የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 10/1 ገጽ 26-29
  • ተግሣጽን በመቀበል መታዘዝን ተማር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ተግሣጽን በመቀበል መታዘዝን ተማር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላክ መታዘዝን የሚመለከተው እንዴት ነው?
  • ታዛዥነትን መማር አለብን—ለምንና እንዴት
  • ታዛዥ በመሆን ታዛዥነትን አስተምር
  • “በሁሉ . . . ታዘዙ”
  • የታዛዥነትን ጠቃሚ ጎን ተመልከቱ
  • ታዛዥነት—በልጅነት ሊሰጥ የሚገባ አስፈላጊ ትምህርት ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ‘ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • “መታዘዝን ተማረ”
    “ተከታዬ ሁን”
  • ይሖዋ ታዛዥነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 10/1 ገጽ 26-29

ተግሣጽን በመቀበል መታዘዝን ተማር

ቃል በቃል ዓለምን ቁልቁል የምትመለከት መስሎ በሚሰማህ ረዥም ተራራ ጫፍ ገደልማ አናት ላይ እንደቆምክ አድርገህ አስብ። ምንኛ የሚያስደስት የነፃነት ስሜት ይሰማሃል!

ሆኖም ነፃነትህ በእርግጥ በጣም ውስን ነው። የስበት ሕግ እያንዳንዱን እንቅስቃሴህን ይገድብብሃል። አንድ የተሳሳተ እርምጃ ሞት ሊያስከትልብህ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው የስበት ሕግ በሕዋ ውስጥ ያለ ምንም ረዳት ተንሳፍፈህ እንዳትቀር እንደሚከላከልልህ ማወቁ በጣም ያስደስታል። ስለዚህ ሕጉ ለራስህ ደህንነት የሚበጅ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተራራው ላይ ስትሆን ሕጉ በእንቅስቃሴህ ላይ የሚጭንብህን ገደቦች መቀበል ጠቃሚና እንዲያውም ሕይወት አድን ነው።

አዎ፣ አንዳንድ ጊዜ ሕጎችና ለሕጎች መታዘዝ ነፃነታችንን ይገድብብን ይሆናል። ታዲያ ይህ ስለሆነ መታዘዝ አስፈላጊ አይደለም ማለት ነውን?

አምላክ መታዘዝን የሚመለከተው እንዴት ነው?

ይሖዋ “ታላቅ ፈጣሪ” እንደመሆኑ መጠን “የሕይወት ምንጭ” ነው። በዚህም ምክንያት ፍጥረታቱ በሙሉ ለእርሱ መታዘዛቸው ተገቢ ነው። መዝሙራዊው ተገቢውን ዝንባሌ በማሳየት “ኑ፣ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፣ እኛ የማሰማሪያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና” በማለት ጽፎአል።—መክብብ 12:1፤ መዝሙር 36:9፤ 95:6, 7

ይሖዋ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍጥረታቱ ታዛዥነትን ጠይቋል። አዳምና ሔዋን በገነት በመኖር መቀጠል መቻላቸው የተመካው በታዛዥነት ላይ ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) መላእክት ከሰዎች የበለጡ ሕያዋን ፍጥረታት ቢሆኑም ከእነርሱም ታዛዥነት ይጠበቅባቸው ነበር። ከእነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት አንዳንዶቹ “የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም”። በዚህም ምክንያት “በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ” በመጣል ቅጣታቸውን አግኝተዋል።—1 ጴጥሮስ 3:19, 20፤ 2 ጴጥሮስ 2:4

በግልጽ እንደሠፈረው አምላክ ታዛዥነትን የሚመለከተው ሞገሱን ለማግኘት እንደሚያስፈልግ መሥፈርት አድርጎ ነው። እንዲህ እናነባለን፦ “በውኑ የእግዚአብሔርን [የይሖዋን አዓት] ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።”—1 ሳሙኤል 15:22

