“መሲሕን አግኝተናል”!
“እርሱ [እንድርያስ] አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና፦ መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው።—ዮሐንስ 1:41
1. መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ምን ምሥክርነት ሰጥቷል? እንድርያስስ ስለ መሢሑ ምን ተገነዘበ?
እንድርያስ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተብሎ የሚጠራውን አይሁዳዊ ሰው ትኩር ብሎ ተመለከተው። ኢየሱስ የንጉሥ ወይም የጥበበኛ ሰው ወይም የራቢ [የአይሁድ መምህራን] ቁመና አልነበረውም። ንጉሣዊ አለባበስ ወይም ሽበት ወይም ለስላሳ እጆችና ነጣ ያለ ቆዳ አልነበረውም። ኢየሱስ የጉልበት ሠራተኛ ስለነበረ መጅ ያወጡ እጆችና በፀሐይ የጠቆረ ቆዳ የነበረው የ30 ዓመት ዕድሜ ጎልማሳ ነበር። ስለዚህ እንድርያስ ኢየሱስ አናጺ መሆኑን ሲያውቅ እምብዛም አልተገረመም ይሆናል። የሆነ ሆኖ ዮሐንስ መጥምቁ ስለዚህ ሰው “እነሆ የእግዚአብሔር በግ!” በማለት ተናግሮአል። ከዚያ በፊት በነበረው ቀን ዮሐንስ “እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ነው” በማለት ከዚህ ይበልጥ የሚያስደንቅ ነገር ተናግሮ ነበር። ታዲያ ይህ የተናገረው ቃል እውነት ነበርን? እንድርያስ በዚያ ቀን ኢየሱስ ሲያስተምር እያዳመጠው ጥቂት ጊዜ አብሮት ቆየ። ኢየሱስ ምን እንደተናገረ ባናውቅም ቃሎቹ የእንድርያስን ሕይወት እንደለወጡት እናውቃለን። ወንድሙን ስምዖንን ለማግኘት ፈጥኖ ሄደና “መሢሕን አግኝተናል!” ብሎ በአድናቆት ነገረው።—ዮሐንስ 1:34-41
2. ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች መመርመር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 እንድርያስና ስምዖን (ስምዖን ኢየሱስ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ሰው ነው) በኋላ የኢየሱስ ሐዋርያት ሆኑ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ ከሁለት ዓመታት በኋላ ጴጥሮስ ለኢየሱስ “አንተ ክርስቶስ [መሲሕ] የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎታል። (ማቴዎስ 16:16) በኋለኞቹ ዓመታት ታማኞቹ ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት ለዚህ እምነታቸው ለመሞት እንኳን ፈቃደኞች ሆነዋል። ዛሬም በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ሰዎች ከእነዚህ ሐዋርያት ባላነሰ መጠን ለኢየሱስ ያደሩ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ይህን አቋም የወሰዱት በምን ማስረጃ ላይ ተመርኩዘው ነው? ትክክለኛ እምነትና መታለል የሚለየው በማስረጃው ትክክለኛነትና ትክክለኛ አለመሆን ነው። (ዕብራውያን 11:1ን ተመልከቱ።) ስለዚህ ኢየሱስ በእርግጥ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሦስት ዓይነት አጠቃላይ ማስረጃዎችን እንመልከት።
የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ
3. የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌሎች ስለ ኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ምን ይዘረዝራሉ?
