ይሖዋ በብዙ ምሕረት ይቅር ይላል
“ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ይመለስ . . . ይቅርታውም ብዙ ነውና።”—ኢሳይያስ 55:7
1. በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን ይቅርታ ያገኙ ሰዎች በምን ነገር ተባርከዋል?
ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይምራል። በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ የአእምሮ ሰላም አግኝተው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ” የሚሉትን ብቃቶች ስለሚያሟሉ ነው።—ኢሳይያስ 55:6, 7
2. (ሀ) በኢሳይያስ 55:6, 7 ላይ እንደተጠቀሰው ‘ይሖዋን መፈለግ’ እና “ወደ እርሱ መመለስ” ምን ማለት ነው? (ለ) በባቢሎን የነበሩት የአይሁድ ምርኮኞች ወደ ይሖዋ መመለስ ያስፈለጋቸው ለምን ነበር? አንዳንዶቹስ ምን ደርሶባቸዋል?
2 አንድ ክፉ ሰው “ይሖዋን ለመፈለግ” ና ተቀባይነት ባለው መንገድ እርሱን ለመጥራት ከፈለገ የኃጢአተኛነት መንገዱንና ሌሎችን ለመጉዳት ያለውን ማንኛውንም ዓይነት አሳብ መተው አለበት። “ወደ ይሖዋ መመለስ” አስፈላጊ መሆኑ ኃጢአተኛው በአንድ ወቅት ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና እንደነበረውና በኋላ ግን አምላክን እንደተወ ያመለክታል። ለአምላክ ታማኞች ባለመሆናቸው ምክንያት ወደ ባቢሎን ምርኮ በተወሰዱት የይሁዳ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ይህን የመሰለ ሁኔታ ነበር። አይሁዳውያን ምርኮኞች ወደ ባቢሎን እንዲማረኩና የትውልድ አገራቸው ትንቢት ለተነገረላቸው 70 ዓመታት ባድማ እንድትሆን ካደረገው መጥፎ ድርጊት ንስሐ በመግባት ወደ ይሖዋ መመለስ ያስፈልጋቸው ነበር። በዚህች ምድር በ537 ከዘአበ በመንግሥታዊ አዋጅ ከባቢሎን የተለቀቁት ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው የአይሁድ ቀሪዎች እንደገና ሠፈሩ። (ዕዝራ 1:1-8፤ ዳንኤል 9:1-4) የአይሁድ ወደ አገራቸው መመለስ ያስገኘው ውጤት በጣም አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ የይሁዳ ምድር ከኤደን ገነት ጋር ተመሳስላለች።—ሕዝቅኤል 36:33-36
3. የመንፈሳዊ እሥራኤል ቀሪዎች ወደ ይሁዳ የተመለሱትን ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ምርኮኞች የመሰለ ተሞክሮ ያጋጠማቸው እንዴት ነበር?
3 መንፈሳዊ እሥራኤላውያን ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ወደ ይሁዳ ሲመለሱ ያጋጠማቸውን ተሞክሮ የሚመስል ነገር አጋጥሞአቸዋል። (ገላትያ 6:16) የመንፈሳዊ እሥራኤል ቀሪዎች አንደኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ወዲያውኑ በመንገዳቸውና በአስተሳሰባቸው ላይ አንዳንድ ለውጦችን አድርገው ነበር። በ1919 የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ግዛት ውስጥ ከአምላክ ሙሉ ሞገስ ተገልለው የነበሩበት ግዞት አበቃ። ሰውን በመፍራትና በይሖዋ አገልግሎት በድን በመሆን ከሠሩት ኃጢአት ንስሐ በመግባታቸው ምክንያት ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ አውጥቶ ወደ ሕጋዊ መንፈሳዊ ርስታቸው አመጣቸውና የመንግሥቱ መልእክት በእነርሱ አማካኝነት መሰበኩ እንዲቀጥል አደረገ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ መንፈሳዊ ገነት በአምላክ ሕዝቦች መካከል አብቦ ለይሖዋ ቅዱስ ስም ታላቅ ክብር አስገኝቶአል። (ኢሳይያስ 55:8-13) ስለዚህ በጥላነት ከተፈጸመው የጥንት ሁኔታም ሆነ በዘመናችን እውነተኛ የትንቢት ፍጻሜ መለኮታዊ ይቅርታ በረከቶችን እንደሚያስገኝና ይሖዋ በእርግጥም ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን በእጅጉ እንደሚምር በግልጽ አረጋግጦልናል።
4. አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ፍርሃት አላቸው?
