የቤተሰብ ጭንቀት—የጊዜያችን መለያ ምልክት
የቤተሰብ ጭንቀት—ብዙዎች ባሕላዊ የጋብቻና የወላጅነት ሕጎች ጊዜ እንዳለፈባቸው የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ሌሎች ደግሞ የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የኅብረተሰባዊ ለውጥ ውጤት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ሌሎች ደግሞ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ካደረሳቸው ጉዳቶች እንደ አንዱ አድርገው ይመለከቱታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ ቤተሰቦችን እየተናነቃቸው ያለው ችግር ከዚህ በጣም የበለጠ ነገርን ያመለክታል። በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-4 ላይ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ልብ በሉ፦
“ነገር ግን በመጨረሻው ቀብ የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።”
እነዚህ ቃላት የዛሬዎቹ ችግሮች ዋነኛ መሠረት ምን እንደሆነ አያስረዱምን? የዛሬው የቤተሰብ ጭንቀት በዚህ ዓለም የመጨረሻ ቀናት እንደሚፈጸሙ የተተነበየላቸው ሁኔታዎች አንዱ ውጤት እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ የጭንቀት ጊዜ በ1914 እንደጀመረ የሚያሳዩ አሳማኝ ማስረጃዎች አሉ።a ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የሚጠራው ከሰው በላይ የሆነው መንፈሳዊ ፍጡር ተፅዕኖ በተለየ ሁኔታ የሚገድል ሆኗል።—ማቴዎስ 4:8-10፤ 1 ዮሐንስ 5:19
ሰይጣን ከ1914 ጀምሮ በምድር አካባቢ ብቻ በመወሰኑ “ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ” ታላቅ ቁጣ ተቆጥቷል። (ራእይ 12:7-12) ሰይጣን “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ እውነተኛ ስሙን የሚያገኝበት” የአምላክ ዋነኛ ጠላት እንደመሆኑ መጠን ምድር ለቤተሰቦች አደገኛ ቦታ እየሆነች ብትሄድ የሚያስደንቅ ነውን? (ኤፌሶን 3:15) ሰይጣን ሁሉንም የሰው ዘር ከአምላክ ለማራቅ ቆርጧል። ታዲያ ይህንን ለመፈጸም ችግሮችን በማስነሳት በቤተሰብ ላይ ጥቃት ከማድረስ ሌላ ምን የተሻለ መንገድ ያገኛል?
ቤተሰቦችን እንዲህ ካለው ከሰው በላይ ከሆነው ፍጡር የሚመጣውን ጥቃት ለመከላከል ባለሞያዎች ከሚያቀርቧቸው ጥልቀት የሌላቸው ሐሳቦች የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የእርሱን አሳብ አንስተውምና” በማለት ስለ ሰይጣን ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) ጥቃቱን ከሚያመጣባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዳንዶቹን ማወቅ የመከላከያ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል።
ገንዘብና ሥራ