3 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚሰጧቸው ማስረጃዎች የመጀመሪያው የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መሢሑ ከንጉሥ ዳዊት የቤተሰብ መሥመር እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (መዝሙር 132:11, 12፤ ኢሳይያስ 11:1, 10) የማቴዎስ ወንጌል “የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” በማለት ይጀምራል። ማቴዎስ የኢየሱስን የትውልድ ሐረግ አወራረድ በአሳዳጊ አባቱ በዮሴፍ በኩል በመቁጠር ለዚህ በድፍረት ለተናገረው ቃል ማስረጃ ያቀርባል። (ማቴዎስ 1:1-16) የሉቃስ ወንጌል የኢየሱስን ትውልድ በወላጅ እናቱ በማርያም በኩል በዳዊትና በአብርሃም በኩል አልፎ እስከ አዳም ይቆጥራል። (ሉቃስ 3:23-38)a በመሆኑም የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ በሕጋዊም ሆነ በዘር ሐረጉ ምክንያት የዳዊት ወራሽ ነው በማለት የጻፉትን ቃል በጥንቃቄ በማስረጃ አረጋግጠዋል።
4, 5. (ሀ) በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ኢየሱስ የዳዊት ዘር አይደለም ብለው ተከራክረዋልን? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ታሪካዊ ምንጮች የኢየሱስን የዘር ሐረግ የሚደግፉት እንዴት ነው?
4 የኢየሱስን መሲሕነት በጣም የሚጠራጠር ተቃዋሚም እንኳን ኢየሱስ የዳዊት ልጅ እንደሆነ የተነገረውን ቃል አሌ ሊል አይችልም። ለምን? ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንዱ ምክንያት ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ ኢየሱስ የዳዊት ልጅ መሆኑ በሠፊው ተደጋግሞ የተነገረ ነገር ነበር። (ከማቴዎስ 21:9፤ ከሥራ 4:27፤ 5:27, 28 ጋር አወዳድሩ።) ኢየሱስ የዳዊት ልጅ መባሉ ሐሰት ቢሆን ኖሮ ብዙ ተቃዋሚዎች ስለነበሩት ከእነዚህ ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ የኢየሱስን ትውልድ ከሕዝቡ የዘር ግንድ በማጣራት ብቻ ኢየሱስ እንዳጭበረበረ ያረጋግጥ ነበር።b ነገር ግን ኢየሱስ የንጉሥ ዳዊት ዝርያ መሆኑን አልቀበልም ያለ አንድም ሰው እንደነበረ በታሪክ አልተመዘገበም። በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስ የዳዊት ልጅ መባሉ ምንም አያከራክርም ነበር። ማቴዎስና ሉቃስ ወንጌሎቻቸውን ሲጽፉ ትውልዱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጓቸውን ስሞች ከሕዝብ መዝገቦች በቀጥታ እንደገለበጡ ጥርጥር የለውም።
5 ሁለተኛ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ምንጮች የኢየሱስ የዘር ሐረግ አጠቃላይ ተቀባይነት እንደነበረው ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ ያህል የአይሁድ ታልሙድ በአራተኛው መቶ ዘመን የነበረ አይሁዳዊ ራቢ በኢየሱስ እናት በማርያም ላይ ‘ከአናጺዎች ጋር ግልሙትና እንደፈጸመች’ አድርጎ በብልግና እንደወነጀላት አሥፍሯል። ነገር ግን ይኸው ጽሑፍ ማርያም “የመሳፍንትና የገዢዎች ዝርያ ነበረች” በማለት እውነቱን ሳይሸሽግ ይናገራል። ሌላው ከዚያ ቀደም ያለ ማስረጃ ደግሞ የሁለተኛው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ሄጀሲፐስ ነው። የሮማው ቄሳር ዶሚሺያን የዳዊት ዘር የሆነን ማንኛውም ሰው ለማጥፋት በፈለገ ጊዜ አንዳንድ የቀድሞ ክርስቲያኖች ጠላቶች የሆኑ ሰዎች የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነውን የይሁዳን የልጅ ልጆች “የዳዊት ዘሮች ናቸው ብለው” እንዳጋለጡአቸው ተርኳል። ይሁዳ የታወቀ የዳዊት ዘር ከነበረ ኢየሱስስ የታወቀ የዳዊት ዘር አይደለምን? ይህን መካድ አይቻልም።—ገላትያ 1:19፤ ይሁዳ 1
መሲሐዊ ትንቢቶች
6. በዕብራይስጡ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉ መሢሐዊ ትንቢቶች ብዛታቸው ምን ያህል ነው?