4 ስለዚህ የይሖዋ ዘመናዊ አገልጋዮች በእርሱ ይቅር ባይነት ሊተማመኑ ይችላሉ። ሆኖም አንዳንዶች ከዚህ በፊት ባደረጉአቸው ስህተቶቻቸው ይተክዛሉ ወይም በጥፋተኛነት ስሜት ቅስማቸው ተሰብሮአል። ራሳቸውን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር የማይገባቸው ሰዎች አድርገው ይመለከታሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፈፅሞ ምሕረት የሌለው ኃጢአት እንደሠሩና የይሖዋን ይቅርታ እንደማያገኙ በማሰብ ይፈራሉ። ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነውን?
አንዳንድ ኃጢአቶች ምሕረት የማይደረግላቸው ናቸው
5. አንዳንድ ኃጢአቶች ይቅርታ የማይደረግላቸው ናቸው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
5 አንዳንድ ኃጢአቶች ምህረት የማይደረግላቸው ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፣ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:31) ስለዚህ በአምላክ መንፈስ ቅዱስ ወይም በአምላክ ሠራተኛ ኃይል ላይ የስድብ ወይም የተቃውሞ ቃል የሚናገር አይሰረይለትም ወይም ይቅርታ አያገኝም። ሐዋርያው ጳውሎስም “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማል” በማለት ሲጽፍ ይህንን ማንሳቱ ነበር።—ዕብራውያን 6:4-6
6. አንድ ኃጢአተኛ ይቅርታ የሚያገኝ መሆን አለመሆኑን የሚወስነው ምንድን ነው?
6 አንድ ሰው ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት መፈጸም አለመፈጸሙን የሚያውቀው አምላክ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፣ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ” በማለት በጻፈ ጊዜ ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት ምን ዓይነት ስለመሆኑ ፍንጭ ሰጥቷል። (ዕብራውያን 10:26, 27) አንድን ነገር ወዶ የሚያደርግ ሰው “ሐሳበ ግትርና በራሱ መጥፎ ፈቃድ የሚመራ ነው።” (የዌብስተር ኒው ኮሌጂየት ዲክሽነሪ) እውነትን ካወቀ በኋላ ወዶ በሐሳበ ግትርነትና በእልከኝነት ኃጢአት በማድረግ የሚቀጥል ማንኛውም ሰው ይቅርታ አይደረግለትም። ስለዚህ ኃጢአቱ ይቅርታ የሚገባው መሆን አለመሆኑን የሚወስነው ኃጢአቱ ራሱ ሳይሆን የልቡ ሁኔታና ሆን ብሎ በሐሳበ ግትርነትና በእልከኝነት ኃጢአት መሥራቱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ኃጢአት የፈጸመ ክርስቲያን ስለ ሠራው ኃጢአት በጥልቅ መረበሹ ምን ሊያመለክት ይችላል? ሁኔታው በጣም ያሳሰበው መሆኑ ራሱ ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት ያላደረገ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል።
ኃጢአታቸው ይቅርታ የማይገባው ነበረ
7. አንዳንድ የኢየሱስ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ይቅርታ የማይሰጠው ኃጢአት ፈጽመዋል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስን የተቃወሙት አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ወደውና በሐሳበ ግትርነት ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት ፈጽመው ነበር። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ በሚያደርጋቸው ተአምራት አማካኝነት የአምላክ መንፈስ ቅዱስ ሲሠራ እያዩ ኢየሱስ ተአምራት የሠራበትን ኃይል ያገኘው ከብኤል ዜቡል ወይም ከሰይጣን ዲያብሎስ ነው አሉ። ሊካድ የማይችለውን የአምላክ መንፈስ አሠራር አሳምረው እያወቁ ድርቅ ብለው በመካዳቸው ኃጢአት ሠሩ። በዚህም ምክንያት ይቅርታ የማያገኝ ኃጢአት በመሥራታቸው ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም” ብሏል።—ማቴዎስ 12:22-32
8. የአስቆሮቱ ይሁዳ ኃጢአት ይቅርታ የማይገባው የሆነው ለምንድን ነው?
