የሰው ልጅ በእርግጥ መሲሕ ያስፈልገዋልን?
“ዓለም መሲሕ እንደሚያስፈልገው ባለ ሥልጣኑ ይናገራሉ”
ይህ የዜና ርዕስ የወጣው በ1980 በቶሮንቶ ካናዳ ዘ ፋይናንሺያል ፖስት በተባለው መጽሔት ላይ ነበር። የተጠቀሱት ባለሥልጣን በቴክኖሎጂያዊና በማህበራዊ ችግሮች ላይ ጥናት የሚያደርገውና የሮም ክለብ በመባልብሎ የሚጠራው ታዋቂ ተቋም ፕሬዚዳንትና መሥራች የሆኑት አውሬል ፔቻ ናቸው። ፖስቱ እንደገለጸው ፔቻ “ሥልጣኔን ለማጥፋት ካሰጉት ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ብጥብጦች መድኅን ሊሆነን የሚችለው ሕዝቦች በፍላጎት የሚታዘዙለትና የሰዎችን የታማኝነት ስሜት የሚያነሳሳ ሳይንሳዊ፣ ፖለቲካዊ ወይም ሃይማኖታዊ መሪ ብቻ መሆኑን” ያምናሉ። እናንተስ ምን ይመስላችኋል? የሰው ልጅ መሲሕ እስከሚያስፈልገው ድረስ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቋልን? እስቲ በዚህ ዓለም ላይ ከተጋረጡት ችግሮች አንዱን ረሀብን ተመልከቱ።
በጋዜጣ ወይም በመጽሔት ላይ ከወጣ ሥዕል ሁለት ትልልቅ ቡናማ ዓይኖች አፍጥጠው ሲመለከቱህ ታያለህ። እነዚህ ዓይኖች አምስት ዓመት እንኳን ያልሞላት የአንዲት ህፃን ሴት ልጅ ዓይኖች ናቸው። ይሁን እንጂ ፈገግ እንድትል የሚያደርጉህ ዓይኖች አይደሉም። የሕፃንነት ወዝ፣ አድናቆት የተሞላበት ደስታ፣ የእርጋታና የመተማመን መንፈስ አይታይባቸውም። በዚህ ፈንታ ግራ በሚያጋባ ሥቃይ፣ በሚነዘንዝ ሕመም፣ ተስፋ አስቆራጭ በሆነ የረሀብ ስሜት የተሞሉ ናቸው። ሕፃኗ ተርባለች። ከሥቃይና ከረሀብ የተለየ ነገር አታውቅም።
ምናልባት አንተም እንደ ብዙዎቹ ሰዎች እነዚህን ሥዕሎች አተኩረህ መመልከት አትወድ ይሆናልና ቶሎ ብለህ ሥዕሉ ያለበትን ገጽ በመገልበጥ ሥዕሉን ከዓይንህ ታርቀው ይሆናል። ይህን የምታደርገው ስለማይሰማህ ወይም ግድ ስለሌለህ ሳይሆን ይህች ልጅ እስካሁን ሞታ ይሆናል ብለህ በማሰብ የተስፋ መቁረጥ ኃዘን ስለሚሰማህ ነው። የመነመነው እጅና እግሯ፣ የተነፋው ሆዷ ሰውነቷ ራሱን በራሱ መብላት እንደ ጀመረ የሚያሳይ ነው። ይህን ሥዕል ከማየትህ በፊትም ሞታ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ዕጣ የደረሰው በዚህች ልጅ ላይ ብቻ አለመሆኑ ይበልጥ ያሳዝናል።
ይህ የረሀብ ችግር ምን ያህል የተስፋፋ ነው? 14 ሚልዮን ሕፃናት በረሀብ እንደሚሠቃዩ መገመት ትችላለህን? አብዛኞቻችን የዚህን ቁጥር ብዛት መገመት ያዳግተናል። ምክንያቱም ይህ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በዓይነ ሕሊና ለመሳል ያስቸግራል። ምን ያህል ብዙ ቁጥር እንደሆነ ለመገመት እንዲረዳህ 40,000 ሕዝብ ሊያስቀምጥ ስለሚችል አንድ ስታዲየም አስብ። ይህ ስታዲየም ከረድፍ እስከ ረድፍ በሕፃናቶች ፊት ብቻ የተሞላ ውቅያኖስ እስኪመስል ድረስ በሕፃናት ጢም ብሎ ሞልቶአል። ይህም እንኳን ቢሆን ለመገመት አዳጋች ነው። ሆኖም 14 ሚልዮን ሕፃናትን ለማስቀመጥ ይህን ስታዲየም የሚያክሉ 350 እስቴዲየሞች ያስፈልጋሉ። ዩኒሴፍ (በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት) በሰጠው ዘገባ መሠረት በታዳጊ አገሮች በየዓመቱ በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎችና በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚሞቱት ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ልጆች ብዛት ይህን ያክላል። በጣም የሚያስደነግጥ ቁጥር ነው። ይህም ማለት በየቀኑ ከላይ የተገለጸውን 40,000 ሰዎች የሚይዝ አንድ ስታዲየም የሚሞሉ ሕፃናት ይሞታሉ ማለት ነው! በዚህ ላይ ረሐብተኛ የሆኑት ትልልቅ ሰዎች ቁጥር ሲጨመርበት በዓለም ዙሪያ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በጠና የሚሰቃዩትን ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ቢልዮን ያደርሰዋል።
ይህን ያህል ረሀብ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜ ይህች ፕላኔት ሰዎች በልተው ከሚጨርሱት የበለጠ ምግብ ታመርታለች። ከዚህም የበለጠ የማምረት አቅም አላት። ሆኖም በየደቂቃው በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና በበሽታ ምክንያት 26 ሕፃናት ይሞታሉ። በዚሁ አንድ ደቂቃ ውስጥ ዓለም ለጦርነት ዝግጅት $2,000,000 ያህል ገንዘብ ያጠፋል። ይህ ሁሉ ገንዘብ፣ እንዲያውም የዚህ ገንዘብ ጥቂቱ ክፍል ብቻ ለእነዚህ 26 ሕፃናት ምን ሊያደርግላቸው ይችል እንደነበረ ልትገምት ትችላለህን?