የኢኮኖሚ ተጽእኖ በጣም ኃይለኛ ከሆኑት የሰይጣን የማጥቂያ መሣሪያዎች አንዱ ነው። እነዚህ ‘የሚያስጨንቁ ጊዜያት’ ወይም ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን በ2 ጢሞቴዎስ 3:1 ላይ እንደሚለው “የውጥረት ጊዜያት” ናቸው። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሥራ አጥነት፣ ዝቅተኛ ደሞዝና መሠረታዊ የሆኑ አስፈላጊ ነገሮች እጥረት ከባድ የቤተሰብ ችግር ምክንያቶች ናቸው። ይሁን እንጂ በአንፃራዊ ሁኔታ ባለጸጋ በሆነችው በዩናይትድ ስቴትስ እንኳን የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎች ከባድ ጉዳት አድርሰዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት ገንዘብ የቤተሰብ ግጭት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ አሳይቷል። አንዳንድ ቤተሰቦች ጠንካራ የሆኑበት ምስጢር የተባለው መጽሐፍ ሲያብራራ የተቀጠሩበት መሥሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚውለው “ጊዜ፣ ትኩረት፣ [እና] ኃይል” ራሱ የጋብቻን ግዴታ ማሟላትን የሚያዳክም “ረቂቅ ጠላት” ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ሁኔታዎች ብዙ ሴቶችን ወደ ሥራው ዓለም እንዲገቡ አስገድደዋቸዋል። ቫንስ ፓካርድ የተባሉት ጸሐፊ “በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ዓመት በታች ካሉ ድክ ድክ የሚሉ የአሜሪካ ሕፃናት ቢያንስ ከአራቱ አንዱ ከቤት ውጭ ሥራ የያዘች እናት አለው” በማለት ዘግበዋል። ለትንንሽ ልጆች የሚያስፈልጉትን ማለቂያ የሌላቸው ነገሮች ለማሟላት ሥራ መሥራት ለወላጆችም ሆነ ለልጆች ጎጂ ውጤት ያለውና እጅግ በጣም አድካሚ ነው። ፓካርድ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሕፃናት የእንክብካቤ መስጫ ዝግጅት እጥረት ስላለ “በዛሬው ጊዜ በትንሽነታቸው ጥሩ እንክብካቤ ያላገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች አሉ” ሲሉ አክለዋል።—በአደጋ ላይ የወደቁት ልጆቻችን
አብዛኛውን ጊዜ የሥራ ቦታው ራሱ ለቤተሰብ ስምምነት ጠንቅ ሆኗል። ብዙ ሠራተኞች ከሥራ ጓደኞቻቸው ጋር የተከለከሉ የጾታ ግንኙነቶች ወደ ማድረግ አዘንብለዋል። ሌሎች ደግሞ ዋጋ ቢስ ለሆነ የሙያ ማሻሻያና ተጨማሪ ዕድገት ለማግኘት ሲሉ የቤተሰባቸውን ሕይወት መሥዋዕት አድርገዋል። (ከመክብብ 4:4 ጋር አወዳድር) አንድ ሰውዬ በሽያጭ ተወካይነት ሥራው በጣም በመያዙ የተነሳ ሚስቱ “ባል ቢኖራትም ሁሉንም የወላጅነት ሥራዎች እንደምታከናውን ነጠላ ወላጅ” አድርጋ ራሷን ገልጻለች።
እየላላ የሄደው የጋብቻ ማሰሪያ
የጋብቻ ተቋም ራሱ ጥቃት እየደረሰበት ነው። የቤት ውስጥ ሁኔታ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ አለ፦ “ባለፉት ጊዜያት የተጋቡ ባልና ሚስት ከመካከላቸው አንደኛው ዝሙት፣ ጭካኔ፣ ከፍ ያለ ቸልተኝነት ካልፈጸመ በስተቀር እንደተጋቡ እንደሚቆዩ ይጠበቅ ነበር። አሁን ብዙ ሰዎች የጋብቻን ዓላማ የሚመለከቱት የግል ፍላጎታቸውን ማሟያ እንደሆነ አድርገው ነው።” አዎን ጋብቻ መከፋትን፣ መሰልቸትን ወይም ብቸኝነትን መቋቋሚያ እንጂ የአንድ ሰው የዕድሜ ልክ ቃል ኪዳን እንደሆነ ተደርጎ አይታይም። በአሁኑ ጊዜ ትኩረት የሚደረግበት ነገር ከጋብቻው የሚገኘው ነገር እንጂ ለጋብቻው የምታደርገው አስተዋፅዖ አይደለም። (ከሥራ 20:35 ጋር አነፃፅር።) ይህ “በጋብቻ ዙሪያ ላሉት ነገሮች የሚሰጠው ግምት መለወጡ” የጋብቻን ማሰሪያ በጣም አዳክሞታል። እናገኘዋለን ብለው ያሰቡት ነገር አልጨበጥ ሲል አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስት እንደ ፈጣን መፍትሔ አድርገው የሚወስዱት መፋታትን ነው።