8 የአስቆሮቱ ይሁዳም ኃጢአት ይቅርታ የማይገባው ነበረ። ኢየሱስን አሳልፎ መስጠቱ በሐሳበ ግትርነት ሆን ተብሎ የተደረገ የግብዝነትና የሸፍጥ አካሄዱ መደምደሚያ ነበረ። ለምሳሌ ያህል ይሁዳ ማርያም ኢየሱስን በውድ ሽቶ ስትቀባው ባየ ጊዜ “ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው?” ብሎ ጠይቋል። ሐዋርያው ዮሐንስ የሚከተለውን አክሎ ጽፏል፦ “ይህን የተናገረው ሌባ ስለነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለነበረ ነው።” ከዚያ በኋላ ብዙ ሳይቆይ ይሁዳ ኢየሱስን ለ30 ብር አሳልፎ ሰጠው። (ዮሐንስ 12:1-6፤ ማቴዎስ 26:6-16) እውነት ነው፣ ይሁዳ ተጸጽቶ ራሱን ገድሏል። (ማቴዎስ 27:1-5) ይሁን እንጂ ሆን ተብሎ በሐሳበ ግትርነት የተደረገው የራስ ወዳድነት ተግባሩና የከዳተኝነት እርምጃው በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት መሥራቱን ስለሚያንፀባርቅ ይቅርታ አላገኘም። ኢየሱስ ይሁዳን “የጥፋት ልጅ” ብሎ መጥራቱ ምንኛ ተገቢ ነበር!—ዮሐንስ 17:12፤ ማርቆስ 3:29፤ 14:21
ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸዋል
9. ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በፈጸመው ኃጢአት አምላክ ምሕረት ያደረገለት ለምንድን ነው?
9 ሆን ተብለው የተሠሩ ኃጢአቶች በአምላክ ምሕረት ካገኙ በደሎች በጣም የተለዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የእሥራኤል ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንመልከት። ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጸመና በኋላም ኢዮአብ ኦርዮንን በዘዴ በጦርነት እንዲያስገድለው አደረገ። (2 ሳሙኤል 11:1-27) ታዲያ አምላክ ለዳዊት ምሕረት ያደረገለት ለምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት የመንግሥት ቃል ኪዳን የተገባለት ሰው መሆኑ ሲሆን በተጨማሪም ዳዊት ራሱ መሐሪ በመሆኑና እውነተኛ ንስሐ በማሳየቱ ምክንያት ነበር።—1 ሳሙኤል 24:4-7፤ 2 ሳሙኤል 7:12፤ 12:13
10. ጴጥሮስ ከባድ ኃጢአት ቢሠራም አምላክ ምሕረት ያደረገለት ለምንድን ነው?
10 ሐዋርያው ጴጥሮስንም ተመልከቱ። ኢየሱስን ደጋግሞ በመካድ ከባድ ኃጢአት ሠርቷል። ታዲያ አምላክ ለምን ምሕረት አደረገለት? ጴጥሮስ ከአስቆሮቱ ይሁዳ በተለየ ሁኔታ አምላክንና ክርስቶስን በሐቀኝነት ሲያገለግል ቆይቷል። የዚህ ሐዋርያ ኃጢአት በሥጋ ድካም ምክንያት የተደረገ ነበር፣ በዚህም ምክንያት ከልቡ ተጸጽቶ ‘መራራ ልቅሶ አልቅሶአል።’—ማቴዎስ 26:69-75
11. “ንስሐ መግባት” ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ከልቡ ንስሐ የገባ ከሆነ ምን ማድረግ አለበት?