6 ኢየሱስ መሲሕ ለመሆኑ ሌላ ማስረጃ የሚሆኑት ፍጻሜያቸውን ያገኙት ትንቢቶች ናቸው። በዕብራይስጡ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በመሢሑ ላይ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው ብዙ ትንቢቶች አሉ። አልፍሬድ ኤዴርሺም የመሲሑ የኢየሱስ ሕይወትና ዘመን በተሰኘው የጽሑፍ ሥራቸው ላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የጥንት ራቢዎች መሢሐዊ እንደሆኑ ይመለከቱአቸው የነበሩትን 456 ምንባቦች በዝርዝር መዝግበዋል። ይሁን እንጂ ራቢዎቹ ስለ መሲሕ ብዙ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ነበሩአቸው። መሢሐዊ እንደሆኑ ያመለከቱአቸው የሚበዙት ምንባቦች ጭራሹኑ መሢሑን የሚመለከቱ አልነበሩም። ሆኖም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁ ብዙ ትንቢቶች አሉ።—ከራእይ 19:10 ጋር አወዳድሩ።
7. ኢየሱስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን የፈጸማቸው አንዳንድ ትንቢቶች ምንድን ናቸው?
7 ከእነርሱም መካከል የሚወለድበት ከተማ (ሚክያስ 5:2፤ ሉቃስ 2:4-11)፣ ከልደቱ በኋላ የደረሰው የሕፃናት ጭፍጨፋ (ኤርምያስ 31:15፤ ማቴዎስ 2:16-18)፣ ከግብፅ እንደሚጠራ (ሆሴዕ 11:1፤ ማቴዎስ 2:15)፣ የአሕዛብ መሪዎች እርሱን ለማጥፋት እንደሚተባበሩ (መዝሙር 2:1, 2፤ ሥራ 4:25-28)፤ ለ30 ብር አልፎ እንደሚሰጥ (ዘካርያስ 11:12፤ ማቴዎስ 26:15)፣ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚሞትም እንኳን ሳይቀር በትንቢት ተነግሮ ነበር።—መዝሙር 22:16, የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከቱ፤ ዮሐንስ 19:18, 23፤ 20:25, 27c
የሚመጣበት ጊዜ በትንቢት ተነግሯል
8. (ሀ) መሢሑ የሚመጣበትን ጊዜ ለይቶ የሚያመለክተው የትኛው ትንቢት ነው? (ለ) ይህን ትንቢት ለመረዳት ምን ሁለት ነገሮች መታወቅ አለባቸው?
8 በአንድ ትንቢት ላይ ብቻ እናተኩር። በዳንኤል 9:25 ላይ መሲሕ መቼ እንደሚመጣ ለአይሁዳውያን ተነግሮአቸው ነበር። እንዲህ ይነበባል፦ “ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትዕዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሲሕ ድረስ ሰባት ሱባኤና ስድሳ ሁለት ሱባኤ ይሆናል።” ይህ ትንቢት መጀመሪያ ሲታይ ምሥጢራዊ ይመስላል። ነገር ግን ባጠቃላይ መልኩ ሁለት መረጃዎችን ብቻ እንድንፈልግ የሚጠይቅ ነው። እነርሱም ጊዜው መቆጠር የሚጀምርበት ጊዜና የጊዜው ርዝማኔ ናቸው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል “በከተማው መናፈሻ ውስጥ ካለው ምንጭ በስተምሥራቅ በኩል 50 ዘንግ ርቀት ላይ” የተቀበረ ሀብት እንዳለ የሚያመለክት ካርታ ቢኖርህ ምንጩ የት እንደሚገኝ ወይም ‘ዘንጉ’ ምን ያህል ርዝማኔ እንዳለው የማታውቅ ከሆነ የተገለጸውን ቦታ ማወቅ ያዳግትሃል። ታዲያ የተቀበረው ሀብት ያለበትን ቦታ ለማግኘት እነዚህን ሁለት ማስረጃዎች ለማወቅ አትመረምርምን? የዳንኤል ትንቢትም ዘመኑ መቆጠር የሚጀምርበትን ጊዜና ማለፍ የሚኖርበትን የጊዜ መጠን ማወቅ የሚጠይቅ ከመሆኑ በስተቀር ከዚህ ምሳሌ የሚለይ አይደለም።
9, 10. (ሀ) 69ኙ ሳምንታት የሚቆጠሩት ከየት ጀምሮ ነው? (ለ) 69ኙ ሳምንታት ርዝማኔያቸው ምን ያህል ነው? ይህንንስ የምናውቀው እንዴት ነው?