በእነዚህ “የመጨረሻ ቀናት” ውስጥ ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የአምልኮ መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” ተብለው በትንቢታዊ መንገድ ተገልጸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:4, 5) ብዙ ሊቃውንት የሃይማኖት ማሽቆልቆል ለጋብቻ መመንመን ድርሻ እንዳለው ይሰማቸዋል። ፍቺ ለምን መቅረት አለበት በሚባለው መጽሐፋቸው ላይ ዶክተር ዳያን ሜደቬድ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “እንደ ብዙዎቹ ሃይማኖቶች አባባል አምላክ ጋብቻ ቋሚ እንዲሆን አስቦ ነበር። ስለ አምላክ እርግጠኛ ካልሆንክ ወይም በእርሱ የማታምን ከሆነ የፈለግኸውን ለማድረግ ትጋበዛለህ።” በዚህም ምክንያት ጋብቻው ችግር ሲነሳበት ባልና ሚስት ጥሩ መፍትሔ ለማግኘት አይጥሩም። “በችኮላ ጋብቻውን ለውድቀት ይዳርጉታል።”
ወጣቶች ጥቃት ይደርስባቸዋል
ልጆች ዛሬ ካሉት ግፊቶች የተነሣ መከራቸውን እያዩ ናቸው። ቁጥራቸው የሚዘገንን ልጆች በራሳቸው ወላጆች ይደበደባሉ፣ ይሰደባሉ ወይም በጾታ ይነወራሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ በፍቺ ምክንያት የሁለት ወላጆችን ፍቅራዊ እንክብካቤ የማግኘት መብታቸውን ተነፍገዋል። አብዛኛውን ጊዜም የወላጆች መፋታት ቁስሉ ዕድሜ ልክ አብሮ ይቆያል።
ወጣቶች ከልዩ ልዩ አቅጣጫ ኃይለኛ ተፅዕኖ እየወረደባቸው ነው። አንድ አሜሪካዊ ወጣት 14 ዓመት ሲሆነው በቴሌቪዥን አማካኝነት 18,000 ግድያዎችን እንዲሁም ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌሎች የዓመፅ ዓይነቶችን፣ የጾታ ብልግናዎችን፣ የጭካኔ ድርጊቶችን እንዲሁም ወንጀሎችን ይመለከታል። ሙዚቃም በወጣቶች ላይ ትልቅ ኃይል አለው። አብዛኞቹ ሙዚቃዎች የሚሰቀጥጥ ብልግና ያለባቸው፣ ስለ ፍትወተ ሥጋ በግልጽ የሚናገሩ፣ ወይም ደግሞ ይዘታቸው ሰይጣናዊ የሆኑ ናቸው። ትምህርት ቤቶች ወጣቶችን እንደ ዝግመተ ለውጥ ለመሰሉ በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት ለሚሸረሽሩ ጽንሰ ሐሳቦች ያጋልጡአቸዋል። የዕድሜ እኩዮቻቸው ግፊትም ብዙዎች ከጋብቻ በፊት በሚደረግ የጾታ ግንኙነትና ጠጪነት ወይም በአደንዛዥ መድኃኒቶች አላግባብ በመጠቀም እንዲሳተፉ ገፋፍቷቸዋል።
የቤተሰብ ጭንቀት መንስኤዎች
ስለዚህ በቤተሰብ ላይ የሚሠነዘረው ጥቃት ስፋት ያለውና ከፍተኛ ጥፋት ማድረስ የሚችል ነው። ቤተሰቦች ከውድቀት እንዲድኑ ምን ሊረዳቸው ይችላል? የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት ጆን ብራድሻው “የወላጅነት ሕጎቻችን በ150 ዓመታት ውስጥ እንደ ጊዜው ሁኔታ በደንብ አልተሻሻሉም። . . . የድሮዎቹ ሕጎች ደግሞ ከአሁን ወዲያ አይሠሩም ብዬ አምናለሁ” በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ሰው ሠራሽ ሕጎች ማውጣቱ መፍትሔ አይሆንም። የቤተሰብ መሥራች ይሖዋ አምላክ ነው። የቤተሰብ ሕይወት በግል ደስታችን ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ ሚና እንደሚጫወት እንዲሁም ቤተሰብን ደስተኛና ጠንካራ ለማድረግ ምን እንደሚያስፈልግ ከማንም በተሻለ ሁኔታ ያውቃል። እንግዲያው ቃሉ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ ጭንቀት መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑ ሊያስደንቀን ይገባልን?