11 ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች አንድ ከባድ ኃጢአት የሠራ ሰውም እንኳን ቢሆን የይሖዋ አምላክን ምሕረት ሊያገኝ የሚችል መሆኑን ያሳያሉ። ይሁን እንጂ ይቅርታ ለማግኘት ምን ዓይነት ዝንባሌ ያስፈልጋል? አንድ ኃጢአት የሠራ ክርስቲያን የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ከፈለገ እውነተኛ ንስሐ መግባት ይኖርበታል። ንስሐ መግባት ማለት “ቀደም ሲል በተሠራ በደል ተጸጽቶ ከኃጢአት መመለስ” ወይም “አንድን ነገር በመሥራት ወይም ሳይሠሩ በመቅረት ምክንያት በተሠራ በደል ማዘን ወይም መቆጨት” ማለት ነው። (ዌብስተርስ ሠርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ) ከልቡ ንስሐ የገባ ሰው ኃጢአቱ በይሖዋ ስምና በድርጅቱ ላይ ባስከተለው ስድብ፣ ነቀፌታ፣ ኀዘን፣ ወይም ችግር መጸጸቱን ያሳያል። በተጨማሪም ንስሐ የገባው ኃጢአተኛ ለንስሐ የሚገባ ሥራ በመሥራት ለኃጢአቱ ማካካሻ የሚሆን ፍሬ ያፈራል። (ማቴዎስ 3:8፤ ሥራ 26:20) ለምሳሌ ያህል በአንድ ሰው ላይ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሞ ከነበረ ያደረሰውን ኪሳራ ለማካካስ ምክንያታዊ እርምጃዎችን ይወስዳል። (ሉቃስ 19:8) እንዲህ ዓይነቱ ንስሐ የገባ ክርስቲያን ይሖዋ በታላቅ ምሕረቱ ይቅር እንደሚለው እርግጠኛ ለመሆን የሚያስችሉት ጠንካራ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አሉት። እነዚህ ጠንካራ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
በአምላክ ይቅር ባይነት እንድንተማመን የሚያስችሉን ምክንያቶች
12. መዝሙር 25:11 አንድ ንስሐ የገባ ሰው ይቅርታ ለማግኘት ምንን መሠረት በማድረግ ሊጸልይ እንደሚችል ያመለክታል?
12 አንድ ንስሐ የገባ በደለኛ ሰው የይሖዋን ስም መሠረት በማድረግ ይቅርታ እንዲደረግለት በእርግጠኝነት ሊጸልይ ይችላል። ዳዊት “አቤቱ [ይሖዋ ሆይ፣ አዓት] ኃጢአቴ እጅግ ታላቅ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ” በማለት ለምኗል። (መዝሙር 25:11) ኃጢአተኛው በአምላክ ስም ላይ ላደረሰው ለማንኛውም ስድብና ነቀፌታ የሚያሳየው ንስሐ እንዲህ ዓይነቱ ጸሎት ሲታከልበት ለወደፊቱ ከባድ ኃጢአት ከመሥራት እንዲርቅ ያደርገዋል።
13. መለኮታዊ ይቅርታ በማግኘት ረገድ ጸሎት ምን ድርሻ አለው?
13 ይሖዋ አምላክ ኃጢአት ሠርተው ንስሐ የሚገቡ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ከልብ የመነጨ ጸሎት ይመልሳል። ለምሳሌ ያህል ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የሠራው ኃጢአት በጣም ከባድ መሆኑን ከተገነዘበ በኋላ ምሕረት ለማግኘት ያቀረበውን ልባዊ ጸሎት ይሖዋ ከመስማት ጆሮውን አልመለሰም። እንዲያውም በመዝሙር 51 ላይ ያሉት የዳዊት ቃላት የብዙ ልመና አቅራቢዎችን ስሜት የሚገልጹ ናቸው። እርሱ እንዲህ በማለት ለምኗል፦ “አቤቱ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌም ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ አምላክ ሆይ! አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።”—መዝሙር 51:1, 2, 17
14. ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሚያምኑ ሰዎች ይቅርታ እንደሚያደርግ ማረጋገጫ የሚሰጡት እንዴት ነው?
14 አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ለሚያምኑ ሰዎች ይቅርታ ያደርጋል። ጳውሎስ “በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 1:7) ሐዋርያው ዮሐንስም ተመሳሳይ መልእክት ሲያስተላልፍ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ልጆቼ ሆይ፣ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።”—1 ዮሐንስ 2:1, 2
15. አንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ የአምላክን ይቅርታ በማግኘት ለመቀጠል ምን ማድረግ አለበት?