9 በመጀመሪያ የሚያስፈልገን ዘመኑ መቆጠር የሚጀምርበትን ጊዜ ማለትም ‘ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትዕዛዙ የሚወጣበትን ጊዜ’ ነው። ቀጥሎ ከዚያ መነሻ ጊዜ አንስቶ እነዚህ 69 (7 ሲደመር 62) ሳምንታት ምን ያህል እንደሆኑ ለማወቅ ርዝማኔውን ማወቅ ያስፈልገናል። ሁለቱንም ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። ኢየሩሳሌም የታደሰች ከተማ እንድትሆን ቅጥር እንዲሠራላት ትዕዛዝ የወጣው “በንጉሡ በአርጤክስስ በሃያኛው ዓመት” እንደነበረ ነህምያ ግልጽ በሆነ መንገድ ይነግረናል። (ነህምያ 2:1, 5, 7, 8) ይህም ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው በ455 ከዘአበ መሆኑን ያረጋግጣል።d
10 69ኙ ሳምንታትስ እያንዳንዳቸው የሰባት ቀኖች ርዝመት ያላቸው ቃል በቃል ሳምንታት ናቸውን? አይደሉም። ምክንያቱም ኢየሱስ ከ455 ከዘአበ በኋላ ከአንድ ዓመት ጥቂት ብቻ በለጥ ከሚል ጊዜ በኋላ አልመጣም። በመሆኑም አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና በርካታ ተርጓሚዎች (በዳንኤል 9:25 የግርጌ ማስታወሻ ላይ መግለጫ የሰጠውን የአይሁድ ታናክ ጨምሮ) እነዚህ ሳምንታት “የዓመታት” ሳምንታት እንደሆኑ ተስማምተዋል። ይህ ‘የዓመታት ሳምንታት’ ወይም የየሰባት ዓመት ዙረት ወይም ዑደት ጽንሰ ሐሳብ በጥንታውያን አይሁድ ዘንድ የታወቀ ነበር። በየሰባቱ ቀን የሰንበትን ቀን ያከብሩ እንደነበረ ሁሉ በየሰባቱ ዓመትም የሰንበትን ዓመት ያከብሩ ነበር። (ዘጸአት 20:8-11፤ 23:10, 11) ስለዚህ 69 የዓመታት ሳምንታት ማለት የሰባት ዓመታት ብዜት ወይም 483 ዓመታት ይሆናሉ። አሁን የቀረን ነገር መቁጠር ብቻ ነው። ከ455 ከዘአበ ጀምረን 483 ዓመታት ስንቆጥር ኢየሱስ ወደተጠመቀበትና መሲሕ ወይም ማሺያክ ወደሆነበት ዓመት እንደርሳለን።—ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 899 “ሰባ ሳምንታት” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።
11. ይህ የዳንኤልን ትንቢት ለመተርጎም የተደረገ ዘመናዊ ዘዴ ነው ለሚሉን ሰዎች መልስ ልንሰጥ የምንችለው እንዴት ነው?