ታዛዥነትን መማር አለብን—ለምንና እንዴት

ታዛዥነት ከአምላክ ጋር የጽድቅ አቋም እንዲኖረን ያስችላል፣ ስለዚህ እርሱን መማራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! አንድን የውጭ አገር ቋንቋ እንደ መማር ሁሉ የታዛዥነትን ልማድም በሕፃንነታችን ልንማረው እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሠልጠንን አጥብቆ የሚያሳስበው ለዚህ ነው።—ኢያሱ 8:35

አንዳንድ ዘመናውያን ከልጆች ታዛዥነትን መጠበቅ አእምሮአቸውን እንደመድፈር የሚቆጠር ነው በማለት የመጽሐፍ ቅዱስን አመለካከት ይቃረናሉ። ልጆች አዋቂዎች ጣልቃ ሳይገቡባቸው የሚኖሩበትን የራሳቸው የሆነ የግል አስተሳሰብና የጠባይ ደረጃ እንዲያሳድጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለው ይከራከራሉ።

ነገር ግን ብዙ ወላጆች ይህን አስተሳሰብ በያዙባቸው የ1960ዎቹ ዓመታት የሥነ ልቡና አስተማሪ፣ ፀሐፊና ፕሮፌሰር የሆኑት ቪልሄልም ሃንሰን በወቅቱ ከነበረው አስተሳሰብ ጋር አልተስማሙም ነበር። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “አንድ ልጅ በዕድገቱ የመጀመሪያ ደረጃዎች፣ ከወላጆቹ ጋር ያለው ዝምድና በጣም ወሳኝ በሆነባቸው ዓመታት፣ ‘መጥፎ’ ማለት ወላጆቹ የሚከለክሉት ነገር ሲሆን ‘ጥሩ’ ማለት ደግሞ እነርሱ የሚያበረታቱት ወይም የሚያመሰግኑት ነገር ነው። ስለዚህ ከሥነ ምግባር ሥርዓቶች ጋር ላለው ዝምድና መሠረት በሚሆኑት በመልካም ሥነ ምግባርማ በዋና ዋና ሰናይ ምግባሮች የሚመራው ታዛዥነት ብቻ ነው።”—ከምሳሌ 22:15 ጋር አወዳድር።

የአምላክ ቃል ታዛዥነትን የመማርን አስፈላጊነት አጥብቆ ይገልጻል። እንዲህ እናነባለን፦ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” (ኤርምያስ 10:23) ሰዎች በራሳቸው ደንብ በመመራት ራሳቸው የሳሉትን የኑሮ ካርታ በመከተላቸው ምክንያት ወደ ከባድ ችግሮች መግባታቸውን በሚያሳዩ ሁኔታዎች የተሞላ ነው። ይህ አይነቱ ሁኔታ አዘውትሮ የሚደርሰው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰዎች ያለ አምላክ እርዳታ የራሳቸውን የኑሮ ጎዳና ለመንደፍ የሚያስችል እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል ስለሚጎድላቸው ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ የወረሱት ዝንባሌ አለ። ከኖኅ የጥፋት ውኃ በኋላ ወዲያውኑ ይሖዋ ስለ ሰው “የሰው ልብ አሳብ (ዝንባሌ) ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” በማለት ተናግሯል።—ዘፍጥረት 8:21

ስለዚህ ለይሖዋ የመታዘዝን ዝንባሌ በውርስ የሚያገኝ አንድም ሰው የለም። ይህን ዝንባሌ በልጆቻችን ውስጥ ልናሳድረውና እኛም በሕይወታችን ሁሉ ልንማረው ያስፈልገናል። እያንዳንዳችን “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ” በማለት የጻፈውን የንጉሥ ዳዊት የልብ ዝንባሌ ልንኮተኩት ያስፈልገናል።—መዝሙር 25:4, 5