ይህ የጥንት መጽሐፍ የቤተሰብ ኑሮ እንዴት እንደተበላሸ ይነግረናል። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን ውብ በሆነ የአትክልት ቦታ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደረገና መላዋን ምድር ወደ ገነት መለወጥን የመሰለ የድካማቸውን ዋጋ የሚመልስ ሥራ ተሰጣቸው። አምላክ አዳም የቤተሰቡ ራስ እንዲሆን ደንግጎ ነበር። ሔዋን ደግሞ እንደ “ረዳት” ወይም “ማሟያ” ሆና ከራስነቱ ቦታ ጋር መተባበር ነበረባት። ይሁን እንጂ ሔዋን በዚህ ዝግጅት ላይ ዓመፀች። የባልዋን የራስነት ቦታ በመቀማት አምላክ በእነሱ ላይ የደነገገውን ብቸኛውን እገዳ አፈረሰች። አዳምም የራስነት ቦታውን ለእርሷ ለቀቀና በዓመፁ ተባበራት።—ዘፍጥረት 1:26 እስከ 3:6
ከአምላክ ዝግጅት ፈቀቅ ማለቱ ያመጣው አፍራሽ ውጤት ወዲያውኑ መታየት ጀመረ። ከዚያ ወዲህ ንጹሕና ኃጢአት የሌለባቸው ስላልሆኑ አዳምና ሔዋን የእፍረትና የጥፋተኛነት ስሜት አደረባቸው። በፊት ሚስቱን በግጥም በጥሩ ሁኔታ የገለጻት አዳም አሁን በቀዘቀዘ መንፈስ ‘አንተ የሰጠኸኝ ሴት’ ብሎ ጠራት። ይህ የቅሬታ አነጋገር የጋብቻ ችግር መጀመሪያ ነበር። አዳም የራስነት ቦታውን ለማስመለስ የሚያደርገው ከንቱ ሙከራ ሁሉ ‘ገዢዋ’ መሆንን አስከትሏል። ሔዋን ደግሞ ምናልባትም ከመጠን ባለፈ ወይም ሚዛናዊ ባልሆነ ሁኔታ ‘ፈቃዷ’ ወደ ባሏ ይሆናል።—ዘፍጥረት 2:23፤ 3:7-16
እንግዲያው የአዳምና የሔዋን የጋብቻ ግጭት በዝርያዎቻቸው ላይ አፍራሽ ግፊት ማስከተሉ አያስደንቅም። የመጀመሪያ ልጃቸው ቃየን ጨካኝ ገዳይ ሆነ። (ዘፍጥረት 4:8) የቃየን ዝርያ የሆነው ላሜህ ደግሞ ከአንድ በላይ ሚስት በማግባቱ በታሪክ የተመዘገበ የመጀመሪያው ሰው በመሆን የቤተሰብ ሕይወት ማሽቆልቆሉ እንዲጨምር አደረገ። (ዘፍጥረት 4:19) አዳምና ሔዋን ኃጢአትንና ሞትን ብቻ ሳይሆን እስካሁን ድረስ የሰው ልጆች ዕጣ ፈንታ የሆነውን ጤናማ ያልሆነ የቤተሰብ ኑሮም አስተላልፈዋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የቤተሰብ አለመስማማት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
እያበቡ ያሉ ቤተሰቦች
ይሁን እንጂ ዛሬ ባሉት ተጽዕኖዎች እየፈራረሱ ያሉት ሁሉም ቤተሰቦች አይደሉም። ለምሳሌ አንድ ባል ከሚስቱና ከሁለት ሴቶች ልጆቹ ጋር በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአንድ አነስተኛ መንደር ይኖራል። ምንም እንኳን ከጎረቤቶቻቸው አብዛኞቹ በወላጆችና በልጆች መካከል የትውልድ መራራቅ ቢኖርም እሱና ሚስቱ ግን ይህ ችግር የለባቸውም። ሴቶች ልጆቻቸው አደንዛዥ ዕፅ መውሰድን ወይም የጾታ ግንኙነትን ይሞክሩ ይሆን ብለው አይጨነቁም። ሰኞ ሰኞ ምሽት ላይ ሌሎች ወጣቶች ዓይናቸውን በቴሌቪዥን ላይ ተክለው በተመስጦ እየተከታተሉ ባሉበት ጊዜ መላው ቤተሰብ ግን በሳሎን ጠረጴዛቸው ዙሪያ ለመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ይሰበሰባሉ። “ሰኞ ማታ አብረን በመሆን እርስ በእርስ የምንነጋገርባት ልዩ ምሽታችን ናት” በማለት ያብራራል። “ሁለቱ ሴቶች ልጆቻችን ችግሮቻቸውን ከእኛ ጋር በመወያየት ለመፍታት ነፃነት ይሰማቸዋል።”