11 አንዳንድ ሰዎች ይህ ትንቢቱን ከታሪክ ጋር ለማስማማት የተደረገ ዘመናዊ አተረጓጎም ብቻ ነው ብለው ይቃወሙ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች መሲሑ በዚያ ጊዜ እንደሚገለጥ ይጠባበቁ የነበረው ለምንድን ነው? በዚያ ዘመን አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኑ ታሪክ ጸሐፊ ሉቃስ፣ የሮማ ታሪክ ጸሐፊዎች ታሲተስና ሱቶኒየስ፣ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስና አይሁዳዊው ፈላስፋ ፊሎ ሁሉም አይሁዳውያን መሲሕን ስለመጠባበቃቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። (ሉቃስ 3:15) በአሁኑ ጊዜ ያሉ አንዳንድ ምሁራን በዚያ ዘመን አይሁድ መሲሕን እንዲጠባበቁ ያደረጋቸው በሮማ መንግሥት የደረሰባቸው ጭቆና ነው ብለው ይከራከራሉ። ይሁንና አይሁድ ከዚያ በፊት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በግሪክ የጭካኔ ስደት ሲደርስባቸው መሲሑን ያልተጠባበቁትና ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ በተገለጠበት ዘመን ብቻ ይጠባበቁ የነበሩት ለምንድን ነው? ታሲተስ አይሁዳውያን ኃይለኛ መሪዎች ከይሁዳ እንደሚመጡና “ዓለም አቀፍ ግዛት እንደሚኖራቸው” እንዲጠባበቁ ያደረጓቸው “ምሥጢራዊ ትንቢቶች” ናቸው ያለው ለምን ነበር? አባ ሂለል ሲልቨር የመሢሐዊ ግምቶች ታሪክ በእስራኤል በተሰኘ ጽሑፋቸው “በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ሁለተኛው ሩብ አካባቢ መሲሕ እንደሚገለጥ ይጠበቅ የነበረው” በሮማ ስደት ምክንያት ሳይሆን “በዚያ ዘመን በነበረው የታወቀ የዘመን አቆጣጠር ምክንያት ነበር” በማለት የገለጡ ሲሆን ይህም የዘመን አቆጣጠር በከፊል ከዳንኤል መጽሐፍ የተወሰደ ነበር።
ኢየሱስ መሲሕ ለመሆኑ ከላይ ተመስክሮለታል
12. ይሖዋ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይቶ ያሳወቀው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ መሲሕ ለመሆኑ ሦስተኛው ማስረጃ አምላክ ራሱ የሰጠው ምስክርነት ነው። በሉቃስ 3:21, 22 መሠረት ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ በጣም ቅዱስና ኃያል በሆነው ኃይል ይኸውም በይሖዋ አምላክ መንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል። ይሖዋም በራሱ ድምፅ ኢየሱስ የሚወደው ልጁ እንደሆነ ገልጿል። በሌሎችም ሁለት ወቅቶች ማለትም አንድ ጊዜ ከኢየሱስ ሐዋርያት ሦስቱ በተገኙበት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተመልካች ሰዎች እየሰሙ ይሖዋ ኢየሱስን እንደሚወደውና እንደሚደግፈው ለማመልከት ከሰማይ ተናግሮለታል። (ማቴዎስ 17:1-5፤ ዮሐንስ 12:28, 29) በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም መሲሕ መሆኑን እንዲመሰክሩ መላእክት ከሰማይ ተልከዋል።—ሉቃስ 2:10, 11