ታዛዥ በመሆን ታዛዥነትን አስተምር

የኢየሱስ እናትና አሳዳጊ አባቱ በኢየሱስ ልደት አካባቢ የነበሩትን ሁኔታዎች አሳምረው ያውቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማዎች ፍጻሜ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ድርሻ እንዳለው ተገንዝበው ነበር። (ከሉቃስ 1:35, 46, 47 ጋር አወዳድር።) ለእነርሱ “እነሆ፣ ልጆች የይሖዋ ስጦታ ናቸው” የሚሉት ቃላት ልዩ ትርጉም ነበራቸው። (መዝሙር 127:3) የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ተገንዝበው ነበር፣ ስለዚህም ወደ ግብፅ እንዲሸሹ ወይም በኋላ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ የተነገሯቸውን የመሳሰሉ መለኮታዊ ትዕዛዞች ለመታዘዝ ፈጣኖች ነበሩ።—ማቴዎስ 2:1-23

የኢየሱስ ወላጆች ተግሣጽን በሚመለከትም ኃላፊነታቸውን ተገንዝበው ነበር። እውነት ነው፣ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊትም ቢሆን ዘወትር በታዛዥነት ኖሮአል። በምድር ላይ ሳለ ግን ፈጽሞ አዲስ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር መታዘዝን ተማረ። መጀመሪያ ነገር ፍጹም ልጅም እንኳን ቢሆን በትምህርትና በማሠልጠኛ መልክ ተግሣጽ መቀበል ስለሚያስፈልገው ፍጹም ላልሆኑ ወላጆቹ መታዘዝ ነበረበት። ይህንንም ትምህርትና ማሠልጠኛ ወላጆቹ አቅርበውለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ለኢየሱስ ተግሣጽን በቅጣት መልክ መስጠት አስፈላጊ አልነበረም። ኢየሱስ ምንጊዜም ታዛዥ ነበር፣ አንድ ነገር እንዲያደርግ ሁለት ጊዜ እንዲነገረው አያስፈልግም ነበር። እንዲህ እናነባለን፦ “ከእነርሱም [ከወላጆቹም] ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፣ ይታዘዝላቸውም ነበር።”—ሉቃስ 2:51

ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን በምሳሌነት እንዴት እንደሚያስተምሩትም ያውቁ ነበር። ለምሳሌ ያህል “ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር” የሚል እናነባለን። (ሉቃስ 2:41) ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ለመሄድ ዝግጅት በማድረግ ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው አሳቢነት እንደነበረውና የይሖዋን አምልኮ አክብዶ ይመለከት እንደነበረ አሳይቷል። እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ነበር! በአሁኑ ጊዜም በተመሳሳይ መንገድ ወላጆች በአምልኮ ጉዳዮች ረገድ ባላቸው ታዛዥነት ለልጆቻቸው ታዛዥነትን ሊያስተምሩአቸው ይችላሉ።

ዮሴፍና ማርያም በበኩላቸው በጽድቅ መንገድ በሰጡት ጥሩ ተግሣጽ ምክንያት “ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።” ይህስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆች ሊከተሉት የሚገባ ምንኛ ጥሩ ምሳሌ ነው!—ሉቃስ 2:52

“በሁሉ . . . ታዘዙ”

“ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።” (ቆላስይስ 3:20) የኢየሱስ ወላጆች ለይሖዋ ያላቸው ታዛዥነት ከኢየሱስ ወይም ከግማሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ምንም ዓይነት ነገር እንዳይጠይቁ ያደርጋቸው ስለነበር ኢየሱስ ለወላጆቹ በሁሉ ሊታዘዝላቸው ይችል ነበር።

በዛሬው ጊዜ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው በሁሉ ታዛዦች እንዲሆኑ በማስተማር ተሳክቶላቸዋል። ልጅ የማሳደግ ዘመናቸውን ካሳለፉ በኋላ በአሁኑ ጊዜ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ የሚያገለግሉ ሦስት አባቶች የተናገሩትን አዳምጡ።

