁት ሁሉ ትክክል ነው ብዬ ፈጽሞ አልቀበልም፤ እስከምሞትበት ቀን ድረስ እውነተኛነቴን [ፍጹም አቋሜን አዓት] አልተውም” በማለት ነግሯቸዋል። (ኢዮብ 27:5 የ1980 ትርጉም) አዎ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ፍጹም አቋም ጠባቂዎች ምንጊዜም ለጽድቅ ሲሉ መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው። (1 ጴጥሮስ 4:14-16) መጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜም ለአምላክ እውነተኛ ፍቅር ስለነበራቸውና እንዲሁም እርሱን ለማክበርና ሰይጣን ሁሉንም ሰዎች ከይሖዋ አርቃለሁ ብሎ የተናገረው ቃል ሐሰት መሆኑን ለማረጋገጥ የጽድቅ አኗኗር ስለሚኖሩ ብዙ ሰዎች ይናገራል። ለአምላክ ፍጹም አቋሙን በመጠበቁ ምክንያት መከራ የሚቀበል ማንኛውም ግለሰብ ዲያብሎስን ሐሰተኛ በማድረጉና የይሖዋን ልብ በማስደሰቱ ደስተኛ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 27:11
አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ መከራ ሲደርስባቸው በደንታ ቢስነት ዝም ብሎ አይመለከትም። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፣ የወደቁትንም ያነሳቸዋል” ብሏል። (መዝሙር 145:14) ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎች ሁሉ የኑሮን ችግሮችና የአምላክ ሕዝቦች በመሆናቸው የሚደርስባቸውን ስደት ብቻቸውን ለመሸከም የሚያስችል በቂ የግል ጥንካሬ የላቸውም። ነገር ግን የሚያጠነክራቸውና ኃይላቸውን የሚያድስላቸው እንዲሁም መከራዎቻቸውን ሁሉ ለመቻል የሚያስፈልገውን ጥበብ የሚሰጣቸው አምላክ ነው። (መዝሙር 121:1-3፤ ያዕቆብ 1:5, 6) አሳዳጆች አንዳንዶቹን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ቢገድሏቸውም ከአምላክ ያገኙት የትንሣኤ ተስፋ አላቸው። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) አምላክን የሚወዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን የመከራ ውጤቶች በሙሉ፣ ሞትንም እንኳን ቢሆን አምላክ ለመሻር ይችላል። የኢዮብ መከራ እንዲያበቃ አድርጎ ይህን ጻድቅ ሰው አብዝቶ ባርኮታል። እኛም ይሖዋ በዘመናችን ያሉትን ሕዝቡን እንደማይተው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ኢዮብ 42:12-16፤ መዝሙር 94:14
በቅርቡ—መከራ አይኖርም!
እንግዲያስ ማንም ሰው መከራ የሚደርስበት በተወረሰው አለፍጽምናና በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ባለው ኑሮ ምክንያት ነው። አምላካዊ የሆኑ ግለሰቦችም ለይሖዋ ያላቸውን ፍጹም አቋም በመጠበቃቸው ምክንያት መከራ እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ይሁን እንጂ አምላክ በቅርቡ እንባዎችን፣ ሞትን፣ ኀዘንን፣ ጩኸትንና ሥቃይን ስለሚያጠፋ ሊደሰቱ ይችላሉ። ይህን በሚመለከት ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ጽፏል፦
“አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። በዙፋንም የተቀመጠው፦ እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም፦ እነዚህ ቃላት የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”—ራእይ 21:1-5
በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” በማለት ተናግሯል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ወደፊት የሚመጡት ተስፋዎች ምንኛ አስደናቂ ናቸው! በገነት ምድር ላይ የመኖር አስደሳች መብት ልታገኙ ትችላላችሁ። (ሉቃስ 23:43) ስለዚህ የአሁኑ ዘመን መከራ እንዲያስመርራችሁ አትፍቀዱ። በዚህ ፈንታ የወደፊቱን ጊዜ በብሩሕ ተስፋ ተጠባበቁ። ተስፋችሁንና ትምክህታችሁን በጣም ቀርቦ ባለው በአምላክ አዲስ ዓለም ላይ አድርጉ። በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አኗኗር ተከተሉ፣ ከዚያ በኋላ ከማንኛውም ዓይነት መከራ ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ልትኖሩ ትችላላችሁ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ መከራ ቢደርስበትም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አኗኗር ተከትሎአል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከማንኛውም ዓይነት መከራ ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ልትኖሩ ትችላላችሁ
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Collier’s Photographic History of the European War