13, 14. ይሖዋ ኢየሱስ መሲሕ ለመሆኑ ያለውን ድጋፍ ተግባራዊ በሆነ መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ ለመሢሑ ታላላቅ ሥራዎችን እንዲሠራ የሚያስችል ኃይል በመስጠት እንደሚወደው አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አንዳንዶቹ እስከ ዘመናችን የሚደርሱ ታሪክን አስቀድመው በዝርዝር የሚገልጹ ትንቢቶችን ተናግሯል።e የተራቡ ሕዝቦችን መመገብንና ሕሙማንን መፈወስን የመሳሰሉ ተአምራቶችንም ፈጽሟል። ሙታንን ሳይቀር አስነስቷል። እነዚህን ሁሉ ታሪኮች ከጊዜ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ፈጥረው የጻፉአቸው ናቸውን? ኢየሱስ ብዙዎቹን ተአምራቱን የፈጸመው ብዙ የዓይን ምስክሮች፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት ነበር። የኢየሱስ ጠላቶችም እንኳን ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች እንዳደረገ ሊክዱ አልቻሉም ነበር። (ማርቆስ 6:2፤ ዮሐንስ 11:47) ከዚህም ሌላ የኢየሱስ ተከታዮች እንዲህ ዓይነቶቹን ታሪኮች ፈጥረው ለመጻፍ ከቻሉ የራሳቸውን ድካም ሳይቀር እስከ መግለጽ ድረስ ግልጽ ይሆኑ ነበርን? እነሱ ራሳቸው በፈጠሩት ተረት ላይ ለተመሠረተ እምነት ለመሞት ፈቃደኞች ይሆኑ ነበርን? አይሆኑም ነበር። የኢየሱስ ተአምራት የታሪክ ሐቆች ነበሩ።
14 አምላክ ኢየሱስ መሲሕ ለመሆኑ የሰጠው ምስክርነት ከዚህም አልፎ የሚሄድ ነው። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በጽሑፍ እንዲሠፍርና በታሪክ በሙሉ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በሠፊው የተተረጎመና የተሠራጨ መጽሐፍ ክፍል እንዲሆን አድርጓል።
አይሁድ ኢየሱስን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?
15. (ሀ) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁት ማስረጃዎች ምን ያህል ብዙ ናቸው? (ለ) ብዙዎቹ አይሁዶች ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው እንዳይቀበሉት ያደረጋቸው ምን የራሳቸው ግምት ነው?
15 በጠቅላላው እነዚህ ሦስት የማስረጃ ክፍሎች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁ ቃል በቃል በመቶዎች የሚቆጠሩ ማስረጃዎችን ያጠቃልላሉ። ታዲያ ይህ በቂ አይደለምን? የመኪና መንጃ ፈቃድ ወይም የሒሳብ ማስገቢያ ካርድ ለማግኘት ብታመለክትና ሦስት መለያዎች ወይም መታወቂያዎች ስለማይበቁ በመቶዎች የሚቆጠር መታወቂያ ማምጣት አለብህ ብትባል እስቲ ይታይህ። ምንኛ ምክንያተ ቢስ ጥያቄ ነው! እንግዲያውስ ኢየሱስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ማንነቱ ተለይቶ ተገልጿል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ የራሱ ሕዝቦች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚገልጸውን ይህን ሁሉ ማስረጃ ያልተቀበሉት ለምንድን ነው? ማስረጃ ለእውነተኛ እምነት አስፈላጊ ቢሆንም ለእምነት መኖር ዋስትና አይሆንም። የሚያሳዝነው ነገር ብዙ ሰዎች በጣም ብዙ ማስረጃ ቢኖርም የሚያምኑት ለማመን የፈለጉትን ብቻ ነው። በመሢሑ ረገድም ብዙ አይሁድ ስለሚፈልጉት ነገር በጣም ግልጽ የሆነ ምስል ነበራቸው። የሚፈልጉት ፖለቲካዊ መሲሕ፣ የሮማ ጭቆና እንዲያበቃ አድርጎ በቁሳዊ ረገድ እሥራኤልን በሰሎሞን ዘመን ወደነበረችበት ሁኔታ የሚመልስ መሲሕ ነበር። ታዲያ ይህን ለፖለቲካ ወይም ለሀብት ደንታ ቢስ የሆነውን ተራ የናዝሬት አናጺ እንዴት ይቀበሉት? በተለይም ደግሞ ከተሠቃየና በመከራ እንጨት ላይ የውርደት ሞት ከሞተ እንዴት መሲሕ ሊሆን ይችላል?
16. የኢየሱስ ተከታዮች ስለ መሢሑ የነበራቸውን ግምት ማስተካከል የነበረባቸው ለምንድን ነው?