ታኦ እርሱና ሚስቱ አምስት ወንዶች ልጆች እንዴት እንዳሳደጉ ይናገራል። እርሱም እንዲህ ይላል፦ “ገና ከመጀመሪያው አዋቂዎችም እንደሚሳሳቱ ለልጆች ማሳወቅ አስፈላጊ ነው። እንዲያውም የሚያሳዝነው ስህተቶችን በመደጋገም ስለምንሠራ ሰማያዊ አባታችንን ሳናቋርጥ ምሕረትና እርዳታ መጠየቅ አለብን። ልጆቻችን ከወጣትነት ጭንቀቶች ጋር እንደሚታገሉ ሁሉ እኛም ከአዋቂዎች ችግር ጋር እየታገልን እንዳለን ሆነ ብለን እንዲገነዘቡ አደረግን።”

አንድ ልጅ ታዛዥነትን እንዲማር ከተፈለገ በወላጆቹና በእርሱ መካከል ፍቅራዊ ዝምድና መኖሩ አስፈላጊ ነው። ሄርማን ስለ ሚስቱ እንዲህ ይላል፦ “እርሷ ለወንዶች ልጆቻችን እናት ብቻ ሳትሆን ጓደኛቸውም ነበረች። እነርሱም ይህንን ያደንቁ ስለነበረ መታዘዝ አስቸጋሪ አይሆንባቸውም ነበር።” ከዚያም የወላጅና የልጅን ዝምድና እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ተግባራዊ የሆነ ምክር ሲያክል “ለአያሌ ዓመታት ዕቃዎች በእጅ እንዲታጠቡና እንዲደርቁ ሆን ብለን የዕቃ ማጠቢያ መኪና እንዳይኖረን አደረግን። ወንዶች ልጆቻችን በየተራ ዕቃዎቹን እንዲያደርቁ ይመደቡ ነበር። ላልታሰበበት የሐሳብ ልውውጥ ከዚህ የተሻለ ጊዜ አልነበረም” ብሏል።

ፍቅራዊ የሆነ የወላጅና የልጅ ዝምድና አንድ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር ሊኖረው ለሚገባው ዝምድና ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል። ሩዶልፍ እርሱና ሚስቱ ልጆቻቸው እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳት እንዴት እንደሠሩ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “መሠረታችን የዘወትር የቤተሰብ ጥናት ነበረ። ለልጆቹ ተስማሚ የሆኑ በርካታ ርዕሶችን እንዲመረምሩ እንደለድል ነበር። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን አንድ ላይ ሆነን እናነብና ባነበብነው ነገር ላይ እንወያይበት ነበር። ልጆቻችን ይሖዋ ከልጆች ብቻ ሳይሆን ከወላጆችም ታዛዥነት እንደሚጠብቅባቸው ሊገነዘቡ ይችሉ ነበር።”

ክርስቲያን ወላጆች “የተግሣጽ በትር የሕይወት መንገድ ነውና” የሚለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ጥቅስ ለእነርሱ ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም እንደሚሠራ ይገነዘባሉ። ስለዚህ ልጆች ለወላጆቻቸው በሁሉ ታዛዥ ለመሆን ግዴታ ያለባቸው ሲሆን ወላጆችም ይሖዋ በሚፈልግባቸው ሁሉ ታዛዦች መሆን አለባቸው። ወላጆችና ልጆች በመካከላቸው ያለውን ዝምድና ከማጠንከራቸው በተጨማሪ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድናም ለማጠንከር ይፈልጋሉ።—ምሳሌ 6:23

የታዛዥነትን ጠቃሚ ጎን ተመልከቱ

የአምላክ ቃል ልጆችን ስለማሳደግ እንዲህ የመሰለ ተግባራዊ ምክር ስለሚያቀርብልን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን! (ሣጥኑን ተመልከቱ።) በጽድቅ ተግሣጽን ከሚሰጧቸው ወላጆቻቸው ታዛዥነትን የሚማሩ ልጆች ለመላው የክርስቲያን ወንድማማቾች እውነተኛ የደስታ ምንጭ ናቸው።