የዓለም ረሀብ በምግብ ወይም በገንዘብ እጥረት ላይ ብቻ ሊመካኝ እንደማይችል ግልጽ ነው። ከዚህ የበለጠ ክብደትና ጥልቀት ያለው ችግር ነው። የአርጀንቲናው ፕሮፌሰር ጆርጅ ኢ ሃርዶይ እንደገለጹት “ዓለም ባጠቃላይ ምቾቱን፣ ኃይሉን፣ ጊዜውን፣ ሀብቱንና እውቀቱን ይበልጥ ለሚያስፈልጓቸው ሰዎች ለማካፈል አለመቻል ከተጠናወተው ቆይቷል” ብለዋል። አዎ፣ ችግሩ ሰው ራሱ እንጂ ሀብት ማጣቱ አይደለም። ስስትና ራስ ወዳድነት ሰብአዊውን ኅብረተሰብ የሚቆጣጠሩ ኃይሎች የሆኑ ይመስላል። ከዓለም ሕዝብ ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ባለ ጠጎች አንድ አምስተኛ የሚሆኑት የዓለም ድሀ ሕዝቦች ከሚያገኙት ሸቀጥና አገልግሎት 60 ጊዜ ያህል የሚበልጠውን ያገኛሉ።
እውነት ነው፣ አንዳንዶች ለተራቡ ሰዎች ምግብ ለማድረስ ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ጥረታቸው በአብዛኛው ከቁጥጥራቸው በላይ በሆኑ ምክንያቶች ይደናቀፋል። አብዛኛውን ጊዜ ረሀብ የሚያጠቃው በእርስ በርስ ጦርነት ወይም በዓመፅ የተገነጣጠሉትን አገሮች ስለሆነ ተፋላሚ ኃይሎች የእርዳታ አቅርቦቶች ለችግረኞች እንዳይደርስ መከልከላቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። ሁለቱም ተቃዋሚ ኃይሎች ምግብ በጠላት ክልል ለሚኖሩ የተራቡ ሲቪሎች እንዲደርስ ቢፈቅዱ ጠላቶቻቸውን መመገብ ይሆናል ብለው ይፈራሉ። መንግሥታት ራሳቸውም ቢሆኑ ረሀብን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል።
መፍትሔ የለውምን?
ይሁን እንጂ በዘመናዊው ሰው ፊት የተጋረጠው ችግር በሚልዮን የሚቆጠሩ ረሀብተኞች ችግር ብቻ አይደለም። በጣም የተስፋፋው የአካባቢ ጥፋትና መመረዝ፣ በሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት የሚያጠፋው የማያቋርጠው የጦርነት መቅሠፍት፣ በየትኛውም ቦታ ፍርሃትና አለመተማመን የሚያስከትለው ዓመፅና ወንጀል፣ እንዲሁም ከእነዚህ ችግሮች ለአብዛኞቹ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚታመነው ከምንጊዜውም ይበልጥ እየተበላሸ የሚሄደው የሥነ ምግባር መበላሸት፣ እነዚህ ዓለም አቀፍ ችግሮች በሙሉ አንድ ላይ ተባብረው አንድ የማያሻማ እውነት ያረጋግጣሉ። ይህም እውነት የሰው ልጅ ራሱን በራሱ በተሳካ ሁኔታ ለማስተዳደር የማይችል መሆኑ ነው።
ብዙ ሰዎች ለዓለም ችግሮች መፍትሔ ከመፈለግ ተስፋ የሚቆርጡትም በዚህ ምክንያት ነው። ሌሎች ደግሞ በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሱት ኢጣሊያዊ ምሁር እንደ አውሬሊዮ ፔቻ ያለ ስሜት አላቸው። መፍትሔ እንዲገኝ ከተፈለገ መፍትሔው ልዩ ከሆነ፣ ምናልባትም ከሰው የሚበልጥ ኃይል ካለው ምንጭ መምጣት አለበት ብለው ያስባሉ። በመሆኑም አንድ መሲሕ የማስፈለጉ ጽንሰ ሐሳብ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶአል። ይሁን እንጂ በአንድ መሲሕ ተስፋ ማድረግ ተጨባጭነት አለውን? ወይስ እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ የሕልም እንጀራ ሆኖ ይቀራል?
[በገጽ 2 ላይ የሚገኘው የሥዕል ምንጭ]
Cover photos: Top: U.S. Naval Observatory photo; Bottom: NASA photo
[በገጽ 3 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
WHO photo by P. Almasy
[በገጽ 4 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
WHO photo by P. Almasy
U.S. Navy photo