15 የይሖዋ ምሕረት ለአንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ምሕረት እንደሚደረግለት ለመተማመን የሚያስችለው ማረጋገጫ ይሰጣል። ነህምያ “አንተ ግን ይቅር ባይ፣ ቸርና መሐሪ አምላክ፣ ለቁጣም የምትዘገይ፣ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ” ብሏል። (ነህምያ 9:17፤ ከዘጸአት 34:6, 7 ጋር አወዳድሩ።) እርግጥ ኃጢአተኛው ሰው መለኮታዊ ምሕረት በማግኘት ለመቀጠል ከፈለገ የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ መጣር ይኖርበታል። መዝሙራዊው እንደተናገረው “ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፣ በሕይወትም በትር [በሕይወት እንድኖር ምሕረትህ ትምጣልኝ]፣ አቤቱ ቸርነትህ [ይሖዋ ሆይ፣ ምሕረትህ አዓት] እጅግ ብዙ ነው፣ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ።”—መዝሙር 119:77, 156
16. ይሖዋ የኃጢአተኝነት ባሕሪያችንን ከግምት እንደሚያስገባ ማወቅ በምን መንገድ ያጽናናል?
16 ይሖዋ የምንገኝበትን የኃጢአተኝነት ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ይቅርታ የሚያደርግልን መሆኑ አንድን ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ከማጽናናቱም በላይ አምላክ ይቅርታ እንደሚያደርግለት በመተማመን እንዲጸልይ የሚያስችለው ምክንያት ይሰጠዋል። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) መዝሙራዊው ዳዊት “[ይሖዋ] እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ [ፍቅራዊ ምሕረቱ ለሚፈሩት ሁሉ ከፍ ያለ ነው አዓት] ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና [አፈር እንደሆንን ያስባል አዓት]” በማለት የሚያጽናና ማረጋገጫ ሰጥቷል። (መዝሙር 103:10-14) አዎ፣ ሰማያዊ አባታችን ከአንድ ሰብአዊ ወላጅም እንኳን የበለጠ መሐሪና ሩህሩህ ነው።
17. አንድ ሰው ለአምላክ የታማኝነት አገልግሎት በማቅረብ ስላሳለፈው የቀድሞ ታሪኩ ምሕረት ከማግኘት ጋር ምን ግንኙነት አለው?
17 አንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ይሖዋ ያለፈውን የታማኝነት አገልግሎቱን እንደማይረሳበት እርግጠኛ በመሆን ይቅርታ እንዲደረግለት ሊጸልይ ይችላል። ነህምያ ለሠራው ኃጢአት ምሕረት መለመኑ ባይሆንም “አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ” በማለት ተናግሯል። (ነህምያ 13:31) አንድ ንስሐ የገባ ክርስቲያን “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” በሚሉት ቃላት ሊጽናና ይችላል።—ዕብራውያን 6:10
ከሽማግሌዎች የሚገኝ እርዳታ
18. አንድ ክርስቲያን የሠራው ኃጢአት በመንፈሳዊ እንዲታመም ካደረገው ምን መደረግ ይኖርበታል?
18 አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ለመኖር እንደማይበቃ ቢሰማው ወይም ኃጢአቱ በመንፈሳዊ እንዲታመም ስላደረገው መጸለይ ቢያቅተውስ? “የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም [በይሖዋም አዓት] ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት” በማለት ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ጽፏል። “የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም [ይሖዋም አዓት] ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል።” አዎ፣ የጉባኤ ሽማግሌዎች አንድን ንስሐ የገባ የእምነት ባልደረባ ወደ ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት ለመመለስ ተስፋ በማድረግ ከእርሱ ጋር ሆነው የሚያቀርቡለት ጸሎት በጣም ይጠቅመዋል።—ያዕቆብ 5:14-16
19. አንድ ሰው ተወግዶ ከሆነ ምሕረት ለማግኘትና ለመመለስ ምን ማድረግ አለበት?