16 የኢየሱስ የራሱ ደቀ መዛሙርትም እንኳን በእርሱ መሞት በጣም ተረብሸው ነበር። በግልጽ እንደምናየው ከክብራማ ትንሣኤው በኋላ ወዲያውኑ ‘ለእሥራኤል መንግሥትን ይመልሳል’ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። (ሥራ 1:6) ይሁን እንጂ ይህ የግል ተስፋቸው ስላልተፈጸመ ብቻ የኢየሱስን መሲሕነት አንቀበልም አላሉም። በተገኘው በቂ ማስረጃ ተመሥርተው በእርሱ አመኑ፤ ማስተዋላቸውም ቀስ በቀስ አደገ። ምስጢር የሆኑባቸውም ነገሮች ግልጽ እየሆኑ መጡ። መሢሑ ሰው ሆኖ ባሳለፈው አጭር ጊዜ ውስጥ እርሱን የሚመለከቱ ትንቢቶችን በሙሉ ሊፈጽም እንደማይችል ተገነዘቡ። አንዱ ትንቢት ትሑት ሆኖ በአህያ ላይ ተቀምጦ እንደሚመጣ ሲናገር ሌላው ደግሞ ከሰማይ ደመናት ጋር በክብር እንደሚመጣ ይናገር ነበር! ታዲያ ሁለቱም ትንቢቶች በአንድ ጊዜ እንዴት ሊፈጸሙ ይችላሉ? ሁለተኛ ጊዜ መምጣት እንደነበረበት ግልጽ ነበር።—ዳንኤል 7:13፤ ዘካርያስ 9:9
መሲሑ መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
17. መሢሑ መሞት እንደነበረበት የዳንኤል ትንቢት ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው? መሞት የነበረበትስ ለምን ዓላማ ነው?
17 በተጨማሪም መሢሐዊ ትንቢቶች መሢሑ መሞት እንደነበረበት በግልጽ ይናገሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል መሢሑ መቼ እንደሚመጣ የተነበየው የዳንኤል ትንቢት ቀጥሎ ባሉት ቁጥሮች ላይ “ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሲሕ ይገደላል” በማለት ተንብዮአል። (ዳንኤል 9:26) “ይገደላል” ተብሎ የተተረጎመው ካራዝ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል በሙሴ ሕግ ሥር ይፈጸም የነበረውን የሞት ቅጣት ለማመልከት የሚያገለግል ቃል ነበር። መሲሕ መሞት እንደነበረበት ጥርጥር አልነበረም። ለምን? ዳንኤል 9:24 መልሱን ይሰጠናል፦ “ዓመፃን ይጨርስ፣ ኃጢአትንም ይፈጽም፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ . . . ዘንድ።” አይሁድ በደልን ሊያስተሰርይ የሚችለው የተሠዋ ወይም የተገደለ ነገር ብቻ መሆኑን አሳምረው ያውቁ ነበር።—ዘሌዋውያን 17:11፤ ከዕብራውያን 9:22 ጋር አወዳድሩ።
18. (ሀ) ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 መሢሑ መሠቃየትና መሞት እንዳለበት የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ትንቢት ምን የሚጋጭ የሚመስል ሐሳብ አስነስቷል?