ለአምላክ መታዘዝ ማለት ሕይወት ስለሆነ የአምላክ ትዕዛዞች በግል ነፃነታችን ላይ የሚጥሉብንን እገዳዎች ለአንድ አፍታም እንኳን ቢሆን ለመጣስ ከማሰብ መቆጠብ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል የስበትን ሕግ ለአጭር ጊዜ ለመጣስ ቻልን እንበል። ነፃነታችንን ምንም የሚያግድብን ነገር ሳይኖር ከተራራው ጫፍ ላይ በመብረር በሰማይ ላይ ማንዣበብ እንዴት ደስ ያሰኛል! ብለን እናስብ ይሆናል። ስበቱ እንደገና መሥራት ሲጀምር ግን ምን ይሆናል? ምን እንደሚጠብቀን አስቡት!

ተግሣጽን በመቀበል ታዛዥነትን መማር ለተመዛዘነ የባሕርይ ዕድገት ተጨማሪ ድርሻ አለው፣ ድካሞቻችንንም እንድንገነዘብ ይረዳናል። ለሌሎች ሰዎች መብቶችና ፍላጎቶች ደንታ የሌለንና ለራሳችን ብቻ ይደረግልን ባዮች ከመሆን እንድንቆጠብ ይረዳናል። የግራ መጋባትን መንገድ እንድናስወግድ ይረዳናል። ባጭሩ ደስታ ያስገኝልናል።

ስለዚህ አዋቂም ሆንክ ልጅ “መልካም እንዲሆንልህ” በተጨማሪም “ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” ተግሣጽን በመቀበል ታዛዥነትን ተማር። (ኤፌሶን 6:1-3) ተግሣጽን ባለመቀበል ታዛዥነትን ሳይማር በመቅረቱ ምክንያት ለዘላለም የመኖር ተስፋውን በአደጋ ላይ ለመጣል የሚፈልግ ማን አለ?—ዮሐንስ 11:26

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ በጽድቅ ተግሣጽን በመስጠት ታዛዥነትን አስተምሩ

1. ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ ሕጎችና ሥነ ሥርዓቶች መሠረት ተግሣጽ ስጡ ወይም አሠልጥኑ።

2. እንዲሁ ታዛዥነትን በመጠየቅ ሳይሆን ታዛዥነት ለምን የጥበብ መንገድ እንደሆነ በማስረዳት ተግሣጽ ስጡ።—ማቴዎስ 11:19ለ

3. በቁጣ ወይም በጩኸት ተግሣጽ አትስጡ።—ኤፌሶን 4:31, 32

4. በፍቅርና በአሳቢነት ላይ በተመሠረተ ልባዊ ዝምድና ተመሥርታችሁ ተግሣጽ ስጡ።—ቆላስይስ 3:21፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7, 8፤ ዕብራውያን 12:5-8

5. ለልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ተግሣጽ ስጡ።—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15

6. በተደጋጋሚና ሐሳባችሁን ባለመለዋወጥ ተግሣጽ ስጡ።—ዘዳግም 6:6-9፤ 1 ተሰሎንቄ 2:11, 12

7. በመጀመሪያ ለራሳችሁ ተግሣጽ ስጡና ከዚያም በምሳሌነታችሁ አስተምሩ።—ዮሐንስ 13:15፤ ከማቴዎስ 23:2, 3 ጋር አወዳድሩ።

8. ይሖዋ እርዳታውን እንዲሰጣችሁ በጸሎት በመጠየቅ ሙሉ በሙሉ በእርሱ በመተማመን ተግሣጽ ስጡ።—መሳፍንት 13:8-10

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የተግሣጽ ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነው”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