በሌላ በኩል ደግሞ በኒው ዮርክ ከተማ ከሁለት ሴቶች ልጆቿ ጋር ሆና ልዩ በሆነ የቤተሰብ አንድነት የምትደሰት አንዲት ነጠላ ወላጅ አለች። ደስታ ልታገኝ የቻለችበት ምሥጢር ምንድን ነው? “እስከ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ድረስ ቴሌቪዥኑን አጥፍተነው እንቆያለን” በማለት ታብራራለች። “በየቀኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የሚደረግ ውይይት አለን። እንዲሁም ለቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይታችን አንድ ምሽት መድበናል።”
ሁለቱም ቤተሰቦች የይሖዋ ምስክሮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ የሚሰጠውን ምክር ይከተላሉ፤ የተፈለገውንም ውጤት አስገኘላቸው። ሆኖም ይህን ውጤት ያገኙት እነርሱ ብቻ አይደሉም። ልክ እንደነሱ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ ለቤተሰብ የተሰጡ ሕጎችን በሥራ ላይ በማዋላቸው ጥሩ ውጤት እያገኙ ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችም አሉ።b እነዚያ ሕጎች ምንድን ናቸው? አንተንና ቤተሰብህንስ ሊጠቅሙ የሚችሉት እንዴት ነው? ለመልሱ ከሚቀጥለው ገጽ ጀምሮ የቀረቡትን ክፍሎች እንድትመለከታቸው እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የመጨረሻዎቹ ቀናት በ1914 ስለመጀመራቸው ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን በምድር ላይ ለዘላለም በገነት መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 18ን ተመልከት።
b የይሖዋ ምስክሮች በቤተሰብ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ለማዋል እንዲቻል ነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ የግል እርዳታ ያገኛሉ። ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች በመጻፍ ልታገኛቸው ትችላለህ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች በቤተሰብ ውስጥ ለሚኖረው ትልቅ ጭንቀት መንስኤ ናቸው
[ምንጭ]
U.S. Navy photo
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋል ብዙ ቤተሰቦች ዛሬ ያሉትን ግፊቶች እየተቋቋሟቸው ነው