18 ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 መሢሑ የሌሎችን ኃጢአት ለመሸፈን መሠቃየትና መሞት የሚኖርበት የይሖዋ ልዩ ባሪያ መሆኑን ይናገራል። ቁጥር 5 “እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ” ይላል። ይኸው ትንቢት ራሱ መሢሑ “ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት” ለማድረግ መሞት እንዳለበት ከነገረን በኋላ “ዕድሜውም ይረዝማል፣ የእግዚአብሔርም [የይሖዋም አዓት] ፈቃድ በእጁ ይከናወናል” በማለት ይገልጽልናል። (ቁጥር 10) ይህ የሚጋጭ አባባል አይደለምን? መሢሑ ሊሞትና ከዚያ በኋላ “ዕድሜው ሊረዝም” የሚችለው እንዴት ነው? መሥዋዕት ሆኖ ሊሞትና ከሞተ በኋላ ደግሞ ‘የይሖዋ ፈቃድ በእጁ ሊከናወን’ የሚችለው እንዴት ነው? በእርግጥ መሢሑ ስለ እርሱ የተነገሩትን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ትንቢቶች ማለትም ንጉሥ ሆኖ ለዘላለም እንደሚገዛና ለመላው ዓለም ሰላምና ደስታ እንደሚያመጣ የተነገሩትን ትንቢቶች ሳይፈጽማቸው ሞቶ በዚያው ሊቀር ይችላልን?—ኢሳይያስ 9:6, 7
19. የኢየሱስ ትንሣኤ ስለ መሢሑ የተነገሩትን የሚጋጩ የሚመስሉ ትንቢቶች የሚያስታርቃቸው እንዴት ነው?
19 ይህ እርስ በርሱ የሚቃረን የሚመስል አባባል በአንድ ነጠላና አስደናቂ ተአምር አማካኝነት ተፈታ። ኢየሱስ ትንሣኤ አገኘ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው አይሁድ ለዚህ ክብራማ እውነት የዓይን ምሥክሮች ሆነዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:6) ቆየት ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ “እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፣ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 10:10, 12, 13) አዎ፣ ኢየሱስ በመጨረሻ ንጉሥ ሆኖ በአባቱ በይሖዋ ጠላቶች ላይ እርምጃ የሚወስደው ለሰማያዊ ሕይወት ከሞት ከተነሳና ለተወሰነ ጊዜ “ከጠበቀ” በኋላ ነበር። መሢሑ ኢየሱስ በሰማያዊ ንጉሥነቱ የሚፈጽማቸው ተግባሮች በአሁኑ ጊዜ የሚኖረውን የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ይነካል። በምን መንገድ? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን ይህን ይገልጻል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኤሊ የማርያም ወላጅ አባት ስለሆነ ሉቃስ 3:23 “ዮሴፍ፣ የኤሊ ልጅ” ሲል “አማች” ማለት መሆኑ ግልጽ ነው።—ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 913-17
b የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ የራሱን የትውልድ ሐረግ መዘርዘሩ ከ70 እዘአ አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት እንዲህ ዓይነት መዛግብት እንደነበሩ ግልጽ ያደርገዋል። በግልጽ መረዳት እንደምንችለው እነዚህ መዝገቦች ከኢየሩሳሌም ከተማ ጋር ስለ ጠፉ ከዚያ በኋላ ለመጡ መሲሕ ነን ባዮች የትውልድ ሐረጋቸውን ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኖአል።
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ ጥራዝ 2, ገጽ 387
d ከጥንታዊት ግሪክ፣ ከባቢሎናዊና ከፋርስ ምንጮች አርጤክስስ መግዛት የጀመረበት ዓመት በ474 እንደነበረ የሚያመለክት አስተማማኝ ማስረጃ አለ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2, ገጽ 614-16, 900
e ከእነዚህ ትንቢቶች በአንዱ ላይ ከእርሱ በኋላ ብዙ የሐሰት መሲሖች እንደሚነሱ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:23-26) የፊተኛውን ርዕሰ ትምህርት ተመልከቱ።
እንዴት ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ኢየሱስ ተስፋ የተገባው መሲሕ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ማስረጃውን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?
◻ የኢየሱስ የዘር ሐረግ መሲሕነቱን የሚደግፈው እንዴት ነው?
◻ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዱት እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ በበኩሉ የኢየሱስን መሲሕነት ለይቶ ያረጋገጠው እንዴት ነው?
◻ ብዙ አይሁድ ኢየሱስን መሲሕ ነው ብለው ያልተቀበሉት ለምንድን ነው? ይህ አስተሳሰባቸውስ የተሳሳተ የነበረው ለምንድን ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የፈጸመው እያንዳንዱ ተአምር ለመሲሕነቱ ተጨማሪ ማስረጃ ሰጥቷል