19 አንድ የፍርድ ኮሚቴ አንድን ንስሐ ያልገባ ኃጢአተኛ ቢያስወግደውም እንኳን ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት ፈጽሟል ለማለት አይችልም። ይሁን እንጂ ይቅርታ እንዲደረግለትና ወደ ጉባኤው እንዲመለስ ከፈለገ የአምላክን ሕጎች መታዘዝ፣ ለንስሐ የሚገቡ ፍሬዎችን ማፍራትና ወደ ጉባኤው እንዲመለስ ሽማግሌዎቹን መጠየቅ አለበት። አንድ አመንዝራ ሰው ከጥንቱ የቆሮንቶስ ጉባኤ ከተወገደ በኋላ ጳውሎስ “እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። [ስለዚህ ለእርሱ ያላችሁን ፍቅር እንድታረጋግጡ አዓት] እለምናችኋለሁ በማለት ጽፎላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 2:6-8፤ 1 ቆሮንቶስ 5:1-13
አምላክ ብርታት ይሰጣል
20, 21. አንድ ሰው የፈጸመው ኃጢአት ምሕረት የማያገኝ እንደሆነ በማሰብ ጭንቀት ካጋጠመው ምን ሊረዳው ይችላል?
20 አንድ ሰው ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት እንደሠራ ሆኖ እንዲሰማው የሚያደርገውና የሚያስጨንቀው የጤንነቱ መጎሳቆል ወይም የጭንቀት ስሜት ከሆነ በቂ ዕረፍትና እንቅልፍ ማግኘት ሊረዳው ይችላል። ይሁን እንጂ በይበልጥ “እርሱ [አምላክ] ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚሉትን የጴጥሮስ ቃላት ማስታወስ ይኖርባችኋል። ጴጥሮስ በመጨመር “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” በማለት ስለተናገረ ሰይጣን ተስፋ እንዲያስቆርጣችሁ ፈጽሞ አትፍቀዱለት።—1 ጴጥሮስ 5:6-10
21 ስለዚህ በሠራኸው ኃጢአት ብትጸጸትም ምሕረት የማታገኝ መስሎህ ፍርሃት ካደረብህ የአምላክ መንገዶች የጥበብ፣ የፍትሕና የፍቅር መሆናቸውን አስታውስ። ስለዚህ በእምነት ወደ እርሱ ጸልይ። “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ መመገብህን ቀጥል። (ማቴዎስ 24:45-47) ከእምነት ባልደረቦችህ ጋር ያለህን ግንኙነት አጠናክር፣ በመስክ አገልግሎትም አዘውትረህ ተካፈል። ይህም እምነትህን ያጠነክርልህና ይቅርታ የማይገባው ኃጢአት እንደፈጸምክ ከሚሰማህ ፍርሃት ያላቅቅሃል።
22. ቀጥሎስ ምን እንመለከታለን?
22 በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ይሖዋ በታላቅ ምሕረቱ ይቅር እንደሚል በማወቃቸው ሊጽናኑ ይችላሉ። ሆኖም የአሁኑ ጊዜ ሕይወታቸው ከችግር ነፃ የሆነ አይደለም። ምናልባት የሚወዱት ሰው ሞቶባቸው ወይም የሚወዱት ጓደኛ በጣም ታሞባቸው ተክዘው ሊሆን ይችላል። በእነዚህና በሌሎችም ሁኔታዎች ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ሕዝቡን እንደሚረዳና እንደሚመራ ወደ ፊት እንመለከታለን።
ምን ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ይሖዋ “በብዙ ምሕረት ይቅር እንደሚል” የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
◻ ምሕረት የማይገባው ምን ዓይነት ኃጢአት ነው?
◻ አንድ ሰው ለኃጢአቱ ምሕረት የሚያገኘው በምን ሁኔታዎች ነው?
◻ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች በአምላክ ይቅር ባይነት ሊተማመኑ የሚችሉት ለምንድን ነው?
◻ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ምን እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊትና ጴጥሮስ ምሕረት ያገኙበትንና ይሁዳ ግን ያላገኘበትን ምክንያት ታውቃላችሁን?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጉባኤ ሽማግሌዎች የሚሰጥ እርዳታ አንድን ክርስቲያን በመንፈሳዊ ብዙ ሊረዳው ይችላል